Saturday, June 28, 2025

እይታ | Perception

                                                              ስንፍና

  ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉን መስራት አይችልም ። ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ብቻ ነው ። ደካማ ጎን የሌለው ፣ ጠንካራ ጎኑ ብቻ የሚነገርለት አካል ፈጣሪ ብቻ ነው ። የሰው ልጅ ግን ደካማ እና ጠንካራ ጎን አለው ። አንዱ ጠንካራ በሆነበት ሌላው ደካማ ሊሆን ይችላል ። ሌላው ጠንካራ በሆነበት አንደኛው ደግሞ ደካማ ነው ። በቃ ይህ የህይወት እውነታ ነው ። በአንድ ነገር ደካማ መሆን ግን ስንፍና አይደለም ። ስንፍና መስራት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ፣ ምንም መስራት አለመቻል ነው ። መስራት እየቻሉ መለገም ፣ ማንበብ እየቻሉ ማሳበብ ፣ መድረስ እየቻሉ መቅረት ፣ መራመድ እየቻሉ መቆም ፣ መቆም እየቻሉ መቀመጥ ፣ መቀመጥ እየቻሉ መቆመጥ ነው ስንፍና ።

 ድክመት የተፈጥሮ ውጤት ነው ። ስንፍና ግን የምርጫ ውጤት ነው ። ሰው መርጦ ደካማ መሆን አይችልም ። መርጦ ግን ሰነፍ መሆን ይችላል ። ድክመትን ማሻሻል ይቻላል ፣ ማስወገድ ግን በፍጹም አይቻልም ። ስንፍናን ማስወገድ ግን ይቻላል ። ድክመትን ለማሻሻል ፈጣሪን መማጸን ግድ ነው ። ስንፍናን ለማስወገድ ግን ራስን ማሳመን በቂ ነው ። ድክመትን መቀበል እንጅ መቃወም አይቻልም ። ስንፍናን መቀበልም መቃወምም ይቻላል ። ጠንካራ ሰው ስንፍናን መቃወም የሚችል ነው ። በዚያው ልክ ድክመቱን አምኖ መቀበል የሚችል ነው ። ዳተኛ ሰው ግን ስንፍናን መቃወም አይችልም ። ድክመቱንም አምኖ መቀበል አይችልም ። ለሚያደርገው የስንፍና ድርጊት ሰበብ መፍጠር ነው የሚችለው ።

ለችግሩ መፍትሄ የማያጣ ሳይሆን ፣ ለስንፍናው ምክንያት የማያጣ ፍጥረት ነው ። ሰነፍ ማለት ደክሞ ሳይሆን አውቆ የተኛ ነው ። ’’ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም ። ‘’ ይል የለ ያገሬ ሰው ፣ ሰነፍ እንደዛ ነው ። እየቻለ የማያደርግ እያወቀ ዝም የሚል ነው ።

  ንግግር አለመቻል ስንፍና አይደለም ድክመት ነው ። መናገር እየቻሉ ዝም ማለት ነው ስንፍና ። በተፈጥሮ ንግግር ላይ ደካማ የሆነ ሰው ፣ በጥረት የንግግር ችሎታውን ማሻሻል ቢችልም ፣ በፍጹም አንደበተ ርቱዕ ሊሆን አይችልም ። አንደበተ ርቱዕ ካልሆንኩ ብሎ ከሚታገል ፣ ድክመቱን አምኖ ቢቀበል ይሻለዋል ። ‘’  Change the changeable, accept the unchangeable. ‘’ እንዳለው የህይወት ክህሎት አሰልጣኙ ፣ የሚለወጠውን መለወጥ ፣ የማይለወጠውን መቀበል የተሻለ ነው ። የሚችሉት ላይ አድምቶ መስራት ፣ የማይችሉትን ለሚችሉት አሳልፎ መስጠት ብልሀት ነው ። ሁሉን ካልቻልኩ ማለት ፣ ምንም አለመቻልን ነው የሚፈጥረው ። ምንም አለመሞከር ደግሞ ስንፍናን ነው የሚፈጥረው ። መሞከር ሁሉን ወደ መቻል ሳይሆን ወደ መቻል ነው የሚወስደን ። አለመሞከር ግን ወደ ምንም አልመቻል ነው የሚወስደን ። ስንሞክር የምንችለውን እናውቃለን ፣ የማንችለውን እንለያለን ። ያኔ ድክመትን ከስንፍና እናጠራለን ።

በሁሉም ነገር ላይ ጎበዝ መሆን አይቻልም ። በምንም ነገር ላይ ጎበዝ አለመሆን ግን እርሱ ስንፍና ነው ። ሰው ያለችሎታ አይፈጠርም ። ችሎታውን ማወቅ ግደታው ነው ። ምንም ችሎታ የሌለው ሰነፍ ነው ። ሁሉም ሰው የሚችለውን አለመቻልም ስንፍና ነው ።የሰው ልጅ ሁሉ መማር ማንበብ መጻፍ እንዲችል ተደርጎ ነው የተፈጠረው ። እኔ ትምህርት ንባብ ፅሁፍ አይሆነኝም ማለት ትልቅ ስንፍና ነው ። እኔ ስእል አይሆነኝም ማለት ይቻላል ። ምክንያቱም ስእል ልዩ ተሰጥኦ ይፈልጋል ። ለአንድነት የሚሰጥ ሳይሆን ለልዩነት የሚቸር ነው ። በደፈናው እኔ ትምህርት አይሆነኝም ማለት ግን ስንፍና ነው ።

   ችሎታ በሁለት ይከፈላል ። ለልዩነት የሚሰጥ እና ለአንድነት የሚሰጥ ችሎታ ነው ። ሁሉም ሰው የሚችለው ነገር የአንድነት ችሎታ ነው ። የተወሰኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ግን ለልዩነት የተሰጠ ነው ። መናገር መቻል ለሁሉ የተሰጠ ነው ። አሳምሮ መናገር ግን በልዩነት የሚሰጥ ነው ። ቀላል ሂሳብን መስራት ሁሉም ሰው ይችለዋል ። ከባድ እና ውስብስብ ሂሳብን መስራት ግን ልዩ የተፈጥሮ ዝንባሌን ይጠይቃል ። መኪናን መንዳት ለሁሉም ሰው ይቻላል ። መኪናን መስራት ግን ሁሉም ሰው አይችለውም ። ስለዚህ የአንድነት ችሎታን ማጣት ስንፍና ነው ። የልዩነት ችሎታን ማጣት ግን ድክመት ነው ወይም ያለቦታ የመገኘት ውጤት ነው ። 

   ‘’ ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል ። ‘’ ይላል ታላቁ መጽሀፍ ። ለጣረ ሁሉ ይቻለዋል ግን አላለም ። ምክንያቱም ከጥረት እምነት ይበልጣል ። ሰው ሁሉን ማድረግ ባይችልም ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችለው ፈጣሪ ፣ በእምነቱ ምንም ማድረግ ይችላል ። ይህ የሚሆነው ስለጣረ ስለለፋ ሳይሆን ስላመነ ነው ። እዚህ ጋር ከሰው ችሎታው በላይ እምነቱ በጣም ወሳኝ ነው ። ለዚህም ነው የእምነት ሰዎች ፣ የጥረት ሰዎች ብዙ የሚደክሙበትን ፣ በቀላሉ የሚያከናውኑት ።

 የሰው ልጅ ደካማ ጎኑ የሚሸፈነው በእምነት ነው ። ስንፍናው ግን በምንም አይሸፈንም ። ባይሆን በቅጣት ይወራረዳል ።

   አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ አለመቻል ፣ ስንፍና ስላልሆነ ብዙ መጨነቅ ተገቢ አይደለም ። ሰው መጨነቅ ያለበት ማድረግ እየቻለ ባለማድረጉ ነው ። ምንም አለመጨነቅ ልክ አይደለም ለስንፍና ይዳርጋል ። በሁሉም ነገር መጨነቅም ልክ አይደለም ፣ ለአእምሮ ህመም ይዳርጋል ። ሰው የሚችለውን ለማድረግ በመጠኑ መጨነቅ አለበት ። የማይችለውን ለማድረግ ግን ማመን እንጅ መጨነቅ የለበትም ። የሚችለውን ለመስራት በመጨነቁ ስንፍናውን ያስወግዳል ። የማይችለውን ለማድረግ ማመኑ ፣ ድክመቱን አምኖ ለመቀበል ይረዳዋል ።

