Saturday, May 31, 2025

እይታ | Perception

                                              ፍትህ

  ፍትህ የስራ ውጤት ነው ። ሰው የስራውን ካላገኘ ፍትህ የለም ማለት ነው ። ፍትህ ካለ ጥሩ የሰራ ይሸለማል ። መጥፎ የሰራ ደግሞ ይቀጣል ። በተቃራኒው ፍትህ ከሌለ ፣ መጥፎ የሰራ አይቀጣም ። ጥሩ የሰራ አይሸለምም ። አለመሸለም ብቻ አይደለም ፣ ጥሩ በመስራቱ ሊቀጣ ይችላል ። ፍትህ ከሌለ የዘሩትን ማጨድ አይቻልም ። መታጨድ እንጅ ማጨድ አይኖርም ። መልካም የሰሩ የዘሩትን ማጨድ ባይችሉም ፣ ክፉዎች ግን ያልዘሩትን ያጭዳሉ ። ያላበሰሉትን ይበላሉ ። ያልሰጡትን ይወስዳሉ ። ያልተንከባከቡትን ፍሬ ይመገባሉ ። ፍትህ በሌለበት ትጋት ከንቱ ነው ። ምክንያቱም ሰርቶ መከበር አይቻልም ። ሰርቆ መከበር ነው የሚቻለው ። ጥሮ ማሳካት እጅግ ከባድ ነው ። አጭበርብሮ ማሳካት ግን ቀላል ነው ። ያለፍትህ ስራ ዋጋው ዝቅ ይላል ። ሴራ ግን ዋጋው ከፍ ይላል ።

ለስራ የሚተጉ ፍትህ ያሰፍናሉ ። ለሴራ የሚተጉ ደግሞ ፍትህ ያዛባሉ ። ለመስራት የሚተጉ ፍትህን ያረጋግጣሉ ። ለመስረቅ የሚተጉ ፍትህን ይረግጣሉ ። መስረቅም መስራትም ትጋት ይፈልጋሉ ። ልዩነቱ መስረቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል ። የደስታ ሰገነት ላይ ያስቀምጣል ። ግን ደግሞ የሀዘን አዘቅት ውስጥ መክተቱ ኣይቀርም ። ስራ በአንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ አያስገኝም ። ደስታውንም በመጠኑ ፣ ገንዘቡንም በልኩ እያሳደገ ነው የሚሄደው ። ሰው በመስረቁ የሰውን ደስታ ይቀማል ። ለዚያ ነው ደስታው ከልክ በላይ የሚሆነው ። የሚገርመው ሀዘኑም ከልክ በላይ መራር ነው ። ምክንያቱም የሚሸከመው ሀዘን የራሱን ብቻ ሳይሆን ፣ የሰውንም ጭምር ነው ።

ሰው በመስራቱ ግን ሀዘኑም ደስታውም በልኩ ነው ። ምክንያቱም የሚቀማው ደስታ የለም ። የሚሸከመውም ተጨማሪ ህዘን የለም ። እርሱ ፍትሐዊ ነው ።

ለመስራት እንጅ ለመስረቅ ፣ ለማስደሰት እንጅ ለማሳዘን ፣ ፍትህን ለማረጋገጥ እንጅ ለማዛባት አትትጉ ። ትጋት ደስ የሚለው ከቅንነት ጋር ነው ። ቅንቅንነት አይመቸውም ። ስኬት የትጋት ውጤት ነው ። ሰው ለፍትህ ከተጋ ፣ ስኬት የሀቀኞች ትሆናለች ። ፍትህን ለማዛባት ከተጋ ግን ፣ ስኬት የአጭበርባሪዎች ትሆናለች ። ፍትህ አለ ማለት የተጉ ስኬትን ይጎናጸፋሉ ፣ የአጭበረበሩ ይቀጣሉ ፣ የማይለፉ ሰነፎች ደግሞ ከሁለቱ ይማራሉ ። ፍትህ ከሌለ ስኬትም ቅጣትም የለም ። ስኬት ከሌለ አርአያ አይኖርም ። ቅጣት ከሌለ መማርያ አይኖርም ። ንቁ ሰው ከአርአያው ይማራል ። ያልነቃው በቅጣት ይማራል ። ፍትህ አለ ማለት በሁለቱም መንገድ መማር አለ ማለት ነው ። ከሌለ ግን መማረር እንጅ መማር አይቻልም ።

ፍትህ ለእውነት መቆም ነው ። በፍትህ ዘንድ ወገንተኝነት አይሰራም ። ጥፋተኛ ዘመድ ስለሆነ ከፍርድ አያመልጥም ። ሌባ ልጅ ስለሆነ ከቅጣት አይድንም ። ወንጀለኛ ወዳጅ ስለሆነ ከእስር አይተርፍም ። ፍትህ ስጋ ብሎ አያዳላም ። ለወዳጅ ብሎ ፍርደ ገምድል አይሆንም ። ለልጅ ብሎ እውነትን አይገፋም ። ለፍትህ መኖር ማለት ለእውነት እየቆሙ ፣ መከራን እየታገሱ መኖር ነው ። እውነት የለም ማለት ፍትህ የለም ማለት ነው ። ለፍትህ የእውነት መኖር ግድ ነው ። እውነት እና ፍትህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ።

ለዚህ ነው ለመርማሪ እውነቱን ማወቅ ከባድ ፈተና የሚሆንበት ። የፍትህ መሰረቱ እውነት ስለሆነ ፣ ፍትህን የሚረግጡ እውነት እንዳትታወቅ ፣ ባለ በሌለ አቅማቸው ይታገላሉ ። ፍትህን ለማስፈን የሚተጉ ፣ እውነቱን ለማግኘት ከባድ ትግል ውስጥ ይገባሉ ። ‘’ እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል ። ‘’ እንዲባል ፣ እውነቱ ግን መታወቁ አይቀርም ። ፍትህን የነበሩት ቢያጡት ፣ የሚመጡት ማግኘታቸው አይቀርም ።

‘’ ለፍትህ እውነት እርቃኑን መሆን አልበት ። ‘’ አለች ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሞፈሪያት ካሚል ። እውነትነት አለው ። ብዙውን ጊዜ እውነት ፣ ወይ ፍቅርን አሊያም ጥላቻን መልበሱ አይቀርም ። ጥላቻን ከሚለብስ ፍቅርን ቢለብስ የተሻለ ነው ። እውነት ጥላቻን ከለበሰ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ። በጥላቻ የሚነገር እውነት ፣ ሰው ውስጥ ሀይለኛ ቁጣን ይቀሰቅሳል ። ፍትህን ለማስፈን ከመጣር ይልቅ ለበቀል ያነሳሳል ። ፍትህ አላማው ማስተማር እና መካስ ነው ። በቀል ክፋትን በክፋት መመለስ ነው ። የፍትህ መጨረሻው ሰላም እና እርቅ ነው ። የበቀል መጨረሻው ግን መጨራረስ ነው ። እውነትን ጥላቻ ማልበስ ፣ ነገርን ወደ በቀል መውሰድ ነው ። ስለዚህ ከቻልን እውነትን ፍቅርን እናልብስ ። ካልሆነ እርቃኑን ይሁን ።

ለሰው ልጅ የሚሻለው ግን ፣ ያለምንም ጥርጥር እውነትን ፍቅርን ማልበስ ነው ። ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ፣ እንደ ሀብት ከትውልድ ትውልድ ፣ ሲሸጋገር የሚመጣን በቀል ማስቆም ይቻላል ። Genetic code ( የዘረ መል ውርስ ) እስኪመስል ፣ በቀልን በደም የሚዋረስ ህብረተሰብ አለ ። በቀል ለትውልድ የሚያወርሱት ሀብት ሳይሆን እርግማን ነው ።

 ምንም ጥቅም የሌለው ርካሽ ተግባር ነው ። የፈሰሰን ውሀ ለማፈስ መታገል ነው ። ይሄ ደግሞ የራስን ውድ አላማ መዘንጋት ነው ። ህልምን ቀብሮ ራእይን አፈር ድሜ ማብላት ነው ። በትላንት ታሪክ ዛሬን ለመኖር መታገል ነው ። ትላንት ለዛሬ ግብዓት እንጅ ግብ አይደለም ። በቀለኞች ግን ለዛሬ ወይም ለነገ የሚሆን ግብ የላቸውም ። የእነርሱ ግባቸውም ህልማቸውም ትላንት ነው ። የወላጅ ክፉ ሀሳብ ማስፈጸም ነው ራእያቸው ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እውነት ጥላቻን ሲለብስ ነው ። እውነት ፍቅርን ሲለብስ ግን በተቃራኒ ነው የሚሆነው ። ወደ ይቅርታ ይመራል ። ሰው የወላጁን ሳይሆን የራሱን ህልም እንዲኖር ይረደዋል ። የራሱ ግብ እንዲኖረው አስተሳሰቡን ይቀይረዋል ። ዛሬና ነገን በአግባቡ እንዲጠቀም ያግዘዋል ። በቀለኛ ሳይሆን ፍትሀዊ እንዲሆን ያስገድደዋል ። ከምንም በላይ ጎጅውን ጥላቻ ሳይሆን ፣ ጠቃሚውን ፍቅር እንዲያስቀድም ያደርገዋል ። ፍትህ የሚረጋገጠው በፍቅር እንጅ በጥላቻ አይደለም ። በቀል ፍትህ አይሆንም ። ፍትህ ይቅርታ ማድረግ ማስተማር መቅጣት እና መካስ ነው ።  

 

 ‘’ እውነትን ፍቅር አልብሱት ፣ ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ። ‘’     

Thursday, May 29, 2025

እይታ | Perception

                                       ከራስ መጣላት

 ከራስ መጣላት የራስን እውነት አለመቀበል ነው ። የገዛ ስሜታችንን መካድ ነው ። በጠቅላላው ራስን አለመቀበል ነው ። የሰውን ልጅ ከራሱ እንዲጣላ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው ። በሰዎች ዘንድ ክብርን ለማግኘት ሲሉ ከራሳቸው የሚጣሉ አሉ ። እነዚህ ሌሎችን ለማሳመን ወሬ በመፍጠር የሚተካከላቸው የለም ። በወሬ ጤፍ ይቆላሉ ጉም ይዘግናሉ ። ያለን ነገር ሳይሆን ፣ የሌለን ነገር መፍጠር ይችላሉ ። ተውሰው መልበስ ይችላሉ ። ሰርተው መልበስ ግን አይችሉም ። ብራንድ ጫማ ማድረግ ይችላሉ ፣ መግዛት ግን አይችሉም ። የሰው ሁሉ የእነርሱ ነው ። እነርሱ ግን የሚረባ አንድም ነገር የላቸውም ። የሚለብሱት የሚጫሙት የሚዘንጡት ሁሉ በሰው ነው ። በቃ እነርሱ ምንም የሌላቸው ባዶ ናቸው ። ሰው ባዶነቱን አምኖ መቀበል ካቃተው ፣ ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም ። ቦዶነቱን አምኖ መቀበል የቻለ ግን ፣ በአዲስ ነገር ባዶነቱን መሙላት ይችላል ። ምክንያቱም ራሱን መቀበል የቻለ ትሁት ነውና ።

ራሱን የተቀበለ ሰው ለመማር ለመስራት ለማወቅ ዝግጁ ነው ። ይህ ደግሞ ባዶ ከመሆን ይጠብቀዋል ። ራስን መቀበል መልካም ነገርን ከሌሎች ለመቀበል ልብን ክፍት ያደርጋል ። መቀበል ከሌለ መለወጥ አይኖርም ። አቀባበላችን ግን ለውጣችንን ይወስነዋል ። የምንቀበለው ጥሩ ነገር ከሆነ ፣ ለውጣችን አዎንታዊ ይሆናል ። የምንቀበለው ግን መጥፎ ከሆነ ፣ ለውጣችን አሉታዊ ይሆናል ። ከራሱ የተጣላ ሰው ሀሳብ መቀበል አይችልም ። ቢቀበልም ጥሩውን ሳይሆን መጥፎውን ነው ። ስጦታ መቀበል እና መዋስ ወይም መበደር ግን ይችልበታል ።

በሰው ዘንድ ለመከበር ብሎ ከራሱ የተጣላ ፣ ትልቁ ችሎታው መዋስ ወይም መበደር ነው ። ምክንያቱም ከራሱ የተጣላ ሰው ይሉኝታ ቢስ ነው ። መስራት ያሳፍረዋል ግን መዋስ ያኮራዋል ። ተናንሶ ከመስራት ይልቅ ፣ በሰው አንሶ ላለመታየት የሚያደርገው ጥረት እጅግ ይገርማል ። ስለዚህ ሰው ለመለወጥ ራሱን መቀበል ባዶነቱን ማመን አለበት ። መዋሸት ማቆም አለበት ። ውሸት የራስን ፍሬ የሚቀብር ክፉ አረም ነው ። አረም ውሸቱን ካልነቀለ ፣ ሰው አለሙን መመልከት አይችልም ። በእጁ ያለውን ወርቅ ማስተዋል አይችልም ። በእጁ የያዘው ተራ ፣ በሌላ ሰው እጅ ያለው ተራራ መስሎ ይታየዋል ። ለመከበር ብላችሁ ከራሳችሁ አትጣሉ ። እውነተኛ ክብርን ለማግኘት ከፈለጋችሁ ፣ ከራሳችሁ ታረቁ ማንነታችሁን ተቀበሉ ።

ሌላው የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ከወዳጅ መቀያየም ነው ። በተለይ የሚያፈቅሩት ሰው ሲያስቀይም በጣም ከባድ ነው ። የተበደለው/ችው ግለሰብ የገዛ የራሱን ስሜት ይከዳል ። ከልብ የሚወዱትን ወይም የሚያፈቅሩትን ሰው ፣ ልባቸው እየፈለገ እነርሱ ግን በአፋቸው አልወደውም ወይም አልወዳትም ይላሉ ። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ እንዳላቸው ለማሳወቅ ፣ አሁንስ አይኑን አያሳየኝ በማለት ይምላሉ ። አያሳየኝ ብለው አፋቸውን ሞልተው ይምላሉ ፣ ነገር ግን በደለ የተባለው ፍቅረኛ ወይም ግለሰብ ሲመጣ ልባቸውን በፍቅር ይሞላሉ ። ያንን ሰው እየናፈቁ መቼም አይናፍቀኝም ይላሉ ። እውነቱ ግን ‘’ ማሽላ በውስጥ እያረረች ከላይ ትስቃለች ‘’ እንደሚባለው ፣ አፋቸው ልባቸውን ይከዳል እንጅ ስር የሰደደ ናፍቆት በውስጣቸው አለ ። እነዚህ ሰዎች ሰው ፊት እየሳቁ ፣ ቤት ገብተው እርር ብለው የሚያለቅሱ ፣ አሳዛኝ ፍጡራን ናቸው ። በፍቅር ምክንያት ከራስ መጣላት በሽታ ነው ።

 ስሜትን አፍኖ መያዝ ፣ ጠንካራ መስሎ ለመታየት ከራስ ጋር መታገል ፣ ላለመሸነፍ በውጥረት ውሎ በጭንቀት ማደር ። ይሄ ሁሉ እየወደዱ መጥላት የሚያመጣው መዘዝ ነው ። ከራስ መጣላት የሚፈጥረው ዱብዳ ነው ። ስለዚህ እየወደዱ ከመጥላት በይቅርታ ሰላም መፍጠር ። በእብሪት አልሸነፍ ባይ ሆኖ ከራስ ከመጣላት ፣ በትህትና እርቅ ማውረድ የተሻለ ነው ። ያኔ ከራስም ከሰውም ሰላም መሆን ይቻላል ።

ከራሳቸው ከሚጣሉ ሰዎች መሀል ፣ ችግር ከራሳቸው የሚያጣላቸው ሰዎች እጅግ ያሳዝናሉ ። እነዚህ ሰዎች ወደው ሳይሆን ተገደው ነው ከራሳቸው የሚጣሉት ። ለመኖር ሲሉ ያላመኑበትን ነገር ያደርጋሉ ። መስጠት እየፈለጉ ይከለክላሉ ። ማዳን እየፈለጉ ይገድላሉ ። መውደድ እየፈለጉ ይጠላሉ ። መቅረብ እየፈለጉ ይርቃሉ ። ማግኘት እየፈለጉ ያጣሉ ። መናገር እየፈለጉ ዝም ይላሉ ። ማልቀስ እየፈለጉ ይስቃሉ ። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ፣ በክፉዎች መሀል የሚኖሩ ሩሩ ናቸው ። ጨካኝ ሌባ እንዳለ ሁሉ ሩሩ ሌባ አለ ። ክፉ ባለስልጣን እንዳለ ሁሉ ሩሩ ባለስልጣንም አለ ። አስቸጋሪ ሰራተኛ እንዳለ ሁሉ መልካም ሰራተኛ አለ ። ችግሩ ያ አይደለም ። ክፉው ከመልካሙ ሲበዛ ነው ችግር የሚፈጠረው ። መልካሞች ከክፉዎች ከበዙ ፣ ችግር ይቀረፋል እንጅ አይፈጠርም ። ከራስ መታረቅ እንጅ ከራስ መጣላት አይኖርም ። ክፎዎች ሲበዙ ግን ከራስ መጣላት ይኖራል ።

 ክፉ ከመልካም ይልቅ ጉልበት ሲኖረው ፣ መልካም ሰዎች አቅም በማጣት ከራሳቸው ይጣላሉ ። ግፍ ሲፈጸም መናገር እየቻሉ ዝም ይላሉ ። ሰው ሲገደል ማዳን እየቻሉ እያለቀሱ ይቀብራሉ ።

ደሀ ሲበደል መድረስ እየቻሉ ይሸሻሉ ። በክፉዎች ፊት አብረው ስቀው ፣ ቤት ገብተው ግን እርር ብለው ያለቅሳሉ ። እድሜ ልክ የህሊና እረፍት አጥተው ይኖራሉ ። ሆን ብሎ ከራስ መጣላት እና ተገዶ ከራስ መጣላት ይለያያል ። ሆን ብለው ከራሳቸው የተጣሉ ፣ አምነው ስለሆነ ጫናው ለእነርሱ ቀላል ነው ። ተገደው ከሆነ ግን ስለማያምኑበት ጫናው እጅግ ከባድ ነው ። በክፉዎች መሀል ቅን ሆኖ መገኘት ከባድ ነው ። በመልካሞች መሀል ቅንቅን ሆኖ መገኘትም ከባድ ነው ። ህይወት ከመልካሞች ጋር ደስ ትላለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት የለም ።  ከክፉዎች ጋር ግን ትመራለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት ሁሌም አለ ። የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ፣ አንደኛው እና ዋነኛው ክፋት ነው ።

 

‘’ ከራስ መጣላት ራስን መካድ ነው ። ራስን መካድ ደግሞ አርቴፊሻል ህይወት መምራት ነው ። ‘’                        

Tuesday, May 27, 2025

እይታ | Perception

                                   እምነት ወይስ እውነት

   ያለ እምነትም ያለ እውነትም መኖር ከባድ ነው ። እውነት ለነጻነት ፣ እምነት ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው ። እምነት በእውነት ላይ ሲመሰረት ፣ ሰው በህይወቱ ሙሉነት ይሰመዋል ። እምነት በጥቅም ላይ ከተመሰረተ ግን ሰው በህይወቱ የሙሉነት ስሜት ይጎድለዋል ። በውሸት ማመን እርሱ የቁም ሬሳ መሆን ነው ። በውሸት ማስመሰል እንጅ መሆን አይቻልም ። ማስመሰል እውነተኛ ደስታን ሊሰጥ አይችልም ። መሆን ነው እውነተኛ ደስታን የሚፈጥረው ። እውነተኛ ደስታ ከእውነት እንጅ ከውሸት በፍጹም ሊገኝ አይችልም ። ብዙዎች ደስታን በውሸት ለማጣጣም ይሞክራሉ ። ነገር ግን እውነታው ደስታ ምን እንደሆነ በቅጡ አይረዱትም ። ምክንያቱም ውሸት የሚፈጥረው ደስታ ርካሽ እና ጊዜያዊ ነው ። እውነት የሚፈጥረው ደስታ ግን ውድ እና ዘላለማዊ ነው ።

  ውሸት እና እምነት ህይወትን እርካታ ቢስ ያደርጋሉ ። እውነት እና እምነት ግን የህሊና እርካታን ይለግሳሉ ። ሰው በውሸት ሲኖር ፣ ደስታን በራሱ መፍጠር አይችልም ። ደስታን ከሌሎች ለማግኘት ይለፋል ይደክማል ፣ ይወጣል ይወርዳል ። ደስታን ከሌሎች ማግኘት ከባድ ነው ። ከራስ ማግኘት ግን ቀላል ነው ። ደስታን ከራሱ የሚያገኝ ፣ በራሱ ደስታን መፍጠር የሚችል ነው ። እንደዚህ አይነት ሰው ደግሞ ሰውን ለማስደሰት ብሎ አይሰራም ፣ ነገር ግን ሰውን የሚያስደስት ስራ መስራት ይችላል ። ደስታን መፍጠርም መጋራትም ማጋራትም ይችላል ። ምክንያቱም ስለእውነት በእውነት ነው የሚኖረው ።

  እምነት በማስመሰል ወይም በውሸት ላይ ሲመሰረት ፣ እውነትን አይፈታተንም ።

ሰው ለብዙ ዓመት አዝሎ የኖረው እምነት ፣ ውሸት እንደሆነ ያወቀ እለት ፣ ያንን እምነት ለመተው ብዙ አይከብደውም ። ምክንያቱም ውሸት እውነትን አይበልጥም ። በውሸት የተፈጠረ እምነት ፣ በእውነት ፊት አቅም የለውም ።

     ለፍቅር እውነትን መደበቅ ግን እውነትን የሚፈታተን እምነትን ይፈጥራል ። ፍቅር የሚፈጥረው እምነት በጣም ጠንካራ ነው ። ሰው ካጣው እውነት በላይ ያገኘው ፍቅር ሲበልጥበት ፣ እውነትን አምኖ ለመቀበል ይቸገራል ። ይህንን እውነት ከሚያውቅ ፣ ባያውቅ ምርጫው ይሆናል ። ሰዎች አንዳንዴ በጣም ለሚወዳቸው ሰዎች ስለፍቅር ሲሉ ፣ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው አብረው ይኖራሉ ። እነርሱን ላለማጣት ፈርተው እውነቱን ሳይናገሩ ይዘው ይቆያሉ ። በእርግጥ  ለጥቅም ሲሉ እውነትን የሚደብቁ ክፉዎች አሉ ። እነዚህ ግን እንደ እነርሱ አይደሉም ፣ ጥቅምን ላለማጣት ሳይሆን ሰውን ላለማጣት ሲሉ ነው ፣ እውነትን የሚደብቁት ። ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር ፣ በወላጅ እና በልጅ መሀል ሲከሰት ይስተዋላል ። የስጋ ዝምድና የሌላቸው ወይም ( Biological ) ያልሆኑ ወላጆች ፣ የአብራካቸው ክፋይ ( Biological )  ያልሆነ ልጅ ያሳድጋሉ ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች እውነቱን ከመናገር ይልቅ ፣ እውነቱን መደበቅ ይመርጣሉ ። ግን በሚገርም የወላጅነት ፍቅር ያሳድጋሉ ። ይህ ፍቅር በልጅ ውስጥ ጠንካራ እምነትን ይፈጥራል ። ይህ እምነት በውሸት ብቻ እንደተፈጠረው እምነት ደካማ አይደለም ። ፍቅር የፈጥረው ሀይለኛ እምነት ነው ። ለእውነት በቀላሉ የማይረታ ብርቱ እምነት ነው ።

     ለሰው ልጅ ፍቅር የፈጠረው እምነት ፣ ከተደበቀበት እውነት ይበልጥበታል ።  

ምክንያቱም በውሸት ቢኖርም ያገኘው ፍቅር የእውነት ነው ። ያጣው እውነት ካገኘው ፍቅር አይበልጥበትም ። ለዚህም ነው ‘’ ፍቅርን ያልሰነቀ እውነት የሞተ ነው ። ‘’ የሚባለው ። ሰው አንዳንዴ እውነትን ከማጣቱ በላይ ፣ እውነትን ማወቁ ይጎዳዋል ። የሚጎዳን እውነት ማወቅ ህይወትን ያናጋል ። የሚጠቅም እውነትን ማወቅ ግን ህይወትን ያስተካክላል ። ስለዚህ ሁሉን እውነት ማወቅ አይጠቅምም ። የነበረንን ጥሩ ነገር የሚያሳጣ እውነት ባይታወቅ ይሻላል ። ያልነበረንን ጥሩ ነገር የሚያመጣ እውነት ግን ሊታወቅ ግድ ነው ። ፍቅርን የሚያሳጣ እውነት ባለበት ተደብቆ ቢቀር ይሻላል ። ፍቅርን የሚጨምር እምነት ግን ፣ ካለበት ተፈትሾ ቢገኝ መልካም ነው ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ እውነት መታወቁ አይጥቅምም ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚፈጥር እና የሚያጠነክር እውነት ተቆፍሮም ቢሆን መገኘት አለበት ። ልክ እንደ ክርስቶስ መስቀል ሱባኤ ሊያዝለት ይገባል ። በግራ በኩል እንደተሰቀለው ወንበዴ መስቀል ፣ ተገኘም አልተገኘም ፍቅርን ሰላምን መተሳሰብን የሚያሳጣ እውነት አያስፈልግም ።

 እውነት ነጻነት ነው ። ግን ሁሉም እውነት ነጻነትን አይለግስም ። ነጻነትን የሚያሳጣ እውነት አለ ። ጤናን የሚያቃውስ እውነት አለ ። ይህንን እውነት መተው የተሻለ ነው ። የሚያበራ እውነት እንጅ የሚያጨልም እውነት መታወቁ አስፈላጊ አይደለም ። ቢታወቅ የሚጎዳ እውነት አስተሳሰብን ይቀይራል ፣ በአዎንታ ሳይሆን በአሉታ ። እምነትን ይበርዛል ። ቢታወቅ መጥቀምም መጉዳትም የማይችል እውነት አለ ። ይህ እውነት ቢታወቅ የሚጨምረው ነገር የለም ። ባይታወቅም የሚቀንሰው ነገር የለም ። ኖረም አልኖረም ዋጋ ቢስ ነው ። ለዚህ እውነት ትኩረት መስጠት ጅልነት ነው ።

  ቢታወቅ የሚጠቅም እውነት ግን ህይወትን ቀያሪ ነው ፣ በአሉታ ሳይሆን በአዎንታ ። ለምሳሌ ፈጣሪን ፣ ሀይማኖትን ፣ ሳይንስን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ የሚጠቅሙ ማህበራዊ እሴቶችን ፣ ደጋግ ሰዎችን ማወቅ ፣ ህይወትን በመልካም መንገድ ይለውጣል ። ከዚህም በተጨማሪ የኔ የምትሉትን ሰው ማወቅ እፎይታን ይሰጣል ። ቤተሰብን ፣ ዘመድን ፣ ወዳጅን ማወቅ ያስደስታል ። እውነት ሀዘንም ደስታም ነው ። ከሚያሳዝን እውነት የሚያስደስት እውነት ይሻላል ። የሚያስደስት እውነት ውስጡ ፍቅር አለ ። ስለዚህ ከሚያሳዝን እውነት ፣ ያለ እውነት በፍቅር የተፈጠረ እምነት ይበልጣል ። የሚያስደስት እውነት ግን ፍቅርን የያዘ ስለሆነ ፣ እርሱ የሚፈጥረው እምነት ፣ ከሁሉም አይነት እምነት ይበልጣል ። ምክንያቱም እምነት ሁሉ በእርሱ መንገድ ነው መቀረጽ ያለበት ።  ጠቃሚ እውነትን ከፍቅር ጋር በመያዝ ። 

   ‘’ እምነት ከሚጎዳ እውነት ይበልጣል ። ከሚጠቅም እውነት ግን ያንሳል ። ‘’                              

Saturday, May 24, 2025

እይታ | Perception

                                            ክብር

    ‘’ ለአንዳንዱ ክብሩ የእሱነቱ መገለጫ ነው ። ለአንዳንዱ ደግሞ ክብሩ ሰውነቱ ነው ። ‘’ አለች ሰላም ተስፋዬ በማርትሬዛ ፊልም ላይ ። ይህን የተናገረችው በልብስ ምክንያት ከባድ ወቀሳ ደርሶባት ነው ። በነገራችን ላይ ልብስ የሰው ልጅ የማንነቱ መገለጫ እንጅ ማንነቱ ግን አይደለም ። ሰውነቱን ከፍም ዝቅም አያደርግም ። ቆሻሻ የለበሰ የአእምሮ ህመምተኛ ሰው ከመባል የሚከለክለው የለም ። ምናልባት ሰው ከሚለው መጠሪያ በፊት ፣ እብድ የሚል ተቀጽላ ከመጨመሩ በስተቀር ። ተቀጽላ ደግሞ ዋናውን የሰውን ማንነት ወይም ሰውነትን የመፋቅ አቅም የለውም ። ቅጽል ወይ ያኮስሳል አልያም ያገናል ። ሰውን ቀይሮ እንስሳ ወይም ግኡዝ ፍጥረት ሊያደርግ አይችልም ። ሰው ንጹህም ለበሰ ቆሻሻ ያው ሰው ነው ።

   ሰውን ከቆሻሻ ልብስ በላይ ክብሩን የሚያሳጣው ቆሻሻ አስተሳሰቡ ነው ። ሰው በንጹህ ልብስ ቆሻሻ ማንነቱን ለመደበቅ ከሚሞክር ፣ በንጹህ አስተሳሰብ ቆሻሻ ማንነቱን ቢያጸዳ መልካም ነው ። ገላን አጥቦ ማጽዳት ቀላል ነው ። አስተሳሰብን አጥቦ ማጽዳት ግን በጣም ከባድ ነው ። ከመነቸከ አስተሳሰብ የመነቸከ ልብስ ይሻላል ። የመነቸከን ልብስ አጥበነው ካቃተን አውጥተነው እንጥላለን ። የመነቸከን አስተሳሰብ ግን አጥበን ለማጽዳትም ፣ አውጥተን ለመጣልም በጣም አስቸጋሪ ነው ። ስለዚህ ሰው በልብሱ ከሚከበር በአስተሳሰቡ ቢከበር የተሻለ ነው ። ልብስ የሚያስከብረው በሩቁ ነው ። በርቀት በልብሱ ያከበሩትን ሲቀርቡት በአስተሳሰቡ ይንቁታል ። በልብስ የበለጸገ በስብእና የረከሰ ማንነት ክብሩ ጊዜያዊ ነው ። ዘላቂ ክብር ያለው በመልካም አስተሳሰብ የሚገነባ ውብ ስብእና ውስጥ ነው ። ልብስ ሳይሆን በዋናነት ልብ ነው ወሳኙ ።

   በቆሻሻ ልብ ላይ ጸዳል ልብስ መልበስ ፣ በአሮጌ አቁማዳ አዲሱን ወይን ማኖር ነው ። ሁለቱ ደግሞ አይስማሙም ። ወይ ወይኑ ይበላሻል አልያም አቁማዳው ይቀረደዳል ። ስለዚህ የሚሻለው አዲሱን ወይን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ነው ። ሰውነትን ባከበረ ማንነት ላይ ንጹህ ልብስ ማኖር ነው ፣ ለሰው ልጅ ዘላቂ ክብር የሚሆነው ። እውነተኛ ክብር ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ነው የሚመነጨው ። በሚታይ ነገር ለመከበር መሞከር ሞኝነት ነው ። ከሚታይ ነገር ይልቅ የማይታይ ነገር ከፍ ያለ ዋጋ አለው ። ለዚህም ነው ከሚታየው ልብስ በላይ ፣ የማይታየው ልብ የሚያስከብረው ። ሰው ለመታየት ሳይሆን ሆኖ ለማሳየት ነው መኖር ያለበት ። ለመታየት መልበስ በቂ ነው ። ለማሳየት ግን ከመልበስ ባሻገር ፣ መስራት ወይም መኖር ግድ ይላል ። የሰው ልጅ እውነተኛ ማንነት ያለው ደግሞ ፣ በመልበስ ውስጥ ሳይሆን በመኖር ውስጥ ወይም በመስራት ውስጥ ነው ። በልብስ አምሮ የሚታይ ፣ ምናልባት እላዩ የሚያምር ውስጡ የሚያማርር ፍጥረት ሊሆን ይችላል ። እላዩ ስላማረ ከሰውነት ከፍ አይልም ። አማራሪ በመሆኑ ግን ከሰውነቱ ዝቅ ባይልም ፣ በማንነቱ ላይ ሌላ ተቀጽላ ይለጠፋል ፣ አስመሳይ የሚል መገለጫ ።

   ጥሩ መልበስ ልክ አይደለም ወይም አያስፈልግም ማለት አይደለም ። ጥሩ መልበስ ራስን መንከባከብ ክብርንም መጠበቅ ነው ። ነገር ግን ሰው ራሱን መጠበቅ ያለበት ፣ በሰው ለመታየት ብቻ  መሆን የለበትም ። ለራሱ ለጤናውም ጭምር መሆን አለበት ።

 በሰው ለመታየት ሲል ጤናውን ምቾቱን ማጣት የለበትም ። ኢኮኖሚው እስኪቃወስ ፣ ኑሮው ኢስኪናጋ አምሮ ለመታየት ብዙ መድከም አይኖርበትም ። ማማር ከጤና አይበልጥም ። መዘነጥ ከአእምሮ ሰላም አይልቅም ። ዋናውን በማጣት የሚገኝ ትርፍ ዋጋ ቢስ ነው ። ዋናውን በመያዝ የሚገኝ ትርፍ ግን ጠቃሚ ነው ። መኖር ከሌለ መቀናጣት አይቻልም ። ቅንጦት ኖረም አልኖረም መኖር ይቻላል ። ለመቀናጣት መኖር ግድ ነው ። ለመኖር ግን መቀናጣት ግዴታ አይደለም ። ሰው ኖረ የሚባለው ስለተቀናጣ ሳይሆን ፣ ጤናውን እና የአእምሮ ሰላሙን መጥበቅ በመቻሉ ነው ። ለአስፈላጊው ነገር ሲባል ፣ ቅንጡውን ነገር መተው እንጅ ፣ ለቅንጡ ነገር ሲባል አስፈላጊውን ነገር ማጣት ተገቢ አይደለም ። በእርግጥ ልብስ አስፈላጊ ነገር ነው ። ነገር ግን የልብስ መሰረታዊ ጥቅሙ ፣ ገላን መሸፈን እንጅ ገላን ማሳየት አይደለም ። ገላን ለማሳየት ሲሉ ብዙዎች ጤናቸውን እስከማጣት ደርሰዋልና ። የሚመቸንን መልበስ አስፈላጊ ነው ። የማይመቸንን መልበስ ግን በሽታ ነው ። የምንችለውን መልበስ ተገቢ ነው ። የማንችለውን መልበስ ግን ቅንጦት ነው ። የሚያምርብን ልብስ ለጤና ጥሩ ነው ። የማያምርብንን ግን መልበስ ለጤና ጠንቅ ነው ። ልብስ ገላን ሲሸፍን ክብርም ውበትም ነው ። ግን ለመከበር አጉል መልበስ ክብር ያሳጣል ።

 ሰውን እኩል የሚያደርግ ልብስ ደንብም ነው ክብርም ነው ። የተማሪዎች ዩኒፎርም ፣ የሰራተኞች የስራ ልብስ ፣ የወታደሮች እና የፖሊሶች የደንብ ልብስ የሚያስከብር እናም ክብር የሚገባው ሊዩ ልብስ ነው ። እነዚህን ልብሶች መልበስ መታደል ነው ።

ነገር ግን በልብስ እከብራለው ባይ ለነዚህ ልብሶች ክብር የለውም ። ምክንያቱም ከሰው እለያለው ባይ ነው ። እሱን ከሰው የሚለየው እንጅ አንድ የሚያደርገው ነገር አይመቸውም ። በእርግጥ ሰው ከሰው ይለያያል ። በሌላ በኩል ከብዙሃኑ አንድ የሚያደርገው ፣ የሚጋራው ነገር ብዙ ነው ። ሁሉም ሰው ሊኖረው በሚችለው ነገር ልዩ ልሁን ማለት አያስከብርም ። ከሌላው በሚለየን ነገር ላይ መስራት ግን ያስከብራል ። ሰውን ከሰው የሚለየው ደግሞ ስራው እንጅ ልብሱ አይደለም ። ፈረንጀቹ ‘’ ( First impression is last impression ) ’’ ይላሉ ። የፈርስት ኢምፕረሽን አንዱ መለኪያ አለባበስ ነው ። እዚህ ጋር አለባበስ ለስራ ያለንን ክብር ነው የሚያሳየው ። ስራን ለማክበር መልበስ ያስከብራል ። ከሰው ሁሉ ለመለየት ወይም ለሰው ብሎ መልበስ ግን አያስከብርም ።

        ‘’ ክብር ልብስ ውስጥ ሳይሆን ልብ ውስጥ ነው የሚገኘው ። ‘’                               

Wednesday, May 21, 2025

እይታ | Perception

                                                   አውቆ መሸነፍ 

     አውቆ መሸነፍ ያማል ። ሰው በማስተዋል ስህተት ሲሰራ ክፉኛ ይጎዳል ። ባለማስተዋል የሚሰራ ጥፋት ብዙ ጫና የለውም ። አውቆ መሸነፍ የትህትና ውጤት ነው ። ለትእቢተኞች አውቆ መሸነፍ የሞት ያህል ከባድ ነው ። ሰው አውቆ የሚሸነፈው በዓላማ ነው ። ያ አላማ ደግሞ መልካም እንጅ ክፉ መሆን የለበትም ። ለክፋት ሆን ብለው የሚሸነፉ ፣ ዓላማቸው ማታለል ነው ። ለመልካም ነገር አውቀው የሚሸነፉ ፣ ዓላማቸው ማስተካከል ወይም ማረም ነው ። ለማታለል አውቆ መሸነፍ ተንኮለኝነት ነው ። ለማስተካከል አውቆ መሸነፍ ግን ጥበበኛነት ነው ። አውቆ መሸነፍ ዓላማው መልካም ከሆነ ፣ ነገርን በጥበብ የማብረድ መንገድ ነው ። ዓላማው መጥፎ ከሆነ ግን ፣ ክፉኛ ሰውን የመጉዳት ስልት ሆኖ ያገለግላል ። ለተንኮለኞች ሆን ብሎ መሸነፍ ፣ መንደርደሪያ ወይም መደራደሪያ ነው ። ሌላውን ለማሳመን የሚውል አሻጥር ነው ። ለጥበበኞች ግን ክፉውን መሻገሪያ እና ማሻገሪያ ነው ።

    በአውቆ መሸነፍ ውስጥ ያለ ዝቅታ ፣ በማሸነፍ ከሚገኝ ከፍታ ይበልጣል ። አውቆ ተሸናፊ በመጀመሪያ ተሸናፊ ፣ በመጨረሻ ግን ድል አድራጊ ነው ። መነሻው ማጣት ነው ፣ መዳረሻው ግን ሁሉን ማግኘት ነው ። ሰው አውቆ የሚሸነፈው አቅም ስላጣ አይደለም ፣ ሰላም ላለማጣት ነው ። ፍቅርን ለማስፈን ፣ እውነትን ለማሳወቅ እናም አብሮነትን ለማጽናት ነው ። መሸነፍ ባይኖር አብሮነት አይኖርም ። አሸንፋለው ባይ በበዛበት ቦታ ፣ ህብረት የሚባል ሀሳብ ፣ ሀሳብ እንጅ በፍጹም ተግባር ሊሆን አይችልም ። በተለይ አውቀው የሚሸነፉ ትሁታን በሌሉበት ።

ለሰላም ሆን ብለው የሚሸነፉ መሪዎች ያስፈልጋሉ ። ለፍቅር አውቀው የሚሸነፉ ምሁራን ሊኖሩ ግድ ይላል ። ለእውነት እጅ የሚሰጡ ባለጸጎች ሊበዙ ይገባል ። ለታማኝነት የሚንበረከኩ ባለሞያዎች ሊጠነክሩ ግድ ይላል ። ሀገር ሰላም ፍቅር መተሳሰብ እንዲሰፍንባት ።

     ሰው አልሸነፍ ባይ መሆን ያለበት ለችግር እንጅ ለሰላም መሆን የለበትም ። ለጠላት እንጅ ለወዳጅ መሆን የለበትም ። ለጥላቻ እንጅ ለፍቅር መሆን የለበትም ። ለውሸት እንጅ ለእውነት መሆን የለበትም ። ለሰላም ለፍቅር ለእውነት ለወዳጅነት የሚሸነፉ ፣ ምንም ይሁን ምን መጨረሻ ላይ ድል የእነርሱ ነች ። እነርሱ እየታመሙ የሚፈውሱ ፣ እያለቀሱ እንባ የሚያብሱ ፣ እየወደቁ የሚያነሱ ፣ እየተዋረዱ የሚያስከብሩ ፣ እያጡ የሚያስገኙ ሩህሩህ እና ጀግና ናቸው ። አውቀው የሚሸነፉ ትሁታን ሩህሩህም ጭምር ናቸው ። ሩህሩህ ስለሆኑ ሰውን የመረዳት አቅማቸው ከፍ ያለ ነው ። ሰውን በጥልቀት መረዳት መቻላቸው ነው ፣ ለመሸነፍ ዝግጁ ያደረጋቸው ። መሸነፍ ውስጥ ፍቅር ሰላም እውነት እና ህብረት አለ ። አልሸነፍ ባይነት ግን እነዚህን ውድ የህይወት እሴቶች ያሳጣል ።

ለችግር አልሸነፍ ባይነት መንፈሰ ጠንካራነት ነው ። ለእውነት አልሸነፍ ባይነት ግን ግትርነት ነው ። ለመከራ አልሸነፍ ባይነት አይበገሬነት ነው ። ለምክር አልሸነፍ ባይነት ግን ንቀት ነው ። ለፈተና እጅ አልሰጥም ባይነት የሞራል ልእልና ነው ። ለፍቅር አልገዛም ባይነት ግን የሞራል ውድቀት ነው ። ለሁሉም ነገር አልሸነፍ ባይነት ኢ ሞራላዊ ያደርጋል ። ለፍቅር አውቆ መሸነፍ ግን የስብእና ከፍታ የሞራል ልእልና ነው ። በድርቅና ከማሸነፍ በፍቅር መሸነፍ የተሻለ ነው ። በግትርነት ከማሸነፍ በእውነት መሸነፍ ልቆ መገኘት ነው ።

አውቆ መሸነፍ ዓለምን ከጦርነት አውድማነት ፣ የሰው ልጅን ከአሰቃቂ ሞት እና ችግር ይታደጋል ። ዛሬ አለማችን ላይ ያለውን የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ብንመለከት ፣ ሌላ የምንም ውጤት አይደለም ፣ የአልሸነፍ ባይነት መዘዝ ነው ። ለባርነት አልሸነፍ ባይነት መልካም ቢሆንም ፣ ለሰላም እጅ አልሰጥም ባይነት ግን ራስወዳድነት ነው ። ራስ ወዳዶች አልሸነፍ ባዮች ናቸው ። ለክብራቸው ጥግ ድረስ ዋጋ ይከፍላሉ ። ለሌላው ክብር ግን ደንታም የላቸውም ። ክብራቸው ከተነካ ዓለም ዶግ አመድ እስክትሆን ይዋጋሉ ። ራስ ወዳዶች ክብራቸውን የሚያጡለት ነገር ከሰውነት ውጪ ነው ። ለሰብአዊነት ቦታ የላቸውም ። ለህሊና አይገዙም ። ህሊና ሲጮህባቸው በአልኮል ያደነዝዙታል ። ያለ የሌለ ሀይላቸውን ተጠቅመው ማሸነፍ እንጅ ፣ መሸነፍ የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላት ውስጥ እንዲገኝ አይፈልጉም ። ስለዚህ በእነርሱ ምክንያት የሚራብ የሚጠማ የሚጎሳቆል የሚፈናቀል የሚንከራተት ሰብአዊ ፍጥረት ግድ አይሰጣቸውም ።

    ለእውነት ለፍቅር ለሰላም መሸነፍ እረፍት ነው ። አለመሸነፍ ግን እረፍት ማጣት ነው ። በማሰቃየት የሚገኝ እረፍት የለም ። በማታለል ውስጥ እፎይታ ሊኖር አይችልም ። አልሸነፍ ባይነት ማታለልን ማሰቃየትን ፣ ለማሸነፍ ስልት አድርጎ ይወስዳል ። አውቆ መሸነፍ ግን በስቃይ ውስጥ በማለፍ ፣ ለራስም ለሌላውም ሰው እረፍት መሆን ነው ።

ከማሸነፍ አውቆ መሸነፍ ከባድ ነው ። ማሸነፍ ሰው ላይ መስራት ነው ። መሸነፍ ግን ራስ ላይ መስራት ነው ። ሰው ሰውን ማረጋጋት ብዙ አይከብደውም ። ራሱን በራሱ ማረጋጋት ግን በጣም ይከብደዋል ። የሰውን ንዴት ለመቆጣጠር ጎበዝ ነው ፣ ነገር ግን የራሱን ንዴት ለመቆጣጠር ግን ሰነፍ ነው ። አውቆ መሸነፍ ራስን ማራጋጋት ይጠይቃል ። ንዴትን የመቆጣጠር ጥበብን ይፈልጋል ። አውቆ ተሸናፊ ራሱን ማረጋጋት ፣ ንደቱን መቆጣጠር የሚችል የስሜት ብስለት ባለቤት ነው ። ማሸነፍ ስኬት ነው ። መሸነፍ ደግሞ ሰብአዊነት ነው ። ሰውን ማሸነፍ ብቻ ሰውና ክቡር አያደርግም ። ለህሊናው ያልተሸነፈ መቼም ቢሆን አሸናፊ አይደለም ። ምክንያቱም ትክክለኛ ማሸነፍ ያለው ለህሊና መሸነፍ ውስጥ ነው ። ሰውነትም የሚኖረው ለህሊና መሸነፍ ውስጥ ነው ። አውቆ መሸነፍም ለህሊና የመገዛት ውጤት ነው ።

   ‘’ አውቆ መሸነፍ ለሰላም መማረክ ፣ ለፍቅር እጅ መስጠት ፣ ለእውነት ክብር መስጠት ፣ ለህሊና መገዛት ነው ። ‘’     

Sunday, May 18, 2025

እይታ | Perception

                                     አጉል ድፍረት

     አንድ ወጣት ነው ፣ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ፣ ከጣቢያው አጥር ጥግ ሽንቱን ይሸናል ። በጣም ነው የሚገርመው ፣ ህግን በሚያስከብር አካል ፊት ስርዓት አልበኛ መሆን ፣ ይህ አጉል ድፍረት ነው ። አጉል ድፍረት ንቀትም ነው ። ህግን መጣስ ድፍረት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ። ነገር ግን ህግን መጣስ ሳይሆን ፣ ህግን ማክበር እናም ማስከበር መቻል ነው ትክክለኛው ድፍረት ። ሰዎች እንደ ስብእናቸው እና አስተሳሰባቸው ድፍረታቸው ይለያያል ። ሰው ለመግደል የሚደፍሩ እንዳሉ ሁሉ ፣ ሰው ለማዳን ደፋር የሆኑ አሉ ። አዲስ ነገር ለመስራት የሚደፍሩ አሉ ። አዲስ ነገር ለመስረቅ ደፋር የሆኑም ብዙ አሉ ።

   ከሰው ጋር ለመጣላት በጣም ደፋር የሆኑ አሉ ። ሰው ፈርቶ ዳር ይዞ የሚመለካተቸውን ሁለት ወጠምሻዎችን ፣ ለማስታረቅ የማይፈሩ ደፋር ግን ጥበበኞች አሉ ። ለመልካም ነገር መድፈር ፣ ድፍረትን ትክክል ያደርገዋል ። ለመጥፎ ነገር መድፈር ፣ እርሱ አጉል ድፍረት ነው ። አጉል ድፍረት ጥፋት ነው ። ትክክለኛ ድፍረት ግን ልማት ነው ። ለመዋሸት መድፈር ስህተት ነው ። እውነትን ለመናገር መድፈር ግን ልክ ነው ። በእርግጥ ሁሉንም እውነት ማፍረጥረት ትክክል አይደለም ። እርሱ አጉል ድፍረት ባይሆንም ፣ የጅል ድፍረት ነው የሚሆነው ። መነገር ያለበትን እውነት መናገር ፣ መነገር የሌለበትን እውነት መያዝ መቻል ነው ትክክለኛ ድፍረት ። ይልቅ እውነቱን ከመናገር ፣ ዝምታ ትክክለኛ እና ትልቅ ድፍረትን ይጠይቃል ።

እዚህ አለም ላይ ምስጢር በማውጣት ከተገደሉት በላይ ፣ ምስጥር በመያዝ ህይወታቸውን ያጡ ይበዛሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ፊልምም ፣ ልቦለድም ፣ የገሀዱ አለም እውነታም ይህን  ነው የሚያንጸባርቁት ።

     ውሸት መናገር አጉል ድፍረት ነው ። ምክንያቱም ሰው ውሸት ሲናገር ፣ ሰውን ብቻ አይደለም የሚዋሸው ፣ የገዛ ህሊናውን እና ፈጣሪውን ጭምር ነው ። በተለይ ሰውን ለመጉዳት አስቦ መዋሸት አጉል ድፍረት ብቻ ሳይሆን ጭካኔም ነው ። ሰው ሰውን ለማዳን ቢዋሽ ፣ በሂደቱ ሳይሆን በውጤቱ ምክንያት ይመሰገናል ። ሰውን ለመጉዳት ሲዋሽ ግን ፣ ሂደቱም ውጤቱም አስከፊ ስለሆነ ፣ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ ክፉኛ ያስወቅሰዋል ። ለመዋሸት ደፋር የሆኑ ሰዎች አሉ እዚህ ምድር ላይ ፣ እነርሱም አስመሳዮች ናቸው ። አስመሳዮች ለመዋሸት ምንም አያንገራግሩም ። አስመሳይነት ለትወና ጥሩ ብቃት ( Good quality) ነው ። ለህይወት ግን መጥፎ ባህሪ ( Bad quality )  ነው ። ለትወና ግብዓቱ ፣ ለኑሮ ግን ግብዓተ መሬቱ ነው አስመሳይነት ።

      ለመዋሸት ድፍረት ማግኘት ትንሽነት ነው ። ለእውነት ግን ደፋር መሆን ጀግንነት ነው ። አጉል ድፍረት ከራስ ጋር ያጣላል ። ሰው የሌለውን አለኝ ፣ ያልሆነውን ነኝ የሚለው በአጉል ድፍረት ነው ። ገንዘብ ሳይኖረው አለኝ የሚል ፣ እውቀት ሳይኖረው አዋቂ ነኝ ብሎ የሚኮራ ፣ ውስጡ በትእቢት ተሞልቶ በአንደበቱ ትሁት ነኝ የሚል ፣ ከራሱ የተጣላ እና አጉል ደፋር የሆነ ሰው ነው ። ውሸት ከራስ ያጣላል ፣ አጉል ድፍረት ከሰውም ከራስም ያጋጫል ። ትክክለኛ ድፍረት ራስን መምሰል ነው ። የሆኑትን ማመን ያልሆኑትን መተው ነው ።

  ራስን መምሰል ከጸጸት ያድናል ። ከአጉል ድፍረትም ይገላግላል ። ራስን መምሰል ከሰው ሊያጋጭ ይችላል ። ከራስ ጋር ግን በፍጹም አያጋጭም ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ሁሌም ከራሳቸው ጋር ሰላም ናቸው ። ከሰዎች ጋር ግን በማያምኑት እና በማይቀበሉት ሀሳብ እና ድርጊት ምክንያት ሰላም ላይሆኑ ይችላሉ ። የሰላም መነሻው ከራስ መታረቅ ነው ። ከራሱ የታረቀ ደግሞ ከሰው መታረቅ ብዙ አይከብደውም ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ከራሳቸውም ከሰው ለመጣላት ሳይሆን ለመታረቅ ደፋር ናቸው ። ከራሳቸው የተጣሉ ሰዎች ግን ፣ ለመታረቅ ፈሪ ለመጣላት ደፋር ናቸው ። ምክንያቱም ከራሳቸው የተጣሉ ሰዎች ፣ ልባቸው ለይቅርታ ዝግ ነው ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ግን ልባቸው ለይቅርታ ክፍት ነው ። ይቅር ለማለትም ፣ ይቅርታ ለመጠየቅም ዝግጁ ናቸው ። አስመሳዮቹ ግን ይቅርታ ሲጠየቁ ደስ ይላቸዋል ። ይቅርታ መጠየቅ ግን ያማቸዋል ።

     ስለዚህ አጉል ድፍረት ራስን ማጣት ነው ። ድፍረትን ያለቦታው መጠቀም ነው ። ድፍረትን ያለቦታው መጠቀም ዋጋ ያስከፍላል ። ዋጋ ያስከፍላል ማለት መጨረሻው አያምርም ማለት ነው ። ድፍረትን በቦታው መጠቀምም ዋጋ ያስከፍላል ፣ ነገር ግን መጨረሻው ያምራል ። ፍጻሜው ሀዘን ሳይሆን ደስታ ነው ማለት ነው ። ድፍረት የእምነት ውጤት ነው ። አጉል እምነት አጉል ድፍረትን ይወልዳል ። ትክክለኛ እምነት ደግሞ ለክ የሆነ ድፍረትን ይፈጥራል ። ስለዚህ ድፍረትን ለማስተካከል እምነትን ማስተካከል ተገቢ ነው ። ለምሳሌ ሰውን በመናቅ የምናምን ከሆነ ፣ ድፍረታችን አጉል ይሆናል ። ሰውን በማክበር የምናምን ከሆነ ግን ፣ ድፍረታችን ትክክል ይሆናል ።

በውሸት የምናምን ከሆነ ፣ ለምንችለው ነገር ድፍረት እናጣና ፣ ለማንችለው ነገር አጉል ድፍረት ይኖረናል ። ድፍረታችን ልክ እንዲኖረው ፣ በልክ ማሰብ እና ማመን ተገቢ ነው ።

   ድፍረት ጀግና ያደርጋል ። አጉል ድፍረት ግን ጀዝባ ያደርጋል ። ያለድፍረት ስኬት የለም ። በአጉል ድፍረትም ስኬት የለም ። ያለድፍረት አዲስ ነገር መፍጠር አይቻልም ። በአጉል ድፍረትም መፍጠር አይቻልም ። ድፍረት ይጠቅማል ፣ አጉል ድፍረት ይጎዳል ። ድፍረትን በልኩና በቦታው እንጠቀም ። ከአጉል ድፍረት ግን እንጠንቀቅ ።

ሴትን ፣ ህጻናትን ፣ ሽማግሌዎችን መድፈር ፣ የአጉል ድፍረት ውጤት ነው ። አጉል ድፍረት ለወንጀል እንጅ ለስራ ትጉ አያደርግም ።

   ‘’ አጉል ድፍረት ፣ አጉል እምነት ነው ። አጉል እምነት ደግሞ የተዛባ አስተሳሰብ ነው ። ‘’                        

Wednesday, May 14, 2025

እይታ | Perception

                                                                         

                              ግጭት

     ‘’ ግጭት የህብረተሰብ አንቀሳቃሽ ሀይል ነው ‘’ ትላለች ህይወት ተፈራ ። በእርግጥ ይሄ ሀሳብ እውነትነት አለው ። ግጭት አንቀሳቃሽ ወይም አራማጅ ሀይል ነው ። ጦርነት አይደለም ግጭት ነው አንቀሳቃሽ ሀይል ። ጦርነትማ አንቀሳቃሽ ሀይል ሳይሆን አስለቃሽ ሀይል ነው ። ግጭት አስለቃሽ የሚሆነው መዳረሻው ጦርነት ሲሆን ነው ። መጨረሻው ጦርነት ካልሆነ ግን ፣ አዲስ ሀሳብ ወልዶ ፣እውቀት ጨምሮ ጥበብ አክሎ ነው የሚያልፈው ። ግጭት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ያለ የሚኖር የሚቀጥል ነገር ነው ። ግጭት እንደ ውሀ ምግብ እና ልብስ ላያስፈልግ ይችላል ። ነገር ግን እኛ ባንፈልገውም ፣ ሰዎች እስከሆንን ድረስ በህይወት ስንኖር ሁል ጊዜ የሚገጥመን የህይወት ሀቅ ነው ።

    ሰው ከራሱ ፣ ከተፈጥሮ ፣ ከሰው እናም ከፈጣሪ ይጋጫል ። ሰው ከራሱ ሲጋጭ ፣ ግጭቱን መቆጣጠር ከቻለ አዲስ ሀሳብ ይወልዳል ። መቆጣጠር ካልቻለ ግን አዲስ ጭንቀት ይወልዳል ። መቆጣጠር ከቻለ ፣ ግጭቱን በጥበብ ይፈታል ። መቆጣጠር ካቃተው ግን በጥበብ ሳይሆን በጠብ ስራ ይፈታል ። ሰው ከተፈጥሮ እና ከፈጣሪ የሚጋጨው ፣ ከራሱ መታረቅ ሲያቅተው ነው ። ከሰው ጋር የሚጋጨው ግን ፣ በአብዛኛው በአንድ ሀሳብ ፣ ስራ ወይም ጉዳይ ላይ መስማማት ወይም መስማት ሲያቅተው ነው ። ከመስማማት መስማት ይቀድማል ። መስማት ከሌለ መስማማት አይኖርም ። በብዛት ሰው ከሰው የሚጋጨው ባለመስማማት ሳይሆን ባለመስማት ነው ማለት ይቻላል ። በመስማት ከባዱ ቀላል ይሆናል ።  

