አውቆ መሸነፍ
አውቆ መሸነፍ ያማል ። ሰው በማስተዋል ስህተት ሲሰራ ክፉኛ ይጎዳል ። ባለማስተዋል የሚሰራ ጥፋት ብዙ ጫና የለውም ። አውቆ መሸነፍ የትህትና ውጤት ነው ። ለትእቢተኞች አውቆ መሸነፍ የሞት ያህል ከባድ ነው ። ሰው አውቆ የሚሸነፈው በዓላማ ነው ። ያ አላማ ደግሞ መልካም እንጅ ክፉ መሆን የለበትም ። ለክፋት ሆን ብለው የሚሸነፉ ፣ ዓላማቸው ማታለል ነው ። ለመልካም ነገር አውቀው የሚሸነፉ ፣ ዓላማቸው ማስተካከል ወይም ማረም ነው ። ለማታለል አውቆ መሸነፍ ተንኮለኝነት ነው ። ለማስተካከል አውቆ መሸነፍ ግን ጥበበኛነት ነው ። አውቆ መሸነፍ ዓላማው መልካም ከሆነ ፣ ነገርን በጥበብ የማብረድ መንገድ ነው ። ዓላማው መጥፎ ከሆነ ግን ፣ ክፉኛ ሰውን የመጉዳት ስልት ሆኖ ያገለግላል ። ለተንኮለኞች ሆን ብሎ መሸነፍ ፣ መንደርደሪያ ወይም መደራደሪያ ነው ። ሌላውን ለማሳመን የሚውል አሻጥር ነው ። ለጥበበኞች ግን ክፉውን መሻገሪያ እና ማሻገሪያ ነው ።
በአውቆ መሸነፍ ውስጥ ያለ ዝቅታ ፣ በማሸነፍ ከሚገኝ ከፍታ ይበልጣል ። አውቆ ተሸናፊ በመጀመሪያ ተሸናፊ ፣ በመጨረሻ ግን ድል አድራጊ ነው ። መነሻው ማጣት ነው ፣ መዳረሻው ግን ሁሉን ማግኘት ነው ። ሰው አውቆ የሚሸነፈው አቅም ስላጣ አይደለም ፣ ሰላም ላለማጣት ነው ። ፍቅርን ለማስፈን ፣ እውነትን ለማሳወቅ እናም አብሮነትን ለማጽናት ነው ። መሸነፍ ባይኖር አብሮነት አይኖርም ። አሸንፋለው ባይ በበዛበት ቦታ ፣ ህብረት የሚባል ሀሳብ ፣ ሀሳብ እንጅ በፍጹም ተግባር ሊሆን አይችልም ። በተለይ አውቀው የሚሸነፉ ትሁታን በሌሉበት ።
ለሰላም ሆን ብለው የሚሸነፉ መሪዎች ያስፈልጋሉ ። ለፍቅር አውቀው የሚሸነፉ ምሁራን ሊኖሩ ግድ ይላል ። ለእውነት እጅ የሚሰጡ ባለጸጎች ሊበዙ ይገባል ። ለታማኝነት የሚንበረከኩ ባለሞያዎች ሊጠነክሩ ግድ ይላል ። ሀገር ሰላም ፍቅር መተሳሰብ እንዲሰፍንባት ።
ሰው አልሸነፍ ባይ መሆን ያለበት ለችግር እንጅ ለሰላም መሆን የለበትም ። ለጠላት እንጅ ለወዳጅ መሆን የለበትም ። ለጥላቻ እንጅ ለፍቅር መሆን የለበትም ። ለውሸት እንጅ ለእውነት መሆን የለበትም ። ለሰላም ለፍቅር ለእውነት ለወዳጅነት የሚሸነፉ ፣ ምንም ይሁን ምን መጨረሻ ላይ ድል የእነርሱ ነች ። እነርሱ እየታመሙ የሚፈውሱ ፣ እያለቀሱ እንባ የሚያብሱ ፣ እየወደቁ የሚያነሱ ፣ እየተዋረዱ የሚያስከብሩ ፣ እያጡ የሚያስገኙ ሩህሩህ እና ጀግና ናቸው ። አውቀው የሚሸነፉ ትሁታን ሩህሩህም ጭምር ናቸው ። ሩህሩህ ስለሆኑ ሰውን የመረዳት አቅማቸው ከፍ ያለ ነው ። ሰውን በጥልቀት መረዳት መቻላቸው ነው ፣ ለመሸነፍ ዝግጁ ያደረጋቸው ። መሸነፍ ውስጥ ፍቅር ሰላም እውነት እና ህብረት አለ ። አልሸነፍ ባይነት ግን እነዚህን ውድ የህይወት እሴቶች ያሳጣል ።
ለችግር አልሸነፍ ባይነት መንፈሰ ጠንካራነት ነው ። ለእውነት አልሸነፍ ባይነት ግን ግትርነት ነው ። ለመከራ አልሸነፍ ባይነት አይበገሬነት ነው ። ለምክር አልሸነፍ ባይነት ግን ንቀት ነው ። ለፈተና እጅ አልሰጥም ባይነት የሞራል ልእልና ነው ። ለፍቅር አልገዛም ባይነት ግን የሞራል ውድቀት ነው ። ለሁሉም ነገር አልሸነፍ ባይነት ኢ ሞራላዊ ያደርጋል ። ለፍቅር አውቆ መሸነፍ ግን የስብእና ከፍታ የሞራል ልእልና ነው ። በድርቅና ከማሸነፍ በፍቅር መሸነፍ የተሻለ ነው ። በግትርነት ከማሸነፍ በእውነት መሸነፍ ልቆ መገኘት ነው ።
አውቆ መሸነፍ ዓለምን ከጦርነት አውድማነት ፣ የሰው ልጅን ከአሰቃቂ ሞት እና ችግር ይታደጋል ። ዛሬ አለማችን ላይ ያለውን የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ብንመለከት ፣ ሌላ የምንም ውጤት አይደለም ፣ የአልሸነፍ ባይነት መዘዝ ነው ። ለባርነት አልሸነፍ ባይነት መልካም ቢሆንም ፣ ለሰላም እጅ አልሰጥም ባይነት ግን ራስወዳድነት ነው ። ራስ ወዳዶች አልሸነፍ ባዮች ናቸው ። ለክብራቸው ጥግ ድረስ ዋጋ ይከፍላሉ ። ለሌላው ክብር ግን ደንታም የላቸውም ። ክብራቸው ከተነካ ዓለም ዶግ አመድ እስክትሆን ይዋጋሉ ። ራስ ወዳዶች ክብራቸውን የሚያጡለት ነገር ከሰውነት ውጪ ነው ። ለሰብአዊነት ቦታ የላቸውም ። ለህሊና አይገዙም ። ህሊና ሲጮህባቸው በአልኮል ያደነዝዙታል ። ያለ የሌለ ሀይላቸውን ተጠቅመው ማሸነፍ እንጅ ፣ መሸነፍ የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላት ውስጥ እንዲገኝ አይፈልጉም ። ስለዚህ በእነርሱ ምክንያት የሚራብ የሚጠማ የሚጎሳቆል የሚፈናቀል የሚንከራተት ሰብአዊ ፍጥረት ግድ አይሰጣቸውም ።
ለእውነት ለፍቅር ለሰላም መሸነፍ እረፍት ነው ። አለመሸነፍ ግን እረፍት ማጣት ነው ። በማሰቃየት የሚገኝ እረፍት የለም ። በማታለል ውስጥ እፎይታ ሊኖር አይችልም ። አልሸነፍ ባይነት ማታለልን ማሰቃየትን ፣ ለማሸነፍ ስልት አድርጎ ይወስዳል ። አውቆ መሸነፍ ግን በስቃይ ውስጥ በማለፍ ፣ ለራስም ለሌላውም ሰው እረፍት መሆን ነው ።
ከማሸነፍ አውቆ መሸነፍ ከባድ ነው ። ማሸነፍ ሰው ላይ መስራት ነው ። መሸነፍ ግን ራስ ላይ መስራት ነው ። ሰው ሰውን ማረጋጋት ብዙ አይከብደውም ። ራሱን በራሱ ማረጋጋት ግን በጣም ይከብደዋል ። የሰውን ንዴት ለመቆጣጠር ጎበዝ ነው ፣ ነገር ግን የራሱን ንዴት ለመቆጣጠር ግን ሰነፍ ነው ። አውቆ መሸነፍ ራስን ማራጋጋት ይጠይቃል ። ንዴትን የመቆጣጠር ጥበብን ይፈልጋል ። አውቆ ተሸናፊ ራሱን ማረጋጋት ፣ ንደቱን መቆጣጠር የሚችል የስሜት ብስለት ባለቤት ነው ። ማሸነፍ ስኬት ነው ። መሸነፍ ደግሞ ሰብአዊነት ነው ። ሰውን ማሸነፍ ብቻ ሰውና ክቡር አያደርግም ። ለህሊናው ያልተሸነፈ መቼም ቢሆን አሸናፊ አይደለም ። ምክንያቱም ትክክለኛ ማሸነፍ ያለው ለህሊና መሸነፍ ውስጥ ነው ። ሰውነትም የሚኖረው ለህሊና መሸነፍ ውስጥ ነው ። አውቆ መሸነፍም ለህሊና የመገዛት ውጤት ነው ።
‘’ አውቆ መሸነፍ ለሰላም መማረክ ፣ ለፍቅር እጅ መስጠት ፣ ለእውነት ክብር መስጠት ፣ ለህሊና መገዛት ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment