ራስን ይቅር አለማለት
ራስን ይቅር አለማለት የከባድ ጸጸት ውጤት ነው ። በነገራችን ላይ ለሰው
ይቅርታ ከማድረግ በላይ ፣ ለራስ ይቅርታ ማድረግ ከባድ ነው ። ምክንያቱም እዚህ ጋር ጥፋት የራስ ነው ። በደል ማድረስ ህመምን
ከባድ ያደርገዋል ። የሰው ልጅ ህሊናውን አሽከር ካላደረገ በስተቀር ፣ ጥፋት በመስራቱ የሚደርስበት ህመም ቀላል እይደለም ። አብዝተው
ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ጥፋት ከሰሩ ለራሳቸው ይቅርታ ለማድረግ በጣም ይቸገራሉ ። በተለይ ሰው በእነርሱ ምክንያት ብዙ ከተጎዳ
፣ የሚደርስባቸውን የህሊና ስቃይ መሸከም ይከብዳቸዋል ። ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ለሰው የሚሳሱ ሲበዛ ስስ ፍጥረቶች ናቸው ።
ሰው ተቸግሮ እያዩ ማለፍ አይችሉም ። ምናልባት ገንዘብ እያዩ ጥለው ሊያልፉ ይችላሉ ። ምክንያቱም እነርሱ ለሰው እንጅ ለገንዘብ
አይሳሱም ። ገንዘብን እያዩ ማለፍ ካልፈለጉም ፣ ለራሳቸው ብለው ሳይሆን መርዳት የሚፈልጉት ሰው ስላለ ይሆናል ።
ለሰው የሚጨነቁ ሰዎች ፣ ሰው እንዳይጎዳባቸው በጣም ጥንቃቄ ያደርጋሉ ።
ጥንቃቄያቸው ከፍቅር ይመነጫል ። በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች አሉ ፣ ሰው እንዳይታመም የሚጨነቁት ፣ ለሰውየው ሳስተው ሳይሆን ፣
ስራቸው እንዳይታጎል ወይም የሚያገኙትን እንዳያጡ ነው ። እነዚህ ግን ትላንት ላወቁትም ፣ እድሜ ልክ ለሚያውቁትም ያላቸው ስሜት
ተመሳሳይ ነው ። ለስራቸው ወይም ለጥቅማቸው ሳይሆን ፣በቃ እንዲሁ
ለሰው በጣም ይሳሳሉ ። ለእነርሱ ማንም ይጎዳ ፣ ሰው እስከሆነ ድረስ ይጨነቃሉ ። የተቸገረ ሰው ሲያዩ ሀዘናቸው ጥልቅ ነው ።
በእነርሱ ምክንያት ሰው ችግር ላይ ወድቆ
ቢያዩ ፣ ሀዘናቸው እጅግ ከባድ ነው የሚሆነው ። በጸጸት ምክንያት ለራሳቸው ይቅርታ ለማድረግ አቅም ያጣሉ ። ይቅርታ መጠየቅ አይከብዳቸውም
ነገር ግን ራሳቸውን ይቅር ለማለት ፣ ከባድ ፈተና ይሆንባቸዋል ። ልባቸው ስስ ስለሆነ ይቅርታ ማድረግ ለእነርሱ በጣም ቀላል ነው
። ሰው ሆኖ ጥፋት የማይሰራ ፣ ስህተት የማይፈጽም የለም ። የእነርሱን ህሊና አንቆ የሚይዘው ግን ፣ ጥፋቱ የሚፈጥረው ጉዳት ነው
። ለዚህ ደግሞ የሰዎችን ጉዳት ለመቀነስ ፣ በቻሉት መጠን ስህተት ላለመስራት ጥረት ያደርጋሉ ። ከሰሩም ይቅርታቸው በቃል ብቻ
የሚወሰን ሳይሆን ፣ በተለያየ ነገር ሰውን ለመካስ ይሞክራሉ ። አልያ በቃል ይቅርታ በመጠየቅ ብቻ ህሊናቸው እረፍት አያገኝም ።
በጸጸት ምክንያት ራሳቸውን ሊጎዱ ይችላሉ ።
ለራስ ይቅርታ
ማድረግ ሰውነትን መቀበል ድክመትን ማመን ነው ። ይቅርታ ለማድረግ መቸገር ግን ፍጹም ለመሆን መታገል ነው ። ሰው ደግሞ በስራው
ፍጹም ሊሆን አይችልም ። ሆን ብሎ ስህተትን መስራት ተንኮል ነው ። ሰውን ለመጉዳት አስበው አቅደው ጥፋት ወይም ስህተት የሚሰሩ
አሉ ። ይህ ሰውነት ሳይሆን አውሬነት ነው ። ሰው ሆኖ አለመሳሳት አይቻልም ። ሆን ብሎ ስህተት መስራት ግን ሰው መሆን አይደለም
። ስምንተኛ ክፍል የስፖርት መምህራችን ‘’ Mistake is humanity, again mistake is stupidity
( ስህተት መስራት ሰብዓዊነት ነው ፣ ስህተትን መድገም ግን ደደብነት ነው ። ) ‘’ ይል ነበር ። ነገር ግን ማወቅ ያለብን ፣
አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ስህተት መስራታችን ፣ ራስን ይቅር ከማለት ሊከለክል አይገባም ።
ሰው ስህተትን የማይደግመው ለራሱ ይቅርታ
ማድረግ ሲችል ነው ። አልያ ስህተትን በሌላ ስህተት እየቀየረ ይኖራል ። ጥፋትን በሌላ ጥፋት እየተካ ይቀጥላል ። ለራሱ ይቅርታ
ማድረግ ካቃተው ፣ ላለመሳሳት ከመጠን በላይ ይጨነቃል ። ላለመሳሳት ሲጨነቅ የበለጠ ስህተት ይሰራል ። በጸጸት ብዛት ስህተትን
ማስቆም አይቻልም ። ጥፋትን መግታት አይታሰብም ። ስህተትን ማመን ፣ ለጥፋት ሀላፊነት መውሰድ ፣ ድክመትን መቀበል ነው ፣ ስህተትንም
ጥፋትንም ባለበት የሚያስቆመው ።
ይቅርታ እረፍት ነው ። መንፈስን የሚያድስ ሀይል ነው ። ያልታደሰ መንፈስ ደካማ ነው ። ስለዚህ ስህተትን ለመደጋገም ቅርብ ነው ። መንፈስ ሲታደስ ብርቱ ይሆናል ። ሰው ውስጡ ሲታደስ ስህተትን ላለመድገም አቅም ያገኛል ። ሰው የሚታደሰው በይቅርታ ስለሆነ ፣ ለራስም ለሌላውም ይቅርታ ማድረግ ወሳኝ ነው ። ሰዎች ልክ እንደተፈጥሮ ሀብት ( Natural resource ) በሁለት ይከፈላሉ ። ታዳሽ እና ታዳሽ ያልሆኑ በመባል ። የይቅርታ ሰዎች ታዳሽ ናቸው ። የበቀል ሰዎች ደግሞ ታዳሽ ያልሆኑ ፍጥረቶች ናቸው ። ታዳሽ የተፈጥሮ ሀብቶች ዘላለማዊ እንደሆኑ ሁሉ ፣ የይቅርታ ሰዎችም ዘላለማዊ ናቸው ። ታዳሽ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ጊዜያዊ ( limited ) ናቸው ። በተመሳሳይ ታዳሽ ያልሆኑ የበቀል ሰዎች ጊዜያዊ ናቸው ። የይቅርታ ሰዎች ህይወትን የሚቀጥሉ ሀይሎች ናቸው ። የበቀል ሰዎች ደግሞ ወይ ህይወትን የሚጨርሱ አልያም ለራሳቸው የሚያልቁ ሀይሎች ናቸው ። ህይወትን የሚቀጥሉ በሰው ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ ። ህይወትን የሚያቃጥሉ ከሰው ልብ በቀላሉ ይሰረዛሉ ። ስለዚህ ህይወትን ለመቀጠል የይቅርታ ሰው እንሁን ።
ከልብ ለመሆን ለራስ ይቅርታ ማድረግ ተገቢ ነው ። ለመበርታት ለመታደስ ይህ ግድ ነው ። በጸጸት ብዛት መኖር ራስን ማቃጠል ነው ። ዘላለማዊ ሳይሆን ጊዜያዊ መሆን ነው ። ይህ ደግሞ ራስን በራስ መግደል ነው ። ስህተት ሰውኛ መሆኑን አምነን ፣ ለራስ ይቅርታ በማድረግ አዲስ ሰው እንሁን ። ለምድር ታዳሽ ሀይል ፣ ለሰዎችም ለራሳችንም ህይወትን ቀጣይ እንሆን ዘንድ ፣ ለራስም ለሌላም ይቅርታ ማድረግን እንለማመድ ። የቱንም ያህል ስህተት ብንሰራም ፣ ለራስ ይቅርታ የማድረግ ሞራል ልናጣ አይገባም ።
‘’ ስህተትን ላለመድገም ለራስ ይቅርታ ማድረግ ቁልፍ ነው ። ‘’
No comments:
Post a Comment