Friday, May 9, 2025

እይታ | Perception

                                  ሞትን መናቅ

         ሞትን መናቅ በጣም ከባድ ነው ። ሞትን ለመናቅ ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል ። ሞት የሚናቀው ተስፋ በመቁረጥ ሳይሆን በቆራጥነት ነው ። ሞትን መናቅ የቆራጥነት የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ለመራብ ቆራጥ ያልሆነ ፣ ለመሞት ድፍረት አይኖረውም ። ክብርን ለማጣት ያልደፈረ ፣ ሞትን ለመናቅ አቅም አይኖረውም ። ለመታመም ፈቃደኛ ያልሆነ ፣ ለመሞት አይደለም ስለሞት ፈጽሞ አያስብም ። በነገራችን ላይ ስኬት ያለ ህመም ጤናማ አይደለም ። ግጭት የሌለበት ወጥ ሰላም ግልጽነት ይጎድለዋል ። ፈተና የሌለበት ስራ ዘላቂ አይሆንም ። ድካም የሌለበት እንጀራ አይጣፍጥም ። መራብ የሌለበት ጥጋብ ስሜት አይኖረውም ። ማጣት የሌለበት ማግኘት ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው ።

              ሞትን ለመናቅ በመጀመሪያ የሰው ልጅ ፣ እነዚህን ነገሮች መለማመድ አለበት ። ለመታመም መፍቀድ አለበት ። ለመራብ መቁረጥ አለበት ። በፈተና መታሸት ይኖርበታል ። ለማጣት ዝግጁ መሆን አለበት ። ለመናቅ መወሰን መቻል አለበት ። በመከራ ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል ። በእነዚህ የህይወት መስመር ውስጥ ሲያልፍ ፣ ለእውነት ጠንካራ ፍቅር ያድርበታል ። ለእምነት ወይም ለታማኝነት ያለው ዋጋ ከፍ ይላል ። ለፍቅር ይንበረከካል ። ለህይወት ዓላማ ያለው እይታ በአግባቡ ይቀረጻል ። በሰብአዊነት ይታነጻል ። በሞራል ያድጋል ። ለፍትህ ይቆረቆራል ። ለሰብአዊ መብት ጠንካራ ተቀናቃኝ ይሆናል ። ለራሱም ለሌላውም ሰው ህይወት ፣ ሀላፊነት የሚሰማው በሳል ሰው ይሆናል ። ለሰው ልጅ ሁሉ ነጻነት የሚታገል ብርሀን ይሆናል ። ያኔ ሞትን ለመናቅ ድፍረት እና ወኔ ያገኛል ።

          ፍቅር ፣ እውነት ፣ እምነት ፣ ነጻነት እነዚህ ነገሮች በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ፣ ከፍ ያለ ዋጋ ነው ያላቸው ። ጥንትም ዛሬም ፣ ድሮም ዘንድሮም ፣ ወደፊትም ቢሆን ሁሌም ዉድ ናቸው ረክሰው አያውቁም ። ፍቅርን የናቀ ይረክሳል ። እውነትን ያጣጠለ ወድቆ ይቀራል ። እምነትን ያረከሰ ይዋረዳል ። ነጻነትን የተጋፋ መጨረሻው ባርነት ይሆናል ። ፍቅር ያስከብራል ። እውነት ነጻ ያወጣል ። እምነት ከሞት በላይ ያደርጋል ። ነጻነት ሰላም እና ደስታን ያጎናጽፋል ። ሞትን መናቅ ፍቅርን የማክበር ፣ እውነትን የማፍቀር ፣ እምነትን የመኖር ፣ ነጻነትን የማወቅ ውጤት ነው ።

          ሰው እስከሞት ድረስ ዋጋ የሚከፍልላቸው ፣ እንቁ እሴቶች ናቸው ፣ ፍቅር ፣ እውነት ፣ እምነት እና ነጻነት ። ያለ እነርሱ ህይወትን ማሰብ እጅግ በጣም ከባድ ነው ። የሚገርመው ህይወትን በእነርሱ መገንባትም ከባድ ነው ። ያለ እነርሱ መኖርም ፣ በእነርሱ መኖርም አስቸጋሪ ነው ። ግን ልዩነቱ እዚህ ጋር ነው ፣ ያለ እነርሱ የሚፈጠረው ችግር መራራ ነው ። በእነርሱ የሚፈጠረው ችግር ግን ጣፋጭ ነው ። ሰው ፍቅርን በመናቁ የሚገጥመው ችግር መፍትሔ አልባ ነው ። መፍትሔ ቢኖርም የሚያድን ሳይሆን የሚገድል ነው ። ስለ ፍቅር ችግር ቢገጥመው ግን የሚፈታ ነው ። መፍትሔው የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም ነው ። ህይወትን የሚያበላሽ ሳይሆን የሚያስተካክል ነው ። ስለ ፍቅር መጎዳት ክብር ነው ። ፍቅርን መናቅ ግን ፍጻሜው ውርደት ነው ።

        እውነትም እንደፍቅር ነው ፣ መጀመሪያ ላይ ዋጋ ያስከፍላል ፣ መጨረሻ ላይ ግን ጥሩ አድርጎ ይከፍላል ። ስለ እውነት የሚገጥም ችግር ወደ ከፍታ ነው የሚወስደው ።

 እውነትን በመተው የሚፈጠር ችግር ግን ጉዞው የቁልቁለት ነው ። እውነትን በመተው የሚገኝ ክብር ጊዜያዊ ነው ። እውነትን የሙጥኝ በማለት የሚገኝ ክብር ግን ዘላለማዊ ነው ። ሰው ከእውነት ጋር ቢኖርም ባይኖርም ችግር ይገጥመዋል ። ያለ እውነት በምቾት ከሚኖር ፣ ስለ እውነት ቢቸገር ይሻለዋል ። የእውነት ችግር ስጦታ እንጅ መርገም አይደለም ። እውነትን በመተው የሚፈጠር ችግር ግን በረከት ሳይሆን መርገም ነው ። ስለዚህ ስለ እውነት ዋጋ እንክፈል ፣ ዋጋ ለሌለው ነገር እውነትን ከምንተው ።

       እምነትም እንደ ፍቅር እና እውነት ተመሳሳይ ነው ። መጀመሪያ ይፈትናል በመጨረሻም ይሸልማል ። ፈተናው መሰላል እንጅ መሰናክል አይደለም ። ወደ ላይ ቢወስድ እንጅ ወደ ታች አይጥልም ። እምነትን በመካድ የሚመጣ ፈተና ግን መሰላል ሳይሆን መሰናክል ነው ። ከከፍታ አንስቶ ትቢያ ላይ ይጥላል ። እምነት የሚፈጥረው ደስታ ዘላቂ ነው ። በክህደት የሚገኝ ደስታ ግን እንደ ጳጉሜ ወር በጣም አጭር ነው ። ደስታው ወጥ ሳይሆን ጋጠወጥ ነው ። አለ ስትሉት ይጠፋል ፣ የለም ስትሉት ብቅ ይላል ። ምክንያቱም ምንጩ ትክክል ስላልሆነ ፣ ደስታውም ስርዓት ያጣል ። ስርዓት ያለው ፣ መከራ የማይበግረው ደስታ ያለው እምነት ዉስጥ ነው ።

     ነጻነት ፍቅርን የማክበር ፣ እውነትን አጥብቆ የመያዝ ፣ እምነትን በልኩ የመኖር ውጤት ነው ። ነጻ መሆን የሚቻለው ከፍቅር ፣ ከእውነት እና ከእምነት ጋር ነው ። ሰው ለውድ እቃ በጣም ብዙ ገንዘብ ሊከፍል ይችላል ፣ ህይወቱን ወይም ነፍሱን ግን በፍጹም አሳልፎ አይሰጥም ። ለምሳሌ ለወርቅ ህይወቱን አይለግስም ። ለአልማዝ ነፍሱን አሳልፎ አይሰጥም ።

 ለነጻነት ግን እስከሞት ድረስ ዋጋ ይከፍላል ። ነፍሱን አሳልፎ ይሰጣል ። ህይወቱን ያለስስት ይለግሳል ። ነጻነት ማለት ለጋራ ህግ እየተገዙ ፣ ህይወትን በራስ መምራት መቻል ነው ። ለራስ ህይወት ሙሉ ሀላፊነትን መቀበል ነው ። ነጻነት የተፈጥሮን ህግ መጻረር አይደለም ፣ ይልቅ በተቃራኒው የተፈጥሮን ህግ በተጠንቀቅ መፈጸም ነው ። የሰው ልጅ ትክክለኛ ተፈጥሮው ነጻነቱ ነው ። ነጻነት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከሆነ ፣ ተፈጥሮንም ሆነ የተፈጥሮን ህግ መቃወም ነጻነት አይደለም ። ለዚህ ነው የሰው ልጅ ነጻነቱ ሲነካ ደሙ የሚፈላው ። ምክንያቱም ነጻነት ለሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው ውድ ስጦታው ነው ።

         የሰው ልጅ የነጻነት ዋጋ ሲገባው ፣ ሞትን በመናቅ በሞት ፊት ደፋር ይሆናል ። የነጻነት ዋጋ በገንዘብ ሳይሆን የሚከፈለው ፣ በፍቅር ፣ በእውነት እናም በእምነት የሚከፈል ነው ። ፍቅር ፣ እውነት እና እምነት ሰውን በሞት ፊት ጀግና የሚያደርጉ ሀይሎች ናቸው ። ሞትን መናቅ የሚችሉ ሰዎች ፣ በፍቅር ፣ በእውነት እና በእምነት ለነጻነት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው ።

       ‘’ ፍቅር እውነት እምነት እና ነጻነት ፣ ሞትን የሚያስንቁ ሀይሎች ናቸው ። ‘’                                                                        

No comments:

Post a Comment

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...