ፍትህ
ፍትህ የስራ ውጤት ነው ። ሰው የስራውን ካላገኘ ፍትህ የለም ማለት ነው ። ፍትህ ካለ ጥሩ የሰራ ይሸለማል ። መጥፎ የሰራ ደግሞ ይቀጣል ። በተቃራኒው ፍትህ ከሌለ ፣ መጥፎ የሰራ አይቀጣም ። ጥሩ የሰራ አይሸለምም ። አለመሸለም ብቻ አይደለም ፣ ጥሩ በመስራቱ ሊቀጣ ይችላል ። ፍትህ ከሌለ የዘሩትን ማጨድ አይቻልም ። መታጨድ እንጅ ማጨድ አይኖርም ። መልካም የሰሩ የዘሩትን ማጨድ ባይችሉም ፣ ክፉዎች ግን ያልዘሩትን ያጭዳሉ ። ያላበሰሉትን ይበላሉ ። ያልሰጡትን ይወስዳሉ ። ያልተንከባከቡትን ፍሬ ይመገባሉ ። ፍትህ በሌለበት ትጋት ከንቱ ነው ። ምክንያቱም ሰርቶ መከበር አይቻልም ። ሰርቆ መከበር ነው የሚቻለው ። ጥሮ ማሳካት እጅግ ከባድ ነው ። አጭበርብሮ ማሳካት ግን ቀላል ነው ። ያለፍትህ ስራ ዋጋው ዝቅ ይላል ። ሴራ ግን ዋጋው ከፍ ይላል ።
ለስራ የሚተጉ ፍትህ ያሰፍናሉ ። ለሴራ የሚተጉ ደግሞ ፍትህ ያዛባሉ ። ለመስራት የሚተጉ ፍትህን ያረጋግጣሉ ። ለመስረቅ የሚተጉ ፍትህን ይረግጣሉ ። መስረቅም መስራትም ትጋት ይፈልጋሉ ። ልዩነቱ መስረቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል ። የደስታ ሰገነት ላይ ያስቀምጣል ። ግን ደግሞ የሀዘን አዘቅት ውስጥ መክተቱ ኣይቀርም ። ስራ በአንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ አያስገኝም ። ደስታውንም በመጠኑ ፣ ገንዘቡንም በልኩ እያሳደገ ነው የሚሄደው ። ሰው በመስረቁ የሰውን ደስታ ይቀማል ። ለዚያ ነው ደስታው ከልክ በላይ የሚሆነው ። የሚገርመው ሀዘኑም ከልክ በላይ መራር ነው ። ምክንያቱም የሚሸከመው ሀዘን የራሱን ብቻ ሳይሆን ፣ የሰውንም ጭምር ነው ።
ሰው በመስራቱ ግን ሀዘኑም ደስታውም በልኩ ነው ። ምክንያቱም የሚቀማው ደስታ የለም ። የሚሸከመውም ተጨማሪ ህዘን የለም ። እርሱ ፍትሐዊ ነው ።
ለመስራት እንጅ ለመስረቅ ፣ ለማስደሰት እንጅ ለማሳዘን ፣ ፍትህን ለማረጋገጥ እንጅ ለማዛባት አትትጉ ። ትጋት ደስ የሚለው ከቅንነት ጋር ነው ። ቅንቅንነት አይመቸውም ። ስኬት የትጋት ውጤት ነው ። ሰው ለፍትህ ከተጋ ፣ ስኬት የሀቀኞች ትሆናለች ። ፍትህን ለማዛባት ከተጋ ግን ፣ ስኬት የአጭበርባሪዎች ትሆናለች ። ፍትህ አለ ማለት የተጉ ስኬትን ይጎናጸፋሉ ፣ የአጭበረበሩ ይቀጣሉ ፣ የማይለፉ ሰነፎች ደግሞ ከሁለቱ ይማራሉ ። ፍትህ ከሌለ ስኬትም ቅጣትም የለም ። ስኬት ከሌለ አርአያ አይኖርም ። ቅጣት ከሌለ መማርያ አይኖርም ። ንቁ ሰው ከአርአያው ይማራል ። ያልነቃው በቅጣት ይማራል ። ፍትህ አለ ማለት በሁለቱም መንገድ መማር አለ ማለት ነው ። ከሌለ ግን መማረር እንጅ መማር አይቻልም ።
ፍትህ ለእውነት መቆም ነው ። በፍትህ ዘንድ ወገንተኝነት አይሰራም ። ጥፋተኛ ዘመድ ስለሆነ ከፍርድ አያመልጥም ። ሌባ ልጅ ስለሆነ ከቅጣት አይድንም ። ወንጀለኛ ወዳጅ ስለሆነ ከእስር አይተርፍም ። ፍትህ ስጋ ብሎ አያዳላም ። ለወዳጅ ብሎ ፍርደ ገምድል አይሆንም ። ለልጅ ብሎ እውነትን አይገፋም ። ለፍትህ መኖር ማለት ለእውነት እየቆሙ ፣ መከራን እየታገሱ መኖር ነው ። እውነት የለም ማለት ፍትህ የለም ማለት ነው ። ለፍትህ የእውነት መኖር ግድ ነው ። እውነት እና ፍትህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ።
ለዚህ ነው ለመርማሪ እውነቱን ማወቅ ከባድ ፈተና የሚሆንበት ። የፍትህ መሰረቱ እውነት ስለሆነ ፣ ፍትህን የሚረግጡ እውነት እንዳትታወቅ ፣ ባለ በሌለ አቅማቸው ይታገላሉ ። ፍትህን ለማስፈን የሚተጉ ፣ እውነቱን ለማግኘት ከባድ ትግል ውስጥ ይገባሉ ። ‘’ እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል ። ‘’ እንዲባል ፣ እውነቱ ግን መታወቁ አይቀርም ። ፍትህን የነበሩት ቢያጡት ፣ የሚመጡት ማግኘታቸው አይቀርም ።
‘’ ለፍትህ እውነት እርቃኑን መሆን አልበት ። ‘’ አለች ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሞፈሪያት ካሚል ። እውነትነት አለው ። ብዙውን ጊዜ እውነት ፣ ወይ ፍቅርን አሊያም ጥላቻን መልበሱ አይቀርም ። ጥላቻን ከሚለብስ ፍቅርን ቢለብስ የተሻለ ነው ። እውነት ጥላቻን ከለበሰ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ። በጥላቻ የሚነገር እውነት ፣ ሰው ውስጥ ሀይለኛ ቁጣን ይቀሰቅሳል ። ፍትህን ለማስፈን ከመጣር ይልቅ ለበቀል ያነሳሳል ። ፍትህ አላማው ማስተማር እና መካስ ነው ። በቀል ክፋትን በክፋት መመለስ ነው ። የፍትህ መጨረሻው ሰላም እና እርቅ ነው ። የበቀል መጨረሻው ግን መጨራረስ ነው ። እውነትን ጥላቻ ማልበስ ፣ ነገርን ወደ በቀል መውሰድ ነው ። ስለዚህ ከቻልን እውነትን ፍቅርን እናልብስ ። ካልሆነ እርቃኑን ይሁን ።
ለሰው ልጅ የሚሻለው ግን ፣ ያለምንም ጥርጥር እውነትን ፍቅርን ማልበስ ነው ። ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ፣ እንደ ሀብት ከትውልድ ትውልድ ፣ ሲሸጋገር የሚመጣን በቀል ማስቆም ይቻላል ። Genetic code ( የዘረ መል ውርስ ) እስኪመስል ፣ በቀልን በደም የሚዋረስ ህብረተሰብ አለ ። በቀል ለትውልድ የሚያወርሱት ሀብት ሳይሆን እርግማን ነው ።
ምንም ጥቅም የሌለው ርካሽ ተግባር ነው ። የፈሰሰን ውሀ ለማፈስ መታገል ነው ። ይሄ ደግሞ የራስን ውድ አላማ መዘንጋት ነው ። ህልምን ቀብሮ ራእይን አፈር ድሜ ማብላት ነው ። በትላንት ታሪክ ዛሬን ለመኖር መታገል ነው ። ትላንት ለዛሬ ግብዓት እንጅ ግብ አይደለም ። በቀለኞች ግን ለዛሬ ወይም ለነገ የሚሆን ግብ የላቸውም ። የእነርሱ ግባቸውም ህልማቸውም ትላንት ነው ። የወላጅ ክፉ ሀሳብ ማስፈጸም ነው ራእያቸው ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እውነት ጥላቻን ሲለብስ ነው ። እውነት ፍቅርን ሲለብስ ግን በተቃራኒ ነው የሚሆነው ። ወደ ይቅርታ ይመራል ። ሰው የወላጁን ሳይሆን የራሱን ህልም እንዲኖር ይረደዋል ። የራሱ ግብ እንዲኖረው አስተሳሰቡን ይቀይረዋል ። ዛሬና ነገን በአግባቡ እንዲጠቀም ያግዘዋል ። በቀለኛ ሳይሆን ፍትሀዊ እንዲሆን ያስገድደዋል ። ከምንም በላይ ጎጅውን ጥላቻ ሳይሆን ፣ ጠቃሚውን ፍቅር እንዲያስቀድም ያደርገዋል ። ፍትህ የሚረጋገጠው በፍቅር እንጅ በጥላቻ አይደለም ። በቀል ፍትህ አይሆንም ። ፍትህ ይቅርታ ማድረግ ማስተማር መቅጣት እና መካስ ነው ።
‘’ እውነትን ፍቅር አልብሱት ፣ ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ። ‘’