ፍቅር እና መስፈርት
ፍቅር መርህ እንጅ መስፈርት የለውም ። መስፈርት ለፍቅር ምንም ነው ። ለፍቅር ሰው ምንም ይሁን ምን ፣ ይኑረው አይኑረው ሰው መሆኑ ብቻ በቂ ነው ። በፍቅር ዘንድ የሰው መርዘም ወይም ማጠር ፣ ዋጋውን ከፍ ወይም ዝቅ አያደርገውም ። መቅላት ወይም መጥቆር የሚጨምረው የሚቀንሰው ነገር የለም ። ጌታም ይሁን ባርያ ከመፈቀር የሚያግደው አይኖርም ። ለመፈቀር ሰው ዶክተር እንጅነር ፕሮፌሰር ባለጸጋ ወይም አዋቂ መሆን አይጠበቅበትም ፣ መልካም ሰው መሆኑ በቂ ነው ። ለፍቅር የሰው ማእረጉ ሳይሆን መልካምነቱ ነው የሚያስፈልገው ። በትጋት ጎበዝ የሆኑ ሰዎች ፣ ለመልካምነት ግን ሰነፍ የሆኑ ሰዎች ፣ በፍቅር ዘንድ ዋጋ የላቸውም ። ትጋት ያስከብራል ግን ለስራ ባለን ፍቅር እንጅ ለሰው ባለን ፍቅር አይደለም ። ለስራ ያለን ፍቅር ብቻ ሰው አያደርገንም ፣ ለሰው ያለን ፍቅር ነው ሰው የሚያደርገን ። ስለዚህ ስራ ስንሰራ ለሰው እንደምንሰራ እያሰብን እንስራ ። ያኔ ፍቅር ሰውን ለመጥቀም እንጅ ለመጉዳት መስራት እንደሌለብን ያሳስበናል ። ይህ የፍቅር መስፈርት ሳይሆን መርህ ነው ።
ሰው ገንዘብ ስላለው ሊከበር ይችላል ። ያለፍቅር ግን በገንዘቡ ብቻ ሊወደድ አይችልም ። ሰው መወደድም መከበርም የሚችለው ፣ በገንዘቡ ላይ መልካምነትን ሲጨምር ነው ። ገንዘብ ሲቀነስ ፍቅር ፣ እኩል ይሆናል ክብር ሲቀነስ መወደድ ። መወደድ የሌለው ክብር ሰውን በሰው ልብ ውስጥ አያነግስም ። ክብር ከፍቅር ጋር ነው በሰው ልብ ላይ የሚያነግሰው ። ገንዘብ ክብርም ፍቅርም መሆን ይችላል ። ሰው በገንዘቡ መልካም ስራ ከሰራበት ፣ በገንዘቡ ፍቅርንም ክብርንም ያተርፋል ። በገንዘቡ ግን ክፋት ከሰራበት ፣ ተፈርቶ ሊከበር ይችላል ፣ ነገር ግን ተወዶ ሊከበር በፍጹም አይችልም ። ተፈርቶ ከመከበር ተወዶ መከበር የተሻለ ነው ። የክብር የመጨረሻው ከፍታ ( climax ) ፍቅር ነው ። ገንዘብን የክብር ምንጭ ማድረግ የክብርን ከፍታ ሳይሆን የሚያሳየን ፣ የሞራል አዘቅት ነው የሚሆንብን ። ገንዘብ የፍቅር መሳርያ እንጅ ፍቅር የገንዘብ መሳርያ ሊሆን አይችልም ። ገንዘብን የፍቅር መሳርያ ካደረግን ፣ በገንዘባችን መልካም ስራ በመስራት ፣ ከክብር ሁሉ የላቀውን ክብር ማግኘት እንችላለን ። ፍቅርን ግን የገንዘብ መሳርያ ካደረግን ፣ የላቀውን ክብር ሳይሆን በፈጣሪ ዘንድ የተናቀውን ክብር ነው የምናገኘው ። ይህ ክብር እውነተኛ ሳይሆን አርተፊሻል ነው ። ዘላለማዊ ሳይሆን ጊዜያዊ ነው ። ከሰው ልብ ሳይሆን ከሰው አፍ ብቻ የሚገኝ ክብር ነው ። ስለዚህ ፍቅር በገንዘብ አይሰፈርም ፣ ነገር ግን ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም ይችላል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ።
ፍቅርና ውበት አብረው ይሄዳሉ ። ከዉጪ ይልቅ የውስጥ ውበት ለፍቅር ቅርብ ነው ። ፍቅር የሚታይ ሳይሆን የሚኖር ነው ። ውስጣዊ ውበትም በመኖር የሚገነባ ስብእና ነው ። ስለዚህ ውስጣዊ ውበት እና ፍቅር በጣም ይጣጣማሉ ። ውጪያዊ ውበት ግን ለጊዜያዊ ስሜት ቅርብ ነው ። ምክንያቱም ውጪያዊ ውበት የሚታይ እንጅ የሚኖር አይደለም ። '' ሲያዩት ያላመረ ሲበሉት ያቅራል '' ይባላል ። ይህ ለምግብ እንጅ ለሰው ልጅ አይሰራም ። ሲያዩት ያማረ ሰው ፣ አብረው ሲኖሩ ያቅር ይሆናል ። ሲያዩት ያላማረው ግን ለፍቅር ምቹ ሊሆን ይችላል ። የአፍንጫ ጎራዳ ወይም ሰልካካ መሆን ለፍቅር ግድ አይሰጠውም ። ካማረ አይን በላይ ያማረ አመለካከት ለፍቅር አስፈላጊ ነው ። ከዉብ ከንፈር በላይ ውብ ንግግር ፍቅርን ይማርከዋል ። ከለስላሳ ጸጉር በላይ ለስላሳ ባህሪ ፍቅርን ይገዘዋል ። ትህትና ውበት ነው ። ፍቅር ካለ ትህትና አለ ። ችምችም ካለ ጥርስ በላይ ትህትና ሰውን ውብ ያደርጋል ። ትሁት ሰው ውብ ነው ፣ ውጪያዊ ሳይሆን ውበቱ ውስጣዊ ነው ። ደግነት ውበት ነው ። ደግነት የሚኖረው ፍቅር ባለበት ነው ። ከተስተካከለ ቁመና በላይ ደግነት ሰውን ውብ የማድረግ አቅም አለው ። ርህራሄም ውበት ነው ። ያለ ፍቅር ርህራሄ አይታሰብም ። ከአለንጋ ጣት በላይ ርህራሄ ለሰው ልጅ ውበቱ ነው ። የሰው እውነተኛ ውበቶች ርህራሄ ደግነት ትህትና ቅንነት እና የመሳሰሉት ናቸው ። እነዚህ ደግሞ በሌላ አነጋገር የፍቅር መገለጫዎች ናቸው ። ፍቅር ከውብ አካል በላይ ውብ ስብእና ይገዛዋል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ።
ከፍቅር ሁሉ የላቀው ፍቅር ፈጣሪን መውደድ ነው ። ሲቀጥል የሰውን ልጅ መውደድ ነው ። ከእነዚህ አካላት ውጪ የሰው ልጅ አብልጦ ሊወደው የሚችለው ነገር ሊኖር አይገባም ። እነርሱን በማስቀደም ሌላን ነገር መውደድ ይችላል ። ነገር ግን ከእነርሱ አስቀድሞ የሚወደው ነገር ሊኖር አይገባም ። ከሰው አብልጦ ገንዘብን መውደድ ገብጋባነት ነው ። ገብጋባነት ደግሞ እንስሳነት ነው ። ከሰው ይልቅ እንስሳን መውደድ ልበቢስነት ነው ። ልበቢስነት እንሰሳነት ነው ። እንሰሳነትም ልበቢስነት ነው ። ከሰው ይልቅ ሱስን መውደድ ልበ ደንዳናነት ነው ። ከልጆቹ ቁማር የበለጠበት አባት ልበ ደናዳና ነው ። ከሚስቱ ይልቅ አልኮል የሚናፍቀው ባል ልበ ደንዳና ነው ። ለባል ሳይሆን ለሀሜት ቅድሚያ የምትሰጥ ሚስት ልበ ደንዳና ናት ። ከሰው በላይ እውቀትን የሚወዱ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። ከእውቀት ክብርን ለማግኘት ብለው ፍቅረኛቸውን ችላ ያሉ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። እውነተኛ ፍቅር ለሁሉም ውይም ከሁሉ ነገር ይልቅ ሰውን ማስቀደም ነው ። እውቀትን ገንዘብን ቁስን ሱስን አብልጦ መውደድ ሰውን ያሳጣል ። ሰውን አብልጦ መውደድ ግን እውቀትንም ገንዘብንም አያሳጣም ። ሰውን ማጣት ሁሉን ማጣት ነው ። ሰውን ማግኘት ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ማለት ሰውን እንደራስ በመውደድ ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ካለ ሁሉም አለ ፣ ፍቅር ከሌለ ምንም የለም ። ይህ ከሁሉ የላቀው የፍቅር መርህ ነው ።
'' ፍቅር መነሻም መድረሻም ነው ። ምክንያቱም የመርሆች ሁሉ አለቃ ነው ። ''
No comments:
Post a Comment