Saturday, September 6, 2025

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት

    እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ስናገኝም ስናጣ ፣ ቢደላንም ባይደላንም ፣ በክፉም ሆነ በበጎ ሁኔታ ውስጥ ይዘን የምንገኘው ማንነት ነው ። ድህነትም ባለጸግነትም ፣ መሀይምነትም ምሁርነትም እምነትን አያስጥልም ። እምነት በፈተና ብዛትም አይፈርስም ። እንዲያውም ፈተና እምነት የሚጠነክርበት ወጌሻ ነው ። ስሜታዊነት የእምነት ተቃራኒ ነው ። ስሜታዊ ሰዎች ሲያገኙ ሌላ ፣ ሲያጡ ደግሞ ሌላ ሰው ናቸው ። ሲያተርፉ አመስጋኝ ሲከስሩ ወቃሽ ናቸው ። ሲሞላ እብሪተኛ ሲጎድል ደግሞ ትሁት ናቸው ። ስሜታዊ ሰዎች ሲደሰቱ ይሆናል ፣ ሲያዝኑ ደግሞ አይሆንም ማለት ይቀናቸዋል ። እምነት ግን በሀዘንም ሆነ በደስታ ይሆናል ማለት ነው ። ስሜታዊነት መለወጥ ሳይሆን መለዋወጥ ነው ። እምነት በሂደት አንድ ጊዜ ሊለወጥ ይችላል ። በአንድ ቀን ግን ሺ ጊዜ አይለዋወጥም ። ስሜታዊነት በአንድ ጀምበር ብዙ ጊዜ መለዋወጥ ነው ። በአንድ ቀን ውስጥ ሶስት ወይም አራት ሰው መሆን ነው ። በአንድ አካል ውስጥ ብዙ ሰው መሸከም ነው ። ጥዋት እና ማታ ፣ ቀንና ጨለማ ሲፈራረቁ አብሮ መፈራረቅ ነው ስሜታዊነት ። ስሜታዊ ሰዎች በአጭሩ እምነት የለሽ ናቸው ማለት ይቻላል ።

    እምነት ሙሉነት ነው ። የሚያምን ሰው ልበ ሙሉ ነው ። በወዳጅም በጠላትም ፊት ያው ነው ። ለጠላት ፈርቶ የሚቀይረው ነገር አይኖርም ። ለወዳጅ አዝኖ የሚለውጠው ነገር የለም ። ምክንያቱም እምነት እውቀት ላይ ነው የሚመሰረተው ። እውቀት ደግሞ እውነት ላይ ነው የሚመሰረተው ። ስለዚህ በእምነት መኖር ለማንም ሳይሆን ለእውነት መወገን ነው ። እውነት ሁል ጊዜም እውነት ነው ። በጊዜ መቀየር ውስጥ አብሮ አይቀየርም ። ጥዋት እውነት የነበረው ከሰአት ውሸት አይሆንም ። ትላንት እውነት የነበረው ነገ ውሸት አይሆንም ። በዘመን ብዛት እውነት አያረጅም ። ከዚህ በተቃራኒ ስሜታዊነት ባዶነት ነው ። ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ  እንደሚወስደው ባዶ ፈስታል መሆን ነው ። በስሜታዊነት ውስጥ ይዞ መልቀቅ እንጅ ይዞ መጽናት የለም ። ለቆ መያዝ ፣ ይዞ መልቀቅ የተለመደ ነው ። በአንዴ ሙሉ መሆን ፣ ከዚያ ደግሞ ወዲያው ባዶ መሆን የሜታዊነት ውጤት ነው ። በጣም የሚያሳዝነው ስሜታዊ ሰዎች ፣ መርጦ መያዝም ሆነ መልቀቅ አይችሉም ። ሲይዙም ሲለቁም ሳይመርጡ ነው ። ወይ ባዶ አልያም ሙሉ የሚሆኑትም ለዚያ ነው ። ስለዚህ በአግባቡ መቀበልም ሆነ መስጠት አይችሉም ። 

    ስሜታዊ ሰዎች ዘመድ ሲያዩ ሙሉ ይሆናሉ ። ባዳ መሀል ሲገኙ ባዶ ይሆናሉ ። ሲያገኙ ልባቸውን ያሳብጣሉ ። ሲያጡ ደግሞ ይጎብጣሉ ። በሰው መተማመን ይችላሉ ፣ በራሳቸው መተማመን ግን አይችሉም ። አይደለም የማይችሉትን የሚችሉትን መስራት ይፈራሉ ። ሰዎች በእነርሱ ችሎታ እያመኑ ፣ እነርሱ ግን ያላቸውን ችሎታ አምነው አይቀበሉም ። ሁል ጊዜም ውጪያዊ ማረጋገጫ ( external validation ) ይፈልጋሉ ። በራስ ሞራል ሳይሆን በሰው ሞራል መስራት ይወዳሉ ። የሚያሞግስ ሲኖር ወዲያው ይሞቃሉ ። ሲወቀሱ በቅጽበት ቅዝቅዝ ይላሉ ። ሲደነቁ በፍጥነት ይሮጣሉ ። ሲተቹ ደግሞ ለመራመድ ይዘገያሉ ። ጥንቸል የነበሩት ኤሊ ይሆናሉ ። ስሜታዊ ሰዎች ፎርጅድ ባትሪ ናቸው ። ቻርጅ ሲደረግ ወዲያው የሚሞላ ፣ ሲነቀል ደግሞ ዜሮ የሚሆን የደከመ ባትሪ ናቸው ። ወለል ብሎ የተከፈተ ወይም ጥርቅም ብሎ የተዘጋ በራፍንም ይመስላሉ ። ልባቸውን ገርበብ ማድረግ አይችሉም ። የመጣውን ነገር ወይ በሙሉ ይቀበሉታል አልያም ምኑንም አይቀበሉትም ። በእምነት መኖር ግን ልብን ገርበብ ማድረግ ነው ። መርጦ መቀበል እና መጣል ነው ። እንደፍላሽ የሚጫነውን ሁሉ መቀበል ሳይሆን ፣ እንደወንፊት እያጣሩ መውሰድ ነው ። ጉድለትን እየሞሉ መሄድ እንጅ በአንዴ ሙሉ ወይም ባዶ መሆን አይደለም ። 

    እምነት ሚዛናዊነት ነው ። እምነት ውስጥ እውነትነት አለ ። እውነትነት ውስጥ ደግሞ ሚዛናዊነት አለ ። በእምነት መኖር ፍትሀዊ ያደርጋል ። ምክንያቱም ሰው በእምነት ሲኖር በአጀብም ብዛት ሆነ ፣ በወጀብም ፍርሀት ከእውነት አይሸሽም ። በአጀብ ብዛት ጽንፍ አይዝም ። በወጀብ ፍርሀት ጥግ አይዝም ። መሀል ላይ እውነትን ይዞ ነው የሚገኘው ። እውነት ደግሞ ከምንም በላይ ወሳኝ ሚዛን ነው ። ያለ እውነት ሚዛናዊ ያለ እምነት ፍትሀዊ መሆን ከባድ ነው ። ከዚህ በተቃራኒ ስሜታዊነት ኢ-ሚዛናዊነት ነው ። ስሜታዊ ሰዎች አጀብ ሲበዛ እውነቱን ሳያጣሩ ጽንፍ ይይዛሉ ። ወጀብ ሲገጥማቸው ደግሞ እውነቱን ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ ። እነርሱ ወደ ነፈሰው የሚነፍሱ ነፍስ አልባ ፈጥረቶች ናቸው ። ለእነርሱ ሚዛን እውነት ሳይሆን ብዛት ነው ። እውነት ደግሞ በብዙ ልብ ውስጥ ሳይሆን በንጹህ ልብ ውስጥ ነው የሚገኘው ። ስሜታዊ ሰዎች ንጹህ ልብ የላቸውም ። ምክንያቱም መርጠው መቀበል አይችሉም ። መምረጥ አለመቻል ንጽህናን ያሳጣል ። ንጽህና በሌለበት ሚዛናዊነት ፈጽሞ አይታሰብም ። ሚዛናዊ ለመሆን ከዘረኝነትም ከጽንፈኝነትም ንጹህ መሆን ያስፈልጋል ። ስሜታዊነት ወይ ዘረኛ አልያም ጽንፈኛ ያደርጋል ፣ ሚዛን ያስታል ።

    የስሜት ብስለት የእምነት ውጤት ነው ። ምክንያቱም የሚያምን ሰው ከጊዜያዊ ስሜት ይልቅ ለዘላቂ ስሜት ተገዥ ነው ። ዘላቂ ስሜት የስሜት ብስለት ማሳያ ነው ። ጊዜያዊ ስሜት ግን የስሜት ብስለት ሳይሆን የስሜት ስለት ነው ። በጊዜያዊ ስሜት ተነሳስተው ያለሙ ሳይሆን ያጠፉ ብዙ ናቸው ። የገነቡ ሳይሆን ያፈረሱ ጥቂት አይደሉም ። በግ ሳይሆን ሰው ያረዱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ። በስሜት ለመብሰል በእምነት መጠንከር ግድ ነው ። በትእግስት የሚያምን ሰው በንዴት ቶሎ ቱግ አይልም ። በትህትና የሚያምን ሰው ለቁጣ አይቸኩልም ። በየዋህነት የሚያምን ሰው በቂም ራሱን ሲመርዝ አይኖርም ። በቅንነት የሚያምን ለነገር ፈጣን አይሆንም ። በልባምነት የሚያምን ሁሉን በመቀበል እና በመስጠት አይኖርም ጠንቃቃ ነው ። እምነት የቀደመው ስሜት ጠቃሚ ነው ። እምነትን የቀደመ ስሜት ግን ጎጂ ነው ። ስሜት ለእምነት ሲገዛ የሰው ልጅ ክብሩ ከፍ ይላል ። እምነት ለስሜት የተገዛ እለት ግን የሰው ልጅ ክብሩ ዝቅ ይላል ። ስለዚህ ስሜትን ለእምነት እንጅ ፣ እምነትን ለስሜት አናስገዛ ።

   '' ስሜታዊነት በአንድ እግር መቆም ነው ። እምነት ግን በሁለት እግር መቆም ነው ። ''              

           

Tuesday, August 12, 2025

እይታ | Perception

                                                            የማያዛልቅ ነገር

    የማያዛልቅ ነገር ጊዜያዊ ነው ። መጨረሻ የሌለው ቅጽበታዊ ነገር ነው ። አለ ሲባል የሚጠፋ ፣ ጠፋ ሲባል የሚኖር አወዛጋቢ ነገር ነው ። የማያዛልቅ ነገር ስሜትን የመናጥ አቅም አለው ። ስሜትን ሰቅዞ በመያዝ ሰውን በቀላሉ ምርኮ ማድረግ ይችላል ። በቶሎ የሚለመድ ግን በቀላሉ የማይላቀቅ መንቻካ ነው ። አያዛልቅም ግን ደግሞ አይላቀቅም ። የማያዛልቅ ነገር ክብርን ፍቅርን ስሜትን ስልጣንን ጊዜያዊ ነው የሚያደርገው ። የማያዛልቅ ነገር መርህ አይመቸውም ። መርህ ደግሞ ለማያዛልቅ ነገር ቦታ የለውም ። መርህ የማይለዋወጥ ወጥ ነገር ነው ። የማያዛልቅ ነገር ግን ጋጠወጥ ነው ። በመርህ መኖር ፣ በህግና በስርዓት መኖር ነው ። ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ፣ ህገወጥ እና ስርዓት አልበኛ ያደርጋል ። 

    መርህም ሆነ ስርዓት በሂደት ነው የሚገነቡት ። በአንድ ጀምበር የማይለመዱ ፣ ውድ ነገሮች ( quality ) ናቸው ። ወድ ስለሆኑ ሰውንም ውድ ክብሩንም ዘላለማዊ ማድረግ ይችላሉ ። ቅጽበታዊ ነገር ርካሽ ነው ። ለቅጽበታዊ ነገር መገዛት ርካሽነት ነው ። ጥራት የጎደለው እቃ ርካሽ እንደሚሆነው ፣ ለማያዛልቅ ነገር የሚገዛ ሰው ርካሽ ነው የሚሆነው ። ወርቅ መሆን የሚችለው መዳብ ይሆናል ። ሸክላ መሆን የነበረበት ገል ይሆናል ። ሊቅ መሆን የነበረበት ደቂቅ ይሆናል ። ምሁር መሆን የሚችለው መሀይም ይሆናል ። ባለጸጋ መሆን የሚችለው ደሀ ይሆናል ። ክቡር መሆን የሚችለው ወራዳ ይሆናል ። ምክንያቱም መርህ አልባ ሰዎች ጎደሎ ናቸው ።

     ለማያዛልቅ ነገር መገዛት በጉድለት ውስጥ መኖር ነው ። እየጎደሉ ሙሉ መሆን አይቻልም ። እያነሱ መብዛት አይኖርም ። እየገደሉ ማዳን የማይታሰብ ነው ። በመርህ መኖር የጎደለን እየሞሉ መሄድ ነው ። በሂደት መልካም ነገርን ማሳደግ ፣ ክብርንም መጨመር ነው ። በመርህ ውስጥ የጎደለ ይሞላል ፣ ያነሰ ይበዛል ፣ የተዋረደ ከፍ ይላል ፣ የተበላሸ ሁሉ ይስተካከላል ። ለጊዜያዊ ነገር መገዛት ግን መስተካከል የሌለው መበላሸት ነው ፣ መመለስ የሌለው መውጣት ነው ፣ መዳን የሌለው መታመም ነው ፣ መነሳት የሌለው መውድቅ ነው ። በመርህ መኖር መጀመሪያ ያማል ፣ መጨረሻው ግን ያምራል ። ጊዜያዊ ነገር መጀመሪያ ያምራል ፣ መጨረሻ ለይ ግን ያማል ። ሰው ደግሞ መጀመሪያው አማረም አላመረም ችግር የለውም ። መጨረሻው ሲያምር ነው ደስ የሚለው ። ተከብሮ ከመዋረድ ፣ ተዋርዶ መከበር ይሻላል ። ይህ የሚሆነው በመርህ መኖር ሲቻል ነው ።  

    ዓላማ እና የማያዛልቅ ነገር አይዋደዱም ፣ ሆድና ጀርባ ናቸው ። የማያዛልቅ ነገር ለዓላማ እንቅፋት ነው ። ዓላማ ደግሞ ለጊዜያዊ ነገር አለርጂ ነው ። በዓላማ መኖር ሩቅ አስቦ ሩቅ ለማደር መታገል ነው ። ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ቅርብ አስቦ ቅርብ ማደር ነው ። ዓላማ የማይታየውን ማሳየት ይችላል ። በዓላማ መኖር ከሚታየው በላይ ለማይታየው ነገር ዋጋ መስጠት ነው ። በማያዛልቅ ነገር መሸነፍ ለማይታየው ሳይሆን ለሚታየው ነገር ዋጋ መስጠት ነው ። ለሚታይ ነገር መገዛት እንጭጭነት ነው ። ለማይታይ ነገር መገዛት ግን ብስለት ነው ። ሰው እምነተ ጠንካራ የሚሆነው ፣ እምነቱን በሚያየው ነገር ላይ ሲመስርት ሳይሆን ፣ በማይታይ ነገር ላይ ሲመሰርት ነው ። እምነተ ደካሞች በሚታይ ነገር ያምናሉ ። እምነተ ጠንካሮች በሚታይም በማይታይም ነገር ያምናሉ ። ተጠራጣሪዎች በሚታየውም በማይታየውም ቶሎ አያምኑም ።

   በጊዜያዊ ነገር ማመን ፣ እምነተ ደካማ መሆን ነው ። የዓላማ ሰዎች ግን እምነተ ጠንካሮች ናቸው ። ለዓላማ መኖር ከቅርቡ ይልቅ የሩቁን መመልከት ነው ። ለማያዛልቅ ነገር እጅ መስጠት የሩቁን ሳይሆን የቅርቡን ማየት ነው ። የቅርቡን ማየት ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ማለት አይደለም ። የቅርብ ነገሮች ዋጋ የሚኖራቸው ፣ ለሩቁ ነገር ግብዓት ሲሆኑ ነው ። ሩቅ ላለ ነገር ግብዓት መሆን ያልቻለ ቅርብ ነገር ፣ ዋጋ ያሳጣል እንጅ ዋጋ አያሰጥም ። ዋጋው ይወርዳል እንጅ ከፍ አይልም ። ወርቅ የሚሆነው መዳብ ይሆናል ። አልማዝ የሚሆነው ተራ የመንደር ድንጋይ ይሆናል ። የሩቁን ነገር አጥርቶ መመልከት ፣ የቅርቡን ነገር በአግባቡ ለመጠቀም ይረዳል ። በአላማ ስንኖር እጃችን ላይ ያለውን ነገር ትክክለኛ ዋጋ እናውቃለን ። የማያዛልቅ ነገር ዓላማን የሚጋርድ ጥቁር መጋረጃ ነው ። 

