እምነት ወይስ እውነት
ያለ እምነትም ያለ እውነትም መኖር ከባድ ነው ። እውነት ለነጻነት ፣ እምነት ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው ። እምነት በእውነት ላይ ሲመሰረት ፣ ሰው በህይወቱ ሙሉነት ይሰመዋል ። እምነት በጥቅም ላይ ከተመሰረተ ግን ሰው በህይወቱ የሙሉነት ስሜት ይጎድለዋል ። በውሸት ማመን እርሱ የቁም ሬሳ መሆን ነው ። በውሸት ማስመሰል እንጅ መሆን አይቻልም ። ማስመሰል እውነተኛ ደስታን ሊሰጥ አይችልም ። መሆን ነው እውነተኛ ደስታን የሚፈጥረው ። እውነተኛ ደስታ ከእውነት እንጅ ከውሸት በፍጹም ሊገኝ አይችልም ። ብዙዎች ደስታን በውሸት ለማጣጣም ይሞክራሉ ። ነገር ግን እውነታው ደስታ ምን እንደሆነ በቅጡ አይረዱትም ። ምክንያቱም ውሸት የሚፈጥረው ደስታ ርካሽ እና ጊዜያዊ ነው ። እውነት የሚፈጥረው ደስታ ግን ውድ እና ዘላለማዊ ነው ።
ውሸት እና እምነት ህይወትን እርካታ ቢስ ያደርጋሉ ። እውነት እና እምነት ግን የህሊና እርካታን ይለግሳሉ ። ሰው በውሸት ሲኖር ፣ ደስታን በራሱ መፍጠር አይችልም ። ደስታን ከሌሎች ለማግኘት ይለፋል ይደክማል ፣ ይወጣል ይወርዳል ። ደስታን ከሌሎች ማግኘት ከባድ ነው ። ከራስ ማግኘት ግን ቀላል ነው ። ደስታን ከራሱ የሚያገኝ ፣ በራሱ ደስታን መፍጠር የሚችል ነው ። እንደዚህ አይነት ሰው ደግሞ ሰውን ለማስደሰት ብሎ አይሰራም ፣ ነገር ግን ሰውን የሚያስደስት ስራ መስራት ይችላል ። ደስታን መፍጠርም መጋራትም ማጋራትም ይችላል ። ምክንያቱም ስለእውነት በእውነት ነው የሚኖረው ።
እምነት በማስመሰል ወይም በውሸት ላይ ሲመሰረት ፣ እውነትን አይፈታተንም ።
ሰው ለብዙ ዓመት አዝሎ የኖረው እምነት ፣ ውሸት እንደሆነ ያወቀ እለት ፣ ያንን እምነት ለመተው ብዙ አይከብደውም ። ምክንያቱም ውሸት እውነትን አይበልጥም ። በውሸት የተፈጠረ እምነት ፣ በእውነት ፊት አቅም የለውም ።
ለፍቅር እውነትን መደበቅ ግን እውነትን የሚፈታተን እምነትን ይፈጥራል
። ፍቅር የሚፈጥረው እምነት በጣም ጠንካራ ነው ። ሰው ካጣው እውነት በላይ ያገኘው ፍቅር ሲበልጥበት ፣ እውነትን አምኖ ለመቀበል
ይቸገራል ። ይህንን እውነት ከሚያውቅ ፣ ባያውቅ ምርጫው ይሆናል ። ሰዎች አንዳንዴ በጣም ለሚወዳቸው ሰዎች ስለፍቅር ሲሉ ፣ እውነተኛ
ማንነታቸውን ደብቀው አብረው ይኖራሉ ። እነርሱን ላለማጣት ፈርተው እውነቱን ሳይናገሩ ይዘው ይቆያሉ ። በእርግጥ ለጥቅም ሲሉ እውነትን የሚደብቁ ክፉዎች አሉ ። እነዚህ ግን እንደ እነርሱ
አይደሉም ፣ ጥቅምን ላለማጣት ሳይሆን ሰውን ላለማጣት ሲሉ ነው ፣ እውነትን የሚደብቁት ። ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር ፣
በወላጅ እና በልጅ መሀል ሲከሰት ይስተዋላል ። የስጋ ዝምድና የሌላቸው ወይም ( Biological ) ያልሆኑ ወላጆች ፣ የአብራካቸው ክፋይ (
Biological ) ያልሆነ ልጅ ያሳድጋሉ ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች
እውነቱን ከመናገር ይልቅ ፣ እውነቱን መደበቅ ይመርጣሉ ። ግን በሚገርም የወላጅነት ፍቅር ያሳድጋሉ ። ይህ ፍቅር በልጅ ውስጥ
ጠንካራ እምነትን ይፈጥራል ። ይህ እምነት በውሸት ብቻ እንደተፈጠረው እምነት ደካማ አይደለም ። ፍቅር የፈጥረው ሀይለኛ እምነት
ነው ። ለእውነት በቀላሉ የማይረታ ብርቱ እምነት ነው ።
ለሰው ልጅ ፍቅር የፈጠረው እምነት ፣ ከተደበቀበት እውነት ይበልጥበታል ።
ምክንያቱም በውሸት ቢኖርም ያገኘው ፍቅር የእውነት ነው ። ያጣው እውነት ካገኘው ፍቅር አይበልጥበትም ። ለዚህም ነው ‘’ ፍቅርን ያልሰነቀ እውነት የሞተ ነው ። ‘’ የሚባለው ። ሰው አንዳንዴ እውነትን ከማጣቱ በላይ ፣ እውነትን ማወቁ ይጎዳዋል ። የሚጎዳን እውነት ማወቅ ህይወትን ያናጋል ። የሚጠቅም እውነትን ማወቅ ግን ህይወትን ያስተካክላል ። ስለዚህ ሁሉን እውነት ማወቅ አይጠቅምም ። የነበረንን ጥሩ ነገር የሚያሳጣ እውነት ባይታወቅ ይሻላል ። ያልነበረንን ጥሩ ነገር የሚያመጣ እውነት ግን ሊታወቅ ግድ ነው ። ፍቅርን የሚያሳጣ እውነት ባለበት ተደብቆ ቢቀር ይሻላል ። ፍቅርን የሚጨምር እምነት ግን ፣ ካለበት ተፈትሾ ቢገኝ መልካም ነው ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ እውነት መታወቁ አይጥቅምም ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚፈጥር እና የሚያጠነክር እውነት ተቆፍሮም ቢሆን መገኘት አለበት ። ልክ እንደ ክርስቶስ መስቀል ሱባኤ ሊያዝለት ይገባል ። በግራ በኩል እንደተሰቀለው ወንበዴ መስቀል ፣ ተገኘም አልተገኘም ፍቅርን ሰላምን መተሳሰብን የሚያሳጣ እውነት አያስፈልግም ።
እውነት ነጻነት ነው ። ግን ሁሉም እውነት ነጻነትን አይለግስም ። ነጻነትን የሚያሳጣ እውነት አለ ። ጤናን የሚያቃውስ እውነት አለ ። ይህንን እውነት መተው የተሻለ ነው ። የሚያበራ እውነት እንጅ የሚያጨልም እውነት መታወቁ አስፈላጊ አይደለም ። ቢታወቅ የሚጎዳ እውነት አስተሳሰብን ይቀይራል ፣ በአዎንታ ሳይሆን በአሉታ ። እምነትን ይበርዛል ። ቢታወቅ መጥቀምም መጉዳትም የማይችል እውነት አለ ። ይህ እውነት ቢታወቅ የሚጨምረው ነገር የለም ። ባይታወቅም የሚቀንሰው ነገር የለም ። ኖረም አልኖረም ዋጋ ቢስ ነው ። ለዚህ እውነት ትኩረት መስጠት ጅልነት ነው ።
ቢታወቅ የሚጠቅም እውነት ግን ህይወትን ቀያሪ ነው ፣ በአሉታ ሳይሆን በአዎንታ ። ለምሳሌ ፈጣሪን ፣ ሀይማኖትን ፣ ሳይንስን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ የሚጠቅሙ ማህበራዊ እሴቶችን ፣ ደጋግ ሰዎችን ማወቅ ፣ ህይወትን በመልካም መንገድ ይለውጣል ። ከዚህም በተጨማሪ የኔ የምትሉትን ሰው ማወቅ እፎይታን ይሰጣል ። ቤተሰብን ፣ ዘመድን ፣ ወዳጅን ማወቅ ያስደስታል ። እውነት ሀዘንም ደስታም ነው ። ከሚያሳዝን እውነት የሚያስደስት እውነት ይሻላል ። የሚያስደስት እውነት ውስጡ ፍቅር አለ ። ስለዚህ ከሚያሳዝን እውነት ፣ ያለ እውነት በፍቅር የተፈጠረ እምነት ይበልጣል ። የሚያስደስት እውነት ግን ፍቅርን የያዘ ስለሆነ ፣ እርሱ የሚፈጥረው እምነት ፣ ከሁሉም አይነት እምነት ይበልጣል ። ምክንያቱም እምነት ሁሉ በእርሱ መንገድ ነው መቀረጽ ያለበት ። ጠቃሚ እውነትን ከፍቅር ጋር በመያዝ ።
‘’ እምነት ከሚጎዳ እውነት ይበልጣል ። ከሚጠቅም እውነት ግን ያንሳል ። ‘’
No comments:
Post a Comment