  ‘’ ስንፍና ልዩነትን መፍጠር አለመቻል ነው ። ድክመት ልዩነትን አምኖ መቀበል ነው ። ‘’                            

Monday, June 16, 2025

እይታ | Perception

                                                     

                              ራስን ማጣት

     

       ራስን ማጣት መልከ ብዙ ነው ። ሰው ራሱን የሚያጣበት ምክንያት ብዙ ነው ። ራስን ከሚያሳጡ ነገሮች መሀል አንዱ ስሜታዊነት ነው ። ስሜታዊነት ሰውን ሌላ ሰው የማድረግ አቅም አለው ። ሰው ሲቆጣ ሲያዝን ሲፈራ እና ሲደሰት ፣ ከነበረው ማንነቱ የተለየ ማንነትን ይላበሳል ። ለዚህ ነው ስሜታዊ የሆኑ ሰዎች ፣ ባህሪያቸው በቀላሉ የማይለይ ፣ ስብእናቸው ተለዋዋጭ እየሆነ የሚያስቸግረው ። ስሜታዊ ሰዎች ሲደሰቱ ሌላ ፣ ሲያዝኑ ሌላ ሰው ናቸው ። በቀላሉ ራሳቸውን ያጣሉ ። ሲጀመር ዋስትና ያለው ባህሪ ወይም ስብእና ስለማይኖራቸው ፣ እንደ እስስት በቀላሉ የመለዋወጥ ባህሪ ይኖራቸዋል ። ለእነርሱ ከባዱ ራስን ማጣት ሳይሆን ራስን ማግኘት ነው ። በስሜት ለመገንባት ብርቱ ናቸው ። የዚያኑ ያህል በንዴት ለማፍረስ ጎበዝ ናቸው ። ሆ ብሎ መስራት ወዲያው ደግሞ ሆ ብሎ ማበላሸት መለያ ባህሪያቸው ነው ። ባጭሩ በስሜታዊነት ራስን ማጣት እንጅ ራስን ማግኘት ፣ ወደ ራስ መመለስ አይኖርም ።

ሌላኛው ራስን የሚያሳጣ ነገር ዝለት ነው ። ዝለት ሲባል የመንፈስም የአካልም ነው ። በእርግጥ የአካል ዝለት ፣ ያን ያህል የባህሪ ወይም የስብእና መዛባትን አይፈጥርም ። የመንፈስ ዝለት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፣ የባህሪ መረበሽን ፣ የስሜት መቃወስን ፣ የስብእና መዛባትን ያስከትላል ። ዝለት ቀላሉን ነገር ከባድ ያደርጋል ። ተግባቢ የነበረውን ነጭናጫ ያደርገዋል ። ትእግስተኛ የነበረውን ቁጡ ያደርገዋል ። ትሁት የነበረውን ትእቢተኛ ያደርገዋል ። ብርቱ የነበረውን ደካማ ያደርገዋል ።

 በዝለት ውስጥ ስራ በጥረት እንጅ በጥራት አይሰራም ።በዝለት ውስጥ ለመጣር የተወሰነ አቅም ይኖራል ፣ ለማጣራት ግን በቂ አይሆንም ። ምክንያቱም ዝለት አቅላችንን ያስተናል ፣ ራሳችንንም ያሳጣናል ። ዝለት የስራ መብዛት ውጤት ነው ። ከአቅም በታች መስራት ዘልዛላ ያደርጋል ። ከአቅም በላይ መስራት ደግሞ ለዝለት ይዳርጋል ። ስለዚህ ሰው ራሱን ላለማጣት አቅሙን ማወቅ አለበት ። በአቅሙ ልክ መስራት አለበት ።  

   ራሳቸውን የሚያጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ራሳቸውን የማያውቁ ሰዎች ናቸው ። ራስን ማወቅ የራስን አቅም ስሜት ድክመት ጥንካሬ እና ሀሳብ ወይም አላማ ማወቅ ነው ። እነዚህን የራሱ የሆኑትን ነገር ያላወቀ ሰው ፣ በስራ ቦታ ፣ በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ በቀላሉ ራሱን ያጣል ። ምክንያቱም ችግር ሲገጥመው የሚታገስለት አላማ የለውም ። ድክመቱን አውቆ ነገርን  በማሸሽ ወይም በመሸሽ ፣ ከራሱ አያርቅም ። ራሱን ለማሸነፍም ጠንካራ ጎኑ ምን እንደሆነ መለየት አይችልም ። በመጨረሻም ራሱን በማጣት ብዙ ነገሩን ያጣል ። በእርግጥ ራስን ከማጣት በላይ ከባድ ችግር የለም ። ሰው ያለውን ሁሉ ቢያጣ ችግር የለውም ። ከባድ ችግር የሚፈጠረው ግን ራሱን ያጣ እለት ነው ።       

   ራስን ማጣት የነበረንን መጥፎ ነገር ማጣት ሳይሆን ፣ ያለንን ጥሩ ነገር ማጣት ነው ። ሰው ያለውን መጥፎ ነገር ቢያጣማ መልካም ነው ። ያኔ ራሱን አጣ ሳይሆን ፣ ራሱን አገኘ ነው የሚባለው ። የነበረውን ቁጣ ትቶ ፣ ያልነበረውን ትእግስት ቢላበስ እሰየው ነው ። ትእቢቱን ረስቶ ትህትናን ከያዘ ፣ ይህ መልካም ነው ። ስስትን ትቶ ደግ መሆን ከጀመረ ፣ ያኔ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ፣ ወደ ሰውነቱ ተመለሰ ማለት ነው ። ራስን ማጣት መልካም ነገርን ማጣት ነው ። ትእግስትን ትህትናን እምነትን እውነትን ደግነትን ማጣት ነው ። ሰው እንደ ድሮ  አይደለህም ተለውጠሃል ፣ ወደራስህ ተመለስ የሚባለው ፣ የነበረውን መልካም ነገር ሲያጣ ነው ።

   አንዳንድ ሰው ገንዘብ ሲያገኝ ትህትናውን ያጣል ። በነገራችን ላይ ማግኘት የሚያስከትለው ማጣት በሽታ ነው ። ሰው ራሱን ከሚያጣ ገንዘብን ቢያጣ ይሻለዋል ። ምክንያቱም ገንዘብ ሲያገኝ ራሱን የሚያጣ ከሆነ ፣ ገንዘብ መልሚያው ሳይሆን መጥፊያው ይሆናል ። ማግኘት ማንነትን ሊያጠነክር እንጅ ሊያፈርስ አይገባም ። ሰው በገንዘቡ የተሻለ ነገር ለመስራት ፣ ራሱን ላለማጣት በተጠንቀቅ መጠበቅ ይኖርበታል ። ገንዘብ ራስን ከሚያሳጡ ነገሮች ዋነኛው ነው ።

   ስልጣን ሲያገኙ ጨካኝ የሚሆኑ አሉ ። መራራት እስኪያቅታቸው ድረስ ራሳቸውን የሚያጡ አሉ ። ከስልጣን በፊት ሰው የነበሩ ፣ ስልጣን ሲሰጣቸው ወደ አውሬነት ይቀየራሉ ። ለሰው የሚራሩ ምርጥ የነበሩ ፣ በሰው የሚጨክኑ ምጥ ይሆናሉ ። በስልጣን ምክንያት ራሳቸውን ያጡ ፣ ብዙ የድርጅት የማህበረሰብ የሀይማኖት እና የሀገር መሪዎች አሉ ። የነበራቸውን መልካም ነገር አጥተው ፣ ያልነበራቸውን ክፉ ነገር የታጠቁ ብዙ ናቸው ። በስብእናቸው ይመሩናል ተብለው ተመርጠው ፣ በስልጣን ምክንያት ስብእናቸውን በማጣት ፣በትክክል የመሩን ሳይሆን በትግል የመረሩን ብዙ ናቸው ። በስልጣናችሁ ክቡር ፣ በመሪነታችሁ ምስጉን ለመሆን ፣ ስልጣን ስታገኙ ራሳችሁን ላለማጣት መጠንቀቅ አለባችሁ ። ያልነበራችሁን እውቀትና ልምድ የምታገኙበት እንጅ ፣ የነበራችሁን መልካም ስብእና የምታጡበት መሆን የለበትም ።