    የማያዛልቅ ነገር ደማቅ ነው ፣ አይነ ግቡ ነው ። ከፍተኛ የስበት ሀይል ( gravitational force ) አለው ። የማያዛልቅ ነገርን መከላከል እንጅ መጋፈጥ ብዙ አያዋጣም ። '' ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ '' እንደሚባለው ፣ ለጊዜያዊ ነገር ቅድመ ጥንቃቄ ነው የሚያስፈልገው ። ለምሳሌ ጫትን ብንወስድ ለብዙ ወጣቶች ደምቆ ነው የሚታየው ፣ በጣም ያስጎመጃል ነገር ግን እድሜን ይፈጃል ። ጫት ለጊዜያዊ ደስታ እንጅ ለዘላቂ ደስታ ምንም አስተዋጸኦ የለውም ። መጀመሪያ ያደምቃል መጨረሻ ላይ ግን ያደቃል ። ጅማሬው ደስታ ነው ፣ ፍጻሜው ግን ሀዘን ነው ። ሱሰኛ ነገን ዛሬ አይኖርም ። ነገን ዛሬ ይገድላል ። በዛሬ ውስጥ የሞተ ነገ ደግሞ እድሜን በእጥፉ ነው የሚቀንሰው ። የማያዛልቅ ነገር እድሜ ማባከኛ እንጅ ፣ እድሜ ማራዘሚያ ወይም መጠቀሚያ ሊሆን አይችልም ። የማያዛልቅ ነገርን የሙጥኝ ማለት መጨረሻው ብክነት ነው ። 

     የማያዛልቅ ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አይደለም ። ነገር ግን ስሜት ለማያዛልቅ ነገር ቅድሚያ በመስጠት የተካነ ነው ። ሰው ደግሞ ከምንም በላይ ለስሜቱ ተገዥ ነው ። ስሜቱን መቆጣጠር የቻለ ሰው ፣ ለማያዛልቅ ነገር ፊት አይሰጥም ። ስሜታቸውን መግዛት የተሳናቸው ሰዎች ግን ፣ ፊታቸውን ብቻ አይደለም ልባቸውን ጭምር ነው ለማያዛልቅ ነገር አሳልፈው የሚሰጡት ። ሰው ልቡ ለጊዜያዊ ነገር ሲገዛ ፣ ማክበር ያለበትን ይንቃል ፣ መያዝ ያለበትን ይለቃል ። መገንባት ያለበትን ያፈርሳል ። ማንሳት ያለበትን ነገር ይጥላል ። መተው ያለበትን ነገር የሙጥኝ ይላል ። የሚጎዳውን እየተከተለ ፣ የሚጠቅመውን እየሸሸ ይኖራል ። ጥሩ ነገር የሚያመው ፣ መጥፎ ነገር የሚያስደስተው ብላሽ ይሆናል ። ለማያዛልቅ ነገር ፊት መስጠት መጨረሻው መበላሸት ነው ። 

     የማያዛልቅ ነገር ከጤና ይልቅ በሽታ ነው ። ክብር ሳይሆን ውርደት ነው ። ነጻነት ሳይሆን ባርነት ነው ። ሱስ ህመም ነው ፣ ሀሜት ውርደት ነው ፣ ሌብነት ባርነት ነው ። አለው አለው ባይነት መጨረሻው ባዶነት ነው ። ስርዓት ማጣት ፍጻሜው ሰውነትን ማጣት ነው ። መዝናናት ማብዛት መጨረሻው መጉላላት ነው ። ፊልም ሲበዛ ህይወትን ቅዠት ያደርጋል ። አሉባልታ ሲበዛ ህይወትን ጣዕም አልባ ያደርጋል ። በጠቅላላው ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ፣ የህይወትን ጉዞ የከፍታ ሳይሆን የቁልቁለት ነው የሚያደርገው ። ለሁሉ ነገር ትክክለኛ ዋጋ እንዲኖረን የህይወት ዓላማ ይኑረን ። በመርህ እንኑር ። ያኔ መዳቡ ወርቅ ይሆናል ። ተራ ድንጋይ የመሰለን የከበረ አልማዝ ይሆናል ። 

       '' የሁሉም ነገር ዋጋ ያለው አላማ ውስጥ ነው ። አላማ ከሌለን አይደለም የሌላን ነገር ዋጋ ፣ የራሳችንን ዋጋ አናውቅም ። ''            


Saturday, August 9, 2025

እይታ | Perception

                                                             አጋጣሚን መፍጠር 

    አጋጣሚ ያልታሰበ ነገር ነው ። የታሰበ ነገር ሁሉ አጋጣሚ ሊሆን አይችልም ። አጋጣሚ ድንገቴ ነው ። በድንገት ማጣት መሞት መለያየት መክሰር መጎዳት አጋጣሚዎች ናቸው ። ማጣት ብቻ አይደለም ፣ ማግኘትም ድንገተኛ ከሆነ አጋጣሚ ነው ። አጋጣሚ ሀዘንም ደስታም ነው ። ዕጣም ጣጣም ነው ። መርገምም በረከት ነው ። ስኬትም ውድቀትም ነው ። ክብርም ውርደትም ነው ። አጋጣሚ ብዙ ነገር ነው ። አጋጣሚ የምን ውጤት ነው ቢባል ፣ በቀላሉ መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ነው ። በቃ አጋጣሚ የእጣ ፈንታ ጉዳይ ነው ። በአጋጣሚ የማያምኑ ሰዎች ፣ አጋጣሚ የሚባል ነገር የለም ይላሉ ፣ ነገር ግን እነርሱ የለም ስላሉ አጋጣሚ አይኖርም ማለት አይደለም ። አጋጣሚ የፈጣሪ ድንቅ ጥበብ መገለጫ ነው ። አጋጣሚ የለም ማለት ሰው የተጻፈለት ታሪክ እንጅ ራሱ የሚጽፈው ታሪክ የለውም ማለት ነው ። የራሱ አሻራ ( legacy ) አይኖረውም ። የመምረጥ ነጻነትም ሊኖረው አይችልም ። የሰው ልጅ የነጻነቱ ማሳያ አንዱ አጋጣሚ ነው ። ፈጣሪ የሰው ልጅ የተጻፈለትን ብቻ እንዲኖር ሳይሆን ፣ አዲስ ታሪክ ጽፎ እንዲኖር ነጻ አድርጎ ነው የፈጠረው ። በዚህ የነጻነት ጉዞ ውስጥ ፣ አጋጣሚ ለሰው ልጅ ፈተና እና እድል ሆኖ ይከሰታል ። 

   አጋጣሚ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል ። ጥሩ አጋጣሚ እድል ነው ። መጥፎ አጋጣሚ ፈተና ነው ። ብልሆች መጥፎ አጋጣሚን ወይም ፈተናን ወደ እድል መቀየር ይችሉበታል ። ጥሩ አጋጣሚን ወይም እድልን በአግባቡ መጠቀምም ያውቁበታል ። ሰነፎች ግን ፈተናን ወይም መጥፎ አጋጣሚን ወደ እድል መቀየር አይችሉም ። እድልን ወይም ጥሩ አጋጣሚን መጠቀምም አይችሉም ። ሰነፎች እድልን ወደ ፈተና ፣ በረከትን ወደ መርገም ፣ መፍትሄን ወደ ችግር ፣ ዕጣን ወደ ጣጣ መለወጥ ነው የሚችሉት ። ድንገት ያገኙትን ምርጥ ወዳጅ ጠላት ያደርጉታል ። እድል ሆኖ የመጣላቸውን ገንዘብ ሱስ ይገዙበታል ። መኪና የሚገዙበትን እድል ቁማር ላፍ ያደርግባቸዋል ። የሚከበሩበትን እድል አላግባብ በመጠቀም ይዋረዱበታል ። ፍቅሩን ጥላቻ ፣ ፈውሱን በሽታ ፣ መድሀኒቱን መርዝ ያደርጋሉ ። አጋጣሚ ከምንም በላይ መማሪያ ነው ። ጥሩ አጋጣሚ ማለፊያ ነው ። መጥፎ አጋጣሚ ደግሞ መማሪያ ነው ። እንዲህ የሚሆነው ግን ለሰነፎች ሳይሆን ለብልሆች ነው ። ለሰነፎች ጥሩ አጋጣሚ መዋረጃ ፣ መጥፎ አጋጣሚ ደግሞ መማሪያ ሳይሆን መማረሪያ ነው ። 

