Monday, June 16, 2025

እይታ | Perception

                                                     

                              ራስን ማጣት

     

       ራስን ማጣት መልከ ብዙ ነው ። ሰው ራሱን የሚያጣበት ምክንያት ብዙ ነው ። ራስን ከሚያሳጡ ነገሮች መሀል አንዱ ስሜታዊነት ነው ። ስሜታዊነት ሰውን ሌላ ሰው የማድረግ አቅም አለው ። ሰው ሲቆጣ ሲያዝን ሲፈራ እና ሲደሰት ፣ ከነበረው ማንነቱ የተለየ ማንነትን ይላበሳል ። ለዚህ ነው ስሜታዊ የሆኑ ሰዎች ፣ ባህሪያቸው በቀላሉ የማይለይ ፣ ስብእናቸው ተለዋዋጭ እየሆነ የሚያስቸግረው ። ስሜታዊ ሰዎች ሲደሰቱ ሌላ ፣ ሲያዝኑ ሌላ ሰው ናቸው ። በቀላሉ ራሳቸውን ያጣሉ ። ሲጀመር ዋስትና ያለው ባህሪ ወይም ስብእና ስለማይኖራቸው ፣ እንደ እስስት በቀላሉ የመለዋወጥ ባህሪ ይኖራቸዋል ። ለእነርሱ ከባዱ ራስን ማጣት ሳይሆን ራስን ማግኘት ነው ። በስሜት ለመገንባት ብርቱ ናቸው ። የዚያኑ ያህል በንዴት ለማፍረስ ጎበዝ ናቸው ። ሆ ብሎ መስራት ወዲያው ደግሞ ሆ ብሎ ማበላሸት መለያ ባህሪያቸው ነው ። ባጭሩ በስሜታዊነት ራስን ማጣት እንጅ ራስን ማግኘት ፣ ወደ ራስ መመለስ አይኖርም ።

ሌላኛው ራስን የሚያሳጣ ነገር ዝለት ነው ። ዝለት ሲባል የመንፈስም የአካልም ነው ። በእርግጥ የአካል ዝለት ፣ ያን ያህል የባህሪ ወይም የስብእና መዛባትን አይፈጥርም ። የመንፈስ ዝለት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፣ የባህሪ መረበሽን ፣ የስሜት መቃወስን ፣ የስብእና መዛባትን ያስከትላል ። ዝለት ቀላሉን ነገር ከባድ ያደርጋል ። ተግባቢ የነበረውን ነጭናጫ ያደርገዋል ። ትእግስተኛ የነበረውን ቁጡ ያደርገዋል ። ትሁት የነበረውን ትእቢተኛ ያደርገዋል ። ብርቱ የነበረውን ደካማ ያደርገዋል ።

 በዝለት ውስጥ ስራ በጥረት እንጅ በጥራት አይሰራም ።በዝለት ውስጥ ለመጣር የተወሰነ አቅም ይኖራል ፣ ለማጣራት ግን በቂ አይሆንም ። ምክንያቱም ዝለት አቅላችንን ያስተናል ፣ ራሳችንንም ያሳጣናል ። ዝለት የስራ መብዛት ውጤት ነው ። ከአቅም በታች መስራት ዘልዛላ ያደርጋል ። ከአቅም በላይ መስራት ደግሞ ለዝለት ይዳርጋል ። ስለዚህ ሰው ራሱን ላለማጣት አቅሙን ማወቅ አለበት ። በአቅሙ ልክ መስራት አለበት ።  

   ራሳቸውን የሚያጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ራሳቸውን የማያውቁ ሰዎች ናቸው ። ራስን ማወቅ የራስን አቅም ስሜት ድክመት ጥንካሬ እና ሀሳብ ወይም አላማ ማወቅ ነው ። እነዚህን የራሱ የሆኑትን ነገር ያላወቀ ሰው ፣ በስራ ቦታ ፣ በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ በቀላሉ ራሱን ያጣል ። ምክንያቱም ችግር ሲገጥመው የሚታገስለት አላማ የለውም ። ድክመቱን አውቆ ነገርን  በማሸሽ ወይም በመሸሽ ፣ ከራሱ አያርቅም ። ራሱን ለማሸነፍም ጠንካራ ጎኑ ምን እንደሆነ መለየት አይችልም ። በመጨረሻም ራሱን በማጣት ብዙ ነገሩን ያጣል ። በእርግጥ ራስን ከማጣት በላይ ከባድ ችግር የለም ። ሰው ያለውን ሁሉ ቢያጣ ችግር የለውም ። ከባድ ችግር የሚፈጠረው ግን ራሱን ያጣ እለት ነው ።       

   ራስን ማጣት የነበረንን መጥፎ ነገር ማጣት ሳይሆን ፣ ያለንን ጥሩ ነገር ማጣት ነው ። ሰው ያለውን መጥፎ ነገር ቢያጣማ መልካም ነው ። ያኔ ራሱን አጣ ሳይሆን ፣ ራሱን አገኘ ነው የሚባለው ። የነበረውን ቁጣ ትቶ ፣ ያልነበረውን ትእግስት ቢላበስ እሰየው ነው ። ትእቢቱን ረስቶ ትህትናን ከያዘ ፣ ይህ መልካም ነው ። ስስትን ትቶ ደግ መሆን ከጀመረ ፣ ያኔ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ፣ ወደ ሰውነቱ ተመለሰ ማለት ነው ። ራስን ማጣት መልካም ነገርን ማጣት ነው ። ትእግስትን ትህትናን እምነትን እውነትን ደግነትን ማጣት ነው ። ሰው እንደ ድሮ  አይደለህም ተለውጠሃል ፣ ወደራስህ ተመለስ የሚባለው ፣ የነበረውን መልካም ነገር ሲያጣ ነው ።

   አንዳንድ ሰው ገንዘብ ሲያገኝ ትህትናውን ያጣል ። በነገራችን ላይ ማግኘት የሚያስከትለው ማጣት በሽታ ነው ። ሰው ራሱን ከሚያጣ ገንዘብን ቢያጣ ይሻለዋል ። ምክንያቱም ገንዘብ ሲያገኝ ራሱን የሚያጣ ከሆነ ፣ ገንዘብ መልሚያው ሳይሆን መጥፊያው ይሆናል ። ማግኘት ማንነትን ሊያጠነክር እንጅ ሊያፈርስ አይገባም ። ሰው በገንዘቡ የተሻለ ነገር ለመስራት ፣ ራሱን ላለማጣት በተጠንቀቅ መጠበቅ ይኖርበታል ። ገንዘብ ራስን ከሚያሳጡ ነገሮች ዋነኛው ነው ።

   ስልጣን ሲያገኙ ጨካኝ የሚሆኑ አሉ ። መራራት እስኪያቅታቸው ድረስ ራሳቸውን የሚያጡ አሉ ። ከስልጣን በፊት ሰው የነበሩ ፣ ስልጣን ሲሰጣቸው ወደ አውሬነት ይቀየራሉ ። ለሰው የሚራሩ ምርጥ የነበሩ ፣ በሰው የሚጨክኑ ምጥ ይሆናሉ ። በስልጣን ምክንያት ራሳቸውን ያጡ ፣ ብዙ የድርጅት የማህበረሰብ የሀይማኖት እና የሀገር መሪዎች አሉ ። የነበራቸውን መልካም ነገር አጥተው ፣ ያልነበራቸውን ክፉ ነገር የታጠቁ ብዙ ናቸው ። በስብእናቸው ይመሩናል ተብለው ተመርጠው ፣ በስልጣን ምክንያት ስብእናቸውን በማጣት ፣በትክክል የመሩን ሳይሆን በትግል የመረሩን ብዙ ናቸው ። በስልጣናችሁ ክቡር ፣ በመሪነታችሁ ምስጉን ለመሆን ፣ ስልጣን ስታገኙ ራሳችሁን ላለማጣት መጠንቀቅ አለባችሁ ። ያልነበራችሁን እውቀትና ልምድ የምታገኙበት እንጅ ፣ የነበራችሁን መልካም ስብእና የምታጡበት መሆን የለበትም ።

   እውቀት ሲያገኙ ራሳቸውን በደምብ ማወቅ ሲገባቸው ፣ በተቃራኒው ራሳቸውን የሚያጡ ብዙ ናቸው ። መሃይምነት ከምሁርነት ይሻላል የሚያስብሉ ፣ እውቀት ሲያገኙ ራሳቸውን ያጡ ምሁራን ብዙ ናቸው ። እውቀት ሰይጣን ያደረጋቸው ብዙ አዋቂዎች አሉ ። ለሰው በእውቀታቸው መድሃኒት ሳይሆን ፣ መርዝ እስከ መስራት የደረሱ ብዙ ናቸው ። መፍትሄ ሳይሆን ችግር የፈበረኩ ብዙ ናቸው ። አዋቂነት አውሬነት የሆነባቸው ተማራማሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ። በእውቀታቸው ዓለምን የጦርነት ማእከል ያደረጉ ፣ የፖለቲካውን አለም የሴራ ማምረቻ እንዲሆን የቀረጹ ፣ ትምህርት ቤቶችን የዝሙት ማስፋፊያ ያደረጉ ብዙ ናቸው ። እውቀት ሰውን ወደ ሰውነት እንጅ ወደ ሰይጣንነት ሊወስደው አይገባም ። ወደ ራሱ ሊመልሰው እንጅ ራሱን ሊያሳጣው አይገባም ። ለዚህ ደግሞ እውቀትን መምረጥ ተገቢ ነው ። ፈጣሪ የፈቀደውን መልካሙን ሁሉ ማወቅ ፣ ክፉውን መተው አስፈላጊ ነው ።

      ‘’ ለማግኘት ራስን ማጣት ልክ አይደለም ። ከክፉ ነገር ራስን መጠበቅ ፣ ማጣት ሳይሆን ራስን ማግኘት ነው ። ‘’    

No comments:

Post a Comment

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...