Monday, April 21, 2025

እይታ | Perception

                                                        የትውልድ ቅብብሎሽ

               ለውጥ ስር ነቀል ሲሆን የትውልድ ቅብብሎሽ አይኖርም ። ለውጥ ስር ነቀል ነው  ብሎ ማመን ፣ ትላንት ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ፣ ጥሩ ነገር የለውም ማለት ነው ። ህይወት ጥቁር ወይም ነጭ እንጅ ግራጫ መልክ የላትም እንደ ማለት ነው ። የህይወት እውነታ ግን ይህን አያሳይም ። ትላንት ፍጹም ጥሩ ወይም ፍጹም መጥፎ ሊሆን አይችልም ። ሙሉ በሙሉ ትክክል ወይም ስህተት ሊሆን አይችልም ። የትላንት ታሪክ የሰዎች ታሪክ ነው ። የትላንት ስራ የሰዎች ስራ ነው ። ሰዎች ደግሞ ትክክልም ስህተትም ይሰራሉ ። ጥሩም መጥፎም ያደርጋሉ ። በስር ነቀል ለውጥ ማመን ፣ ይህንን መሰረታዊ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መካድ ወይም አለመቀበል ነው ። 

             የሰው ልጅ በብዛት መጥፎ ከሰራ ፣ በቀጣዩ ትውልድ በመጥፎ ታሪኩ ይወሳል ። ያ ማለት ግን ምንም ጥሩ ስራ የለውም ማለት አይደለም ። ከመጥፎ ስራው ብዛት አንጻር ፣ ጥሩ ስራው በቀላሉ የመታወስ እድል  ስለማይኖረው ነው ። በሌላ በኩል በብዛት ጥሩ ከሰራ ፣ ጥሩ ታሪኩ ለትውልዱ ይነገርለታል ። ይህ ማለት ግን መጥፎ ስራ የለውም ፣ መልአክ ነው ማለት አይደለም ። ከጥሩ ስራው አንጻር ፣ መጥፎ ታሪኩ ወደ ፊት ከመቀጠል ይልቅ በቀላሉ ስለሚቃጠል ነው ። ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ ስለሚረሳ ነው ። የስራ የመታወስ አቅሙ ብዛቱ ነው ። ብዙ ጥሩ ከሰራን ፣ በብዙ ሰዎች እና በትውልድ ልብ ውስጥ በመልካምነት እንታወሳለን ። ትንሽ ከሰራን ግን ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ እንረሳለን ። በተመሳሳይ ብዙ መጥፎ ከሰራን ፣ በክፋት ስማችን በትውልዱ ይነሳል ። ትንሽ ከሰራን ግን ፣ አይደለም ለትውልድ ሊሻገር ፣ ከቤት የማይሻገር ታሪክ ሆኖ ይቀራል ። 

            ጥሩ ከመጥፎ ሲበዛ መልካም ያስብላል ። መጥፎ ከጥሩ ሲበዛ ክፉ ያስብላል ። ልክነት ከስህተት ሲበዛ ጎበዝ ያሰኛል ። ስህተት ከልክነት ሲበዛ ሰነፍ ያሰኛል ። መልካም ፣ ጎበዝ እና ክፉ ሰዎች ታሪክ ይኖራቸዋል ። ሰነፎች ግን ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። ሰው ጎበዝ ሆኖ ክፉ ከሆነ ፣ ትውልድ ከክፋቱ ሳይሆን ከጉብዝናው ይማራል ። ጎበዝም መልካምም ከሆነ ፣ ከጉብዝናውም ከመልካምነቱም ይማራል ። ሰነፍ ከሆነ ግን ምንም ስለሌለው ፣ ትውልድ ከእርሱ ምንም አይማርም ። ሰነፍ ሰው እና ዳተኛ ትውልድ ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። አይደለም የታሪክ አሻራ ፣ የጣት አሻራ ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም ። ክፉ እውቀት ከመሀይምነት ይከፋል ( Bad knowledge is more danger than ignorance ) ቢባልም ፣ ምንም አለማወቅ ክፉ ባያደርግም ፣ የክፋት ተባባሪ ያደርጋል ። ምንም አለማወቅ የዋህ ሳይሆን ጅል ነው የሚያደርገው ። የዋህነት ከክፋት ነጻ መሆን ነው ። ጅልነት ግን ከእውቀት ነጻ መሆን ነው ። ከክፉም ከመልካም እውቀት ባዶ መሆን ነው ። ከክፉ እውቀት ይልቅ ፣ ከእውቀት ነጻ መሆን ቢሻልም ግን ጥሩ አይደለም ። ጥሩውም ልኩም ፣ መልካሙን መያዝ ክፉውን መጣል ነው ። ሁሉን መያዝ ፣ ሁሉን መጣል አይቻልም ። መርጦ መያዝ ፣ መርጦ መተው ግን ይቻላል ። ስለዚህ ምርጫችንን እናስተካክል ። ምክንያቱም ምርጫችን ነው ሰውም አውሬ የሚያደርገን ። መልአክም ሰይጣንም የሚያደርገን ። ስንፍና ግን በምንም ሚዛን አያዋጣም ። 

