ኢላማ
ኢላማ ሰው ዓላማውን ፣ ፍላጎቱን ፣ ውጥኑን ለማሳካት የሚወስደው እርምጃ ነው ። ሰውን ወደ መዳረሻው የሚወስደው
፣ የትኩረት አቅጣጫ ነው ። ኢላማ ከሌለ ስኬት የለም ። ስኬት የለም ማለት ግን ኢላማ የለም ማለት አይደለም ። ስኬት ቢኖርም
ባይኖርም ፣ ኢላማ ይኖራል ። ስኬት ግን ያለ ኢላማ ፈጽሞ አይታሰብም ። ሰው ኢላማው ትክክል ከሆነ ፣ ከስኬት ጫፍ ይደርሳል ።
ኢላማው ትክክል ካልሆነ ግን ፣ ከውድቀት አፋፍ ይደርሳል ። በእርግጥ ትክክለኛ ኢላማ ኖሮትም ፣ ከስኬት ጫፍ የማይደርስ ሰው አለ
። ምክንያቱ ወይ የአቅም ማነስ ነው ፣ አልያም የባህሪ ጉድለት ነው ። ጥሩ ባህሪ እናም በቂ አቅም ኖሮት ፣ ኢላማው ግን የተሳሳተ
ከሆነ ፣ ሰው ለስኬት አይበቃም ። ጥሩ ባህሪ ባይኖረውም ፣ በቂ አቅም ካለው ፣ ኢላማው ትክክል ከሆነ ከስኬት የመድረስ እድሉ
አለው ። ጥሩ ባህሪ ኖሮት ፣ በቂ አቅም ከሌለው ፣ ኢላማው ትክክል ቢሆንም ፣ ስኬት እና እርሱ ሆድ እና ጀርባ ናቸው ። ጥሩ
ባህሪ ከበቂ አቅም ጋር ሲደመር ትክክለኛ ኢላማ ፣ ያለምንም ጥርጥር ከስኬት ማማ ያደርሳሉ ።
ኢላማ በመጀመሪያ አቅምን ያማከለ መሆን አለበት ። ‘’ አቅምን
አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው ። ’’ አይደል ያለው አንጋፋው ዘፋኝ መሀሙድ አህመድ ። የሰው ልጅ ትልቁ ችሎታው አቅሙን
ማወቁ ነው ። አቅሙን የማያውቅ ሰው ተሰባሪ ነው ። ስብራቱ ደግሞ የልብም የአካልም ነው ። ያለአቅሙ ያልምና አልሆን ሲለው ፣
በራስ መተማመኑን ያጣል ። እምነቱን ሲያጣ ልቡ ይሰበራል ። ልቡ ሲሰበር ክፉኛ በሀዘን ይጎዳል ። ሀዘኑ በመጨረሻ ለጤና መታወክ
እና ለአካል ጉዳት ይዳርገዋል ። ህጻን ልጅን ጥሬ ስጋ ማብላት መጨረሻው ህመም ነው ። የአስር አመትን ልጅ ፣ ሀምሳ ኪሎ ዱቄት
ማሸከም ፍጻሜው የአካል ጉዳት ነው ።
የአስራ አምስት አመትን
ልጅ ፣ የፍልስፍና መጽሐፍ ማስነበብ ፣ መጨረሻው ሜዳሊያ ሳይሆን ሜዳ ላይ መውደቅ ነው ። ስለዚህ ኢላማ እና አቅም መመጣጠን አለባቸው
። በእርግጥ ኢላማ ከፍ ብሎ አቅም ከሚያንስ ፣ አቅም ከፍ ብሎ ኢላማ ቢያንስ የተሻለ ነው ። ኢላማ ዝቅ ማለቱ ግን እድገትን ሊገታ
ይችላል ። እኩል ሲሆኑ ወይም ትንሽ ከፍ ቢል ፣ ጤናማ እድገት ይኖራል ።
ኢላማ አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆን የለበትም ። አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን
ጎደሎ ለመሙላት ፣ የሌላው መጉደል አለበት ብለው ያምናሉ ። የራሳቸውን እንጀራ ለመጋገር ፣ የሌላውን ዳቦ መርገጥ አለብን ይላሉ
። ጠቅመው መጠቀም ሳይሆን ፣ ጎድተው መጠቀም ይፈልጋሉ ። ጥቅምን መጋራትም ሆነ ማጋራት ደስ አይላቸውም ። ብቻውን የበላ ብቻውን
ይሞታል ቢባሉ ፣ አብሮስ የበላ መች አብሮ ሞተ ብለው ይመልሳሉ ። ብቻውን የበላ ሳይራብ ይሞታል ። አብሮ የበላ በራብ ይደፋል
ብለው ያምናሉ ። መኖር በጋራ መሞት በግል ነው ፣ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው ። እነርሱ ጋር ግን መኖርም መሞትም በግል ነው ። የሚኖሩት
ለራሳቸው ነው ። ሌላው እስከጠቀማቸው ያኖሩታል ። ካልጠቀማቸው ደግሞ ያሽቀነጥሩታል ። አተርፍ ባይ አጉዳይ የሆነ ኢላማ ፣ ከስህተትም
በላይ ትልቅ ስህተት ነው ። ትክክለኛ ትርፍ የጎደለን በመሙላት የሚገኝ ነው ። የሞላን በማጉደል ማትረፍ ግን ፣ ትርፍ ገንዘብ
