ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት
በብዛት
ሰዎች መከራ ሲበዛባቸው ፣ ችግር ሲደራረብባቸው ፣ ለፍተው ደክመው ጠብ የሚል ነገር ሲያጡ አሁንስ ትእግስቴ አለቀ ይላሉ ። በርግጥ
እውነት ነው ፣ የሰው ልጅ ትእግስቱ ውስን ነው እናም ማለቁ አይቀርም ። ያልቃል ማለት ግን አይታደስም ማለት አይደለም ፣ ህይወት
አበቃላት ማለትም አይደለም ። የሰው ልጅ ትእግስቱ ቢያልቅ ይታደሳል ። ዳግም በትእግስት ሃይል ይሞላል ። ትእግስት የማያልቅበት
ፈጣሪ ፣ እንደገና በአዲስ ትእግስት ይሰራዋል ።
ዋናው ነገር የትእግስት ማለቅ ወይም አለማለቅ አይደለም ። ትእግስት
በጊዜው ሲያልቅ እና ያለ ጊዜው ሲያልቅ ይለያያል ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ጉዳቱ የከፋ ነው ። የሚታደስ ሳይሆን ፣ ባለበት
የሚቆም ወይም ጭልጥ ብሎ የሚጠፋ ነው ። ለዚህም ነው ትእግስት የሌላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲጎዱ የሚታዩት ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ
ትእግስት ፣ ሰውን ትእግስተኛ ሳይሆን እልከኛ ነው የሚያደርገው ። ስለዚህ ለጥፋት እንጅ ለልማት አይሆንም ። ለውድቀት እንጅ ለስኬት
አይዳርግም ። ለሃዘን እንጅ ለደስታ አይሆንም ። ወደ በቀል እንጅ ወደ ይቅርታ ልብን አይመራም ።
ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት ጥሩ ምልክት ሳይሆን የአደጋ ምልክት ነው ። አምቡላንስ
ከሳይረን ድምጹ እና ከቀይ መብራቱ ጋር እንደማለት ነው ። ከጊዜው ያጠረ ትእግስት ማስጀመር እንጅ ማስጨረስ አይችልም ። ለማሳቀድ
እንጅ ለማስፈጸም በቂ አቅም የለዉም ። ተስፋ ልማስቆረጥ እንጅ ሪቫን ለማስቆረጥ እድል አይሰጥም ።
ትእግስት ያለጊዜው ሲያልቅ ነገን ብሩህ አድርጎ ሳይሆን አጨልሞ ነው የሚያሳየው
። እምነትን ገድሎ ጥርጣሬን በልባችን ላይ ይዘራል ። አስተሳሰባችንን አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ ያደርገዋል ። ይሳካል ይሆናል ከማለት
ይልቅ ፣ አይሳካም አይሆንም ማለት ቃላችን እና ልማዳችን ይሆናል ። የልቦናን አይን ሞራ ገፎ ከመጣል ይልቅ ፣ የስራ ሞራልን ገፎ
ይጥላል ። የሰው ልጅን በእቅድ እንዳይኖር ፣ በዘፈቀደ እንዲኖር ያስገድደዋል ። ማቀድን ሞኝነት ተስፋ ማድረግን ጅልነት አድርጎ
ያሳያል ። መኖርን ከንቱ ፣ መሞትን ምርጥ መፍትሔ ያደርጋል ። ስለዚህ የትእግስት ማለቅ ሳይሆን ዋናው ቁም ነገር ፣ ያለ ጊዜው
ትእግስት እንዳያልቅ መጠንቀቅ ነው የሚያስፈልገው ።
ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ፣ በጊዜው ከሚያልቅ ትእግስት የሚለይባቸው
ነገሮች ብዙ ናችው ። ለምሳሌ ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ ድክም ያደርጋል ።
ያለ ጊዜው ሲያልቅ ቱግ ያደርጋል ። በጊዜው ሲሆን ይታደሳል ፣ የወደፊት ጉዞን
እንድንቀጥል ያደርገናል ። ያለ ጊዜው ሲሆን በፍጹም አይታደስም ፣ የወደፊት ጉዞን እንድንቀጥል ሳይሆን እንድናቆም ያስገድደናል
። ከመሄድ መመለስ አምራጭ የሌለው ምርጫ ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ መጨረሻው አቅም ማጣት ነው ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ
ግን መጨረሻው ተስፋ ማጣት ነው ። አቅም ስናጣ ፈጣሪ አቅም ይሆነናል ። ተስፋ ስናጣ ግን ፈጣሪ አቅም አይሆነንም ። ምክንያቱም
ተስፋ ስናጣ ፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ነውና የምናጣው ። መንፈሰ ጠንካራ ሰዎች አቅም ሊያጡ ይችላሉ ። በፍጹም ግን በፈጣሪ
ላይ ያላቸውን እምነት እና ተስፋ አያጡም ። መንፈሰ ጠንካራ ያልሆኑ ሰዎች ግን ፣ አቅም አጥተው ሳይሆን አቅም እያላቸው በፈጣሪ
ተስፋ ይቆርጣሉ ፣ እምነታቸውን ያጣሉ ። አዲስ አቅም አያገኙም ፣ ባይሆን የነበራቸውን አቅም ያጣሉ ። ስለዚህ ትእግስት በጊዜው
ሲያልቅ መንፈሰ ጠንካራ ያደርጋል ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ ግን መንፈሰ ደካማ ያደርጋል ።
ያለ ጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ውጤቱ ስሜታዊነት ነው ። ሳያስቡ
ሳያሰላስሉ ሳያመዛዝኑ ፣ ዘሎ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ግን መጨረሻው ምክንያታዊነት ነው ።
ከመወሰን በፊት ማሰብን ማስቀደም መርህ ይሆናል ። ማሰብን መወሰን ሲቀድም ስሜታዊነት ነው ።
ውሳኔን ሀሳብ ሲቀድም ምክንያታዊነት ነው ። ውሳኔ ሲፈጥንም ሲዘገይም ችግር
ይፈጠራል ። ሲፈጥን የስሜት ውጤት ስለሆነ ራሳችንን ያሳጣናል ። ሲዘገይ ደግሞ ፍጹምነትን ( perfectionism ) መፈለግ
ስለሆነ የምንፈልገውን ያሳጣናል ። ራሳችንንም ሆነ የምንፈልገውን እንዳናጣ ፣ ትእግስታችን ያለ ጊዜው ሳይሆን በጊዜው እንዲያልቅ
ጥንቃቄ እናድርግ ። ችግር በገጠመን ቁጥር ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። ያኔ ለውሳኔ ያልፈጠነ ግን ደግሞ ያልዘገየ
ምርጥ ሰው እንሆናለን ።
ትእግስት ያለ ጊዜው ሲያልቅ መማሪያ ያደርጋል ። በጊዜው
ሲያልቅ ግን አርአያ ያደርጋል ። ሰው መማሪያ ሲሆን ፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንደሌለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን ግን
፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንዳለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን የስኬት ተምሳሌት ይሆናል ። መማሪያ ሲሆን ደግሞ የውድቀት
ምሳሌ ይሆናል ። ድክም እስኪለን ከታገስን ብንወድቅም እንንሳለን ። ቱግ ካልን ግን ላንነሳ እንወድቃለን ። እስከ መጨረሻው የታገሰ
ጥሩ ታሪክ ትቶ ያልፋል ። እስከ መጨረሻው ያልታገሰ ግን መጥፎ ታሪክ ጥሎ ያልፋል ። ትእግስት መጨረሻ አለው ። ለዚህም ነው ታላቁ
መጽሐፍ ‘’ እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል የሚለው ’’ ። ቱግ ማለት
የትእግስት መጨረሻው ሳይሆን ያለማለቁ ምልክት ነው ። ድካም ግን የትእግስት መጨረሻ ማሳያ ነው ። ስንናደድ ልንጠፋ ነው ። ስንደክም
ግን ልንድን ነው ።
መዳን ማለት መትረፍ መትረፍረፍ ፣ የጥሩ ነገር ምሳሌ ፣ የስኬት ተምሳሌት
መሆን ነው ። መጥፋት ማለት ደግሞ የመጥፎ ነገር ፣ የውድቀት ምሳሌ መሆን ነው ። ስለዚህ ሀደራ ትእግስታችን ያለ ጊዜው እንዳያልቅብን
፣ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። መጨረሻችን መዳን እንጅ መጥፋት አይሆንም ።
‘’ ትእግስት የህይወት ቁልፍ መርህ ነው ። ’’
No comments:
Post a Comment