ጀግንነት
ጀግንነት ጠላትን ማሸነፍ ነው ። የሰው ልጅ
የመጀመሪያ ጠላቱ ደግሞ አሉታዊ አስተሳሰቡ ነው ። ክፉ ሀሳቡን ማሸነፍ ያልቻለ እርሱ ጀግና አይደለም ። ጀግና ሳይሆን ደንዳና
ነው ። ራሱን ለፍቅር አምበርክኮ ፣ የሌላውን ልብ በፍቅር የማረከ እርሱ ነው ጀግና ። በሀይል ወይም በጉልበት መማረክ አምባገነንነት
ነው ። በፍቅር መማረክ ግን ጥበበኛነት ነው ። ስለዚህ ጀግንነት ፍቅር ውስጥ እንጅ ፣ ሀይል ውስጥ ወይም ጉልበት ዉስጥ አይገኝም
። የፍቅር ጉልበት ከፈረጠመ የአካል ጉልበት ይበረታል ። የፍቅር ሀይል ከሰራዊት ሀይል ይበልጣል ። በፍቅር ሁሉን ማሸነፍ ይቻላል
። በጉልበት ወይም በሀይል ግን ሁሉን አይደለም ጥቂቱን ማሸነፍ አይቻልም ። ሀይል ወይም ጉልበት በሂደት ይዝላል ይከዳል ። የማይከዳ
ሀይል ከፈለጋችሁ ለፍቅር ተማረኩ ፣ በፍቅር ማርኩ ። ያኔ የእውነት ጀግና ትሆናላችሁ ። ጀግንነት መግደል ሳይሆን ማዳን ነው ። ህዝብን ለማዳን እንደ ዳዊት ጎልያድን
መግደል ጀግንነት ነው ። ለቁራሽ መሬት ግን ወንድምን መግደል ጅልነት ነው ። ማዳንን አላማው ያላደረገ አሸናፊነት ጀግንነት አይሆንም
። ምክንያቱም ሰውን ከማሸነፍ በላይ ጀግንነት ራስን ማሸነፍ ነውና ። ለክብሩ ለጥቅሙ ለስሙ ሲል ሽዎችን የሚደመስስ ሳይሆን ጀግና
፣ ለሺዎች ክብር ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ ነው ጀግና ።
ከመግደል ይልቅ ለእውነት ለፍቅር ለፍትህ ለሰብአዊነት መሞት ነው ጀግንነት
። ለብዙዎች ህይወትን መስጠት እንጅ ፣ የብዙዎችን ህይወት ማጥፋት በፍጹም ጀግንነት ሊሆን አይችልም ። ማስፈራራት ወይም ማስደንገጥ
ሳይሆን ፣ ማረጋጋት እና ሰላም መስጠት ነው ጀግንነት ። ማስፈራራት የሚወዱ ጀብደኞች እንጅ ጀግኖች አይደሉም ። ጀብደኞች ደግሞ
ወረተኛ ማንነት እንጅ እውነተኛ ማንነት የላቸውም ። ጀግና ግን ሁል ጊዜም እውነተኛ ነው ። ለመወደስ ብሎ አያስመስልም ። ላለመወቀስ
ፈርቶም ነጩን እውነት አይክድም ። እርሱ ምን ጊዜም የትም ቦታ ያው ራሱ ነው ። ካናዳም ሄደ ጅዳ ፣ አሜሪካም ሆነ ደቡብ አፍሪካ
፣ ኢትዮጵያም ይኑር ዩጎስላቪያ ለእርሱ ለውጥ የለዉም ። የትም ይሁን ከሰዉነቱ ከፍ ዝቅ አይልም ። በቃ ሰው ነው ራሱን የሆነ
ሰው ። ጀግንነት አለማስመሰል እውነተኝነት ራስን መሆን ነው ።
ጀግንነት ችግር መፍታት እንጅ ችግር መፍጠር አይደለም ። ከተማን ማመስ
ጀግንነት አይደለም ። እንደ እናቶቻችን ምጣድ ማመስ ነው ጀግንነት ። ዛሬ ሁላችንም በሚባል ደረጃ ለክብር የበቃነው ፣ በጀግኖች
እናቶቻችን በታመሰ ምጣድ ላይ በተጋገረ እንጀራ ነው ። ክብር ለእናቶቻችን
! ጀግንነት እንዲህ ነው ። ሰው እንዲበላ ምግብ መስጠት እንጅ ፣ ሰው እንዲራብ ምግብ መከልከል ጀግንነት አይደለም ። ጀግንነት
መስጠት እንጅ መከልከል አይደለም ስራ መስራት እንጅ ሴራ ወይም ተንኮል
መሸረብ አይደለም ። ሆ ብሎ ማመጽ ሳይሆን ሆ ብሎ መስራት ነው ጀግንነት ። በጋራ ማፍረስ ሳይሆን በአንድነት መገንባት ነው ጀኝነት
። እርስ በእርስ መጋደል ሳይሆን ፣ በህብረት ጥላቻን መግደል ነው ጀግንነት ። የእርስ በእርስ ጦርነት ጀግና የለውም ። ጀግናም
ካለ ለጦርነቱ መቆም ፣ የቶክስ አቁም ስምምነት ያወጀ ነው ። ጀግንነት ሰውን መግደል ሳይሆን ፣ የጥላቻን ሃሳብ እና አስተሳሰብ
መግደል ነው ። ልክ እንደ አብርሀም ሊንከን ጠላትን በጦር ሳይሆን ፣ በፍቅር ገድሎ ጀግና መሆን ። ድል በሀይል ከተገኘ ኢ እኩልነት
ይፈጠራል ፣ ፍትህ ይዛባል ። ድል በፍቅር እውን ከሆነ ግን ፣ እኩልነት ይሰፍናል ፍትህ ይረጋገጣል ። በምድራችን የሰው ልጅ እኩልነት
እንዲሰፍን ፣ መትረየስን ሳይሆን ፍቅርን መሳሪያ እናድርግ ።
ጀግንነት በመከራ ውስጥ ተስፋን መያዝ ነው ። ከድቅድቁ ጨለማ ጀርባ
የብርሀን ጮራ እንዳለ ማሰብ ነው ። ከህመም ለጥቆ ጤና ፣ ከችግር ቀጥሎ መፍትሔ ፣ ከጭንቀት ባሻገር መረጋጋት ፣ ከጦርነት ጀርባ
ሰላም እንደሚመጣ ማመን ነው ።
በጦርነት ተስፋ ከመቁረት ይልቅ ፣ ወደ ሰላም
ትኬት መቁረት ነው ጀግንነት ። በማጣት ተስፋ ከመቁረት ይልቅ ፣ ለማግኘት ቆርጦ መነሳት ነው ጀግንነት ። ፈተና ዉስጥ እድል ፣
ዝቅታ ዉስጥ ከፍታ ፣ መናቅ ዉስጥ ክብር እንዳለ ማየት ነው ጀግንነት ። ሲወድቁ ተስፋ ቢስ መሆን ሳይሆን ፣ ለመነሳት ጥረት ማድረግ
ነው ጀግንነት ።
እውነተኛ ጀግና የሚፈጠረው ፣ በጦር ብዛት
ሳይሆን ፣ በእምነት እና በተስፋ ብዛት ነው ። ከሁለቱ በማይለየው ነገር ግን ከሁለቱ በሚበልጠው ፍቅር ደግሞ ፣ ከሁሉ የላቀ ጀግና
ይወለዳል ።
‘’ እምነት ተስፋ ፍቅር በአንድነት ይጸናሉ
፣ ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል ። ’’ እንዲል ታላቁ መጽሐፍ ።
‘’ ጀግንነት የሀይል መገለጫ ሳይሆን ፣ የፍቅር መገለጫ ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment