Sunday, April 27, 2025

እይታ | Perception

 

                       የጋራ ዓላማ

       የጋራ ዓላማ ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን አንድ ግለሰብ ፣ የራሱ አላማ ከሌለው ፣ የጋራ አላማ ሊኖረው አይችልም ። አላማ የሌለው ሰው ፣ የአላማ ህልውና አይገባውም ። የሰው ልጅ ለአላማ እንደተፈጠረ መረዳት አይችልም ። የሰው ልጅ ለመብላት ብቻ ሳይሆን ፣ ለማብላት ጭምር እንደተፈጠረ አይታየውም ። በመልበስ ብቻ ሳይሆን ፣ በማልበስ መደሰት እንደሚችል አይሰማውም ። ያለ ዓላማ የሚኖር ሰው ፣ የማግኘት እንጅ የመገኘት ትርጉም አይገባውም ። የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን ፣ የሚለብሰውን ካገኘ በቃው ። መብላት መጠጣት መልበስ ፈልገው ፣ ለሚጣሩ ድምጾች መገኘት መቻል ለእርሱ ዋጋ ቢስ ነው ። የእርሱ መኖር ለሌሎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አያውቅም ። በሌሎች መኖር ውስጥ ፣ የእርሱ እስትንፋስ እንዳለች አይረዳም ። ህይወትን በአጋጣሚ እንጅ በእቅድ መኖር አይችልም ። በእርግጥ ሰው በእቅዱ ልክ መኖር አይችልም ። ያለእቅድ መኖር ግን ትልቅ ስንፍና ነው ። ሰው በአጋጣሚ ኖሮ ፣ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል እጅግ ያሳዝናል ። በእቅድ ኖሮ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል ፣ የተፈጥሮ ሂደት ነው አምኖ ለመቀበል ብዙ አይከብድም ። ምክንያቱም አቅዶ የሚሞት ማንም የለም ። ምናልባት በኑሮ ጫና ወይም በተለያየ ምክንያት ፣ ሰው ራሱን ለማጥፋት ካላሰበ በቀር ። ያም ቢሆን ታስቦ ታቅዶ ሳይሆን ፣ በስሜት የሚከወን ድርጊት ነው ። ሰው አስቦ ራሱን ያድናል እንጅ ራሱን አይገድልም ። ማሰብ ማለት የሚጠቅመውን የተሻለውን መምረጥ ነው ። አለማሰብ ደግሞ የሚጎዳውን የባሰውን መወሰን ወይም መምረጥ ነው ።

        ያለ ዓላማ መኖር ያለ ማሰብ ውጤት ነው ። ሰውን ሰው የሚያደርገው ማሰብ መቻሉ ነው ። በደመ ነፍስ ከመኖር የሚታደገው ማሰቡ ነው ። የማይታየውን ማየት ፣ የማይሰማውን መስማት ፣ ከቁሱ አለም ጀርባ መንፈሳዊ አለም እንዳለ ማመን እና ማረጋገጥ የቻለው በማሰቡ ነው ። እንስሳት ለመኖር ምቹ ተፈጥሮ ይፈልጋሉ ። ምክንያቱም ተፈጥሮን ምቹ የማድረግ ብቃት የላቸውም ። እነርሱ ጫካው ምድረ በዳ ሲሆን ጥለው ይሸሻሉ ። አልያ ሁሉም አንድ በአንድ ፣ የሞት ሲሳይ ይሆናሉ ። ይህ የሚሆነው ማሰብ ስለማይችሉ ነው ። ሰው ግን እንደዛ አይደለም ፣ ማሰብ ስለሚችል ተፈጥሮ ምቹ ባትሆንም ፣ ምቹ ተፈጥሮን መፍጠር ይችላል ። ምድረበዳን ዉብ መኖርያ ማድረግ ይችላል ። ግን ይህን የማድረግ ብቃት ያለው ፣ ዓላማ ያለው ሰው ነው ። ዓላማ የሌለውማ ማሰብ ስለማይችል ፣ እንደ እንስሶቹ ምቹ ተፈጥሮን ይፈልጋል ። አልያ ሞት አፈፍ አድርጎ ይቀበለዋል ። የተሻለ ለማሰብ ዓላማ ያስፈልጋል ። ሰው ዓላማ ከሌለው ደመነፍሳዊ ይሆናል ። በደመነፍስ ያለ ሰው ፣ በስሜት እንጅ በማስተዋል መኖር አይችልም ። በስሜት ደግሞ የተሻለ ማሰብ በፍጹም አይቻልም ።

           አላማ አቅጣጫ ነው ። የህይወት መነሻም መድረሻም ነው ። አላማ የሌለው ሰው አቅጣጫ ቢስ ነው ። መነሻም መድረሻም የለውም ። እድሜው እንዲሁ ይሄዳል ፣ እርሱ ግን መሄጃ የለውም ። ቀን ይመሻል ይነጋል ፣ ለእርሱ ግን መሸም ነጋ ለውጥ የለውም ። ምክንያቱም መለወጥ አይፈልግም ። ለውጥ ጠላቱ ነው ። ከማላውቀው መልአክ ፣ የማውቀውን ሰይጣን የሙጥኝ ብል ይሻላል ብሎ የሚኖር ነው ።

ሰይጣን ስላወቅነው ደግ አይሆንም ። ባናውቀውም ከክፋቱ ፈቀቅ አይልም ። ክፉ ሰውም እንደዛ ነው ። ስለቀረብነው የዋህ አይሆንም ። ስለራቅነውም ተንኮሉን መስራት አያቆምም ። የለመድነው ክፉ ነገር ፣ እኛ ስለወደድነው መልካም አይሆንም ። ከጠላነው ግን ነገሩ ባይለወጥም ፣ እኛ እንለወጣለን ። ክፉን ነገር መውደዳችን የነገሩ እስረኛ ያደርገናል ። መጥላታችን ግን ነጻ ያወጣናል ። ነጻ ለመውጣት ግን ዋጋ ያስከፍላል ። ያለ ዋጋ የሚገኝ ነጻነት የለምና ። አላማ የሌለው ሰው ክፉን ወይም መጥፎን ነገር ለመተው በጣም ይከብደዋል ። በተመሳሳይ ጥሩውን ነገር ለመቀበል እጅግ ይጨንቀዋል ። የጋራ አላማ ለውጥ ይፈልጋል ። መለወጥ የማይችል ሰው ለጋራ አላማ እንቅፋት ነው ። አላማ የሌለው ሰው ፣ ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ ስላልሆነ ፣ ለጋራ አላማ መሰናክል ነው ።

      ዓላማ ያለው ሰው ግን ቢያውቅም ባያውቅም መልአክን አይጠላም ።

መልካም ነገርን አይተውም ። መልአክ መልአክ ነው ፣ እኛ ስለፈራነው መልካምነቱ አይቀየርም ብሎ ያምናል ። ከዘመድ ሰይጣን ፣ ባዳ መልአክ ይሻላል የሚል እይታ አለው ። ሁሌም አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አለው ። ለመለወጥ ዝግጁ ነው ። በጋራ መስራት በአንድነት ወደፊት መሄድ ደስታው ነው ። ነገር ግን የጋራ መልካም አላማ እንጅ ፣ ክፉ አላማ ካላቸው ጋር በፍጹም አይተባበርም ። አብረን እንስራ ከሚሉት ጋር እንጅ ፣ አብረን እናጭበርብር ከሚሉት ጋር ህብረት የለውም ። ሰርተን እንገባ እንጅ ፣ ሰርቀን እንገባ አይመቸውም ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል ሳይሆን ፣ እኔ ኖሬ ሰርዶ ላብቅል የሚል ነው ። ለዛሬ ሲል ነገን አያፈርስም ። ለነገ ዛሬ ይኖራል ።

የእርሱ ማጣት ሳይሆን ፣ የልጆቹ ማግኘት ይታየዋል ። የልጆቹ መጥገብ በምናብ ስለሚታየው ፣ የእርሱ መራብ ብዙ አይስጨንቀውም ። አላማ ያለው ሰው ፣ በዛሬ ዉስጥ ነገ ስለሚታየው ለጋራ አላማ ምቹ ፍጥረት ነው ።

     ምቾትን የሚፈልጉ ሰዎች ፣ ዓላማ ቢኖራቸውም ለጋራ ዓላማ ብዙ አይመቹም ። ትራፊ ለመስጠት ፣ ትርፍ መኪናቸውን ማጣት ይፈራሉ ። ልብሳቸውን ከመስጠት ይልቅ ፣ ቁም ሳጥናቸውን የልብስ ሙዚየም ማድረግ ይመርጣሉ ። ሀኪም ካላዘዛቸው ፣ ባዶ እግር መሄድ ይፈራሉ ። በባዶ እግር የሚሄዱትንም ይፈራሉ ። መኖር እንጅ ማኖር አይችሉም ። መስራት እንጅ ማሰራት አይሆንላቸውም ። መቀመጥ እንጅ ማስቀመጥ ህመማቸው ነው ። ሲደመጡ ደስ ይላቸዋል ። ሲያዳምጡ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል ። ሲከበሩ ጮቤ ይረግጣሉ ። ሲናቁ መብት ይረግጣሉ ። ለመከበር የተፈጠሩ እንጅ ፣ ለማክበር የተፈጠሩ አይመስላቸውም ። ለጥቅማቸው ይሽቆጠቆጣሉ ። ለክብራቸው ግን ያንቀጠቅጣሉ ። ምርጥ እና ቆንጆው የእነርሱ ፣ መጥፎ እና ቆሻሻው የሌላ ይመስላቸዋል ። አላማቸው ፍቅርን ማብዛት ሳይሆን ፣ ገንዘብን ቁስን ጌጥን ማብዛት ነው ። ራሳቸውን ጭምር ማብዛት አይፈልጉም ። ያወቁትን በማሳወቅ ፣ የቻሉትን በማሳየት ፣ እነርሱን የሚመስሉ ሌሎች እንዲፈጠሩ ምንም ጥረት አያደርጉም ። በአጭሩ ለምቾት የሚኖሩ ፣ ለጋራ አላማ አይመቹም ።

      የጋራ አላማ የተስተካከለ የግለሰብ አላማን ይፈልጋል ። በፓፒዮ መጽሐፍ ላይ ፣ እንደ ተተረከው ታሪክ አላማን ማስተካከል ያስፈልጋል ። ፓፒዮ ከእስር ቤት እንደ ወጣ ፣ ዓላማው ገንዘብ ማግኘት ነበር ።

ይህ ዓላማው ግን ህገ ወጥ እንዳደረገው ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ዉስጥ መረዳት ቻለ ። በመቀጠል አላማውን አስተካከለ ። በጀመሪያ ገነዘብ ሳይሆን ስራ ማግኘት እንዳለበት ራሱን አሳመነ ። ከስራ ገንዘብን ካስቀደምን ፣ ሥርዓት አልበኛ ወይም ህገወጥ የመሆን እድላችን ሰፊ ነው ። ከገንዘብ ስራን ካስቀደምን ግን ፣ ስርዓትም ይኖረናል ፣ ህጋዊም እንሆናለን ። ልክ ፓፒዮ እንዳደረገው ፣ ገንዘብን ከስራ ካስቀደምን ፣ ሀሳባችን መስራት ሳይሆን መስረቅ ይሆናል ። ስራን ከገንዘብ ካስቀደምን ግን ፣ ሀሳባችን መስራት እንጅ መስረቅ አይሆንም ።

               

            ‘’ የተስተካከለ አላማ ያለው የጋራ አላማን መፍጠር ይችላል ። ‘’ 

                               ክፍል 1                             

No comments:

Post a Comment

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...