ባለ መስማት ግን ቀላሉ ከባድ ይሆናል ። ቀላሉ ነገር ከባድ ሲሆን ፣ ግጭት በቀላሉ ይፈጠራል ። ከባድ የመሰለው ነገር ቀለል ሲል ግን ፣ ግጭት በቀላሉ ይፈታል ።

      ግጭት ለድራማ እና ለፊልም ውበት ነው ። ለገሀዱ ዓለም ግን መፈታት ከቻለ ውበት ነው ። መፈታት ካልቻለ ግን ውበት ሳይሆን ወበቅ ነው ። ለልቦለድ የሚያሞቅ እሳት ነው ። ለገሀዱ አለም መፈታት ከቻለ ፣ በጨለማ ውስት ያለ ውብ የእሳት ብርሀን ነው ። ካልተፈታ ግን የእሳት ብርሀን ሳይሆን ትኩሳት ነው ። ግጭትን አንቀሳቃሽ ሀይል ማድረግ የሚቻለው በጥበብ ነው ። ግጭት በአብዛኛው የሚፈጠረው ፣ በነበረ ነገር ሳይሆን ፣ እንደ አዲስ በሚፈጠር ነገር ነው ። በታየ ነገር ሳይሆን ፣ ባልታየ ነገር ነው ። በተሞከረ ሳይሆን ባልተሞከረ ፣ በተለመደ ሳይሆን ባልተለመደ ነገር ነው ።

       ሰው አዲስ ነገርን በቀላሉ ለመቀበል ይቸገራል ። አዲስ ነገር ጠቃሚም ይሁን ጎጂ ፣ በቀላሉ በሰው ዘንድ ተቀባይነትን አያገኝም ። በእርግጥ ጎጂ ነገር ፣ ከጠቃሚ ነገር ይልቅ በፍጥነት የመለመድ እድል አለው ። በዚም ተባለ በዚያ አዲስ ነገር ግጭት መፍጠሩ አይቀርም ። ግጭትን በአግባቡ ማስተናገድ የቻለ ፣ ጎጂውን በመተው ጠቃሚውን አዲስ ነገር መቀበል እናም መጠቀም ይችላል ። በአግባቡ ማስተናገድ ያልቻለ ግን ፣ ጎጂውንም ጠቃሚውንም አዲስ ነገር ሳይቀበል እናም ሳይጠቀም ይቀራል ። ግጭትን መጠቀም የሚቻለው በአግባቡ ማስተናገድ ሲቻል ነው ። አልያ ግጭት ጥቅመ ቢስ አድርጎ ያስቀረናል ።

 አዲስ ነገር አዲስ ሀሳብ ፣ አዲስ ቦታ ፣ አዲስ ልብስ ፣ አዲስ ቁስ ፣አዲስ ቁርስም ሊሆን ይችላል ።

 የሰው ልጅ በዚህ የቴክኖሎጂ እና የመረጃ ዘመን ፣ ብዙ አዲስ ነገር ይገጥመዋል ። በቅርብ ቀን አዲስ ፊልም ፣ አዲስ ፕሮግራም ፣ አዲስ እንግዳ ፣ ምን አዲስ ነገር የሚሉ የሚዲያ ልፈፋዎች ፣ ሆን ተብለው የሰው ጆሮ ለማደንቆር የሚፈጠሩ ይመስላሉ ። ነገር ግን ከሁሉም አዲስ ነገር ፣ ከባዱ አዲስ ነገር ቢኖር ፣ አዲስ ሀሳብ ነው ። ሀሳብ ከግጭት ቀጥሎ ነው ተግባር የሚሆነው ። ያለ ግጭት የሚተገበር ሀሳብ ያለ አይመስለኝም ፣ ተራ ሀሳብ ካልሆነ በስተቀር ። ተራ ሀሳብ ግጭት አያስፈልገውም ። ተራ ሀሳብ ግጭት የሚፈጥረው ፣ በነገር አካባጆች መካከል ነው ። በነገር አቅላዮች ዘንድ ፣ ተራ ሀሳብ ቦታ የለውም ። የነገር አቅላይነት ( simplicity ) አንዱ ጥቅም ፣ በተራ ሀሳብ ጊዜን አለማጥፋት ነው ።

      የሰውን ልጅ ጊዜ ከሚበሉ ነገሮች መካከል አንዱ ነገርን ማካበድ ነው ። ትንሹን ነገር ትልቅ ማድረግ ፣ ቀላሉን ነገር ማወሳሰብ ። ነገርን ማካበድ በሀሳብ እና በተግባር መካከል ያለ ግድግዳ ነው ። ሀሳብ እንዳይተገበር አመድ የሚያደርግ አሲድ ነው ። በሀሳብ እና በተግባር መሀል ከባድ ግጭት የሚፈጥረው ፣ ነገርን ማካበድ ነው ። ከራሳቸውም ከሰውም በመጋጨት በብዛት የሚታወቁት ፣ ነገርን የሚያከብዱ ሰዎች ናቸው ። ግጭት ለእነዚህ ሰዎች ፣ ወደፊት አራማጅ ሳይሆን ፣ ነገርን አላማጅ ነው ። የሚማሩበት ሳይሆን የሚኮሩበት ነው ። ግጭት ለእነርሱ የበላይነትን ማሳያ እንጅ ፣ የተሻለ ነገር ማሳያ መስታወት አይደለም ። ሌሎችን አስለቃሽ ጭስ እነርሱን አስነጋሽ ዘውድ ነው ለእነርሱ ግጭት ። ስለዚህ ለግጭት ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል አንዱ ፣ ነገርን ማካበድ ነው ማለት ይቻላል ። ነገርን በማካበድ ከግጭት ጋር ወደፊት መሄድ አይቻልም ።

          ነገርን ማቅለል የሚችሉ ሰዎች ናቸው ፣ ግጭትን እንደመስታወት የሚጠቀሙት ። ለእነርሱ ግጭት አንቀሳቃሽ ሀይል ነው ማለት ይቻላል ። በግጭት ውስጥ ራሳቸውን ያያሉ ይማራሉ ። ለእነርሱ ሀሳብ እና ተግባር አይን እና አፍንጫ ናቸው ። በሀሳብ እና በተግባር መሀል ግጭት ቢፈጠር በቀላሉ ስለሚፈቱት ፣ ሀሳብን መኖር አይከብዳቸውም ። ነገርን ማቅለል ካለ ሀሳብ ተግባር ነው ። በተቃራኒው ነገር የሚካበድ ከሆነ ፣ ሀሳብ ተግባር ሳይሆን ሀሳር ነው የሚሆነው ። በነገር ማቅለል ውስጥ ግጭት ጠቃሚ ነው ። በነገር አካባጅነት ውስጥ ግን ግጭት ጎጂ ነው ።

      ‘’ ነገርን ማቅለል ካለ ግጭት አንቀሳቃሽ ሀይል ነው ። ‘’

Friday, May 9, 2025

እይታ | Perception

                                  ሞትን መናቅ

         ሞትን መናቅ በጣም ከባድ ነው ። ሞትን ለመናቅ ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል ። ሞት የሚናቀው ተስፋ በመቁረጥ ሳይሆን በቆራጥነት ነው ። ሞትን መናቅ የቆራጥነት የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ለመራብ ቆራጥ ያልሆነ ፣ ለመሞት ድፍረት አይኖረውም ። ክብርን ለማጣት ያልደፈረ ፣ ሞትን ለመናቅ አቅም አይኖረውም ። ለመታመም ፈቃደኛ ያልሆነ ፣ ለመሞት አይደለም ስለሞት ፈጽሞ አያስብም ። በነገራችን ላይ ስኬት ያለ ህመም ጤናማ አይደለም ። ግጭት የሌለበት ወጥ ሰላም ግልጽነት ይጎድለዋል ። ፈተና የሌለበት ስራ ዘላቂ አይሆንም ። ድካም የሌለበት እንጀራ አይጣፍጥም ። መራብ የሌለበት ጥጋብ ስሜት አይኖረውም ። ማጣት የሌለበት ማግኘት ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው ።

              ሞትን ለመናቅ በመጀመሪያ የሰው ልጅ ፣ እነዚህን ነገሮች መለማመድ አለበት ። ለመታመም መፍቀድ አለበት ። ለመራብ መቁረጥ አለበት ። በፈተና መታሸት ይኖርበታል ። ለማጣት ዝግጁ መሆን አለበት ። ለመናቅ መወሰን መቻል አለበት ። በመከራ ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል ። በእነዚህ የህይወት መስመር ውስጥ ሲያልፍ ፣ ለእውነት ጠንካራ ፍቅር ያድርበታል ። ለእምነት ወይም ለታማኝነት ያለው ዋጋ ከፍ ይላል ። ለፍቅር ይንበረከካል ። ለህይወት ዓላማ ያለው እይታ በአግባቡ ይቀረጻል ። በሰብአዊነት ይታነጻል ። በሞራል ያድጋል ። ለፍትህ ይቆረቆራል ። ለሰብአዊ መብት ጠንካራ ተቀናቃኝ ይሆናል ። ለራሱም ለሌላውም ሰው ህይወት ፣ ሀላፊነት የሚሰማው በሳል ሰው ይሆናል ። ለሰው ልጅ ሁሉ ነጻነት የሚታገል ብርሀን ይሆናል ። ያኔ ሞትን ለመናቅ ድፍረት እና ወኔ ያገኛል ።

          ፍቅር ፣ እውነት ፣ እምነት ፣ ነጻነት እነዚህ ነገሮች በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ፣ ከፍ ያለ ዋጋ ነው ያላቸው ። ጥንትም ዛሬም ፣ ድሮም ዘንድሮም ፣ ወደፊትም ቢሆን ሁሌም ዉድ ናቸው ረክሰው አያውቁም ። ፍቅርን የናቀ ይረክሳል ። እውነትን ያጣጠለ ወድቆ ይቀራል ። እምነትን ያረከሰ ይዋረዳል ። ነጻነትን የተጋፋ መጨረሻው ባርነት ይሆናል ። ፍቅር ያስከብራል ። እውነት ነጻ ያወጣል ። እምነት ከሞት በላይ ያደርጋል ። ነጻነት ሰላም እና ደስታን ያጎናጽፋል ። ሞትን መናቅ ፍቅርን የማክበር ፣ እውነትን የማፍቀር ፣ እምነትን የመኖር ፣ ነጻነትን የማወቅ ውጤት ነው ።

          ሰው እስከሞት ድረስ ዋጋ የሚከፍልላቸው ፣ እንቁ እሴቶች ናቸው ፣ ፍቅር ፣ እውነት ፣ እምነት እና ነጻነት ። ያለ እነርሱ ህይወትን ማሰብ እጅግ በጣም ከባድ ነው ። የሚገርመው ህይወትን በእነርሱ መገንባትም ከባድ ነው ። ያለ እነርሱ መኖርም ፣ በእነርሱ መኖርም አስቸጋሪ ነው ። ግን ልዩነቱ እዚህ ጋር ነው ፣ ያለ እነርሱ የሚፈጠረው ችግር መራራ ነው ። በእነርሱ የሚፈጠረው ችግር ግን ጣፋጭ ነው ። ሰው ፍቅርን በመናቁ የሚገጥመው ችግር መፍትሔ አልባ ነው ። መፍትሔ ቢኖርም የሚያድን ሳይሆን የሚገድል ነው ። ስለ ፍቅር ችግር ቢገጥመው ግን የሚፈታ ነው ። መፍትሔው የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም ነው ። ህይወትን የሚያበላሽ ሳይሆን የሚያስተካክል ነው ። ስለ ፍቅር መጎዳት ክብር ነው ። ፍቅርን መናቅ ግን ፍጻሜው ውርደት ነው ።

        እውነትም እንደፍቅር ነው ፣ መጀመሪያ ላይ ዋጋ ያስከፍላል ፣ መጨረሻ ላይ ግን ጥሩ አድርጎ ይከፍላል ። ስለ እውነት የሚገጥም ችግር ወደ ከፍታ ነው የሚወስደው ።

 እውነትን በመተው የሚፈጠር ችግር ግን ጉዞው የቁልቁለት ነው ። እውነትን በመተው የሚገኝ ክብር ጊዜያዊ ነው ። እውነትን የሙጥኝ በማለት የሚገኝ ክብር ግን ዘላለማዊ ነው ። ሰው ከእውነት ጋር ቢኖርም ባይኖርም ችግር ይገጥመዋል ። ያለ እውነት በምቾት ከሚኖር ፣ ስለ እውነት ቢቸገር ይሻለዋል ። የእውነት ችግር ስጦታ እንጅ መርገም አይደለም ። እውነትን በመተው የሚፈጠር ችግር ግን በረከት ሳይሆን መርገም ነው ። ስለዚህ ስለ እውነት ዋጋ እንክፈል ፣ ዋጋ ለሌለው ነገር እውነትን ከምንተው ።

       እምነትም እንደ ፍቅር እና እውነት ተመሳሳይ ነው ። መጀመሪያ ይፈትናል በመጨረሻም ይሸልማል ። ፈተናው መሰላል እንጅ መሰናክል አይደለም ። ወደ ላይ ቢወስድ እንጅ ወደ ታች አይጥልም ። እምነትን በመካድ የሚመጣ ፈተና ግን መሰላል ሳይሆን መሰናክል ነው ። ከከፍታ አንስቶ ትቢያ ላይ ይጥላል ። እምነት የሚፈጥረው ደስታ ዘላቂ ነው ። በክህደት የሚገኝ ደስታ ግን እንደ ጳጉሜ ወር በጣም አጭር ነው ። ደስታው ወጥ ሳይሆን ጋጠወጥ ነው ። አለ ስትሉት ይጠፋል ፣ የለም ስትሉት ብቅ ይላል ። ምክንያቱም ምንጩ ትክክል ስላልሆነ ፣ ደስታውም ስርዓት ያጣል ። ስርዓት ያለው ፣ መከራ የማይበግረው ደስታ ያለው እምነት ዉስጥ ነው ።

     ነጻነት ፍቅርን የማክበር ፣ እውነትን አጥብቆ የመያዝ ፣ እምነትን በልኩ የመኖር ውጤት ነው ። ነጻ መሆን የሚቻለው ከፍቅር ፣ ከእውነት እና ከእምነት ጋር ነው ። ሰው ለውድ እቃ በጣም ብዙ ገንዘብ ሊከፍል ይችላል ፣ ህይወቱን ወይም ነፍሱን ግን በፍጹም አሳልፎ አይሰጥም ። ለምሳሌ ለወርቅ ህይወቱን አይለግስም ። ለአልማዝ ነፍሱን አሳልፎ አይሰጥም ።

 ለነጻነት ግን እስከሞት ድረስ ዋጋ ይከፍላል ። ነፍሱን አሳልፎ ይሰጣል ። ህይወቱን ያለስስት ይለግሳል ። ነጻነት ማለት ለጋራ ህግ እየተገዙ ፣ ህይወትን በራስ መምራት መቻል ነው ። ለራስ ህይወት ሙሉ ሀላፊነትን መቀበል ነው ። ነጻነት የተፈጥሮን ህግ መጻረር አይደለም ፣ ይልቅ በተቃራኒው የተፈጥሮን ህግ በተጠንቀቅ መፈጸም ነው ። የሰው ልጅ ትክክለኛ ተፈጥሮው ነጻነቱ ነው ። ነጻነት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከሆነ ፣ ተፈጥሮንም ሆነ የተፈጥሮን ህግ መቃወም ነጻነት አይደለም ። ለዚህ ነው የሰው ልጅ ነጻነቱ ሲነካ ደሙ የሚፈላው ። ምክንያቱም ነጻነት ለሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው ውድ ስጦታው ነው ።

         የሰው ልጅ የነጻነት ዋጋ ሲገባው ፣ ሞትን በመናቅ በሞት ፊት ደፋር ይሆናል ። የነጻነት ዋጋ በገንዘብ ሳይሆን የሚከፈለው ፣ በፍቅር ፣ በእውነት እናም በእምነት የሚከፈል ነው ። ፍቅር ፣ እውነት እና እምነት ሰውን በሞት ፊት ጀግና የሚያደርጉ ሀይሎች ናቸው ። ሞትን መናቅ የሚችሉ ሰዎች ፣ በፍቅር ፣ በእውነት እና በእምነት ለነጻነት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው ።

       ‘’ ፍቅር እውነት እምነት እና ነጻነት ፣ ሞትን የሚያስንቁ ሀይሎች ናቸው ። ‘’                                                                        

Tuesday, May 6, 2025

እይታ | Perception

                                                              ኢላማ

    ኢላማ  ሰው ዓላማውን ፣ ፍላጎቱን ፣ ውጥኑን ለማሳካት የሚወስደው እርምጃ ነው ። ሰውን ወደ መዳረሻው የሚወስደው ፣ የትኩረት አቅጣጫ ነው ። ኢላማ ከሌለ ስኬት የለም ። ስኬት የለም ማለት ግን ኢላማ የለም ማለት አይደለም ። ስኬት ቢኖርም ባይኖርም ፣ ኢላማ ይኖራል ። ስኬት ግን ያለ ኢላማ ፈጽሞ አይታሰብም ። ሰው ኢላማው ትክክል ከሆነ ፣ ከስኬት ጫፍ ይደርሳል ። ኢላማው ትክክል ካልሆነ ግን ፣ ከውድቀት አፋፍ ይደርሳል ። በእርግጥ ትክክለኛ ኢላማ ኖሮትም ፣ ከስኬት ጫፍ የማይደርስ ሰው አለ ። ምክንያቱ ወይ የአቅም ማነስ ነው ፣ አልያም የባህሪ ጉድለት ነው ። ጥሩ ባህሪ እናም በቂ አቅም ኖሮት ፣ ኢላማው ግን የተሳሳተ ከሆነ ፣ ሰው ለስኬት አይበቃም ። ጥሩ ባህሪ ባይኖረውም ፣ በቂ አቅም ካለው ፣ ኢላማው ትክክል ከሆነ ከስኬት የመድረስ እድሉ አለው ። ጥሩ ባህሪ ኖሮት ፣ በቂ አቅም ከሌለው ፣ ኢላማው ትክክል ቢሆንም ፣ ስኬት እና እርሱ ሆድ እና ጀርባ ናቸው ። ጥሩ ባህሪ ከበቂ አቅም ጋር ሲደመር ትክክለኛ ኢላማ ፣ ያለምንም ጥርጥር ከስኬት ማማ ያደርሳሉ ።

         ኢላማ በመጀመሪያ አቅምን ያማከለ መሆን አለበት ። ‘’ አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው ። ’’ አይደል ያለው አንጋፋው ዘፋኝ መሀሙድ አህመድ ። የሰው ልጅ ትልቁ ችሎታው አቅሙን ማወቁ ነው ። አቅሙን የማያውቅ ሰው ተሰባሪ ነው ። ስብራቱ ደግሞ የልብም የአካልም ነው ። ያለአቅሙ ያልምና አልሆን ሲለው ፣ በራስ መተማመኑን ያጣል ። እምነቱን ሲያጣ ልቡ ይሰበራል ። ልቡ ሲሰበር ክፉኛ በሀዘን ይጎዳል ። ሀዘኑ በመጨረሻ ለጤና መታወክ እና ለአካል ጉዳት ይዳርገዋል ። ህጻን ልጅን ጥሬ ስጋ ማብላት መጨረሻው ህመም ነው ። የአስር አመትን ልጅ ፣ ሀምሳ ኪሎ ዱቄት ማሸከም ፍጻሜው የአካል ጉዳት ነው ።

የአስራ አምስት አመትን ልጅ ፣ የፍልስፍና መጽሐፍ ማስነበብ ፣ መጨረሻው ሜዳሊያ ሳይሆን ሜዳ ላይ መውደቅ ነው ። ስለዚህ ኢላማ እና አቅም መመጣጠን አለባቸው ። በእርግጥ ኢላማ ከፍ ብሎ አቅም ከሚያንስ ፣ አቅም ከፍ ብሎ ኢላማ ቢያንስ የተሻለ ነው ። ኢላማ ዝቅ ማለቱ ግን እድገትን ሊገታ ይችላል ። እኩል ሲሆኑ ወይም ትንሽ ከፍ ቢል ፣ ጤናማ እድገት ይኖራል ።

       ኢላማ አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆን የለበትም ። አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ጎደሎ ለመሙላት ፣ የሌላው መጉደል አለበት ብለው ያምናሉ ። የራሳቸውን እንጀራ ለመጋገር ፣ የሌላውን ዳቦ መርገጥ አለብን ይላሉ ። ጠቅመው መጠቀም ሳይሆን ፣ ጎድተው መጠቀም ይፈልጋሉ ። ጥቅምን መጋራትም ሆነ ማጋራት ደስ አይላቸውም ። ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል ቢባሉ ፣ አብሮስ የበላ መች አብሮ ሞተ ብለው ይመልሳሉ ። ብቻውን የበላ ሳይራብ ይሞታል ። አብሮ የበላ በራብ ይደፋል ብለው ያምናሉ ። መኖር በጋራ መሞት በግል ነው ፣ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው ። እነርሱ ጋር ግን መኖርም መሞትም በግል ነው ። የሚኖሩት ለራሳቸው ነው ። ሌላው እስከጠቀማቸው ያኖሩታል ። ካልጠቀማቸው ደግሞ ያሽቀነጥሩታል ። አተርፍ ባይ አጉዳይ የሆነ ኢላማ ፣ ከስህተትም በላይ ትልቅ ስህተት ነው ። ትክክለኛ ትርፍ የጎደለን በመሙላት የሚገኝ ነው ። የሞላን በማጉደል ማትረፍ ግን ፣ ትርፍ ገንዘብ ሊያስገኝ ቢችልም ለህሊና ኪሳራ ይዳርጋል ። የጎደለን መሙላት ለሚፈልጉ ሰዎች ፣ ችግር ሲሳይ ነው ። አተርፍ ባይ አጉዳይ ለሆኑ ሰዎች ግን ችግር ስቃይ ነው ። በነገራችን ላይ ሳይንሳዊ ጥናት አላማው ጉድለት መሙላት ( Gap fill ) ነው ። ስለዚህ ችግርን እንደ ሲሳይ እንጅ እንደ ስቃይ አይመለከትም ። ለማደግ ችግርን ይፈታል እንጅ ችግርን አይፈጥርም ። እነ አትርፍ ባይ አጉዳዮች ግን ለማትረፍ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ችግርን ይፈጥራሉ ።

       አተርፍ አጉዳይ መሆን ፈጣሪ አያደርግም ። በአብዛኛው ፈጣሪዎች ሰው እናትርፍ ብለው እንጅ ገንዘብ እናትርፍ ብለው ስራ አይጀምሩም ። በሽታ ሲከሰት ሳይንቲስቱ መድሀኒት የሚፈጥረው ሰው ለማዳን ነው ። ሁለቱ ወንድማማቾች (  Right Brothers ) አውሮፕላንን የፈበረኩት የሰውን ድካም ለማቅለል ነው ። የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች ፣ የሞባይል መተግበሪያዎች የሚበለጸጉት የሰውን ልጅ ኑሮ ለማቅለል ነው ። በትክክል ከተረዳን እናም ከተጠቀምን ፣ እነዚህ ነገሮች ጫናን ከመፍጠር ይልቅ ይቀንሳሉ ። ፈጣሪዎች ኢላማቸው የተስተካከለ ስለሆነ ፣ አላማቸው ዉብ ነው ። ሰውን እያስለቀሱ ሳይሆን ፣ የሰውን እንባ በማበስ ነው የሚያተርፉት ። ሰውን በማቃለል ሳይሆን ችግርን በማቅለል ነው የሚደሰቱት ። ለዓለም የጎደላትን ይሞላሉ እንጅ ለዓለም ጉድለት አይሆኑም ።

        ትክክለኛ ዓላማ ለተስተካከለ ዒላማ ዋስትና አይሆንም ። ዓላማ ኢላማን አይወስንም ። ኢላማ ግን ዓላማን ይወስናል ። ኢላማችን ልክ ሲሆን ነው ፣ ዓላማችን እውን የሚሆነው ። ኢላማችን ስህተት ከሆነ ግን ዓላማችን ቅዥት ነው የሚሆነው ። መብት ለማግኘት መብት መንፈግ ትክክል አይደለም ። ስልጣን ለመንጠቅ ነፍስ መንጠቅ ተገቢ አይደለም ። እምነትን ለመፍጠር ከሀዲ መሆን ልክ አይደለም ። ለመታረቅ ማጣላት ተንኮል ነው ። ለመቆም መጣል ግፍ ነው ። ሳይነፍጉ ማግኘት ፣ ሳይነጥቁ መውሰድ ፣ ሳይክዱ መታመን ፣ ሳያጣሉ መታረቅ ፣ ሳይጥሉ መቆም ይቻላል ። ትክክለኛ ኢላማ ያለውም እነዚህ ውስጥ ነው ። በአለም ዙሪያ የሚዘወተር አንድ የተሳሳተ ኢላማ አለ ፣ መንግስትን ለመቀየር የህዝብን ሀብት ማውደም ። መንግስትን ለመቀየር ፣ የህዝብን ሀብት ማውደም ሳይሆን መፍትሔው ፣ ህዝብን ማሳመን ኢላማ ማድረግ ነው የሚያዋጣው ። ማውደም ሳይሆን ማሳመን ነው ትክክለኛ ኢላማው ። አባትን ለማሳመን ልጅን ኢላማ ማድረግ የተሳሳተ እርምጃ ነው ።

 ርእሰ መምህሩን ስለጠሉ ትምህርት ቤቱን ማፍረስ አምሮን ማፍረስ ነው ። መብትን ለማስከበር መንገድ መዝጋት እድልን መዝጋት ነው ።

ገበያ ለመፍጠር የሌላውን ገበያ መዝጋት ቀሽምነት ነው ። የተሳሳተ ኢላማ የመሽቀዳደም ውጤት ነው ። በመሽቀዳደም ውስጥ ፣ መቅደም ያለበት ይከተላል ፣ መከተል ያለበት ይቀድምና ነገር ይበላሻል ። ቀኙ ግራ ፣ ግራው ቀኝ ይሆናል ። መሽቀዳደም ራስ ወዳድ ያደርጋል ። ስለዚህ ለትክክለኛ ዓላማ ፣ የተሳሳተ ኢላማ እንዲኖረን ያስገድደናል ። መሽቀዳደም መከባበርን ያሳጣል ። እኔ እሻላለው እንጅ ፣ ሌላው ይሻላል ማለት በመሽቀዳደም ውስጥ ከባድ ነው ። መከበር እንጅ ማክበር ፈጽሞ አይታሰብም ። ስለዚህ አላማችን እውን እንዲሆን ፣ የተስተካከለ ኢላማ እንዲኖረን ፣ መሽቀዳደምን ማስወገድ መቻል አለብን ።

       ‘’ ኢላማ ሲስተካከል ዓላማ እውን ይሆናል ። ‘’      

Monday, May 5, 2025

እይታ | Perception

                                             

                                ጀግንነት

                               

       ጀግንነት ጠላትን ማሸነፍ ነው ። የሰው ልጅ የመጀመሪያ ጠላቱ ደግሞ አሉታዊ አስተሳሰቡ ነው ። ክፉ ሀሳቡን ማሸነፍ ያልቻለ እርሱ ጀግና አይደለም ። ጀግና ሳይሆን ደንዳና ነው ። ራሱን ለፍቅር አምበርክኮ ፣ የሌላውን ልብ በፍቅር የማረከ እርሱ ነው ጀግና ። በሀይል ወይም በጉልበት መማረክ አምባገነንነት ነው ። በፍቅር መማረክ ግን ጥበበኛነት ነው ። ስለዚህ ጀግንነት ፍቅር ውስጥ እንጅ ፣ ሀይል ውስጥ ወይም ጉልበት ዉስጥ አይገኝም ። የፍቅር ጉልበት ከፈረጠመ የአካል ጉልበት ይበረታል ። የፍቅር ሀይል ከሰራዊት ሀይል ይበልጣል ። በፍቅር ሁሉን ማሸነፍ ይቻላል ። በጉልበት ወይም በሀይል ግን ሁሉን አይደለም ጥቂቱን ማሸነፍ አይቻልም ። ሀይል ወይም ጉልበት በሂደት ይዝላል ይከዳል ። የማይከዳ ሀይል ከፈለጋችሁ ለፍቅር ተማረኩ ፣ በፍቅር ማርኩ ። ያኔ የእውነት ጀግና ትሆናላችሁ ።  ጀግንነት መግደል ሳይሆን ማዳን ነው ። ህዝብን ለማዳን እንደ ዳዊት ጎልያድን መግደል ጀግንነት ነው ። ለቁራሽ መሬት ግን ወንድምን መግደል ጅልነት ነው ። ማዳንን አላማው ያላደረገ አሸናፊነት ጀግንነት አይሆንም ። ምክንያቱም ሰውን ከማሸነፍ በላይ ጀግንነት ራስን ማሸነፍ ነውና ። ለክብሩ ለጥቅሙ ለስሙ ሲል ሽዎችን የሚደመስስ ሳይሆን ጀግና ፣ ለሺዎች ክብር ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ ነው ጀግና ።

 ከመግደል ይልቅ ለእውነት ለፍቅር ለፍትህ ለሰብአዊነት መሞት ነው ጀግንነት ። ለብዙዎች ህይወትን መስጠት እንጅ ፣ የብዙዎችን ህይወት ማጥፋት በፍጹም ጀግንነት ሊሆን አይችልም ። ማስፈራራት ወይም ማስደንገጥ ሳይሆን ፣ ማረጋጋት እና ሰላም መስጠት ነው ጀግንነት ። ማስፈራራት የሚወዱ ጀብደኞች እንጅ ጀግኖች አይደሉም ። ጀብደኞች ደግሞ ወረተኛ ማንነት እንጅ እውነተኛ ማንነት የላቸውም ። ጀግና ግን ሁል ጊዜም እውነተኛ ነው ። ለመወደስ ብሎ አያስመስልም ። ላለመወቀስ ፈርቶም ነጩን እውነት አይክድም ። እርሱ ምን ጊዜም የትም ቦታ ያው ራሱ ነው ። ካናዳም ሄደ ጅዳ ፣ አሜሪካም ሆነ ደቡብ አፍሪካ ፣ ኢትዮጵያም ይኑር ዩጎስላቪያ ለእርሱ ለውጥ የለዉም ። የትም ይሁን ከሰዉነቱ ከፍ ዝቅ አይልም ። በቃ ሰው ነው ራሱን የሆነ ሰው ። ጀግንነት አለማስመሰል እውነተኝነት ራስን መሆን ነው ።

      ጀግንነት ችግር መፍታት እንጅ ችግር መፍጠር አይደለም ። ከተማን ማመስ ጀግንነት አይደለም ። እንደ እናቶቻችን ምጣድ ማመስ ነው ጀግንነት ። ዛሬ ሁላችንም በሚባል ደረጃ ለክብር የበቃነው ፣ በጀግኖች እናቶቻችን በታመሰ ምጣድ ላይ በተጋገረ እንጀራ  ነው ። ክብር ለእናቶቻችን ! ጀግንነት እንዲህ ነው ። ሰው እንዲበላ ምግብ መስጠት እንጅ ፣ ሰው እንዲራብ ምግብ መከልከል ጀግንነት አይደለም ። ጀግንነት መስጠት እንጅ መከልከል አይደለም  ስራ መስራት እንጅ ሴራ ወይም ተንኮል መሸረብ አይደለም ። ሆ ብሎ ማመጽ ሳይሆን ሆ ብሎ መስራት ነው ጀግንነት ። በጋራ ማፍረስ ሳይሆን በአንድነት መገንባት ነው ጀኝነት ። እርስ በእርስ መጋደል ሳይሆን ፣ በህብረት ጥላቻን መግደል ነው ጀግንነት ። የእርስ በእርስ ጦርነት ጀግና የለውም ። ጀግናም ካለ ለጦርነቱ መቆም ፣ የቶክስ አቁም ስምምነት ያወጀ ነው ። ጀግንነት ሰውን መግደል ሳይሆን ፣ የጥላቻን ሃሳብ እና አስተሳሰብ መግደል ነው ። ልክ እንደ አብርሀም ሊንከን ጠላትን በጦር ሳይሆን ፣ በፍቅር ገድሎ ጀግና መሆን ። ድል በሀይል ከተገኘ ኢ እኩልነት ይፈጠራል ፣ ፍትህ ይዛባል ። ድል በፍቅር እውን ከሆነ ግን ፣ እኩልነት ይሰፍናል ፍትህ ይረጋገጣል ። በምድራችን የሰው ልጅ እኩልነት እንዲሰፍን ፣ መትረየስን ሳይሆን ፍቅርን መሳሪያ እናድርግ ።

      ጀግንነት በመከራ ውስጥ ተስፋን መያዝ ነው ። ከድቅድቁ ጨለማ ጀርባ የብርሀን ጮራ እንዳለ ማሰብ ነው ። ከህመም ለጥቆ ጤና ፣ ከችግር ቀጥሎ መፍትሔ ፣ ከጭንቀት ባሻገር መረጋጋት ፣ ከጦርነት ጀርባ ሰላም እንደሚመጣ ማመን ነው ።

በጦርነት ተስፋ ከመቁረት ይልቅ ፣ ወደ ሰላም ትኬት መቁረት ነው ጀግንነት ። በማጣት ተስፋ ከመቁረት ይልቅ ፣ ለማግኘት ቆርጦ መነሳት ነው ጀግንነት ። ፈተና ዉስጥ እድል ፣ ዝቅታ ዉስጥ ከፍታ ፣ መናቅ ዉስጥ ክብር እንዳለ ማየት ነው ጀግንነት ። ሲወድቁ ተስፋ ቢስ መሆን ሳይሆን ፣ ለመነሳት ጥረት ማድረግ ነው ጀግንነት ።

እውነተኛ ጀግና የሚፈጠረው ፣ በጦር ብዛት ሳይሆን ፣ በእምነት እና በተስፋ ብዛት ነው ። ከሁለቱ በማይለየው ነገር ግን ከሁለቱ በሚበልጠው ፍቅር ደግሞ ፣ ከሁሉ የላቀ ጀግና ይወለዳል ።

‘’ እምነት ተስፋ ፍቅር በአንድነት ይጸናሉ ፣ ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል ። ’’ እንዲል ታላቁ መጽሐፍ ።

   

   ‘’ ጀግንነት የሀይል መገለጫ ሳይሆን ፣ የፍቅር መገለጫ ነው ። ‘’                     

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...