   ህይወት አጋጣሚ ባይኖር የሆነ አይነት ጣዕም ይጎድላታል ። አጋጣሚ የህይወት ቅመም ማጣፈጫ ነው ። በመጥፎም ይሁን በጥሩ ፣ መጠቀም ለቻለ አጋጣሚ ቅመም ነው ። መጠቀም ላልቻለ ግን ቅመም ሳይሆን ቂም ነው የሚሆነው ። ቂም ደግሞ የህይወት ማምረሪያ ሬት ነው ። ምክንያቱም ይህ ቂም የሚሆነው በፈጣሪ ላይ ነው ። ሰው ያለምንም እድል እና ፈተና ፣ እቅዱን ማሳካት መቻሉ ደስታውን ሙሉ አያደርግለትም ። እቅድ አጋጣሚን ይወልዳል ፣ አጋጣሚ ደግሞ ደስታን ሙሉ ያደርጋል ። በአጋጣሚ ያልተፈተነ ወይም በእድል ያልታገዘ እቅድ ፣ በሰው ውስጥ አዲስ ስሜትን የመፍጠር አቅም አይኖረውም ። ስለዚህ ህይወት ወይ በድል አሊያም በእድል ነው ሙሉ የምትሆነው ። ስላቀድን ብቻ ህይወት ሙሉ አትሆንም ፣ ሙሉነትም አይሰማንም ። ለዚህም ነው '' plan for expected as well as un expected. '' የሚባለው ። ለምንጠብቀው ብቻ ሳይሆን ለማንጠብቀውም ነገር መዘጋጀት ግድ ነው ። ያኔ አጋጣሚን ለመጠቀም በቂ ስነ ልቦናዊ አቅም ይኖረናል ። አልያ በአጋጣሚ ምክንያት አቅም ሳይሆን የሚፈጠረው ፣ ቅስም ነው የሚሰበረው ።

   ሰው አስቦ አጋጣሚን መፍጠር ባይችልም ፣ አስቦ ማቀዱ ግን አጋጣሚ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል ። መልካም አጋጣሚ የማቀድ ውጤት ነው ። '' ሰው ያቅዳል ፈጣሪ ይፈጽማል ። '' አይደል የሚባለው ። አጋጣሚ ፈጣሪ የሰው ልጅ እቅዱን እንዲያሳካ የሚቸረው ድንቅ ስጦታ ነው ። አጋጣሚ ዝግጁ ለሆነ ሰው እንጅ ፣ ዝግጁ ላልሆነ አይሰጥም ። እቅድ ዝግጅት ነው ። ማቀድ የቻለ ሰው አጋጣሚን ለመቀበል ዝግጁ ነው ። ማቀድ ያልቻለ ደግሞ አጋጣሚን ለመቀበልም ለመጠቀምም አቅም አይኖረውም ። ሰው በአጋጣሚ ብቻ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ። እቅድ እና አጋጣሚ ተባብረው ነው ፣ ለውጥን ዘላቂ የሚያደርጉት ። አጋጣሚን ለመፍጠር በእቅድ መኖር አስፈላጊ ነው ። በአጋጣሚ እየኖረ የከበረ የለም ። በእቅድ እየኖረ በአጋጣሚ የከበረ ግን ብዙ ነው ። እቅድ አጋጣሚን ሲቀድም ለውጥ አዎንታዊ ይሆናል ። አጋጣሚ እቅድን ሲቀድም ግን ለውጥ አሉታዊም አዎንታዊም የመሆን እድል ይኖረዋል ። ይህ የሚወሰነው እንደየሰው አስተሳሰብ እና አቀባበል ነው ። ጎበዝ ሰዎች አጋጣሚን ይፈጥራሉ ይጠቀማሉ ። ሰነፎች ግን የተፈጠረን አጋጣሚ ያባክናሉ ። አጋጣሚ እንዳይባክን በእቅድ እና በዝግጅት እንኑር ።

  ጊዜን ማባከን አጋጣሚን ማባከን ነው ። ጊዜን በግባቡ መጠቀም አጋጣሚን መፍጠርም መጠቀምም ነው ። ጊዜም አጋጣሚም የፈጣሪ ችሮታዎች ናቸው ። በሁለቱም ላይ የሰው ልጅ ስልጣን የለውም ። ሁለቱንም መጠቀም እንጅ ማዘዝ አይችልም ። ለመጠቀም መታዘዝ ፣ ለመታዘዝ ትሁት መሆን አስፈላጊ ነው ። አጋጣሚ ለትሁታን በረከት ነው ። ለእብሪተኞች ግን መቅሰፍት ነው ። '' ለሀጥዓን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል '' እንዲባል ፣ መቅሰፍቱ ለመልካሞች  ሊተርፍ ይችላል ። አጋጣሚ መልካም እንዲሆን ፣ ጊዜን ለመልካም ነገር እናውል ። ጊዜ አጋጣሚን ይጠብቃል ፣ አጋጣሚም ጊዜን ይጠብቃል ። በጊዜው የሚከሰት አጋጣሚ ሸክም አቅላይ ነው ። ያለጊዜው የሚከሰት አጋጣሚ ግን ሸክም አቅላይ ሳይሆን ራሱ ሸክም ነው ። ሸክም አጋጣሚ ነገር የመሸከም ውጤት ነው ። ጥላቻን በቀልን ቂምን የመሸከም ማሳያ ነው ። ስለዚህ በህይወታችን መልካም ነገር እንዲገጥመን ፣ ጥላቻን ቂምን ብቀልን አንሸከም ። ፍቅርን ይቅርታን የዋህነትን እንሽከም ። ያኔ እድል በሆነው መልካም አጋጣሚ ህይወት ሰላም እና ቀላል ትሆናለች ። 

          '' ማቀድ የሰው ድርሻ ነው ። አጋጣሚ የፈጣሪ ችሮታ ነው ። ''   

                                                                

Monday, August 4, 2025

እይታ | Perception

                                                            ፍቅር እና መስፈርት

   ፍቅር መርህ እንጅ መስፈርት የለውም ። መስፈርት ለፍቅር ምንም ነው ። ለፍቅር ሰው ምንም ይሁን ምን ፣ ይኑረው አይኑረው ሰው መሆኑ ብቻ በቂ ነው ። በፍቅር ዘንድ የሰው መርዘም ወይም ማጠር ፣ ዋጋውን ከፍ ወይም ዝቅ አያደርገውም ። መቅላት ወይም መጥቆር የሚጨምረው የሚቀንሰው ነገር የለም ። ጌታም ይሁን ባርያ ከመፈቀር የሚያግደው አይኖርም ። ለመፈቀር ሰው ዶክተር እንጅነር ፕሮፌሰር ባለጸጋ ወይም አዋቂ መሆን አይጠበቅበትም ፣ መልካም ሰው መሆኑ በቂ ነው ። ለፍቅር የሰው ማእረጉ ሳይሆን መልካምነቱ ነው የሚያስፈልገው ። በትጋት ጎበዝ የሆኑ ሰዎች ፣ ለመልካምነት ግን ሰነፍ የሆኑ ሰዎች ፣ በፍቅር ዘንድ ዋጋ የላቸውም ። ትጋት ያስከብራል ግን ለስራ ባለን ፍቅር እንጅ ለሰው ባለን ፍቅር  አይደለም ። ለስራ ያለን ፍቅር ብቻ ሰው አያደርገንም ፣ ለሰው ያለን ፍቅር ነው ሰው የሚያደርገን ። ስለዚህ ስራ ስንሰራ ለሰው እንደምንሰራ እያሰብን እንስራ ። ያኔ ፍቅር ሰውን ለመጥቀም እንጅ ለመጉዳት መስራት እንደሌለብን ያሳስበናል ። ይህ የፍቅር መስፈርት ሳይሆን መርህ ነው ። 

   ሰው ገንዘብ ስላለው ሊከበር ይችላል ። ያለፍቅር ግን በገንዘቡ ብቻ ሊወደድ አይችልም ። ሰው መወደድም መከበርም የሚችለው ፣ በገንዘቡ ላይ መልካምነትን ሲጨምር ነው ። ገንዘብ ሲቀነስ ፍቅር ፣ እኩል ይሆናል ክብር ሲቀነስ መወደድ ። መወደድ የሌለው ክብር ሰውን በሰው ልብ ውስጥ አያነግስም ። ክብር ከፍቅር ጋር ነው በሰው ልብ ላይ የሚያነግሰው ። ገንዘብ ክብርም ፍቅርም መሆን ይችላል ። ሰው በገንዘቡ መልካም ስራ ከሰራበት ፣ በገንዘቡ ፍቅርንም ክብርንም ያተርፋል ። በገንዘቡ ግን ክፋት ከሰራበት ፣ ተፈርቶ  ሊከበር ይችላል ፣ ነገር ግን ተወዶ ሊከበር በፍጹም አይችልም ። ተፈርቶ ከመከበር ተወዶ መከበር የተሻለ ነው ። የክብር የመጨረሻው ከፍታ ( climax ) ፍቅር ነው ። ገንዘብን የክብር ምንጭ ማድረግ የክብርን ከፍታ ሳይሆን የሚያሳየን ፣ የሞራል አዘቅት ነው የሚሆንብን ። ገንዘብ የፍቅር መሳርያ እንጅ ፍቅር የገንዘብ መሳርያ ሊሆን አይችልም ። ገንዘብን የፍቅር መሳርያ ካደረግን ፣ በገንዘባችን መልካም ስራ በመስራት ፣ ከክብር ሁሉ የላቀውን ክብር ማግኘት እንችላለን ። ፍቅርን ግን የገንዘብ መሳርያ ካደረግን ፣ የላቀውን ክብር ሳይሆን በፈጣሪ ዘንድ የተናቀውን ክብር ነው የምናገኘው ። ይህ ክብር እውነተኛ ሳይሆን አርተፊሻል ነው ። ዘላለማዊ ሳይሆን ጊዜያዊ ነው ። ከሰው ልብ ሳይሆን ከሰው አፍ ብቻ የሚገኝ ክብር ነው ። ስለዚህ ፍቅር በገንዘብ አይሰፈርም ፣ ነገር ግን ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም ይችላል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ።     

    ፍቅርና ውበት አብረው ይሄዳሉ ። ከዉጪ ይልቅ የውስጥ ውበት ለፍቅር ቅርብ ነው ። ፍቅር የሚታይ ሳይሆን የሚኖር ነው ። ውስጣዊ ውበትም በመኖር የሚገነባ ስብእና ነው ። ስለዚህ ውስጣዊ ውበት እና ፍቅር በጣም ይጣጣማሉ ። ውጪያዊ ውበት ግን ለጊዜያዊ ስሜት ቅርብ ነው ። ምክንያቱም ውጪያዊ ውበት የሚታይ እንጅ የሚኖር አይደለም ። '' ሲያዩት ያላመረ ሲበሉት ያቅራል '' ይባላል ። ይህ ለምግብ እንጅ ለሰው ልጅ አይሰራም ። ሲያዩት ያማረ ሰው ፣ አብረው ሲኖሩ ያቅር ይሆናል ። ሲያዩት ያላማረው ግን ለፍቅር ምቹ ሊሆን ይችላል ። የአፍንጫ ጎራዳ ወይም ሰልካካ መሆን ለፍቅር ግድ አይሰጠውም ። ካማረ አይን በላይ ያማረ አመለካከት ለፍቅር አስፈላጊ ነው ። ከዉብ ከንፈር በላይ ውብ ንግግር ፍቅርን ይማርከዋል ። ከለስላሳ ጸጉር በላይ ለስላሳ ባህሪ ፍቅርን ይገዘዋል ። ትህትና ውበት ነው ። ፍቅር ካለ ትህትና አለ ። ችምችም ካለ ጥርስ በላይ ትህትና ሰውን ውብ ያደርጋል ። ትሁት ሰው ውብ ነው ፣ ውጪያዊ ሳይሆን ውበቱ ውስጣዊ ነው ። ደግነት ውበት ነው ። ደግነት የሚኖረው ፍቅር ባለበት ነው ። ከተስተካከለ ቁመና በላይ ደግነት ሰውን ውብ የማድረግ አቅም አለው ። ርህራሄም ውበት ነው ። ያለ ፍቅር ርህራሄ አይታሰብም ። ከአለንጋ ጣት በላይ ርህራሄ ለሰው ልጅ ውበቱ ነው ። የሰው እውነተኛ ውበቶች ርህራሄ ደግነት ትህትና ቅንነት እና የመሳሰሉት ናቸው ። እነዚህ ደግሞ በሌላ አነጋገር የፍቅር መገለጫዎች ናቸው ። ፍቅር ከውብ አካል በላይ ውብ ስብእና ይገዛዋል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ። 

   ከፍቅር ሁሉ የላቀው ፍቅር ፈጣሪን መውደድ ነው ። ሲቀጥል የሰውን ልጅ መውደድ ነው ። ከእነዚህ አካላት ውጪ የሰው ልጅ አብልጦ ሊወደው የሚችለው ነገር ሊኖር አይገባም ። እነርሱን በማስቀደም ሌላን ነገር መውደድ ይችላል ። ነገር ግን ከእነርሱ አስቀድሞ የሚወደው ነገር ሊኖር አይገባም ። ከሰው አብልጦ ገንዘብን መውደድ ገብጋባነት ነው ። ገብጋባነት ደግሞ እንስሳነት ነው ። ከሰው ይልቅ እንስሳን መውደድ ልበቢስነት ነው ። ልበቢስነት እንሰሳነት ነው ። እንሰሳነትም ልበቢስነት ነው ። ከሰው ይልቅ ሱስን መውደድ ልበ ደንዳናነት ነው ። ከልጆቹ ቁማር የበለጠበት አባት ልበ ደናዳና ነው ። ከሚስቱ ይልቅ አልኮል የሚናፍቀው ባል ልበ ደንዳና ነው ። ለባል ሳይሆን ለሀሜት ቅድሚያ የምትሰጥ ሚስት ልበ ደንዳና ናት ። ከሰው በላይ እውቀትን የሚወዱ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። ከእውቀት ክብርን ለማግኘት ብለው ፍቅረኛቸውን ችላ ያሉ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። እውነተኛ ፍቅር ለሁሉም ውይም ከሁሉ ነገር ይልቅ ሰውን ማስቀደም ነው ። እውቀትን ገንዘብን ቁስን ሱስን አብልጦ መውደድ ሰውን ያሳጣል ። ሰውን አብልጦ መውደድ ግን እውቀትንም ገንዘብንም አያሳጣም ። ሰውን ማጣት ሁሉን ማጣት ነው ። ሰውን ማግኘት ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ማለት ሰውን እንደራስ በመውደድ ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ካለ ሁሉም አለ ፣ ፍቅር ከሌለ ምንም የለም ። ይህ ከሁሉ የላቀው የፍቅር መርህ ነው ።  

    '' ፍቅር መነሻም መድረሻም ነው ። ምክንያቱም የመርሆች ሁሉ አለቃ ነው ። ''                 

Wednesday, July 30, 2025

እይታ | Perception

                                             ዋናው ኮንቴክስቱ ( አውዱ )

     ሁለት መታወቂያ የተሰኘው ፊልም ላይ ፣ ዳዊት አባተ ወይም በገጸ ባህሪ ስሙ ቢኒያም እንዲህ ሲል ይደመጣል ‘’ በህይወት እውነት ወይም ውሸት ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ፣ ሞራላዊ ወይም ኢ ሞራላዊ የሚባል ነገር የለም ፣ ዋናው አውዱ ( ኮንቴክስቱ ) ነው ። ’’ አውድ ሲባል በዋናነት ሁኔታ ማለት ነው ። ሰው ህይወቱን በአውድ ወይም በሁኔታ የሚመራ ከሆነ ፣ እውነትን በእውነትነቱ ሳይሆን የሚመዝነው ፣ እውነት በሚያመጣው ውጤት ላይ ተመስርቶ ነው ፣ እውነትን የሚለካው ። ይህ ደግሞ የሰውን ልጅ ውጤት ተኮር እንጅ ሂደት ተኮር አያደርገውም ። ነጮቹ ሰው ከውጤቱ በላይ ሂደቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሲመክሩ ‘’ Trust the process! ‘’ ይላሉ ። 

   ከውጤቱ በላይ ለሂደቱ ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች በመርህ የሚመሩ ናቸው ። ከሂደቱ በላይ ለውጤቱ ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ መርህ አልባ ናቸው ። ያው የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ይመቻቸዋል ። አብዝተው ውጤት የሚፈልጉ ሰዎች ፣ መርዝን መድሃኒት ነው እስከማለት ይደርሳሉ ። በእውነት መንገድ ውጤት ከሚያጡ ፣ በውሸት ተጉዘው ውጤት ላይ መድረስ ምርጫቸው ነው ። ለእነርሱ እውነት ከሁኔታ በልጦ አያውቅም ። ሁኔታ ነው ከእውነት የሚበልጥባቸው ። ስለ እውነት ማጣት መራብ መጠማት መዋረድ ፣ ለእነርሱ የጀግና ሳይሆን የቀሽም ሰው ተግባር ነው ። 

    በእርግጥ አውዳዊ ፍቺ የሚያስፈልገው እውነት አለ ። ነገር ግን ሁሉም እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። ለምሳሌ የወል እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። የወል እውነት ቦታ ጊዜ ሁኔታ የማይቀያይሩት እውነት ነው ። ጸሀይ በምስራቅ ወጥታ በምራብ ትጠልቃለች ። ይህ የሰፈር እውነት ሳይሆን የዓለም እውነት ነው ። ውሀ ውሀ እንጅ ነዳጅ አይሆንም ። ነዳጅም እንደዚሁ ውሀ ሊሆን አይችልም ። ይህ እውነት የሆኑ ቡድኖች ያጸደቁት ሳይሆን ፣ ሁሉም ሰው አምኖ የተቀበለው እውነት ነው ። ውጤት ተኮር የሆኑ ሰዎች ግን ፣ ከቻሉ ውሀ እና ነዳጅን ቀላቅለው ፣ ነዳጅ ነው ብለው ይሸጣሉ ። ምክንያቱም ከሂደቱ በላይ የሚተማመኑት በውጤቱ ነው ። ለዚህ ደግሞ ማሳመኛ ይሆናቸው ዘንድ ፣ ውሸትን ብቻ ይዘው አይቀርቡም ። ውሸትን በእውነት ሸፍነው ያቀርባሉ ።

   ውጤት ተኮር መሆን በራሱ ስህተት አይደለም ። ስህተት የሚሆነው ለውጤቱ ሲባል የማጭበርበር ስራ ሲሰራ ነው ። ውጤቱን ጥሩ ለማድረግ ሂደቱን መጥፎ ማድረግ ትክክል አይደለም ። ከሆነ ወይም ከተቻለ ውጤቱንም ጥሩ ሂደቱንም ትክክል ማድረግ ተገቢ ነው ። ካልሆነ ግን ውጤቱ ምንም ቢሆን ፣ ሂደቱን ትክክል ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ። አንድ አንድ ሁኔታዎች ፣ የሰው ልጆች እስከሆንን ድረስ ፣ ሂደቱን በማበላሸት ውጤቱን ማሳመር እንደሚቻል ይጠቁሙናል ። ያኔ የገጠመን እውነት የወል ሳይሆን አንጻራዊ ስለሆነ ፣ ውሳኔያችንን እንደሁኔታው ማድረግ ግድ ይላል ።

    አንጻራዊ እውነት በአማራጭ የተሞላ ነው ። እንደ ሰው ፍጹም ስላልሆንን ፣በዚህ ጊዜ ውሳኔያችን ከሂደቱ በላይ በውጤቱ ላይ ቢመሰረት መልካም ነው ። ምርጫችንም የተሻለ ይሆናል ። በስህተት መንገድ ትክክል የሆነ ውጤት ማምጣት ባይቻልም ፣ በአንጻሩ ጥሩ ነገር ማድረግ ይቻላል ። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲገጥመን ፣ ውሸት ወይም እውነት ፣ ትክክል ወይም ስህተት ሚዛን አይሆኑም ። ሚዛን የሚሆኑት ማዳን ወይም መግደል ፣ ማጥፋት ወይም ማልማት ፣ ማበላሸት ወይም ማስተካከል ናቸው ። በእርግጥ የሀገሬ ሰው '' ካልደፈረሰ አይጠራም ። '' ይላል ። የደፈረሰ ሁሉ ይጠራል ማለት ግን አይደለም ። አንዳንድ ነገሮች ላይጠሩ ይደፈረሳሉ ። ላይቃኑ ይጣመማሉ ፣ ላይስተካከሉ ይበላሻሉ ፣ ላይመለሱ ይለወጣሉ ። ስለዚህ በህይወት ስንኖር ፣ ከውሳኔ በፊት ሁኔታን በጥልቀት መፈተሽ እና መመዘን ያስፈልጋል ። ምክንያቱም ማዳን የምንችለውን ልንገድል እንችላለን ። መስተካከል የሚችለው እንደተበላሸ ሊቀር ይችላል ። መቆም ያለበት ወድቆ እንክትክቱ ሊወጣ ይችላል ። ሰዎች ነን ፍጹም ልንሆን አንችልም ። ስለዚህ ሁኔታን በአንጻራዊ እውነት ከምንመዝን ፣ አንጻራዊ እውነትን በሁኔታ ( context) ብንመዝን የተሻለ ነው ።

   እውነት ከእውነት ይለያያል ። ሁሉም እውነት እኩል መታየት የለበትም ። የሚጠቅም እውነት ከሚጎዳ እውነት ጋር እኩል መታየት አይኖርበትም ። የሚያጣላ እውነት ከሚያፋቅር እውነት ጋር ሊስተካከል አይገባውም ። ጥቁር ታሪክ የተሸከመ እውነት ፣ የጀግንነት ታሪክ ከተሸከመ ታሪክ ጋር እኩል ትኩረት ሊሰጠው አይገባም ። ምክንያቱም ጥቁር ታሪክ ጸጸትን በቀልን ቁጭትን ነው የሚወልደው ። የጀግንነት ታሪክ ግን ሞራልን አሸናፊነትን አንድነትን ነው የሚወልደው ። ስለዚህ ለሁሉም እውነት መታመን ታማኝ አያደርግም ። ትክክለኛ ታማኝነት ፍቅርን ፍትህን አንድነትን ለሚያሰፍን እውነት መታመን ነው ። ለሁሉም እውነት መታመን ጅልነት ነው ። ለምርጥ እውነት መታመን ግን ጀግንነት ነው ። በነገራችን ላይ ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ የሚሆኑ ሰዎች አሉ ፣ እነዚህ ሰዎች ክፉዎች ናቸው ። ምክንያቱም የእነርሱ እውነት ፍቅር የለውም ። ፍቅር የሌለው እውነት ደግሞ የሞተ ነው ። ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ ከመሆን ፣ ሰውን ለማዳን ውሸታም መሆን ይሻላል ። ነገርን ከሰው አንጻር እንጅ ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ልክ አይደለም ። የሚጎዳን እውነት ይዞ መኖር ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ነው ። 

   ዋናው አውዱ ( ኮንተክስቱ ) ማለት በምንም ጉዳይ ቢሆን ሰውን እናስቀድም ማለት ነው ። እውነትም አንጻራዊ እውነት ሰብአዊነትን ማስቀደም አለባቸው ። በእርግጥ የወል እውነት ፣ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰብአዊነትን ቢያስከብር እንጅ አያዋርድም ። አንጻራዊ እውነት ግን አስቸጋሪ ነው ። ፍትህን ለማዛባት ሰብአዊነትን ለመጣስ ሊውል ይችላል ። ስለዚህ አንጻራዊ እውነት ሲገጥመን መጠንቀቅ አለብን ። 

  '' ከሁኔታ የሚበልጠው እውነት የሰውን ልጅ ክብር የሚጨምር ነው ። በሁኔታ የሚገደብ እውነት ግን የሰውን ክብር ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል ። ''    

    

Tuesday, July 15, 2025

እይታ | Perception

                                                             ራስን መመርመር

  ራስን መመርመር ራስን መመልከት ነው ። አንድ የላቦራቶሪ ቴክኒሺያን በሰው ደም ውስጥ ፣ በሽታ አምጪ ህዋስ መኖሩን ለማረጋገጥ ፣ ማይክሮስኮፕን ይጠቀማል ። በተመሳሳይ የሰው ልጅ የስብእና በሽታ ሲገጥመው ፣ ራሱን ለመመርመር የስብእና ግድፈቱን የሚለይበት ማይክሮስኮፕ ያስፈልገዋል ። በሽታውን ለማወቅ ማይክሮስኮፑን በአግባቡ መጠቀም ግድ ይላል ። የሰው ልጅ የራሱን የስብእና በሽታ የሚያይበት ማይክሮስኮፕ አንዱ ጥሞና ነው ። ጥሞና የባህሪ በሽታን የመለየት ከፍተኛ አቅም አለው ። ጥሞና ሰውን ከፍተኛ መረጋጋት ውስጥ ይከታል ። ሰውን እንደ ፍሪጅ አቀዝቅዞ ፣ ባህሪን ከሚበክል ስሜት እና ሀሳብ ነጻ ያደርጋል ። ሰው በሽታውን አውቆ መድሀኒቱን እንዲፈልግ ፣ ጥሞና ብርሃን ይሆነዋል ። ጥሞና ዝምታ ነው ። ፈርቶ ዝም ማለት ሳይሆን አቅዶ ዝም ማለት ነው ።

  ፈርቶ ዝም ማለት ሁለት ገጽ አለው ። አንድም ለኪሳራ በሌላ በኩል ደግሞ ለትርፍ ሊዳርግ ይችላል ። የፍርሀት ዝምታ ከስሜታዊ ሰው ጥቃት ይጠብቀናል ። በስሜታዊ ሰው ፊት በፍርሀትም ይሁን በእውቀት ዝም ማለት ራስን ከአደጋ መከላከል ነው ። የፍርሀት ዝምታ ከዚህ አንጻር ሲታይ ጠቃሚ ነው ። ግን በሌላ ገጹ ሲታይ የፍርሀት ዝምታ ብዙ ነገር ያሳጣል ። ዝምታ ወርቅ ነው የሚባለውን ያህል ውድቅ የሚሆንበት ቦታም አለ ። መናገር ሲኖርብን ዝም ማለት ያሳጣል ። በእርግጥ ዝም ማለት ሲገባ መናገርም ያስቀጣል ። ሁለቱም እኩል ጉዳት አላቸው ። ከሁለቱም ጉዳት ነጻ የሚያወጣን ማስተዋል ነው ። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ጥሞና ነው ። 

 ጥሞና የነገርን ክብደት እና ቅለት ለመለየት ወሳኝ ነው ። ጥሞና የማስተዋል አቅምን ሲጨምር ፣ የፍርሀት ዝምታ ግን ማስተዋልን ይቀንሳል ። በጥሞና ውስጥ ነገርን በልኩ ማወቅ እና መረዳት ይቻላል ። ጤናማውን ከበሽተኛው ለመለየት ቀላል ይሆናል ። ይህ ደግሞ ራስን ለማስተካከል እድል ይሰጣል ። ጥሞና ራስን መመርመሪያ ምርጥ ማይክሮስኮፕ ነው ።

   ሌላኛው ራስን መመርመሪያ ማይክሮስኮፕ ተግባቦት ነው ። ከሰው ጋር መነጋገር ራስን ማያ መስተዋት ነው ። ሰው ፊቱ ላይ ያለውን ጉድፍ ለማጽዳት መስተዋት ይጠቀማል ። የባህሪ ግድፈቱን ለማጽዳት ደግሞ አጠገቡ ያለውን የቅርቤ የሚለውን ሰው ፣ እንደመስተዋት መጠቀም አለበት ። ሰው በምልአት ራሱን ማየት አይችልም ። ለእርሱ የተሰወረው አጠገቡ ላለ ሰው ግልጽ ሊሆን ይችላል ። በተለይ በሳል ሰው ካለ ፣ የማይታየውን ማየት የሚችል አቅም ስላለው ፣ ራስን ለመመርመር እና ለማስተካከል ጥሩ አቅም ይሆነናል ። ሰው ለብቻው ራሱን በመመርመር ውጤታማ አይሆንም ። የሚያግዘው እና የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል ።

   ሰው ራሱን ሲመረምር ሀቀኛ መሆን አለበት ። ስህተቱን ስህተት ፣ ልኩን ትክክል ነው ማለት አለበት ። ስህተቱን ልክ ልኩን ስህተት ካደረገ ግን ፣ ራሱን እየመረመረ ሳይሆን ራሱን እያባበለ ነው ። ራስን በማባበል ደግሞ አሉታዊ እንጅ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ። እየባሱ መሄድ እንጅ መሻሻል አይኖርም ። ሰው ወደ ላይ የሚያድገው እውነትን መቀበል ሲችል ነው ። ወደ ታች የሚወርደው እውነትን መቀበል ሲያቅተው ነው ። ለስህተት ምክንያት እየሰጡ ራስን ከእውነት ማሸሽ ፣ መጨረሻው እድገት ሳይሆን ውርደት ነው ።

 ስለዚህ ራስን መርምሮ ለማሻሻል ፣ እውነትን መቀበል ቁልፍ ብቻ አይደለም ፣ የቁልፎች ሁሉ ቁልፍ ( Master key ) ነው ።

   ትክክለኛ ራሱን መርማሪ ፣ ተንኮል በመስራቱ ራሱን ደግ አደረክ ብሎ አያሞግስም ። ባይሆን በመጸጸት ራሱን ለማስተካከል ይጥራል ። ባደረገው መልካም ነገር ይደሰታል ራሱንም ይሸልማል ። በሰራው ስህተት ደግሞ ራሱን ይወቅሳል ። በልኩ ያዝናል በልኩ ደግሞ ይደሰታል ። ደስታው የበለጠ ተግቶ እንዲሰራ ሀይል ይሆነዋል ። ሀዘኑ ደግሞ ስህተቱን ይቀንስለታል ። በስህተት ማዘን በመልካም ስራ መደሰት ሰውነት ነው ። በተንኮል መደሰት በመልካም ስራ መከፋት አውሬነት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ማታ ላይ ተኝተው ፣ የቀን ስራቸውን የሚያሰላስሉት ፣ በሰሩት ተንኮል ለመሳቅ እና ባደረጉት መልካም ነገር ለማዘን ነው ። ከዚያም በተጨማሪ የተሻለ ተንኮል ለማሰብ እና ለማቀድ ነው ።

     ተንኮል ለማቀድ ራሱን ከሚመረምር ሰው ፣ ራሱን የማይመረምር ብኩን ይሻላል ። ምክንያቱም ስህተትን ሆን ብሎ ሳይሆን ፣ ባለማወቅ ነው የሚሰራው ። አስቦ ራሱን መመርመር ባይችልም ፣ በሂደት በህይወት ልምድ ስህተቱን መቀነሱ አይቀርም ። ይህች ምድር ትልቅ ጥፋትን የምታስተናግደው ፣ ሳያውቁ ስህተት በሚሰሩት ሳይሆን አውቀው ሆን ብለው ስህተት በሚሰሩት ነው ። ክፉ ለማድረግ ራስን መመርመር ፣ ራስን መመርመር ሳይሆን ራስን መራር ማድረግ ነው ። ( Weak acid ) ደካማ አሲድን ጠንካራ አሲድ ( Strong acid ) ማድረግ ነው ። ይህ ደግሞ ከጎጂነት ወደ አጥፊነት መቀየር ነው ። ሰው ራሱን የሚመረምረው አጥፊ ከሆነ አልሚ ለመሆን ነው ። ተንኮለኞች ግን ራሳቸውን የሚመረምሩት የበለጠ አጥፊ ለመሆን ነው ።

   ራሳችንን መመርመር  ለክፋት ሳይሆን መልካም ለማድረግ መሆን አለበት ። ስህተትን ለመቀነስ እንጅ ስህተትን ወደ ተንኮል ለመቀየር መሆን የለበትም ። ራስን ለማረም እንጅ አረም ለማድረግ ራስን መፈተሽ አያስፈልግም ። ስራን ለማስተካከል እንጅ ለማበላሸት ራስን መመርመር አስፈላጊ አይደለም ። በዚህች ምድር ስንኖር ራስን መመርመር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን ራሳችንን መመርመር ያለብን ምድርን ለማልማት እንጅ ለማጥፋት አይሁን ።

    ‘’ ራስን ለማስተካከል ራስን መመርመር ነው ቁልፉ ። ‘’                 

Saturday, July 5, 2025

እይታ | Perception

                                                       

                       መቅናት እና ማስቀናት

      ‘’ የቀናም ያስቀናም ሁሉም ቤት ያፈርሳል ። ‘’ አለ ዘፋኙ ። ምክንያቱም መቅናትም ማስቀናትም የትዳር ማነቆዎች ናቸው ። ትዳርን የማፍረስ አቅም አላቸው ። መቅናት እኔ ብቻ ልወደድ ባይነት ስለሆነ ፣ በፍቅር ውስጥ መጋራትን እንጅ ማጋራትን አይፈቅድም ። ቅናት ከመስጠት ይልቅ መቀበል ላይ ትኩረት ያደርጋል ። ዞሮ ዞሮ ቅናት የፍቅር ተቃራኒ ነው ። ምክንያቱም ፍቅር ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ከፍ ያለ ቦታ መስጠት ነው ። መስጠት ባነሰበት ሁሉ ፍቅር ያንሳል ። በመቀበል ብቻ ደግሞ ፍቅርን ማጎልበት አይቻልም ። መስጠትም መሰጠትም ባለበት ግን ፍቅር ያድጋል ይበዛል ። ያኔ መቅናትም ማስቀናትም አቅም ያጣሉ ። ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ልብ ለቅናት ቦታ የለውም ።

   ቀናተኛ ሰው ለሰው ሲሰጥ ከእርሱ ላይ የተወሰደበት ይመስለዋል ። ካገኘው ይልቅ ያጣው ይታየዋል ። ከተሰጠው ይልቅ የተነፈገው ይጎላበታል ። ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ ምክንያት ይፈልጋል ። ቅናት ልብን ስለሚሰውር ፣ በቀናተኛ ሰው ዘንድ ከእርሱ ውጪ ሌላ ሰው ልክ ሆኖ አያውቅም ። ለእርሱ ልኩ ስህተት ፣ ስህተቱ ደግሞ ልክ ይሆናል ። ይህ ብቻ አይደለም ስህተትን ማጉላት ፣ ልክ የሆነውን ስራ ማኮሰስ ይችላል ። ለራስ መኖር እንጅ ለሌላው መኖር በቀናተኛ ሰው ዘንድ አይታሰብም ። ለሰዎች ሲኖር የማይደሰት ፣ ሰዎች ሲኖሩለት ብቻ የሚደሰት ራስ ወዳድ ፍጥረት ነው ። መኖር ሳይሆን ምን ጊዜም ማኖር ነው የሚፈልገው ። ከራሱ ውጪ ማየት የማይችል እውር ነው ። ቀናተኛ ሰው የራስ መንገድ እንጅ የጋራ መንገድ አይመቸውም ።

የራስ መንገድ አስፈላጊ ቢሆንም ፣ ለጋራ መንገድ ግን ክፍት መሆን አለበት ። የጋራ መንገድን ማስተናገድ የማይችል የራስ መንገድ ግትር ነው የሚያደርገው ። ይህ ደግሞ ከስምምነት ይልቅ ለግጭት ይዳርጋል ። በቀላሉ የሚፈታ ሳይሆን የማይፈታ ግጭት ነው የሚፈጥረው ።

   መቅናት መቃጠልም ማቃጠልም ነው ። መጀመሪያ በሰው ድርጊት መቃጠል ነው ። ሲቀጥል ነገር ማቀጣጠል ነው ። ሲለጥቅ በራስ ድርጊት ሌላውን ማቃጠል ነው ። በቅናት ቤቱን ያፈረሰ እንጅ የገነባ የለም ። ግንኙነቱን የተወ እንጅ በግንኙነቱ ፍሬ ያፈራ የለም ። ያፈረ እንጅ የኮራ ሊኖር አይችልም ። በጥርጣሬ እየተወጉ ሰላምን ማፍረስ እንጅ መገንባት በቅናት ፈጽሞ አይቻልም ። ‘’ ተጠራጥሮ ትዳር ኑሮ መች ያሞቃል ፣ የቀናም ያስቀናም ሁሉም ቤት ያፈርሳል ። ‘’ እንዲል ዘፋኙ ። ቅናት እና ጥርጣሬ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ። ቅናት ባለበት ጥርጣሬ ሊኖር ግድ ነው ። ጥርጣሬ ባለበት ቅናት ሊጠፋ አይችልም ። ሁለቱ ተባብረው ነው ሰውን አንድደው አመድ የሚያደርጉት ። ቅናት እና ጥርጣሬ!

   መቅናት ብቻ አይደለም ማስቀናትም በሽታ ነው ። ለማቃናት ሳይሆን ለማስቀናት የሚለፉ ሰዎች አሉ ። ማስቀናት የሚወዱ ሰዎች ፣ በማስደሰት ሳይሆን በማናደድ የሚያምኑ ናቸው ። በሰው ንዴት የሚደሰቱ ሲበዛ ራስ ወዳድ ናቸው ። ዉድ መሆናቸውን ለማሳየት ፣ ርካሽ መንገድ የሚጠቀሙ ብኩኖች ናቸው ። በማስቀናት ፍቅርን ለማጎልበት የሚጥሩ ጅሎች ናቸው ። ፍቅር በቅናት ይላላል እንጅ አይጠነክርም ። ቅናት በፍቅር ውስጥ የእርጎ ዝንብ ነው ። ልብን የሚበክል ባክቴሪያ ነው ።

ቅናትን በማስቀናት ጎትቶ ማምጣት ፣ ንጹህ ልብን መበከል ነው ። የተበከለ ልብ ደግሞ ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ ምቹ ነው ። የቅናትም የማስቀናትም መጨረሻ ጥላቻ ነው ። ሁለቱም የልብ በካይ ጋስ ( Carbon di oxide ) ናቸው ። ስለዚህ ለማቃናት እንጅ ለማስቀናት አንኑር ።

   በአርአያ ( Role model ) መቅናት ክፋት የለውም ። ይህ ቅናት በጎ ነው ። በሰው ልብ ውስጥ ክፋትን ሳይሆን ፣ ለስራ መነሳሳትን ( Motivation ) ነው የሚፈጥረው ። መጥፎው ቅናት ግን ለስራ ሳይሆን ለነገር ነው ሚያነሳሳው ። እኔ እንደሱ በሆንኩ ማለት እና እኔ ተከብሬ እርሱ በተዋረደ ማለት ይለያያል ። በጎ ቅናት ራስን ለማክበር መመኘት ነው ። መጥፎ ቅናት ደግሞ ሌላውን ለማዋረድ መጣር ነው ። በጎ ቅናት ከሰው እኩል ለመሆን መጣር ነው ። መጥፎ ቅናት ግን ከሰው ሁሉ በልጦ ለመገኘት መታገል ነው ። በሰው ጉብዝና በበጎ የቀና ሰው ፣ እንደሰውየው ጎበዝ ይሆናል ። በክፋት የቀና ሰው ግን ጎበዝ ሳይሆን ግብዝ ነው የሚሆነው ። በነገራችን ላይ በቅናት የሰውን ነገር የራስ ማድረግ አይቻልም ። ነገር ግን በበጎ ቅናት ካደረብን ፣ ቅናቱ በፈጠረው መነሳሳት ፣ ትጉ በመሆን የሰውን ሳይሆን ፣ የራስን ህልም ልክ እንደሌላው እውን ማድረግ ይቻላል ። በክፋት ግን የሰውን ነገር የራስ ለማድረግ ከጣርን ያለንን እናጣለን ።

 እንደ አልበርት አንስታይን የፊዚክስ ሊቅ ብሆን ብሎ መቅናት ችግር የለውም ። እንደ አልበርት አንስታይን ለምን እኔም እኩል ችሎታ አልተሰጠኝም ብሎ መቅናት ግን ትርፉ በሽታ ነው ። ምክንያቱም ህይወት አንተ ራስህን በትጋት ስታገኝ እንጅ የምታከብርህ ፣ በቅናት ስትንጨረጨር ዞር ብላ አታይህም ።

የስኬት ምስጥሩ ሰውን ማየት ሳይሆን ፣ በሰው ውስጥ ራስን ማየት ነው ። እዚች ምድር ላይ ሰውን በማየት ብቻ የከበረ የለም ። በጎ ቅናት በሰው ውስጥ ራስን ማየት ነው ። መጥፎ ቅናት ግን ከሰው ጋር ራስን ማነጻጸር ነው ። ከሰው መማር እንጅ በሰው መማረር አያዋጣም ። መማር ወይ ከሰው እኩል አልያም ከፍ ያደርገናል ። መማረር ግን በምንም ሂሳብ ከሰው እኩል አይደርገንም ። በጎ ቅናት መማር ነው ። መጥፎ ቅናት መማረር ነው ። ስለዚህ በበጎ እንቅና ፣ በክፋት ከመቅናት ግን እንጠንቀቅ ።

   ‘’ መቅናትም ማስቀናትም በሽታ ነው ፣ በበጎ መቅናት ግን መልካም እይታ ነው ። ‘’

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...