   እውቀት ሲያገኙ ራሳቸውን በደምብ ማወቅ ሲገባቸው ፣ በተቃራኒው ራሳቸውን የሚያጡ ብዙ ናቸው ። መሃይምነት ከምሁርነት ይሻላል የሚያስብሉ ፣ እውቀት ሲያገኙ ራሳቸውን ያጡ ምሁራን ብዙ ናቸው ። እውቀት ሰይጣን ያደረጋቸው ብዙ አዋቂዎች አሉ ። ለሰው በእውቀታቸው መድሃኒት ሳይሆን ፣ መርዝ እስከ መስራት የደረሱ ብዙ ናቸው ። መፍትሄ ሳይሆን ችግር የፈበረኩ ብዙ ናቸው ። አዋቂነት አውሬነት የሆነባቸው ተማራማሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ። በእውቀታቸው ዓለምን የጦርነት ማእከል ያደረጉ ፣ የፖለቲካውን አለም የሴራ ማምረቻ እንዲሆን የቀረጹ ፣ ትምህርት ቤቶችን የዝሙት ማስፋፊያ ያደረጉ ብዙ ናቸው ። እውቀት ሰውን ወደ ሰውነት እንጅ ወደ ሰይጣንነት ሊወስደው አይገባም ። ወደ ራሱ ሊመልሰው እንጅ ራሱን ሊያሳጣው አይገባም ። ለዚህ ደግሞ እውቀትን መምረጥ ተገቢ ነው ። ፈጣሪ የፈቀደውን መልካሙን ሁሉ ማወቅ ፣ ክፉውን መተው አስፈላጊ ነው ።

      ‘’ ለማግኘት ራስን ማጣት ልክ አይደለም ። ከክፉ ነገር ራስን መጠበቅ ፣ ማጣት ሳይሆን ራስን ማግኘት ነው ። ‘’    

Friday, June 6, 2025

እይታ | Perception

                                        ራስን ይቅር አለማለት

 

  ራስን ይቅር አለማለት የከባድ ጸጸት ውጤት ነው ። በነገራችን ላይ ለሰው ይቅርታ ከማድረግ በላይ ፣ ለራስ ይቅርታ ማድረግ ከባድ ነው ። ምክንያቱም እዚህ ጋር ጥፋት የራስ ነው ። በደል ማድረስ ህመምን ከባድ ያደርገዋል ። የሰው ልጅ ህሊናውን አሽከር ካላደረገ በስተቀር ፣ ጥፋት በመስራቱ የሚደርስበት ህመም ቀላል እይደለም ። አብዝተው ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ጥፋት ከሰሩ ለራሳቸው ይቅርታ ለማድረግ በጣም ይቸገራሉ ። በተለይ ሰው በእነርሱ ምክንያት ብዙ ከተጎዳ ፣ የሚደርስባቸውን የህሊና ስቃይ መሸከም ይከብዳቸዋል ። ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ለሰው የሚሳሱ ሲበዛ ስስ ፍጥረቶች ናቸው ። ሰው ተቸግሮ እያዩ ማለፍ አይችሉም ። ምናልባት ገንዘብ እያዩ ጥለው ሊያልፉ ይችላሉ ። ምክንያቱም እነርሱ ለሰው እንጅ ለገንዘብ አይሳሱም ። ገንዘብን እያዩ ማለፍ ካልፈለጉም ፣ ለራሳቸው ብለው ሳይሆን መርዳት የሚፈልጉት ሰው ስላለ ይሆናል ።

   ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ሰው እንዳይጎዳባቸው በጣም ጥንቃቄ ያደርጋሉ ። ጥንቃቄያቸው ከፍቅር ይመነጫል ። በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች አሉ ፣ ሰው እንዳይታመም የሚጨነቁት ፣ ለሰውየው ሳስተው ሳይሆን ፣ ስራቸው እንዳይታጎል ወይም የሚያገኙትን እንዳያጡ ነው ። እነዚህ ግን ትላንት ላወቁትም ፣ እድሜ ልክ ለሚያውቁትም ያላቸው ስሜት ተመሳሳይ ነው ።  ለስራቸው ወይም ለጥቅማቸው ሳይሆን ፣በቃ እንዲሁ ለሰው በጣም ይሳሳሉ ። ለእነርሱ ማንም ይጎዳ ፣ ሰው እስከሆነ ድረስ ይጨነቃሉ ። የተቸገረ ሰው ሲያዩ ሀዘናቸው ጥልቅ ነው ።

  በእነርሱ ምክንያት ሰው ችግር ላይ ወድቆ ቢያዩ ፣ ሀዘናቸው እጅግ ከባድ ነው የሚሆነው ። በጸጸት ምክንያት ለራሳቸው ይቅርታ ለማድረግ አቅም ያጣሉ ። ይቅርታ መጠየቅ አይከብዳቸውም ነገር ግን ራሳቸውን ይቅር ለማለት ፣ ከባድ ፈተና ይሆንባቸዋል ። ልባቸው ስስ ስለሆነ ይቅርታ ማድረግ ለእነርሱ በጣም ቀላል ነው ። ሰው ሆኖ ጥፋት የማይሰራ ፣ ስህተት የማይፈጽም የለም ። የእነርሱን ህሊና አንቆ የሚይዘው ግን ፣ ጥፋቱ የሚፈጥረው ጉዳት ነው ። ለዚህ ደግሞ የሰዎችን ጉዳት ለመቀነስ ፣ በቻሉት መጠን ስህተት ላለመስራት ጥረት ያደርጋሉ ። ከሰሩም ይቅርታቸው በቃል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ፣ በተለያየ ነገር ሰውን ለመካስ ይሞክራሉ ። አልያ በቃል ይቅርታ በመጠየቅ ብቻ ህሊናቸው እረፍት አያገኝም ። በጸጸት ምክንያት ራሳቸውን ሊጎዱ ይችላሉ ።

   ለራስ ይቅርታ ማድረግ ሰውነትን መቀበል ድክመትን ማመን ነው ። ይቅርታ ለማድረግ መቸገር ግን ፍጹም ለመሆን መታገል ነው ። ሰው ደግሞ በስራው ፍጹም ሊሆን አይችልም ። ሆን ብሎ ስህተትን መስራት ተንኮል ነው ። ሰውን ለመጉዳት አስበው አቅደው ጥፋት ወይም ስህተት የሚሰሩ አሉ ። ይህ ሰውነት ሳይሆን አውሬነት ነው ። ሰው ሆኖ አለመሳሳት አይቻልም ። ሆን ብሎ ስህተት መስራት ግን ሰው መሆን አይደለም ። ስምንተኛ ክፍል የስፖርት መምህራችን ‘’ Mistake is humanity, again mistake is stupidity ( ስህተት መስራት ሰብዓዊነት ነው ስህተትን መድገም ግን ደደብነት ነው ። ) ‘’ ይል ነበር ። ነገር ግን ማወቅ ያለብን ፣ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ስህተት መስራታችን ፣ ራስን ይቅር ከማለት ሊከለክል አይገባም ።

ሰው ስህተትን የማይደግመው ለራሱ ይቅርታ ማድረግ ሲችል ነው ። አልያ ስህተትን በሌላ ስህተት እየቀየረ ይኖራል ። ጥፋትን በሌላ ጥፋት እየተካ ይቀጥላል ። ለራሱ ይቅርታ ማድረግ ካቃተው ፣ ላለመሳሳት ከመጠን በላይ ይጨነቃል ። ላለመሳሳት ሲጨነቅ የበለጠ ስህተት ይሰራል ። በጸጸት ብዛት ስህተትን ማስቆም አይቻልም ። ጥፋትን መግታት አይታሰብም ። ስህተትን ማመን ፣ ለጥፋት ሀላፊነት መውሰድ ፣ ድክመትን መቀበል ነው ፣ ስህተትንም ጥፋትንም ባለበት የሚያስቆመው ።

   ይቅርታ እረፍት ነው ። መንፈስን የሚያድስ ሀይል ነው ። ያልታደሰ መንፈስ ደካማ ነው ። ስለዚህ ስህተትን ለመደጋገም ቅርብ ነው ። መንፈስ ሲታደስ ብርቱ ይሆናል ። ሰው ውስጡ ሲታደስ ስህተትን ላለመድገም አቅም ያገኛል ። ሰው የሚታደሰው በይቅርታ ስለሆነ ፣ ለራስም ለሌላውም ይቅርታ ማድረግ ወሳኝ ነው ። ሰዎች ልክ እንደተፈጥሮ ሀብት ( Natural resource ) በሁለት ይከፈላሉ ። ታዳሽ እና ታዳሽ ያልሆኑ በመባል ። የይቅርታ ሰዎች ታዳሽ ናቸው ። የበቀል ሰዎች ደግሞ ታዳሽ ያልሆኑ ፍጥረቶች ናቸው ። ታዳሽ የተፈጥሮ ሀብቶች ዘላለማዊ እንደሆኑ ሁሉ ፣ የይቅርታ ሰዎችም ዘላለማዊ ናቸው ። ታዳሽ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ጊዜያዊ ( limited ) ናቸው ። በተመሳሳይ ታዳሽ ያልሆኑ የበቀል ሰዎች ጊዜያዊ ናቸው ። የይቅርታ ሰዎች ህይወትን የሚቀጥሉ ሀይሎች ናቸው ። የበቀል ሰዎች ደግሞ ወይ ህይወትን የሚጨርሱ አልያም ለራሳቸው የሚያልቁ ሀይሎች ናቸው ። ህይወትን የሚቀጥሉ በሰው ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ ። ህይወትን የሚያቃጥሉ ከሰው ልብ በቀላሉ ይሰረዛሉ ። ስለዚህ ህይወትን ለመቀጠል የይቅርታ ሰው እንሁን ።

   ከልብ ለመሆን ለራስ ይቅርታ ማድረግ ተገቢ ነው ። ለመበርታት ለመታደስ ይህ ግድ ነው ። በጸጸት ብዛት መኖር ራስን ማቃጠል ነው ። ዘላለማዊ ሳይሆን ጊዜያዊ መሆን ነው ። ይህ ደግሞ ራስን በራስ መግደል ነው ። ስህተት ሰውኛ መሆኑን አምነን ፣ ለራስ ይቅርታ በማድረግ አዲስ ሰው እንሁን ። ለምድር ታዳሽ ሀይል ፣ ለሰዎችም ለራሳችንም ህይወትን ቀጣይ እንሆን ዘንድ ፣ ለራስም ለሌላም ይቅርታ ማድረግን እንለማመድ ። የቱንም ያህል ስህተት ብንሰራም ፣ ለራስ ይቅርታ የማድረግ ሞራል ልናጣ አይገባም ።

    ‘’ ስህተትን ላለመድገም ለራስ ይቅርታ ማድረግ ቁልፍ ነው ። ‘’            

Saturday, May 31, 2025

እይታ | Perception

                                              ፍትህ

  ፍትህ የስራ ውጤት ነው ። ሰው የስራውን ካላገኘ ፍትህ የለም ማለት ነው ። ፍትህ ካለ ጥሩ የሰራ ይሸለማል ። መጥፎ የሰራ ደግሞ ይቀጣል ። በተቃራኒው ፍትህ ከሌለ ፣ መጥፎ የሰራ አይቀጣም ። ጥሩ የሰራ አይሸለምም ። አለመሸለም ብቻ አይደለም ፣ ጥሩ በመስራቱ ሊቀጣ ይችላል ። ፍትህ ከሌለ የዘሩትን ማጨድ አይቻልም ። መታጨድ እንጅ ማጨድ አይኖርም ። መልካም የሰሩ የዘሩትን ማጨድ ባይችሉም ፣ ክፉዎች ግን ያልዘሩትን ያጭዳሉ ። ያላበሰሉትን ይበላሉ ። ያልሰጡትን ይወስዳሉ ። ያልተንከባከቡትን ፍሬ ይመገባሉ ። ፍትህ በሌለበት ትጋት ከንቱ ነው ። ምክንያቱም ሰርቶ መከበር አይቻልም ። ሰርቆ መከበር ነው የሚቻለው ። ጥሮ ማሳካት እጅግ ከባድ ነው ። አጭበርብሮ ማሳካት ግን ቀላል ነው ። ያለፍትህ ስራ ዋጋው ዝቅ ይላል ። ሴራ ግን ዋጋው ከፍ ይላል ።

ለስራ የሚተጉ ፍትህ ያሰፍናሉ ። ለሴራ የሚተጉ ደግሞ ፍትህ ያዛባሉ ። ለመስራት የሚተጉ ፍትህን ያረጋግጣሉ ። ለመስረቅ የሚተጉ ፍትህን ይረግጣሉ ። መስረቅም መስራትም ትጋት ይፈልጋሉ ። ልዩነቱ መስረቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል ። የደስታ ሰገነት ላይ ያስቀምጣል ። ግን ደግሞ የሀዘን አዘቅት ውስጥ መክተቱ ኣይቀርም ። ስራ በአንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ አያስገኝም ። ደስታውንም በመጠኑ ፣ ገንዘቡንም በልኩ እያሳደገ ነው የሚሄደው ። ሰው በመስረቁ የሰውን ደስታ ይቀማል ። ለዚያ ነው ደስታው ከልክ በላይ የሚሆነው ። የሚገርመው ሀዘኑም ከልክ በላይ መራር ነው ። ምክንያቱም የሚሸከመው ሀዘን የራሱን ብቻ ሳይሆን ፣ የሰውንም ጭምር ነው ።

ሰው በመስራቱ ግን ሀዘኑም ደስታውም በልኩ ነው ። ምክንያቱም የሚቀማው ደስታ የለም ። የሚሸከመውም ተጨማሪ ህዘን የለም ። እርሱ ፍትሐዊ ነው ።

ለመስራት እንጅ ለመስረቅ ፣ ለማስደሰት እንጅ ለማሳዘን ፣ ፍትህን ለማረጋገጥ እንጅ ለማዛባት አትትጉ ። ትጋት ደስ የሚለው ከቅንነት ጋር ነው ። ቅንቅንነት አይመቸውም ። ስኬት የትጋት ውጤት ነው ። ሰው ለፍትህ ከተጋ ፣ ስኬት የሀቀኞች ትሆናለች ። ፍትህን ለማዛባት ከተጋ ግን ፣ ስኬት የአጭበርባሪዎች ትሆናለች ። ፍትህ አለ ማለት የተጉ ስኬትን ይጎናጸፋሉ ፣ የአጭበረበሩ ይቀጣሉ ፣ የማይለፉ ሰነፎች ደግሞ ከሁለቱ ይማራሉ ። ፍትህ ከሌለ ስኬትም ቅጣትም የለም ። ስኬት ከሌለ አርአያ አይኖርም ። ቅጣት ከሌለ መማርያ አይኖርም ። ንቁ ሰው ከአርአያው ይማራል ። ያልነቃው በቅጣት ይማራል ። ፍትህ አለ ማለት በሁለቱም መንገድ መማር አለ ማለት ነው ። ከሌለ ግን መማረር እንጅ መማር አይቻልም ።

ፍትህ ለእውነት መቆም ነው ። በፍትህ ዘንድ ወገንተኝነት አይሰራም ። ጥፋተኛ ዘመድ ስለሆነ ከፍርድ አያመልጥም ። ሌባ ልጅ ስለሆነ ከቅጣት አይድንም ። ወንጀለኛ ወዳጅ ስለሆነ ከእስር አይተርፍም ። ፍትህ ስጋ ብሎ አያዳላም ። ለወዳጅ ብሎ ፍርደ ገምድል አይሆንም ። ለልጅ ብሎ እውነትን አይገፋም ። ለፍትህ መኖር ማለት ለእውነት እየቆሙ ፣ መከራን እየታገሱ መኖር ነው ። እውነት የለም ማለት ፍትህ የለም ማለት ነው ። ለፍትህ የእውነት መኖር ግድ ነው ። እውነት እና ፍትህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ።

ለዚህ ነው ለመርማሪ እውነቱን ማወቅ ከባድ ፈተና የሚሆንበት ። የፍትህ መሰረቱ እውነት ስለሆነ ፣ ፍትህን የሚረግጡ እውነት እንዳትታወቅ ፣ ባለ በሌለ አቅማቸው ይታገላሉ ። ፍትህን ለማስፈን የሚተጉ ፣ እውነቱን ለማግኘት ከባድ ትግል ውስጥ ይገባሉ ። ‘’ እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል ። ‘’ እንዲባል ፣ እውነቱ ግን መታወቁ አይቀርም ። ፍትህን የነበሩት ቢያጡት ፣ የሚመጡት ማግኘታቸው አይቀርም ።

‘’ ለፍትህ እውነት እርቃኑን መሆን አልበት ። ‘’ አለች ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሞፈሪያት ካሚል ። እውነትነት አለው ። ብዙውን ጊዜ እውነት ፣ ወይ ፍቅርን አሊያም ጥላቻን መልበሱ አይቀርም ። ጥላቻን ከሚለብስ ፍቅርን ቢለብስ የተሻለ ነው ። እውነት ጥላቻን ከለበሰ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ። በጥላቻ የሚነገር እውነት ፣ ሰው ውስጥ ሀይለኛ ቁጣን ይቀሰቅሳል ። ፍትህን ለማስፈን ከመጣር ይልቅ ለበቀል ያነሳሳል ። ፍትህ አላማው ማስተማር እና መካስ ነው ። በቀል ክፋትን በክፋት መመለስ ነው ። የፍትህ መጨረሻው ሰላም እና እርቅ ነው ። የበቀል መጨረሻው ግን መጨራረስ ነው ። እውነትን ጥላቻ ማልበስ ፣ ነገርን ወደ በቀል መውሰድ ነው ። ስለዚህ ከቻልን እውነትን ፍቅርን እናልብስ ። ካልሆነ እርቃኑን ይሁን ።

ለሰው ልጅ የሚሻለው ግን ፣ ያለምንም ጥርጥር እውነትን ፍቅርን ማልበስ ነው ። ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ፣ እንደ ሀብት ከትውልድ ትውልድ ፣ ሲሸጋገር የሚመጣን በቀል ማስቆም ይቻላል ። Genetic code ( የዘረ መል ውርስ ) እስኪመስል ፣ በቀልን በደም የሚዋረስ ህብረተሰብ አለ ። በቀል ለትውልድ የሚያወርሱት ሀብት ሳይሆን እርግማን ነው ።

 ምንም ጥቅም የሌለው ርካሽ ተግባር ነው ። የፈሰሰን ውሀ ለማፈስ መታገል ነው ። ይሄ ደግሞ የራስን ውድ አላማ መዘንጋት ነው ። ህልምን ቀብሮ ራእይን አፈር ድሜ ማብላት ነው ። በትላንት ታሪክ ዛሬን ለመኖር መታገል ነው ። ትላንት ለዛሬ ግብዓት እንጅ ግብ አይደለም ። በቀለኞች ግን ለዛሬ ወይም ለነገ የሚሆን ግብ የላቸውም ። የእነርሱ ግባቸውም ህልማቸውም ትላንት ነው ። የወላጅ ክፉ ሀሳብ ማስፈጸም ነው ራእያቸው ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እውነት ጥላቻን ሲለብስ ነው ። እውነት ፍቅርን ሲለብስ ግን በተቃራኒ ነው የሚሆነው ። ወደ ይቅርታ ይመራል ። ሰው የወላጁን ሳይሆን የራሱን ህልም እንዲኖር ይረደዋል ። የራሱ ግብ እንዲኖረው አስተሳሰቡን ይቀይረዋል ። ዛሬና ነገን በአግባቡ እንዲጠቀም ያግዘዋል ። በቀለኛ ሳይሆን ፍትሀዊ እንዲሆን ያስገድደዋል ። ከምንም በላይ ጎጅውን ጥላቻ ሳይሆን ፣ ጠቃሚውን ፍቅር እንዲያስቀድም ያደርገዋል ። ፍትህ የሚረጋገጠው በፍቅር እንጅ በጥላቻ አይደለም ። በቀል ፍትህ አይሆንም ። ፍትህ ይቅርታ ማድረግ ማስተማር መቅጣት እና መካስ ነው ።  

 

 ‘’ እውነትን ፍቅር አልብሱት ፣ ያኔ ፍትህ ይረጋገጣል ። ‘’     

Thursday, May 29, 2025

እይታ | Perception

                                       ከራስ መጣላት

 ከራስ መጣላት የራስን እውነት አለመቀበል ነው ። የገዛ ስሜታችንን መካድ ነው ። በጠቅላላው ራስን አለመቀበል ነው ። የሰውን ልጅ ከራሱ እንዲጣላ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው ። በሰዎች ዘንድ ክብርን ለማግኘት ሲሉ ከራሳቸው የሚጣሉ አሉ ። እነዚህ ሌሎችን ለማሳመን ወሬ በመፍጠር የሚተካከላቸው የለም ። በወሬ ጤፍ ይቆላሉ ጉም ይዘግናሉ ። ያለን ነገር ሳይሆን ፣ የሌለን ነገር መፍጠር ይችላሉ ። ተውሰው መልበስ ይችላሉ ። ሰርተው መልበስ ግን አይችሉም ። ብራንድ ጫማ ማድረግ ይችላሉ ፣ መግዛት ግን አይችሉም ። የሰው ሁሉ የእነርሱ ነው ። እነርሱ ግን የሚረባ አንድም ነገር የላቸውም ። የሚለብሱት የሚጫሙት የሚዘንጡት ሁሉ በሰው ነው ። በቃ እነርሱ ምንም የሌላቸው ባዶ ናቸው ። ሰው ባዶነቱን አምኖ መቀበል ካቃተው ፣ ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም ። ቦዶነቱን አምኖ መቀበል የቻለ ግን ፣ በአዲስ ነገር ባዶነቱን መሙላት ይችላል ። ምክንያቱም ራሱን መቀበል የቻለ ትሁት ነውና ።

ራሱን የተቀበለ ሰው ለመማር ለመስራት ለማወቅ ዝግጁ ነው ። ይህ ደግሞ ባዶ ከመሆን ይጠብቀዋል ። ራስን መቀበል መልካም ነገርን ከሌሎች ለመቀበል ልብን ክፍት ያደርጋል ። መቀበል ከሌለ መለወጥ አይኖርም ። አቀባበላችን ግን ለውጣችንን ይወስነዋል ። የምንቀበለው ጥሩ ነገር ከሆነ ፣ ለውጣችን አዎንታዊ ይሆናል ። የምንቀበለው ግን መጥፎ ከሆነ ፣ ለውጣችን አሉታዊ ይሆናል ። ከራሱ የተጣላ ሰው ሀሳብ መቀበል አይችልም ። ቢቀበልም ጥሩውን ሳይሆን መጥፎውን ነው ። ስጦታ መቀበል እና መዋስ ወይም መበደር ግን ይችልበታል ።

በሰው ዘንድ ለመከበር ብሎ ከራሱ የተጣላ ፣ ትልቁ ችሎታው መዋስ ወይም መበደር ነው ። ምክንያቱም ከራሱ የተጣላ ሰው ይሉኝታ ቢስ ነው ። መስራት ያሳፍረዋል ግን መዋስ ያኮራዋል ። ተናንሶ ከመስራት ይልቅ ፣ በሰው አንሶ ላለመታየት የሚያደርገው ጥረት እጅግ ይገርማል ። ስለዚህ ሰው ለመለወጥ ራሱን መቀበል ባዶነቱን ማመን አለበት ። መዋሸት ማቆም አለበት ። ውሸት የራስን ፍሬ የሚቀብር ክፉ አረም ነው ። አረም ውሸቱን ካልነቀለ ፣ ሰው አለሙን መመልከት አይችልም ። በእጁ ያለውን ወርቅ ማስተዋል አይችልም ። በእጁ የያዘው ተራ ፣ በሌላ ሰው እጅ ያለው ተራራ መስሎ ይታየዋል ። ለመከበር ብላችሁ ከራሳችሁ አትጣሉ ። እውነተኛ ክብርን ለማግኘት ከፈለጋችሁ ፣ ከራሳችሁ ታረቁ ማንነታችሁን ተቀበሉ ።