         መልአክ እና የሰው መልአክ ይለያያሉ ። መልአክ ፍጹም ነው ። የሰው መልአክ ግን ፍጹም አይደለም ። በተመሳሳይ አውሬ እና የሰው አውሬ ይለያያሉ ። አውሬ ርህራሄ የለውም ፣ ፍጹም ጨካኝ ነው ። የሰው አውሬ ግን ፍጹም ጨካኝ አይደለም ። በትንሹም ቢሆን ልቡ መራራቱ አይቀርም ። ሰው ከሰው መልአክ ብዙ መማር አለበት ። ከሰው አውሬ ግን ትንሽ ነው መማር ያለበት ። ትንሽም ተማረ ብዙም ተማረ ፣ ዋናው ነገር መማር መቻሉ ነው ። ለውጥ ደግሞ የመማር ውጤት ነው ። ለመማር ነገርን ከስሩ መንቀል ሳይሆን የሚያዋጣው ፣ ነገርን ከስሩ መመልከት ነው የሚያስፈልገው ። ትላንትን ከስሩ መንቀል ሳይሆን ፣ ችግርን ከስሩ መንቀል ነው መፍትሔው ። '' አረምን መንቀል ስር ሳይሰድ ነው ። '' እንዲሉ አበው ፣ ለለውጥ አረምን እንጅ አለምን መንቀል አያዋጣም ። ስር ነቀል ለውጥ ግን አረምን ሳይሆን አለምን መንቀል ነው ። ስለዚህ ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂ ነው ። ስር ነቀል ለውጥ የዋህነት የጎደለው ልባምነት ፣ ይቅር ባይነት የሌለው ትጋት ነው ። ከሰው መልአክም ከሰው አውሬም መማር አለመቻል ነው ። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ሊኖር የሚችለውን የወደፊት ጉዞ ይገታል ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ትውልድ ያፈርሳል እንጅ አይገነባም ። ታሪክ ያቃጥላል እንጅ አያስቀጥልም ። ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰው ታሪክ ሀብት ነው ። ዝግጁ ላልሆነ ግን ታሪክ ሸክም ነው ። ሉሲ ፣ አክሱም ፣ ፋሲለደስ ፣ ጀጎል እና ላሊበላ ላወቀበት ሀብት ናቸው ። ላላስተዋለ ግን ዘበት ናቸው ። ትክክለኛ ለውጥ ሁሉን ጥሎ ማለፍ ሳይሆን ፣ መጥፎውን ጥሎ ጥሩውን ይዞ መሻገር ነው ። ጥሎም አንጠልጥሎም ማለፍ ነው ። ያኔ እንደ አዲስ የሚገነባ ታሪክ ሳይሆን ፣ በሂደት የሚገነባ ታሪክ ይኖረናል ። መሳሪያ የሚቀባበል ትውልድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እና ስራ የሚቀባበል ትውልድ ይታነጻል ። ሆ ብሎ የሚያቃጥል ሳይሆን ፣ ሀ ብሎ የሚያስቀጥል ትውልድ ይነሳል ። በስሜት የሚያፈርስ ሳይሆን በስሌት የሚገነባ ትውልድ ይፈጠራል ። ስር ነቀል ለውጥ ፣ ለውጥን ከመፍጠር በላይ ነውጥን የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው ። ምክንያቱም በዚህ የለውጥ ሂደት ፣ መነካት የሌለበት የህዝብ ልብ የሚነካ ነገር ሊወድም ይችላል ። መጥፋት የሌለበት ሀገራዊ  ማንነት በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል ። ሀገር ያለ ካስማ እና ያለ ምሶሶ መና ልትቀር ትችላለች ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ፣ ከልማቱ ጥፋቱ ፣ ከአዎንታዊነቱ አሉታዊነቱ ይገዝፋል ። ስለዚህ ለውጥ ጥገናዊ እንጅ ስር ነቀል መሆን የለበትም ። የተበላሸውን እያስተከከሉ ፣ የተዛነፈውን እያቃኑ ፣ የደፈረሰውን እያጠሩ ፣ በነበረው ጥሩ ነገር ላይ አዲስ ነገር እየጨመሩ መሄድ ነው ጥገናዊ ለውጥ ። የዚህ ለውጥ መርህ ፣ ታሪክ እየረሱ እና እየጣሉ መሄድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እየጠበቁ እና እየገነቡ ወደ ፊት መሄድ ነው ። የትውልድ ቅብብሎሽ እውን የሚሆነው ፣ ለውጥ ጥገናዊ ሲሆን ነው ። 

        ጥገናዊ ለውጥ የደግነት እና የትህትና ውጤት ነው ። ለመስጠት ደግነት ያስፈልጋል ። ለመቀበል ትህትና ግድ ይላል ። የሚሰጥ ደግ ኖሮ ፣ የሚቀበል ትሁት ከሌለ ችግር ነው ። የሚቀበል ትሁት ኖሮ ፣ የሚሰጥ ደግ ከሌለ ታሪክን ለመቀበልም ለማስቀጠልም ከባድ ነው ። ስለዚህ ቀዳሚው ትውልድ ለማስተማር እና ለመስጠት ደግ መሆን አለበት ። ተከታዩ ትውልድ ደግሞ ለመማር እና  ለመቀበል ትሁት መሆን አለበት ። ያኔ የትውልድ ቅብብሎሽ እውን ይሆናል ። 

    '' ጥገናዊ ለውጥ ለትውልድ ቅብብሎሽ አስፈላጊ ነው ። ''     

No comments:

Post a Comment

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...