ራስን መመርመር
ራስን መመርመር ራስን መመልከት ነው ። አንድ የላቦራቶሪ ቴክኒሺያን በሰው ደም ውስጥ ፣ በሽታ አምጪ ህዋስ መኖሩን ለማረጋገጥ ፣ ማይክሮስኮፕን ይጠቀማል ። በተመሳሳይ የሰው ልጅ የስብእና በሽታ ሲገጥመው ፣ ራሱን ለመመርመር የስብእና ግድፈቱን የሚለይበት ማይክሮስኮፕ ያስፈልገዋል ። በሽታውን ለማወቅ ማይክሮስኮፑን በአግባቡ መጠቀም ግድ ይላል ። የሰው ልጅ የራሱን የስብእና በሽታ የሚያይበት ማይክሮስኮፕ አንዱ ጥሞና ነው ። ጥሞና የባህሪ በሽታን የመለየት ከፍተኛ አቅም አለው ። ጥሞና ሰውን ከፍተኛ መረጋጋት ውስጥ ይከታል ። ሰውን እንደ ፍሪጅ አቀዝቅዞ ፣ ባህሪን ከሚበክል ስሜት እና ሀሳብ ነጻ ያደርጋል ። ሰው በሽታውን አውቆ መድሀኒቱን እንዲፈልግ ፣ ጥሞና ብርሃን ይሆነዋል ። ጥሞና ዝምታ ነው ። ፈርቶ ዝም ማለት ሳይሆን አቅዶ ዝም ማለት ነው ።
ፈርቶ ዝም ማለት ሁለት ገጽ አለው ። አንድም ለኪሳራ በሌላ በኩል ደግሞ ለትርፍ ሊዳርግ ይችላል ። የፍርሀት ዝምታ ከስሜታዊ ሰው ጥቃት ይጠብቀናል ። በስሜታዊ ሰው ፊት በፍርሀትም ይሁን በእውቀት ዝም ማለት ራስን ከአደጋ መከላከል ነው ። የፍርሀት ዝምታ ከዚህ አንጻር ሲታይ ጠቃሚ ነው ። ግን በሌላ ገጹ ሲታይ የፍርሀት ዝምታ ብዙ ነገር ያሳጣል ። ዝምታ ወርቅ ነው የሚባለውን ያህል ውድቅ የሚሆንበት ቦታም አለ ። መናገር ሲኖርብን ዝም ማለት ያሳጣል ። በእርግጥ ዝም ማለት ሲገባ መናገርም ያስቀጣል ። ሁለቱም እኩል ጉዳት አላቸው ። ከሁለቱም ጉዳት ነጻ የሚያወጣን ማስተዋል ነው ። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ጥሞና ነው ።
ጥሞና የነገርን ክብደት እና ቅለት ለመለየት ወሳኝ ነው ። ጥሞና የማስተዋል አቅምን ሲጨምር ፣ የፍርሀት ዝምታ ግን ማስተዋልን ይቀንሳል ። በጥሞና ውስጥ ነገርን በልኩ ማወቅ እና መረዳት ይቻላል ። ጤናማውን ከበሽተኛው ለመለየት ቀላል ይሆናል ። ይህ ደግሞ ራስን ለማስተካከል እድል ይሰጣል ። ጥሞና ራስን መመርመሪያ ምርጥ ማይክሮስኮፕ ነው ።
ሌላኛው ራስን መመርመሪያ ማይክሮስኮፕ ተግባቦት ነው ። ከሰው ጋር መነጋገር ራስን ማያ መስተዋት ነው ። ሰው ፊቱ ላይ ያለውን ጉድፍ ለማጽዳት መስተዋት ይጠቀማል ። የባህሪ ግድፈቱን ለማጽዳት ደግሞ አጠገቡ ያለውን የቅርቤ የሚለውን ሰው ፣ እንደመስተዋት መጠቀም አለበት ። ሰው በምልአት ራሱን ማየት አይችልም ። ለእርሱ የተሰወረው አጠገቡ ላለ ሰው ግልጽ ሊሆን ይችላል ። በተለይ በሳል ሰው ካለ ፣ የማይታየውን ማየት የሚችል አቅም ስላለው ፣ ራስን ለመመርመር እና ለማስተካከል ጥሩ አቅም ይሆነናል ። ሰው ለብቻው ራሱን በመመርመር ውጤታማ አይሆንም ። የሚያግዘው እና የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል ።
ሰው ራሱን ሲመረምር ሀቀኛ መሆን አለበት ። ስህተቱን ስህተት ፣ ልኩን ትክክል ነው ማለት አለበት ። ስህተቱን ልክ ልኩን ስህተት ካደረገ ግን ፣ ራሱን እየመረመረ ሳይሆን ራሱን እያባበለ ነው ። ራስን በማባበል ደግሞ አሉታዊ እንጅ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ። እየባሱ መሄድ እንጅ መሻሻል አይኖርም ። ሰው ወደ ላይ የሚያድገው እውነትን መቀበል ሲችል ነው ። ወደ ታች የሚወርደው እውነትን መቀበል ሲያቅተው ነው ። ለስህተት ምክንያት እየሰጡ ራስን ከእውነት ማሸሽ ፣ መጨረሻው እድገት ሳይሆን ውርደት ነው ።
ስለዚህ ራስን መርምሮ ለማሻሻል ፣ እውነትን መቀበል ቁልፍ ብቻ አይደለም ፣ የቁልፎች ሁሉ ቁልፍ ( Master key ) ነው ።
ትክክለኛ ራሱን መርማሪ ፣ ተንኮል በመስራቱ ራሱን ደግ አደረክ ብሎ አያሞግስም ። ባይሆን በመጸጸት ራሱን ለማስተካከል ይጥራል ። ባደረገው መልካም ነገር ይደሰታል ራሱንም ይሸልማል ። በሰራው ስህተት ደግሞ ራሱን ይወቅሳል ። በልኩ ያዝናል በልኩ ደግሞ ይደሰታል ። ደስታው የበለጠ ተግቶ እንዲሰራ ሀይል ይሆነዋል ። ሀዘኑ ደግሞ ስህተቱን ይቀንስለታል ። በስህተት ማዘን በመልካም ስራ መደሰት ሰውነት ነው ። በተንኮል መደሰት በመልካም ስራ መከፋት አውሬነት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ማታ ላይ ተኝተው ፣ የቀን ስራቸውን የሚያሰላስሉት ፣ በሰሩት ተንኮል ለመሳቅ እና ባደረጉት መልካም ነገር ለማዘን ነው ። ከዚያም በተጨማሪ የተሻለ ተንኮል ለማሰብ እና ለማቀድ ነው ።
ተንኮል ለማቀድ ራሱን ከሚመረምር ሰው ፣ ራሱን የማይመረምር ብኩን ይሻላል ። ምክንያቱም ስህተትን ሆን ብሎ ሳይሆን ፣ ባለማወቅ ነው የሚሰራው ። አስቦ ራሱን መመርመር ባይችልም ፣ በሂደት በህይወት ልምድ ስህተቱን መቀነሱ አይቀርም ። ይህች ምድር ትልቅ ጥፋትን የምታስተናግደው ፣ ሳያውቁ ስህተት በሚሰሩት ሳይሆን አውቀው ሆን ብለው ስህተት በሚሰሩት ነው ። ክፉ ለማድረግ ራስን መመርመር ፣ ራስን መመርመር ሳይሆን ራስን መራር ማድረግ ነው ። ( Weak acid ) ደካማ አሲድን ጠንካራ አሲድ ( Strong acid ) ማድረግ ነው ። ይህ ደግሞ ከጎጂነት ወደ አጥፊነት መቀየር ነው ። ሰው ራሱን የሚመረምረው አጥፊ ከሆነ አልሚ ለመሆን ነው ። ተንኮለኞች ግን ራሳቸውን የሚመረምሩት የበለጠ አጥፊ ለመሆን ነው ።
ራሳችንን መመርመር ለክፋት ሳይሆን መልካም ለማድረግ መሆን አለበት ። ስህተትን ለመቀነስ እንጅ ስህተትን ወደ ተንኮል ለመቀየር መሆን የለበትም ። ራስን ለማረም እንጅ አረም ለማድረግ ራስን መፈተሽ አያስፈልግም ። ስራን ለማስተካከል እንጅ ለማበላሸት ራስን መመርመር አስፈላጊ አይደለም ። በዚህች ምድር ስንኖር ራስን መመርመር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን ራሳችንን መመርመር ያለብን ምድርን ለማልማት እንጅ ለማጥፋት አይሁን ።
‘’ ራስን ለማስተካከል ራስን መመርመር ነው ቁልፉ ። ‘’
No comments:
Post a Comment