ሌላው የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ከወዳጅ መቀያየም ነው ። በተለይ የሚያፈቅሩት ሰው ሲያስቀይም በጣም ከባድ ነው ። የተበደለው/ችው ግለሰብ የገዛ የራሱን ስሜት ይከዳል ። ከልብ የሚወዱትን ወይም የሚያፈቅሩትን ሰው ፣ ልባቸው እየፈለገ እነርሱ ግን በአፋቸው አልወደውም ወይም አልወዳትም ይላሉ ። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ እንዳላቸው ለማሳወቅ ፣ አሁንስ አይኑን አያሳየኝ በማለት ይምላሉ ። አያሳየኝ ብለው አፋቸውን ሞልተው ይምላሉ ፣ ነገር ግን በደለ የተባለው ፍቅረኛ ወይም ግለሰብ ሲመጣ ልባቸውን በፍቅር ይሞላሉ ። ያንን ሰው እየናፈቁ መቼም አይናፍቀኝም ይላሉ ። እውነቱ ግን ‘’ ማሽላ በውስጥ እያረረች ከላይ ትስቃለች ‘’ እንደሚባለው ፣ አፋቸው ልባቸውን ይከዳል እንጅ ስር የሰደደ ናፍቆት በውስጣቸው አለ ። እነዚህ ሰዎች ሰው ፊት እየሳቁ ፣ ቤት ገብተው እርር ብለው የሚያለቅሱ ፣ አሳዛኝ ፍጡራን ናቸው ። በፍቅር ምክንያት ከራስ መጣላት በሽታ ነው ።

 ስሜትን አፍኖ መያዝ ፣ ጠንካራ መስሎ ለመታየት ከራስ ጋር መታገል ፣ ላለመሸነፍ በውጥረት ውሎ በጭንቀት ማደር ። ይሄ ሁሉ እየወደዱ መጥላት የሚያመጣው መዘዝ ነው ። ከራስ መጣላት የሚፈጥረው ዱብዳ ነው ። ስለዚህ እየወደዱ ከመጥላት በይቅርታ ሰላም መፍጠር ። በእብሪት አልሸነፍ ባይ ሆኖ ከራስ ከመጣላት ፣ በትህትና እርቅ ማውረድ የተሻለ ነው ። ያኔ ከራስም ከሰውም ሰላም መሆን ይቻላል ።

ከራሳቸው ከሚጣሉ ሰዎች መሀል ፣ ችግር ከራሳቸው የሚያጣላቸው ሰዎች እጅግ ያሳዝናሉ ። እነዚህ ሰዎች ወደው ሳይሆን ተገደው ነው ከራሳቸው የሚጣሉት ። ለመኖር ሲሉ ያላመኑበትን ነገር ያደርጋሉ ። መስጠት እየፈለጉ ይከለክላሉ ። ማዳን እየፈለጉ ይገድላሉ ። መውደድ እየፈለጉ ይጠላሉ ። መቅረብ እየፈለጉ ይርቃሉ ። ማግኘት እየፈለጉ ያጣሉ ። መናገር እየፈለጉ ዝም ይላሉ ። ማልቀስ እየፈለጉ ይስቃሉ ። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ፣ በክፉዎች መሀል የሚኖሩ ሩሩ ናቸው ። ጨካኝ ሌባ እንዳለ ሁሉ ሩሩ ሌባ አለ ። ክፉ ባለስልጣን እንዳለ ሁሉ ሩሩ ባለስልጣንም አለ ። አስቸጋሪ ሰራተኛ እንዳለ ሁሉ መልካም ሰራተኛ አለ ። ችግሩ ያ አይደለም ። ክፉው ከመልካሙ ሲበዛ ነው ችግር የሚፈጠረው ። መልካሞች ከክፉዎች ከበዙ ፣ ችግር ይቀረፋል እንጅ አይፈጠርም ። ከራስ መታረቅ እንጅ ከራስ መጣላት አይኖርም ። ክፎዎች ሲበዙ ግን ከራስ መጣላት ይኖራል ።

 ክፉ ከመልካም ይልቅ ጉልበት ሲኖረው ፣ መልካም ሰዎች አቅም በማጣት ከራሳቸው ይጣላሉ ። ግፍ ሲፈጸም መናገር እየቻሉ ዝም ይላሉ ። ሰው ሲገደል ማዳን እየቻሉ እያለቀሱ ይቀብራሉ ።

ደሀ ሲበደል መድረስ እየቻሉ ይሸሻሉ ። በክፉዎች ፊት አብረው ስቀው ፣ ቤት ገብተው ግን እርር ብለው ያለቅሳሉ ። እድሜ ልክ የህሊና እረፍት አጥተው ይኖራሉ ። ሆን ብሎ ከራስ መጣላት እና ተገዶ ከራስ መጣላት ይለያያል ። ሆን ብለው ከራሳቸው የተጣሉ ፣ አምነው ስለሆነ ጫናው ለእነርሱ ቀላል ነው ። ተገደው ከሆነ ግን ስለማያምኑበት ጫናው እጅግ ከባድ ነው ። በክፉዎች መሀል ቅን ሆኖ መገኘት ከባድ ነው ። በመልካሞች መሀል ቅንቅን ሆኖ መገኘትም ከባድ ነው ። ህይወት ከመልካሞች ጋር ደስ ትላለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት የለም ።  ከክፉዎች ጋር ግን ትመራለች ። ምክንያቱም ከራስ መጣላት ሁሌም አለ ። የሰውን ልጅ ከራሱ የሚያጣላው ፣ አንደኛው እና ዋነኛው ክፋት ነው ።

 

‘’ ከራስ መጣላት ራስን መካድ ነው ። ራስን መካድ ደግሞ አርቴፊሻል ህይወት መምራት ነው ። ‘’                        

Tuesday, May 27, 2025

እይታ | Perception

                                   እምነት ወይስ እውነት

   ያለ እምነትም ያለ እውነትም መኖር ከባድ ነው ። እውነት ለነጻነት ፣ እምነት ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው ። እምነት በእውነት ላይ ሲመሰረት ፣ ሰው በህይወቱ ሙሉነት ይሰመዋል ። እምነት በጥቅም ላይ ከተመሰረተ ግን ሰው በህይወቱ የሙሉነት ስሜት ይጎድለዋል ። በውሸት ማመን እርሱ የቁም ሬሳ መሆን ነው ። በውሸት ማስመሰል እንጅ መሆን አይቻልም ። ማስመሰል እውነተኛ ደስታን ሊሰጥ አይችልም ። መሆን ነው እውነተኛ ደስታን የሚፈጥረው ። እውነተኛ ደስታ ከእውነት እንጅ ከውሸት በፍጹም ሊገኝ አይችልም ። ብዙዎች ደስታን በውሸት ለማጣጣም ይሞክራሉ ። ነገር ግን እውነታው ደስታ ምን እንደሆነ በቅጡ አይረዱትም ። ምክንያቱም ውሸት የሚፈጥረው ደስታ ርካሽ እና ጊዜያዊ ነው ። እውነት የሚፈጥረው ደስታ ግን ውድ እና ዘላለማዊ ነው ።

  ውሸት እና እምነት ህይወትን እርካታ ቢስ ያደርጋሉ ። እውነት እና እምነት ግን የህሊና እርካታን ይለግሳሉ ። ሰው በውሸት ሲኖር ፣ ደስታን በራሱ መፍጠር አይችልም ። ደስታን ከሌሎች ለማግኘት ይለፋል ይደክማል ፣ ይወጣል ይወርዳል ። ደስታን ከሌሎች ማግኘት ከባድ ነው ። ከራስ ማግኘት ግን ቀላል ነው ። ደስታን ከራሱ የሚያገኝ ፣ በራሱ ደስታን መፍጠር የሚችል ነው ። እንደዚህ አይነት ሰው ደግሞ ሰውን ለማስደሰት ብሎ አይሰራም ፣ ነገር ግን ሰውን የሚያስደስት ስራ መስራት ይችላል ። ደስታን መፍጠርም መጋራትም ማጋራትም ይችላል ። ምክንያቱም ስለእውነት በእውነት ነው የሚኖረው ።

  እምነት በማስመሰል ወይም በውሸት ላይ ሲመሰረት ፣ እውነትን አይፈታተንም ።

ሰው ለብዙ ዓመት አዝሎ የኖረው እምነት ፣ ውሸት እንደሆነ ያወቀ እለት ፣ ያንን እምነት ለመተው ብዙ አይከብደውም ። ምክንያቱም ውሸት እውነትን አይበልጥም ። በውሸት የተፈጠረ እምነት ፣ በእውነት ፊት አቅም የለውም ።

     ለፍቅር እውነትን መደበቅ ግን እውነትን የሚፈታተን እምነትን ይፈጥራል ። ፍቅር የሚፈጥረው እምነት በጣም ጠንካራ ነው ። ሰው ካጣው እውነት በላይ ያገኘው ፍቅር ሲበልጥበት ፣ እውነትን አምኖ ለመቀበል ይቸገራል ። ይህንን እውነት ከሚያውቅ ፣ ባያውቅ ምርጫው ይሆናል ። ሰዎች አንዳንዴ በጣም ለሚወዳቸው ሰዎች ስለፍቅር ሲሉ ፣ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው አብረው ይኖራሉ ። እነርሱን ላለማጣት ፈርተው እውነቱን ሳይናገሩ ይዘው ይቆያሉ ። በእርግጥ  ለጥቅም ሲሉ እውነትን የሚደብቁ ክፉዎች አሉ ። እነዚህ ግን እንደ እነርሱ አይደሉም ፣ ጥቅምን ላለማጣት ሳይሆን ሰውን ላለማጣት ሲሉ ነው ፣ እውነትን የሚደብቁት ። ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር ፣ በወላጅ እና በልጅ መሀል ሲከሰት ይስተዋላል ። የስጋ ዝምድና የሌላቸው ወይም ( Biological ) ያልሆኑ ወላጆች ፣ የአብራካቸው ክፋይ ( Biological )  ያልሆነ ልጅ ያሳድጋሉ ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች እውነቱን ከመናገር ይልቅ ፣ እውነቱን መደበቅ ይመርጣሉ ። ግን በሚገርም የወላጅነት ፍቅር ያሳድጋሉ ። ይህ ፍቅር በልጅ ውስጥ ጠንካራ እምነትን ይፈጥራል ። ይህ እምነት በውሸት ብቻ እንደተፈጠረው እምነት ደካማ አይደለም ። ፍቅር የፈጥረው ሀይለኛ እምነት ነው ። ለእውነት በቀላሉ የማይረታ ብርቱ እምነት ነው ።

     ለሰው ልጅ ፍቅር የፈጠረው እምነት ፣ ከተደበቀበት እውነት ይበልጥበታል ።  

ምክንያቱም በውሸት ቢኖርም ያገኘው ፍቅር የእውነት ነው ። ያጣው እውነት ካገኘው ፍቅር አይበልጥበትም ። ለዚህም ነው ‘’ ፍቅርን ያልሰነቀ እውነት የሞተ ነው ። ‘’ የሚባለው ። ሰው አንዳንዴ እውነትን ከማጣቱ በላይ ፣ እውነትን ማወቁ ይጎዳዋል ። የሚጎዳን እውነት ማወቅ ህይወትን ያናጋል ። የሚጠቅም እውነትን ማወቅ ግን ህይወትን ያስተካክላል ። ስለዚህ ሁሉን እውነት ማወቅ አይጠቅምም ። የነበረንን ጥሩ ነገር የሚያሳጣ እውነት ባይታወቅ ይሻላል ። ያልነበረንን ጥሩ ነገር የሚያመጣ እውነት ግን ሊታወቅ ግድ ነው ። ፍቅርን የሚያሳጣ እውነት ባለበት ተደብቆ ቢቀር ይሻላል ። ፍቅርን የሚጨምር እምነት ግን ፣ ካለበት ተፈትሾ ቢገኝ መልካም ነው ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ እውነት መታወቁ አይጥቅምም ። አብሮነትን ፣ መተሳሰብን ፣ ሰላምን የሚፈጥር እና የሚያጠነክር እውነት ተቆፍሮም ቢሆን መገኘት አለበት ። ልክ እንደ ክርስቶስ መስቀል ሱባኤ ሊያዝለት ይገባል ። በግራ በኩል እንደተሰቀለው ወንበዴ መስቀል ፣ ተገኘም አልተገኘም ፍቅርን ሰላምን መተሳሰብን የሚያሳጣ እውነት አያስፈልግም ።

 እውነት ነጻነት ነው ። ግን ሁሉም እውነት ነጻነትን አይለግስም ። ነጻነትን የሚያሳጣ እውነት አለ ። ጤናን የሚያቃውስ እውነት አለ ። ይህንን እውነት መተው የተሻለ ነው ። የሚያበራ እውነት እንጅ የሚያጨልም እውነት መታወቁ አስፈላጊ አይደለም ። ቢታወቅ የሚጎዳ እውነት አስተሳሰብን ይቀይራል ፣ በአዎንታ ሳይሆን በአሉታ ። እምነትን ይበርዛል ። ቢታወቅ መጥቀምም መጉዳትም የማይችል እውነት አለ ። ይህ እውነት ቢታወቅ የሚጨምረው ነገር የለም ። ባይታወቅም የሚቀንሰው ነገር የለም ። ኖረም አልኖረም ዋጋ ቢስ ነው ። ለዚህ እውነት ትኩረት መስጠት ጅልነት ነው ።

  ቢታወቅ የሚጠቅም እውነት ግን ህይወትን ቀያሪ ነው ፣ በአሉታ ሳይሆን በአዎንታ ። ለምሳሌ ፈጣሪን ፣ ሀይማኖትን ፣ ሳይንስን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ የሚጠቅሙ ማህበራዊ እሴቶችን ፣ ደጋግ ሰዎችን ማወቅ ፣ ህይወትን በመልካም መንገድ ይለውጣል ። ከዚህም በተጨማሪ የኔ የምትሉትን ሰው ማወቅ እፎይታን ይሰጣል ። ቤተሰብን ፣ ዘመድን ፣ ወዳጅን ማወቅ ያስደስታል ። እውነት ሀዘንም ደስታም ነው ። ከሚያሳዝን እውነት የሚያስደስት እውነት ይሻላል ። የሚያስደስት እውነት ውስጡ ፍቅር አለ ። ስለዚህ ከሚያሳዝን እውነት ፣ ያለ እውነት በፍቅር የተፈጠረ እምነት ይበልጣል ። የሚያስደስት እውነት ግን ፍቅርን የያዘ ስለሆነ ፣ እርሱ የሚፈጥረው እምነት ፣ ከሁሉም አይነት እምነት ይበልጣል ። ምክንያቱም እምነት ሁሉ በእርሱ መንገድ ነው መቀረጽ ያለበት ።  ጠቃሚ እውነትን ከፍቅር ጋር በመያዝ ። 

   ‘’ እምነት ከሚጎዳ እውነት ይበልጣል ። ከሚጠቅም እውነት ግን ያንሳል ። ‘’                              

Saturday, May 24, 2025

እይታ | Perception

                                            ክብር

    ‘’ ለአንዳንዱ ክብሩ የእሱነቱ መገለጫ ነው ። ለአንዳንዱ ደግሞ ክብሩ ሰውነቱ ነው ። ‘’ አለች ሰላም ተስፋዬ በማርትሬዛ ፊልም ላይ ። ይህን የተናገረችው በልብስ ምክንያት ከባድ ወቀሳ ደርሶባት ነው ። በነገራችን ላይ ልብስ የሰው ልጅ የማንነቱ መገለጫ እንጅ ማንነቱ ግን አይደለም ። ሰውነቱን ከፍም ዝቅም አያደርግም ። ቆሻሻ የለበሰ የአእምሮ ህመምተኛ ሰው ከመባል የሚከለክለው የለም ። ምናልባት ሰው ከሚለው መጠሪያ በፊት ፣ እብድ የሚል ተቀጽላ ከመጨመሩ በስተቀር ። ተቀጽላ ደግሞ ዋናውን የሰውን ማንነት ወይም ሰውነትን የመፋቅ አቅም የለውም ። ቅጽል ወይ ያኮስሳል አልያም ያገናል ። ሰውን ቀይሮ እንስሳ ወይም ግኡዝ ፍጥረት ሊያደርግ አይችልም ። ሰው ንጹህም ለበሰ ቆሻሻ ያው ሰው ነው ።

   ሰውን ከቆሻሻ ልብስ በላይ ክብሩን የሚያሳጣው ቆሻሻ አስተሳሰቡ ነው ። ሰው በንጹህ ልብስ ቆሻሻ ማንነቱን ለመደበቅ ከሚሞክር ፣ በንጹህ አስተሳሰብ ቆሻሻ ማንነቱን ቢያጸዳ መልካም ነው ። ገላን አጥቦ ማጽዳት ቀላል ነው ። አስተሳሰብን አጥቦ ማጽዳት ግን በጣም ከባድ ነው ። ከመነቸከ አስተሳሰብ የመነቸከ ልብስ ይሻላል ። የመነቸከን ልብስ አጥበነው ካቃተን አውጥተነው እንጥላለን ። የመነቸከን አስተሳሰብ ግን አጥበን ለማጽዳትም ፣ አውጥተን ለመጣልም በጣም አስቸጋሪ ነው ። ስለዚህ ሰው በልብሱ ከሚከበር በአስተሳሰቡ ቢከበር የተሻለ ነው ። ልብስ የሚያስከብረው በሩቁ ነው ። በርቀት በልብሱ ያከበሩትን ሲቀርቡት በአስተሳሰቡ ይንቁታል ። በልብስ የበለጸገ በስብእና የረከሰ ማንነት ክብሩ ጊዜያዊ ነው ። ዘላቂ ክብር ያለው በመልካም አስተሳሰብ የሚገነባ ውብ ስብእና ውስጥ ነው ። ልብስ ሳይሆን በዋናነት ልብ ነው ወሳኙ ።

   በቆሻሻ ልብ ላይ ጸዳል ልብስ መልበስ ፣ በአሮጌ አቁማዳ አዲሱን ወይን ማኖር ነው ። ሁለቱ ደግሞ አይስማሙም ። ወይ ወይኑ ይበላሻል አልያም አቁማዳው ይቀረደዳል ። ስለዚህ የሚሻለው አዲሱን ወይን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ነው ። ሰውነትን ባከበረ ማንነት ላይ ንጹህ ልብስ ማኖር ነው ፣ ለሰው ልጅ ዘላቂ ክብር የሚሆነው ። እውነተኛ ክብር ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ነው የሚመነጨው ። በሚታይ ነገር ለመከበር መሞከር ሞኝነት ነው ። ከሚታይ ነገር ይልቅ የማይታይ ነገር ከፍ ያለ ዋጋ አለው ። ለዚህም ነው ከሚታየው ልብስ በላይ ፣ የማይታየው ልብ የሚያስከብረው ። ሰው ለመታየት ሳይሆን ሆኖ ለማሳየት ነው መኖር ያለበት ። ለመታየት መልበስ በቂ ነው ። ለማሳየት ግን ከመልበስ ባሻገር ፣ መስራት ወይም መኖር ግድ ይላል ። የሰው ልጅ እውነተኛ ማንነት ያለው ደግሞ ፣ በመልበስ ውስጥ ሳይሆን በመኖር ውስጥ ወይም በመስራት ውስጥ ነው ። በልብስ አምሮ የሚታይ ፣ ምናልባት እላዩ የሚያምር ውስጡ የሚያማርር ፍጥረት ሊሆን ይችላል ። እላዩ ስላማረ ከሰውነት ከፍ አይልም ። አማራሪ በመሆኑ ግን ከሰውነቱ ዝቅ ባይልም ፣ በማንነቱ ላይ ሌላ ተቀጽላ ይለጠፋል ፣ አስመሳይ የሚል መገለጫ ።

   ጥሩ መልበስ ልክ አይደለም ወይም አያስፈልግም ማለት አይደለም ። ጥሩ መልበስ ራስን መንከባከብ ክብርንም መጠበቅ ነው ። ነገር ግን ሰው ራሱን መጠበቅ ያለበት ፣ በሰው ለመታየት ብቻ  መሆን የለበትም ። ለራሱ ለጤናውም ጭምር መሆን አለበት ።

 በሰው ለመታየት ሲል ጤናውን ምቾቱን ማጣት የለበትም ። ኢኮኖሚው እስኪቃወስ ፣ ኑሮው ኢስኪናጋ አምሮ ለመታየት ብዙ መድከም አይኖርበትም ። ማማር ከጤና አይበልጥም ። መዘነጥ ከአእምሮ ሰላም አይልቅም ። ዋናውን በማጣት የሚገኝ ትርፍ ዋጋ ቢስ ነው ። ዋናውን በመያዝ የሚገኝ ትርፍ ግን ጠቃሚ ነው ። መኖር ከሌለ መቀናጣት አይቻልም ። ቅንጦት ኖረም አልኖረም መኖር ይቻላል ። ለመቀናጣት መኖር ግድ ነው ። ለመኖር ግን መቀናጣት ግዴታ አይደለም ። ሰው ኖረ የሚባለው ስለተቀናጣ ሳይሆን ፣ ጤናውን እና የአእምሮ ሰላሙን መጥበቅ በመቻሉ ነው ። ለአስፈላጊው ነገር ሲባል ፣ ቅንጡውን ነገር መተው እንጅ ፣ ለቅንጡ ነገር ሲባል አስፈላጊውን ነገር ማጣት ተገቢ አይደለም ። በእርግጥ ልብስ አስፈላጊ ነገር ነው ። ነገር ግን የልብስ መሰረታዊ ጥቅሙ ፣ ገላን መሸፈን እንጅ ገላን ማሳየት አይደለም ። ገላን ለማሳየት ሲሉ ብዙዎች ጤናቸውን እስከማጣት ደርሰዋልና ። የሚመቸንን መልበስ አስፈላጊ ነው ። የማይመቸንን መልበስ ግን በሽታ ነው ። የምንችለውን መልበስ ተገቢ ነው ። የማንችለውን መልበስ ግን ቅንጦት ነው ። የሚያምርብን ልብስ ለጤና ጥሩ ነው ። የማያምርብንን ግን መልበስ ለጤና ጠንቅ ነው ። ልብስ ገላን ሲሸፍን ክብርም ውበትም ነው ። ግን ለመከበር አጉል መልበስ ክብር ያሳጣል ።

 ሰውን እኩል የሚያደርግ ልብስ ደንብም ነው ክብርም ነው ። የተማሪዎች ዩኒፎርም ፣ የሰራተኞች የስራ ልብስ ፣ የወታደሮች እና የፖሊሶች የደንብ ልብስ የሚያስከብር እናም ክብር የሚገባው ሊዩ ልብስ ነው ። እነዚህን ልብሶች መልበስ መታደል ነው ።

ነገር ግን በልብስ እከብራለው ባይ ለነዚህ ልብሶች ክብር የለውም ። ምክንያቱም ከሰው እለያለው ባይ ነው ። እሱን ከሰው የሚለየው እንጅ አንድ የሚያደርገው ነገር አይመቸውም ። በእርግጥ ሰው ከሰው ይለያያል ። በሌላ በኩል ከብዙሃኑ አንድ የሚያደርገው ፣ የሚጋራው ነገር ብዙ ነው ። ሁሉም ሰው ሊኖረው በሚችለው ነገር ልዩ ልሁን ማለት አያስከብርም ። ከሌላው በሚለየን ነገር ላይ መስራት ግን ያስከብራል ። ሰውን ከሰው የሚለየው ደግሞ ስራው እንጅ ልብሱ አይደለም ። ፈረንጀቹ ‘’ ( First impression is last impression ) ’’ ይላሉ ። የፈርስት ኢምፕረሽን አንዱ መለኪያ አለባበስ ነው ። እዚህ ጋር አለባበስ ለስራ ያለንን ክብር ነው የሚያሳየው ። ስራን ለማክበር መልበስ ያስከብራል ። ከሰው ሁሉ ለመለየት ወይም ለሰው ብሎ መልበስ ግን አያስከብርም ።

        ‘’ ክብር ልብስ ውስጥ ሳይሆን ልብ ውስጥ ነው የሚገኘው ። ‘’                               

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...