ሊያስገኝ ቢችልም ለህሊና ኪሳራ ይዳርጋል ። የጎደለን መሙላት ለሚፈልጉ ሰዎች ፣ ችግር ሲሳይ ነው ። አተርፍ ባይ አጉዳይ ለሆኑ
ሰዎች ግን ችግር ስቃይ ነው ። በነገራችን ላይ ሳይንሳዊ ጥናት አላማው ጉድለት መሙላት ( Gap fill ) ነው ። ስለዚህ
ችግርን እንደ ሲሳይ እንጅ እንደ ስቃይ አይመለከትም ። ለማደግ ችግርን ይፈታል እንጅ ችግርን አይፈጥርም ። እነ አትርፍ ባይ አጉዳዮች
ግን ለማትረፍ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ችግርን ይፈጥራሉ ።
አተርፍ አጉዳይ መሆን ፈጣሪ አያደርግም ። በአብዛኛው ፈጣሪዎች ሰው
እናትርፍ ብለው እንጅ ገንዘብ እናትርፍ ብለው ስራ አይጀምሩም ። በሽታ ሲከሰት ሳይንቲስቱ መድሀኒት የሚፈጥረው ሰው ለማዳን ነው
። ሁለቱ ወንድማማቾች ( Right Brothers )
አውሮፕላንን የፈበረኩት የሰውን ድካም ለማቅለል ነው ። የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች ፣ የሞባይል መተግበሪያዎች የሚበለጸጉት የሰውን
ልጅ ኑሮ ለማቅለል ነው ። በትክክል ከተረዳን እናም ከተጠቀምን ፣ እነዚህ ነገሮች ጫናን ከመፍጠር ይልቅ ይቀንሳሉ ። ፈጣሪዎች
ኢላማቸው የተስተካከለ ስለሆነ ፣ አላማቸው ዉብ ነው ። ሰውን እያስለቀሱ ሳይሆን ፣ የሰውን እንባ በማበስ ነው የሚያተርፉት ።
ሰውን በማቃለል ሳይሆን ችግርን በማቅለል ነው የሚደሰቱት ። ለዓለም የጎደላትን ይሞላሉ እንጅ ለዓለም ጉድለት አይሆኑም ።
ትክክለኛ ዓላማ ለተስተካከለ ዒላማ ዋስትና አይሆንም ። ዓላማ ኢላማን
አይወስንም ። ኢላማ ግን ዓላማን ይወስናል ። ኢላማችን ልክ ሲሆን ነው ፣ ዓላማችን እውን የሚሆነው ። ኢላማችን ስህተት ከሆነ
ግን ዓላማችን ቅዥት ነው የሚሆነው ። መብት ለማግኘት መብት መንፈግ ትክክል አይደለም ። ስልጣን ለመንጠቅ ነፍስ መንጠቅ ተገቢ
አይደለም ። እምነትን ለመፍጠር ከሀዲ መሆን ልክ አይደለም ። ለመታረቅ ማጣላት ተንኮል ነው ። ለመቆም መጣል ግፍ ነው ። ሳይነፍጉ
ማግኘት ፣ ሳይነጥቁ መውሰድ ፣ ሳይክዱ መታመን ፣ ሳያጣሉ መታረቅ ፣ ሳይጥሉ መቆም ይቻላል ። ትክክለኛ ኢላማ ያለውም እነዚህ
ውስጥ ነው ። በአለም ዙሪያ የሚዘወተር አንድ የተሳሳተ ኢላማ አለ ፣ መንግስትን ለመቀየር የህዝብን ሀብት ማውደም ። መንግስትን
ለመቀየር ፣ የህዝብን ሀብት ማውደም ሳይሆን መፍትሔው ፣ ህዝብን ማሳመን ኢላማ ማድረግ ነው የሚያዋጣው ። ማውደም ሳይሆን ማሳመን
ነው ትክክለኛ ኢላማው ። አባትን ለማሳመን ልጅን ኢላማ ማድረግ የተሳሳተ እርምጃ ነው ።
ርእሰ መምህሩን ስለጠሉ ትምህርት ቤቱን ማፍረስ አምሮን ማፍረስ ነው ። መብትን
ለማስከበር መንገድ መዝጋት እድልን መዝጋት ነው ።
ገበያ ለመፍጠር የሌላውን
ገበያ መዝጋት ቀሽምነት ነው ። የተሳሳተ ኢላማ የመሽቀዳደም ውጤት ነው ። በመሽቀዳደም ውስጥ ፣ መቅደም ያለበት ይከተላል ፣ መከተል
ያለበት ይቀድምና ነገር ይበላሻል ። ቀኙ ግራ ፣ ግራው ቀኝ ይሆናል ። መሽቀዳደም ራስ ወዳድ ያደርጋል ። ስለዚህ ለትክክለኛ ዓላማ
፣ የተሳሳተ ኢላማ እንዲኖረን ያስገድደናል ። መሽቀዳደም መከባበርን ያሳጣል ። እኔ እሻላለው እንጅ ፣ ሌላው ይሻላል ማለት በመሽቀዳደም
ውስጥ ከባድ ነው ። መከበር እንጅ ማክበር ፈጽሞ አይታሰብም ። ስለዚህ አላማችን እውን እንዲሆን ፣ የተስተካከለ ኢላማ እንዲኖረን
፣ መሽቀዳደምን ማስወገድ መቻል አለብን ።
No comments:
Post a Comment