ግጭት
‘’ ግጭት የህብረተሰብ አንቀሳቃሽ ሀይል ነው ‘’ ትላለች ህይወት ተፈራ
። በእርግጥ ይሄ ሀሳብ እውነትነት አለው ። ግጭት አንቀሳቃሽ ወይም አራማጅ ሀይል ነው ። ጦርነት አይደለም ግጭት ነው አንቀሳቃሽ
ሀይል ። ጦርነትማ አንቀሳቃሽ ሀይል ሳይሆን አስለቃሽ ሀይል ነው ። ግጭት አስለቃሽ የሚሆነው መዳረሻው ጦርነት ሲሆን ነው ። መጨረሻው
ጦርነት ካልሆነ ግን ፣ አዲስ ሀሳብ ወልዶ ፣እውቀት ጨምሮ ጥበብ አክሎ ነው የሚያልፈው ። ግጭት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ያለ
የሚኖር የሚቀጥል ነገር ነው ። ግጭት እንደ ውሀ ምግብ እና ልብስ ላያስፈልግ ይችላል ። ነገር ግን እኛ ባንፈልገውም ፣ ሰዎች
እስከሆንን ድረስ በህይወት ስንኖር ሁል ጊዜ የሚገጥመን የህይወት ሀቅ ነው ።
ሰው ከራሱ ፣ ከተፈጥሮ ፣ ከሰው እናም ከፈጣሪ ይጋጫል ። ሰው ከራሱ
ሲጋጭ ፣ ግጭቱን መቆጣጠር ከቻለ አዲስ ሀሳብ ይወልዳል ። መቆጣጠር ካልቻለ ግን አዲስ ጭንቀት ይወልዳል ። መቆጣጠር ከቻለ ፣
ግጭቱን በጥበብ ይፈታል ። መቆጣጠር ካቃተው ግን በጥበብ ሳይሆን በጠብ ስራ ይፈታል ። ሰው ከተፈጥሮ እና ከፈጣሪ የሚጋጨው ፣
ከራሱ መታረቅ ሲያቅተው ነው ። ከሰው ጋር የሚጋጨው ግን ፣ በአብዛኛው በአንድ ሀሳብ ፣ ስራ ወይም ጉዳይ ላይ መስማማት ወይም
መስማት ሲያቅተው ነው ። ከመስማማት መስማት ይቀድማል ። መስማት ከሌለ መስማማት አይኖርም ። በብዛት ሰው ከሰው የሚጋጨው ባለመስማማት
ሳይሆን ባለመስማት ነው ማለት ይቻላል ። በመስማት ከባዱ ቀላል ይሆናል ።
ባለ መስማት ግን ቀላሉ ከባድ ይሆናል ።
ቀላሉ ነገር ከባድ ሲሆን ፣ ግጭት በቀላሉ ይፈጠራል ። ከባድ የመሰለው ነገር ቀለል ሲል ግን ፣ ግጭት በቀላሉ ይፈታል ።
ግጭት ለድራማ እና ለፊልም ውበት ነው ። ለገሀዱ ዓለም ግን መፈታት
ከቻለ ውበት ነው ። መፈታት ካልቻለ ግን ውበት ሳይሆን ወበቅ ነው ። ለልቦለድ የሚያሞቅ እሳት ነው ። ለገሀዱ አለም መፈታት ከቻለ
፣ በጨለማ ውስት ያለ ውብ የእሳት ብርሀን ነው ። ካልተፈታ ግን የእሳት ብርሀን ሳይሆን ትኩሳት ነው ። ግጭትን አንቀሳቃሽ ሀይል
ማድረግ የሚቻለው በጥበብ ነው ። ግጭት በአብዛኛው የሚፈጠረው ፣ በነበረ ነገር ሳይሆን ፣ እንደ አዲስ በሚፈጠር ነገር ነው ።
በታየ ነገር ሳይሆን ፣ ባልታየ ነገር ነው ። በተሞከረ ሳይሆን ባልተሞከረ ፣ በተለመደ ሳይሆን ባልተለመደ ነገር ነው ።
ሰው አዲስ ነገርን በቀላሉ ለመቀበል ይቸገራል ። አዲስ ነገር ጠቃሚም
ይሁን ጎጂ ፣ በቀላሉ በሰው ዘንድ ተቀባይነትን አያገኝም ። በእርግጥ ጎጂ ነገር ፣ ከጠቃሚ ነገር ይልቅ በፍጥነት የመለመድ እድል
አለው ። በዚም ተባለ በዚያ አዲስ ነገር ግጭት መፍጠሩ አይቀርም ። ግጭትን በአግባቡ ማስተናገድ የቻለ ፣ ጎጂውን በመተው ጠቃሚውን
አዲስ ነገር መቀበል እናም መጠቀም ይችላል ። በአግባቡ ማስተናገድ ያልቻለ ግን ፣ ጎጂውንም ጠቃሚውንም አዲስ ነገር ሳይቀበል እናም
ሳይጠቀም ይቀራል ። ግጭትን መጠቀም የሚቻለው በአግባቡ ማስተናገድ ሲቻል ነው ። አልያ ግጭት ጥቅመ ቢስ አድርጎ ያስቀረናል ።
አዲስ ነገር አዲስ ሀሳብ ፣ አዲስ ቦታ ፣ አዲስ ልብስ ፣ አዲስ ቁስ ፣አዲስ
ቁርስም ሊሆን ይችላል ።
የሰው ልጅ በዚህ የቴክኖሎጂ እና የመረጃ ዘመን ፣ ብዙ አዲስ ነገር ይገጥመዋል
። በቅርብ ቀን አዲስ ፊልም ፣ አዲስ ፕሮግራም ፣ አዲስ እንግዳ ፣ ምን አዲስ ነገር የሚሉ የሚዲያ ልፈፋዎች ፣ ሆን ተብለው የሰው
ጆሮ ለማደንቆር የሚፈጠሩ ይመስላሉ ። ነገር ግን ከሁሉም አዲስ ነገር ፣ ከባዱ አዲስ ነገር ቢኖር ፣ አዲስ ሀሳብ ነው ። ሀሳብ
ከግጭት ቀጥሎ ነው ተግባር የሚሆነው ። ያለ ግጭት የሚተገበር ሀሳብ ያለ አይመስለኝም ፣ ተራ ሀሳብ ካልሆነ በስተቀር ። ተራ ሀሳብ
ግጭት አያስፈልገውም ። ተራ ሀሳብ ግጭት የሚፈጥረው ፣ በነገር አካባጆች መካከል ነው ። በነገር አቅላዮች ዘንድ ፣ ተራ ሀሳብ
ቦታ የለውም ። የነገር አቅላይነት ( simplicity ) አንዱ ጥቅም ፣ በተራ ሀሳብ ጊዜን አለማጥፋት
ነው ።
የሰውን ልጅ ጊዜ ከሚበሉ ነገሮች መካከል አንዱ ነገርን ማካበድ ነው
። ትንሹን ነገር ትልቅ ማድረግ ፣ ቀላሉን ነገር ማወሳሰብ ። ነገርን ማካበድ በሀሳብ እና በተግባር መካከል ያለ ግድግዳ ነው ።
ሀሳብ እንዳይተገበር አመድ የሚያደርግ አሲድ ነው ። በሀሳብ እና በተግባር መሀል ከባድ ግጭት የሚፈጥረው ፣ ነገርን ማካበድ ነው
። ከራሳቸውም ከሰውም በመጋጨት በብዛት የሚታወቁት ፣ ነገርን የሚያከብዱ ሰዎች ናቸው ። ግጭት ለእነዚህ ሰዎች ፣ ወደፊት አራማጅ
ሳይሆን ፣ ነገርን አላማጅ ነው ። የሚማሩበት ሳይሆን የሚኮሩበት ነው ። ግጭት ለእነርሱ የበላይነትን ማሳያ እንጅ ፣ የተሻለ ነገር
ማሳያ መስታወት አይደለም ። ሌሎችን አስለቃሽ ጭስ እነርሱን አስነጋሽ ዘውድ ነው ለእነርሱ ግጭት ። ስለዚህ ለግጭት ምክንያት ናቸው
ተብለው ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል አንዱ ፣ ነገርን ማካበድ ነው ማለት ይቻላል ። ነገርን በማካበድ ከግጭት ጋር ወደፊት መሄድ አይቻልም
።
ነገርን ማቅለል የሚችሉ ሰዎች ናቸው ፣ ግጭትን እንደመስታወት
የሚጠቀሙት ። ለእነርሱ ግጭት አንቀሳቃሽ ሀይል ነው ማለት ይቻላል ። በግጭት ውስጥ ራሳቸውን ያያሉ ይማራሉ ። ለእነርሱ ሀሳብ
እና ተግባር አይን እና አፍንጫ ናቸው ። በሀሳብ እና በተግባር መሀል ግጭት ቢፈጠር በቀላሉ ስለሚፈቱት ፣ ሀሳብን መኖር አይከብዳቸውም
። ነገርን ማቅለል ካለ ሀሳብ ተግባር ነው ። በተቃራኒው ነገር የሚካበድ ከሆነ ፣ ሀሳብ ተግባር ሳይሆን ሀሳር ነው የሚሆነው ።
በነገር ማቅለል ውስጥ ግጭት ጠቃሚ ነው ። በነገር አካባጅነት ውስጥ ግን ግጭት ጎጂ ነው ።
‘’ ነገርን ማቅለል ካለ ግጭት አንቀሳቃሽ
ሀይል ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment