አጉል ድፍረት
አንድ ወጣት ነው ፣ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ፣ ከጣቢያው አጥር ጥግ ሽንቱን ይሸናል ። በጣም ነው የሚገርመው ፣ ህግን በሚያስከብር አካል ፊት ስርዓት አልበኛ መሆን ፣ ይህ አጉል ድፍረት ነው ። አጉል ድፍረት ንቀትም ነው ። ህግን መጣስ ድፍረት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ። ነገር ግን ህግን መጣስ ሳይሆን ፣ ህግን ማክበር እናም ማስከበር መቻል ነው ትክክለኛው ድፍረት ። ሰዎች እንደ ስብእናቸው እና አስተሳሰባቸው ድፍረታቸው ይለያያል ። ሰው ለመግደል የሚደፍሩ እንዳሉ ሁሉ ፣ ሰው ለማዳን ደፋር የሆኑ አሉ ። አዲስ ነገር ለመስራት የሚደፍሩ አሉ ። አዲስ ነገር ለመስረቅ ደፋር የሆኑም ብዙ አሉ ።
ከሰው ጋር ለመጣላት በጣም ደፋር የሆኑ አሉ ። ሰው ፈርቶ ዳር ይዞ የሚመለካተቸውን ሁለት ወጠምሻዎችን ፣ ለማስታረቅ የማይፈሩ ደፋር ግን ጥበበኞች አሉ ። ለመልካም ነገር መድፈር ፣ ድፍረትን ትክክል ያደርገዋል ። ለመጥፎ ነገር መድፈር ፣ እርሱ አጉል ድፍረት ነው ። አጉል ድፍረት ጥፋት ነው ። ትክክለኛ ድፍረት ግን ልማት ነው ። ለመዋሸት መድፈር ስህተት ነው ። እውነትን ለመናገር መድፈር ግን ልክ ነው ። በእርግጥ ሁሉንም እውነት ማፍረጥረት ትክክል አይደለም ። እርሱ አጉል ድፍረት ባይሆንም ፣ የጅል ድፍረት ነው የሚሆነው ። መነገር ያለበትን እውነት መናገር ፣ መነገር የሌለበትን እውነት መያዝ መቻል ነው ትክክለኛ ድፍረት ። ይልቅ እውነቱን ከመናገር ፣ ዝምታ ትክክለኛ እና ትልቅ ድፍረትን ይጠይቃል ።
እዚህ አለም ላይ ምስጢር በማውጣት ከተገደሉት በላይ ፣ ምስጥር በመያዝ ህይወታቸውን ያጡ ይበዛሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ፊልምም ፣ ልቦለድም ፣ የገሀዱ አለም እውነታም ይህን ነው የሚያንጸባርቁት ።
ውሸት መናገር አጉል ድፍረት ነው ። ምክንያቱም ሰው ውሸት ሲናገር ፣ ሰውን ብቻ አይደለም የሚዋሸው ፣ የገዛ ህሊናውን እና ፈጣሪውን ጭምር ነው ። በተለይ ሰውን ለመጉዳት አስቦ መዋሸት አጉል ድፍረት ብቻ ሳይሆን ጭካኔም ነው ። ሰው ሰውን ለማዳን ቢዋሽ ፣ በሂደቱ ሳይሆን በውጤቱ ምክንያት ይመሰገናል ። ሰውን ለመጉዳት ሲዋሽ ግን ፣ ሂደቱም ውጤቱም አስከፊ ስለሆነ ፣ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ ክፉኛ ያስወቅሰዋል ። ለመዋሸት ደፋር የሆኑ ሰዎች አሉ እዚህ ምድር ላይ ፣ እነርሱም አስመሳዮች ናቸው ። አስመሳዮች ለመዋሸት ምንም አያንገራግሩም ። አስመሳይነት ለትወና ጥሩ ብቃት ( Good quality) ነው ። ለህይወት ግን መጥፎ ባህሪ ( Bad quality ) ነው ። ለትወና ግብዓቱ ፣ ለኑሮ ግን ግብዓተ መሬቱ ነው አስመሳይነት ።
ለመዋሸት ድፍረት ማግኘት ትንሽነት ነው ። ለእውነት ግን ደፋር መሆን ጀግንነት ነው ። አጉል ድፍረት ከራስ ጋር ያጣላል ። ሰው የሌለውን አለኝ ፣ ያልሆነውን ነኝ የሚለው በአጉል ድፍረት ነው ። ገንዘብ ሳይኖረው አለኝ የሚል ፣ እውቀት ሳይኖረው አዋቂ ነኝ ብሎ የሚኮራ ፣ ውስጡ በትእቢት ተሞልቶ በአንደበቱ ትሁት ነኝ የሚል ፣ ከራሱ የተጣላ እና አጉል ደፋር የሆነ ሰው ነው ። ውሸት ከራስ ያጣላል ፣ አጉል ድፍረት ከሰውም ከራስም ያጋጫል ። ትክክለኛ ድፍረት ራስን መምሰል ነው ። የሆኑትን ማመን ያልሆኑትን መተው ነው ።
ራስን መምሰል ከጸጸት ያድናል ። ከአጉል ድፍረትም ይገላግላል ። ራስን መምሰል ከሰው ሊያጋጭ ይችላል ። ከራስ ጋር ግን በፍጹም አያጋጭም ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ሁሌም ከራሳቸው ጋር ሰላም ናቸው ። ከሰዎች ጋር ግን በማያምኑት እና በማይቀበሉት ሀሳብ እና ድርጊት ምክንያት ሰላም ላይሆኑ ይችላሉ ። የሰላም መነሻው ከራስ መታረቅ ነው ። ከራሱ የታረቀ ደግሞ ከሰው መታረቅ ብዙ አይከብደውም ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ከራሳቸውም ከሰው ለመጣላት ሳይሆን ለመታረቅ ደፋር ናቸው ። ከራሳቸው የተጣሉ ሰዎች ግን ፣ ለመታረቅ ፈሪ ለመጣላት ደፋር ናቸው ። ምክንያቱም ከራሳቸው የተጣሉ ሰዎች ፣ ልባቸው ለይቅርታ ዝግ ነው ። ራሳቸውን የሆኑ ሰዎች ግን ልባቸው ለይቅርታ ክፍት ነው ። ይቅር ለማለትም ፣ ይቅርታ ለመጠየቅም ዝግጁ ናቸው ። አስመሳዮቹ ግን ይቅርታ ሲጠየቁ ደስ ይላቸዋል ። ይቅርታ መጠየቅ ግን ያማቸዋል ።
ስለዚህ አጉል ድፍረት ራስን ማጣት ነው ። ድፍረትን ያለቦታው መጠቀም ነው ። ድፍረትን ያለቦታው መጠቀም ዋጋ ያስከፍላል ። ዋጋ ያስከፍላል ማለት መጨረሻው አያምርም ማለት ነው ። ድፍረትን በቦታው መጠቀምም ዋጋ ያስከፍላል ፣ ነገር ግን መጨረሻው ያምራል ። ፍጻሜው ሀዘን ሳይሆን ደስታ ነው ማለት ነው ። ድፍረት የእምነት ውጤት ነው ። አጉል እምነት አጉል ድፍረትን ይወልዳል ። ትክክለኛ እምነት ደግሞ ለክ የሆነ ድፍረትን ይፈጥራል ። ስለዚህ ድፍረትን ለማስተካከል እምነትን ማስተካከል ተገቢ ነው ። ለምሳሌ ሰውን በመናቅ የምናምን ከሆነ ፣ ድፍረታችን አጉል ይሆናል ። ሰውን በማክበር የምናምን ከሆነ ግን ፣ ድፍረታችን ትክክል ይሆናል ።
በውሸት የምናምን ከሆነ ፣ ለምንችለው ነገር ድፍረት እናጣና ፣ ለማንችለው ነገር አጉል ድፍረት ይኖረናል ። ድፍረታችን ልክ እንዲኖረው ፣ በልክ ማሰብ እና ማመን ተገቢ ነው ።
ድፍረት ጀግና ያደርጋል ። አጉል ድፍረት ግን ጀዝባ ያደርጋል ። ያለድፍረት ስኬት የለም ። በአጉል ድፍረትም ስኬት የለም ። ያለድፍረት አዲስ ነገር መፍጠር አይቻልም ። በአጉል ድፍረትም መፍጠር አይቻልም ። ድፍረት ይጠቅማል ፣ አጉል ድፍረት ይጎዳል ። ድፍረትን በልኩና በቦታው እንጠቀም ። ከአጉል ድፍረት ግን እንጠንቀቅ ።
ሴትን ፣ ህጻናትን ፣ ሽማግሌዎችን መድፈር ፣ የአጉል ድፍረት ውጤት ነው ። አጉል ድፍረት ለወንጀል እንጅ ለስራ ትጉ አያደርግም ።
‘’ አጉል ድፍረት ፣ አጉል እምነት ነው ። አጉል እምነት ደግሞ የተዛባ አስተሳሰብ ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment