Saturday, May 24, 2025

እይታ | Perception

                                            ክብር

    ‘’ ለአንዳንዱ ክብሩ የእሱነቱ መገለጫ ነው ። ለአንዳንዱ ደግሞ ክብሩ ሰውነቱ ነው ። ‘’ አለች ሰላም ተስፋዬ በማርትሬዛ ፊልም ላይ ። ይህን የተናገረችው በልብስ ምክንያት ከባድ ወቀሳ ደርሶባት ነው ። በነገራችን ላይ ልብስ የሰው ልጅ የማንነቱ መገለጫ እንጅ ማንነቱ ግን አይደለም ። ሰውነቱን ከፍም ዝቅም አያደርግም ። ቆሻሻ የለበሰ የአእምሮ ህመምተኛ ሰው ከመባል የሚከለክለው የለም ። ምናልባት ሰው ከሚለው መጠሪያ በፊት ፣ እብድ የሚል ተቀጽላ ከመጨመሩ በስተቀር ። ተቀጽላ ደግሞ ዋናውን የሰውን ማንነት ወይም ሰውነትን የመፋቅ አቅም የለውም ። ቅጽል ወይ ያኮስሳል አልያም ያገናል ። ሰውን ቀይሮ እንስሳ ወይም ግኡዝ ፍጥረት ሊያደርግ አይችልም ። ሰው ንጹህም ለበሰ ቆሻሻ ያው ሰው ነው ።

   ሰውን ከቆሻሻ ልብስ በላይ ክብሩን የሚያሳጣው ቆሻሻ አስተሳሰቡ ነው ። ሰው በንጹህ ልብስ ቆሻሻ ማንነቱን ለመደበቅ ከሚሞክር ፣ በንጹህ አስተሳሰብ ቆሻሻ ማንነቱን ቢያጸዳ መልካም ነው ። ገላን አጥቦ ማጽዳት ቀላል ነው ። አስተሳሰብን አጥቦ ማጽዳት ግን በጣም ከባድ ነው ። ከመነቸከ አስተሳሰብ የመነቸከ ልብስ ይሻላል ። የመነቸከን ልብስ አጥበነው ካቃተን አውጥተነው እንጥላለን ። የመነቸከን አስተሳሰብ ግን አጥበን ለማጽዳትም ፣ አውጥተን ለመጣልም በጣም አስቸጋሪ ነው ። ስለዚህ ሰው በልብሱ ከሚከበር በአስተሳሰቡ ቢከበር የተሻለ ነው ። ልብስ የሚያስከብረው በሩቁ ነው ። በርቀት በልብሱ ያከበሩትን ሲቀርቡት በአስተሳሰቡ ይንቁታል ። በልብስ የበለጸገ በስብእና የረከሰ ማንነት ክብሩ ጊዜያዊ ነው ። ዘላቂ ክብር ያለው በመልካም አስተሳሰብ የሚገነባ ውብ ስብእና ውስጥ ነው ። ልብስ ሳይሆን በዋናነት ልብ ነው ወሳኙ ።

   በቆሻሻ ልብ ላይ ጸዳል ልብስ መልበስ ፣ በአሮጌ አቁማዳ አዲሱን ወይን ማኖር ነው ። ሁለቱ ደግሞ አይስማሙም ። ወይ ወይኑ ይበላሻል አልያም አቁማዳው ይቀረደዳል ። ስለዚህ የሚሻለው አዲሱን ወይን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ነው ። ሰውነትን ባከበረ ማንነት ላይ ንጹህ ልብስ ማኖር ነው ፣ ለሰው ልጅ ዘላቂ ክብር የሚሆነው ። እውነተኛ ክብር ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ነው የሚመነጨው ። በሚታይ ነገር ለመከበር መሞከር ሞኝነት ነው ። ከሚታይ ነገር ይልቅ የማይታይ ነገር ከፍ ያለ ዋጋ አለው ። ለዚህም ነው ከሚታየው ልብስ በላይ ፣ የማይታየው ልብ የሚያስከብረው ። ሰው ለመታየት ሳይሆን ሆኖ ለማሳየት ነው መኖር ያለበት ። ለመታየት መልበስ በቂ ነው ። ለማሳየት ግን ከመልበስ ባሻገር ፣ መስራት ወይም መኖር ግድ ይላል ። የሰው ልጅ እውነተኛ ማንነት ያለው ደግሞ ፣ በመልበስ ውስጥ ሳይሆን በመኖር ውስጥ ወይም በመስራት ውስጥ ነው ። በልብስ አምሮ የሚታይ ፣ ምናልባት እላዩ የሚያምር ውስጡ የሚያማርር ፍጥረት ሊሆን ይችላል ። እላዩ ስላማረ ከሰውነት ከፍ አይልም ። አማራሪ በመሆኑ ግን ከሰውነቱ ዝቅ ባይልም ፣ በማንነቱ ላይ ሌላ ተቀጽላ ይለጠፋል ፣ አስመሳይ የሚል መገለጫ ።

   ጥሩ መልበስ ልክ አይደለም ወይም አያስፈልግም ማለት አይደለም ። ጥሩ መልበስ ራስን መንከባከብ ክብርንም መጠበቅ ነው ። ነገር ግን ሰው ራሱን መጠበቅ ያለበት ፣ በሰው ለመታየት ብቻ  መሆን የለበትም ። ለራሱ ለጤናውም ጭምር መሆን አለበት ።

 በሰው ለመታየት ሲል ጤናውን ምቾቱን ማጣት የለበትም ። ኢኮኖሚው እስኪቃወስ ፣ ኑሮው ኢስኪናጋ አምሮ ለመታየት ብዙ መድከም አይኖርበትም ። ማማር ከጤና አይበልጥም ። መዘነጥ ከአእምሮ ሰላም አይልቅም ። ዋናውን በማጣት የሚገኝ ትርፍ ዋጋ ቢስ ነው ። ዋናውን በመያዝ የሚገኝ ትርፍ ግን ጠቃሚ ነው ። መኖር ከሌለ መቀናጣት አይቻልም ። ቅንጦት ኖረም አልኖረም መኖር ይቻላል ። ለመቀናጣት መኖር ግድ ነው ። ለመኖር ግን መቀናጣት ግዴታ አይደለም ። ሰው ኖረ የሚባለው ስለተቀናጣ ሳይሆን ፣ ጤናውን እና የአእምሮ ሰላሙን መጥበቅ በመቻሉ ነው ። ለአስፈላጊው ነገር ሲባል ፣ ቅንጡውን ነገር መተው እንጅ ፣ ለቅንጡ ነገር ሲባል አስፈላጊውን ነገር ማጣት ተገቢ አይደለም ። በእርግጥ ልብስ አስፈላጊ ነገር ነው ። ነገር ግን የልብስ መሰረታዊ ጥቅሙ ፣ ገላን መሸፈን እንጅ ገላን ማሳየት አይደለም ። ገላን ለማሳየት ሲሉ ብዙዎች ጤናቸውን እስከማጣት ደርሰዋልና ። የሚመቸንን መልበስ አስፈላጊ ነው ። የማይመቸንን መልበስ ግን በሽታ ነው ። የምንችለውን መልበስ ተገቢ ነው ። የማንችለውን መልበስ ግን ቅንጦት ነው ። የሚያምርብን ልብስ ለጤና ጥሩ ነው ። የማያምርብንን ግን መልበስ ለጤና ጠንቅ ነው ። ልብስ ገላን ሲሸፍን ክብርም ውበትም ነው ። ግን ለመከበር አጉል መልበስ ክብር ያሳጣል ።

 ሰውን እኩል የሚያደርግ ልብስ ደንብም ነው ክብርም ነው ። የተማሪዎች ዩኒፎርም ፣ የሰራተኞች የስራ ልብስ ፣ የወታደሮች እና የፖሊሶች የደንብ ልብስ የሚያስከብር እናም ክብር የሚገባው ሊዩ ልብስ ነው ። እነዚህን ልብሶች መልበስ መታደል ነው ።

ነገር ግን በልብስ እከብራለው ባይ ለነዚህ ልብሶች ክብር የለውም ። ምክንያቱም ከሰው እለያለው ባይ ነው ። እሱን ከሰው የሚለየው እንጅ አንድ የሚያደርገው ነገር አይመቸውም ። በእርግጥ ሰው ከሰው ይለያያል ። በሌላ በኩል ከብዙሃኑ አንድ የሚያደርገው ፣ የሚጋራው ነገር ብዙ ነው ። ሁሉም ሰው ሊኖረው በሚችለው ነገር ልዩ ልሁን ማለት አያስከብርም ። ከሌላው በሚለየን ነገር ላይ መስራት ግን ያስከብራል ። ሰውን ከሰው የሚለየው ደግሞ ስራው እንጅ ልብሱ አይደለም ። ፈረንጀቹ ‘’ ( First impression is last impression ) ’’ ይላሉ ። የፈርስት ኢምፕረሽን አንዱ መለኪያ አለባበስ ነው ። እዚህ ጋር አለባበስ ለስራ ያለንን ክብር ነው የሚያሳየው ። ስራን ለማክበር መልበስ ያስከብራል ። ከሰው ሁሉ ለመለየት ወይም ለሰው ብሎ መልበስ ግን አያስከብርም ።

        ‘’ ክብር ልብስ ውስጥ ሳይሆን ልብ ውስጥ ነው የሚገኘው ። ‘’                               

No comments:

Post a Comment

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...