ከራስ መጣላት
ከራስ መጣላት የራስን እውነት አለመቀበል ነው ። የገዛ ስሜታችንን መካድ ነው ። በጠቅላላው ራስን አለመቀበል ነው ። የሰውን ልጅ ከራሱ እንዲጣላ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው ። በሰዎች ዘንድ ክብርን ለማግኘት ሲሉ ከራሳቸው የሚጣሉ አሉ ። እነዚህ ሌሎችን ለማሳመን ወሬ በመፍጠር የሚተካከላቸው የለም ። በወሬ ጤፍ ይቆላሉ ጉም ይዘግናሉ ። ያለን ነገር ሳይሆን ፣ የሌለን ነገር መፍጠር ይችላሉ ። ተውሰው መልበስ ይችላሉ ። ሰርተው መልበስ ግን አይችሉም ። ብራንድ ጫማ ማድረግ ይችላሉ ፣ መግዛት ግን አይችሉም ። የሰው ሁሉ የእነርሱ ነው ። እነርሱ ግን የሚረባ አንድም ነገር የላቸውም ። የሚለብሱት የሚጫሙት የሚዘንጡት ሁሉ በሰው ነው ። በቃ እነርሱ ምንም የሌላቸው ባዶ ናቸው ። ሰው ባዶነቱን አምኖ መቀበል ካቃተው ፣ ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም ። ቦዶነቱን አምኖ መቀበል የቻለ ግን ፣ በአዲስ ነገር ባዶነቱን መሙላት ይችላል ። ምክንያቱም ራሱን መቀበል የቻለ ትሁት ነውና ።
ራሱን የተቀበለ ሰው ለመማር ለመስራት ለማወቅ ዝግጁ ነው ። ይህ ደግሞ ባዶ ከመሆን ይጠብቀዋል ። ራስን መቀበል መልካም ነገርን ከሌሎች ለመቀበል ልብን ክፍት ያደርጋል ። መቀበል ከሌለ መለወጥ አይኖርም ። አቀባበላችን ግን ለውጣችንን ይወስነዋል ። የምንቀበለው ጥሩ ነገር ከሆነ ፣ ለውጣችን አዎንታዊ ይሆናል ። የምንቀበለው ግን መጥፎ ከሆነ ፣ ለውጣችን አሉታዊ ይሆናል ። ከራሱ የተጣላ ሰው ሀሳብ መቀበል አይችልም ። ቢቀበልም ጥሩውን ሳይሆን መጥፎውን ነው ። ስጦታ መቀበል እና መዋስ ወይም መበደር ግን ይችልበታል ።
በሰው ዘንድ ለመከበር ብሎ ከራሱ የተጣላ ፣ ትልቁ ችሎታው መዋስ ወይም መበደር ነው ። ምክንያቱም ከራሱ የተጣላ ሰው ይሉኝታ ቢስ ነው ። መስራት ያሳፍረዋል ግን መዋስ ያኮራዋል ። ተናንሶ ከመስራት ይልቅ ፣ በሰው አንሶ ላለመታየት የሚያደርገው ጥረት እጅግ ይገርማል ። ስለዚህ ሰው ለመለወጥ ራሱን መቀበል ባዶነቱን ማመን አለበት ። መዋሸት ማቆም አለበት ። ውሸት የራስን ፍሬ የሚቀብር ክፉ አረም ነው ። አረም ውሸቱን ካልነቀለ ፣ ሰው አለሙን መመልከት አይችልም ። በእጁ ያለውን ወርቅ ማስተዋል አይችልም ። በእጁ የያዘው ተራ ፣ በሌላ ሰው እጅ ያለው ተራራ መስሎ ይታየዋል ። ለመከበር ብላችሁ ከራሳችሁ አትጣሉ ። እውነተኛ ክብርን ለማግኘት ከፈለጋችሁ ፣ ከራሳችሁ ታረቁ ማንነታችሁን ተቀበሉ ።
ሌላው የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ከወዳጅ መቀያየም ነው ። በተለይ የሚያፈቅሩት ሰው ሲያስቀይም በጣም ከባድ ነው ። የተበደለው/ችው ግለሰብ የገዛ የራሱን ስሜት ይከዳል ። ከልብ የሚወዱትን ወይም የሚያፈቅሩትን ሰው ፣ ልባቸው እየፈለገ እነርሱ ግን በአፋቸው አልወደውም ወይም አልወዳትም ይላሉ ። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ እንዳላቸው ለማሳወቅ ፣ አሁንስ አይኑን አያሳየኝ በማለት ይምላሉ ። አያሳየኝ ብለው አፋቸውን ሞልተው ይምላሉ ፣ ነገር ግን በደለ የተባለው ፍቅረኛ ወይም ግለሰብ ሲመጣ ልባቸውን በፍቅር ይሞላሉ ። ያንን ሰው እየናፈቁ መቼም አይናፍቀኝም ይላሉ ። እውነቱ ግን ‘’ ማሽላ በውስጥ እያረረች ከላይ ትስቃለች ‘’ እንደሚባለው ፣ አፋቸው ልባቸውን ይከዳል እንጅ ስር የሰደደ ናፍቆት በውስጣቸው አለ ። እነዚህ ሰዎች ሰው ፊት እየሳቁ ፣ ቤት ገብተው እርር ብለው የሚያለቅሱ ፣ አሳዛኝ ፍጡራን ናቸው ። በፍቅር ምክንያት ከራስ መጣላት በሽታ ነው ።
ስሜትን አፍኖ መያዝ ፣ ጠንካራ መስሎ ለመታየት ከራስ ጋር መታገል ፣ ላለመሸነፍ በውጥረት ውሎ በጭንቀት ማደር ። ይሄ ሁሉ እየወደዱ መጥላት የሚያመጣው መዘዝ ነው ። ከራስ መጣላት የሚፈጥረው ዱብዳ ነው ። ስለዚህ እየወደዱ ከመጥላት በይቅርታ ሰላም መፍጠር ። በእብሪት አልሸነፍ ባይ ሆኖ ከራስ ከመጣላት ፣ በትህትና እርቅ ማውረድ የተሻለ ነው ። ያኔ ከራስም ከሰውም ሰላም መሆን ይቻላል ።
ከራሳቸው ከሚጣሉ ሰዎች መሀል ፣ ችግር ከራሳቸው የሚያጣላቸው ሰዎች እጅግ ያሳዝናሉ ። እነዚህ ሰዎች ወደው ሳይሆን ተገደው ነው ከራሳቸው የሚጣሉት ። ለመኖር ሲሉ ያላመኑበትን ነገር ያደርጋሉ ። መስጠት እየፈለጉ ይከለክላሉ ። ማዳን እየፈለጉ ይገድላሉ ። መውደድ እየፈለጉ ይጠላሉ ። መቅረብ እየፈለጉ ይርቃሉ ። ማግኘት እየፈለጉ ያጣሉ ። መናገር እየፈለጉ ዝም ይላሉ ። ማልቀስ እየፈለጉ ይስቃሉ ። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ፣ በክፉዎች መሀል የሚኖሩ ሩሩ ናቸው ። ጨካኝ ሌባ እንዳለ ሁሉ ሩሩ ሌባ አለ ። ክፉ ባለስልጣን እንዳለ ሁሉ ሩሩ ባለስልጣንም አለ ። አስቸጋሪ ሰራተኛ እንዳለ ሁሉ መልካም ሰራተኛ አለ ። ችግሩ ያ አይደለም ። ክፉው ከመልካሙ ሲበዛ ነው ችግር የሚፈጠረው ። መልካሞች ከክፉዎች ከበዙ ፣ ችግር ይቀረፋል እንጅ አይፈጠርም ። ከራስ መታረቅ እንጅ ከራስ መጣላት አይኖርም ። ክፎዎች ሲበዙ ግን ከራስ መጣላት ይኖራል ።
ክፉ ከመልካም ይልቅ ጉልበት ሲኖረው ፣ መልካም ሰዎች አቅም በማጣት ከራሳቸው ይጣላሉ ። ግፍ ሲፈጸም መናገር እየቻሉ ዝም ይላሉ ። ሰው ሲገደል ማዳን እየቻሉ እያለቀሱ ይቀብራሉ ።
ደሀ ሲበደል መድረስ እየቻሉ ይሸሻሉ ። በክፉዎች ፊት አብረው ስቀው ፣ ቤት ገብተው ግን እርር ብለው ያለቅሳሉ ። እድሜ ልክ የህሊና እረፍት አጥተው ይኖራሉ ። ሆን ብሎ ከራስ መጣላት እና ተገዶ ከራስ መጣላት ይለያያል ። ሆን ብለው ከራሳቸው የተጣሉ ፣ አምነው ስለሆነ ጫናው ለእነርሱ ቀላል ነው ። ተገደው ከሆነ ግን ስለማያምኑበት ጫናው እጅግ ከባድ ነው ። በክፉዎች መሀል ቅን ሆኖ መገኘት ከባድ ነው ። በመልካሞች መሀል ቅንቅን ሆኖ መገኘትም ከባድ ነው ። ህይወት ከመልካሞች ጋር ደስ ትላለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት የለም ። ከክፉዎች ጋር ግን ትመራለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት ሁሌም አለ ። የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ፣ አንደኛው እና ዋነኛው ክፋት ነው ።
‘’ ከራስ መጣላት ራስን መካድ ነው ። ራስን መካድ ደግሞ አርቴፊሻል ህይወት መምራት ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment