ዋናው ኮንቴክስቱ ( አውዱ )
ሁለት መታወቂያ የተሰኘው ፊልም ላይ ፣ ዳዊት አባተ ወይም በገጸ ባህሪ ስሙ ቢኒያም እንዲህ ሲል ይደመጣል ‘’ በህይወት እውነት ወይም ውሸት ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ፣ ሞራላዊ ወይም ኢ ሞራላዊ የሚባል ነገር የለም ፣ ዋናው አውዱ ( ኮንቴክስቱ ) ነው ። ’’ አውድ ሲባል በዋናነት ሁኔታ ማለት ነው ። ሰው ህይወቱን በአውድ ወይም በሁኔታ የሚመራ ከሆነ ፣ እውነትን በእውነትነቱ ሳይሆን የሚመዝነው ፣ እውነት በሚያመጣው ውጤት ላይ ተመስርቶ ነው ፣ እውነትን የሚለካው ። ይህ ደግሞ የሰውን ልጅ ውጤት ተኮር እንጅ ሂደት ተኮር አያደርገውም ። ነጮቹ ሰው ከውጤቱ በላይ ሂደቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሲመክሩ ‘’ Trust the process! ‘’ ይላሉ ።
ከውጤቱ በላይ ለሂደቱ ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች በመርህ የሚመሩ ናቸው ። ከሂደቱ በላይ ለውጤቱ ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ መርህ አልባ ናቸው ። ያው የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ይመቻቸዋል ። አብዝተው ውጤት የሚፈልጉ ሰዎች ፣ መርዝን መድሃኒት ነው እስከማለት ይደርሳሉ ። በእውነት መንገድ ውጤት ከሚያጡ ፣ በውሸት ተጉዘው ውጤት ላይ መድረስ ምርጫቸው ነው ። ለእነርሱ እውነት ከሁኔታ በልጦ አያውቅም ። ሁኔታ ነው ከእውነት የሚበልጥባቸው ። ስለ እውነት ማጣት መራብ መጠማት መዋረድ ፣ ለእነርሱ የጀግና ሳይሆን የቀሽም ሰው ተግባር ነው ።
በእርግጥ አውዳዊ ፍቺ የሚያስፈልገው እውነት አለ ። ነገር ግን ሁሉም እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። ለምሳሌ የወል እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። የወል እውነት ቦታ ጊዜ ሁኔታ የማይቀያይሩት እውነት ነው ። ጸሀይ በምስራቅ ወጥታ በምራብ ትጠልቃለች ። ይህ የሰፈር እውነት ሳይሆን የዓለም እውነት ነው ። ውሀ ውሀ እንጅ ነዳጅ አይሆንም ። ነዳጅም እንደዚሁ ውሀ ሊሆን አይችልም ። ይህ እውነት የሆኑ ቡድኖች ያጸደቁት ሳይሆን ፣ ሁሉም ሰው አምኖ የተቀበለው እውነት ነው ። ውጤት ተኮር የሆኑ ሰዎች ግን ፣ ከቻሉ ውሀ እና ነዳጅን ቀላቅለው ፣ ነዳጅ ነው ብለው ይሸጣሉ ። ምክንያቱም ከሂደቱ በላይ የሚተማመኑት በውጤቱ ነው ። ለዚህ ደግሞ ማሳመኛ ይሆናቸው ዘንድ ፣ ውሸትን ብቻ ይዘው አይቀርቡም ። ውሸትን በእውነት ሸፍነው ያቀርባሉ ።
ውጤት ተኮር መሆን በራሱ ስህተት አይደለም ። ስህተት የሚሆነው ለውጤቱ ሲባል የማጭበርበር ስራ ሲሰራ ነው ። ውጤቱን ጥሩ ለማድረግ ሂደቱን መጥፎ ማድረግ ትክክል አይደለም ። ከሆነ ወይም ከተቻለ ውጤቱንም ጥሩ ሂደቱንም ትክክል ማድረግ ተገቢ ነው ። ካልሆነ ግን ውጤቱ ምንም ቢሆን ፣ ሂደቱን ትክክል ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ። አንድ አንድ ሁኔታዎች ፣ የሰው ልጆች እስከሆንን ድረስ ፣ ሂደቱን በማበላሸት ውጤቱን ማሳመር እንደሚቻል ይጠቁሙናል ። ያኔ የገጠመን እውነት የወል ሳይሆን አንጻራዊ ስለሆነ ፣ ውሳኔያችንን እንደሁኔታው ማድረግ ግድ ይላል ።
አንጻራዊ እውነት በአማራጭ የተሞላ ነው ። እንደ ሰው ፍጹም ስላልሆንን ፣በዚህ ጊዜ ውሳኔያችን ከሂደቱ በላይ በውጤቱ ላይ ቢመሰረት መልካም ነው ። ምርጫችንም የተሻለ ይሆናል ። በስህተት መንገድ ትክክል የሆነ ውጤት ማምጣት ባይቻልም ፣ በአንጻሩ ጥሩ ነገር ማድረግ ይቻላል ። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲገጥመን ፣ ውሸት ወይም እውነት ፣ ትክክል ወይም ስህተት ሚዛን አይሆኑም ። ሚዛን የሚሆኑት ማዳን ወይም መግደል ፣ ማጥፋት ወይም ማልማት ፣ ማበላሸት ወይም ማስተካከል ናቸው ። በእርግጥ የሀገሬ ሰው '' ካልደፈረሰ አይጠራም ። '' ይላል ። የደፈረሰ ሁሉ ይጠራል ማለት ግን አይደለም ። አንዳንድ ነገሮች ላይጠሩ ይደፈረሳሉ ። ላይቃኑ ይጣመማሉ ፣ ላይስተካከሉ ይበላሻሉ ፣ ላይመለሱ ይለወጣሉ ። ስለዚህ በህይወት ስንኖር ፣ ከውሳኔ በፊት ሁኔታን በጥልቀት መፈተሽ እና መመዘን ያስፈልጋል ። ምክንያቱም ማዳን የምንችለውን ልንገድል እንችላለን ። መስተካከል የሚችለው እንደተበላሸ ሊቀር ይችላል ። መቆም ያለበት ወድቆ እንክትክቱ ሊወጣ ይችላል ። ሰዎች ነን ፍጹም ልንሆን አንችልም ። ስለዚህ ሁኔታን በአንጻራዊ እውነት ከምንመዝን ፣ አንጻራዊ እውነትን በሁኔታ ( context) ብንመዝን የተሻለ ነው ።
እውነት ከእውነት ይለያያል ። ሁሉም እውነት እኩል መታየት የለበትም ። የሚጠቅም እውነት ከሚጎዳ እውነት ጋር እኩል መታየት አይኖርበትም ። የሚያጣላ እውነት ከሚያፋቅር እውነት ጋር ሊስተካከል አይገባውም ። ጥቁር ታሪክ የተሸከመ እውነት ፣ የጀግንነት ታሪክ ከተሸከመ ታሪክ ጋር እኩል ትኩረት ሊሰጠው አይገባም ። ምክንያቱም ጥቁር ታሪክ ጸጸትን በቀልን ቁጭትን ነው የሚወልደው ። የጀግንነት ታሪክ ግን ሞራልን አሸናፊነትን አንድነትን ነው የሚወልደው ። ስለዚህ ለሁሉም እውነት መታመን ታማኝ አያደርግም ። ትክክለኛ ታማኝነት ፍቅርን ፍትህን አንድነትን ለሚያሰፍን እውነት መታመን ነው ። ለሁሉም እውነት መታመን ጅልነት ነው ። ለምርጥ እውነት መታመን ግን ጀግንነት ነው ። በነገራችን ላይ ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ የሚሆኑ ሰዎች አሉ ፣ እነዚህ ሰዎች ክፉዎች ናቸው ። ምክንያቱም የእነርሱ እውነት ፍቅር የለውም ። ፍቅር የሌለው እውነት ደግሞ የሞተ ነው ። ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ ከመሆን ፣ ሰውን ለማዳን ውሸታም መሆን ይሻላል ። ነገርን ከሰው አንጻር እንጅ ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ልክ አይደለም ። የሚጎዳን እውነት ይዞ መኖር ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ነው ።
ዋናው አውዱ ( ኮንተክስቱ ) ማለት በምንም ጉዳይ ቢሆን ሰውን እናስቀድም ማለት ነው ። እውነትም አንጻራዊ እውነት ሰብአዊነትን ማስቀደም አለባቸው ። በእርግጥ የወል እውነት ፣ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰብአዊነትን ቢያስከብር እንጅ አያዋርድም ። አንጻራዊ እውነት ግን አስቸጋሪ ነው ። ፍትህን ለማዛባት ሰብአዊነትን ለመጣስ ሊውል ይችላል ። ስለዚህ አንጻራዊ እውነት ሲገጥመን መጠንቀቅ አለብን ።
'' ከሁኔታ የሚበልጠው እውነት የሰውን ልጅ ክብር የሚጨምር ነው ። በሁኔታ የሚገደብ እውነት ግን የሰውን ክብር ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል ። ''
No comments:
Post a Comment