Wednesday, July 30, 2025

እይታ | Perception

                                             ዋናው ኮንቴክስቱ ( አውዱ )

     ሁለት መታወቂያ የተሰኘው ፊልም ላይ ፣ ዳዊት አባተ ወይም በገጸ ባህሪ ስሙ ቢኒያም እንዲህ ሲል ይደመጣል ‘’ በህይወት እውነት ወይም ውሸት ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ፣ ሞራላዊ ወይም ኢ ሞራላዊ የሚባል ነገር የለም ፣ ዋናው አውዱ ( ኮንቴክስቱ ) ነው ። ’’ አውድ ሲባል በዋናነት ሁኔታ ማለት ነው ። ሰው ህይወቱን በአውድ ወይም በሁኔታ የሚመራ ከሆነ ፣ እውነትን በእውነትነቱ ሳይሆን የሚመዝነው ፣ እውነት በሚያመጣው ውጤት ላይ ተመስርቶ ነው ፣ እውነትን የሚለካው ። ይህ ደግሞ የሰውን ልጅ ውጤት ተኮር እንጅ ሂደት ተኮር አያደርገውም ። ነጮቹ ሰው ከውጤቱ በላይ ሂደቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሲመክሩ ‘’ Trust the process! ‘’ ይላሉ ። 

   ከውጤቱ በላይ ለሂደቱ ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች በመርህ የሚመሩ ናቸው ። ከሂደቱ በላይ ለውጤቱ ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ መርህ አልባ ናቸው ። ያው የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ይመቻቸዋል ። አብዝተው ውጤት የሚፈልጉ ሰዎች ፣ መርዝን መድሃኒት ነው እስከማለት ይደርሳሉ ። በእውነት መንገድ ውጤት ከሚያጡ ፣ በውሸት ተጉዘው ውጤት ላይ መድረስ ምርጫቸው ነው ። ለእነርሱ እውነት ከሁኔታ በልጦ አያውቅም ። ሁኔታ ነው ከእውነት የሚበልጥባቸው ። ስለ እውነት ማጣት መራብ መጠማት መዋረድ ፣ ለእነርሱ የጀግና ሳይሆን የቀሽም ሰው ተግባር ነው ። 

    በእርግጥ አውዳዊ ፍቺ የሚያስፈልገው እውነት አለ ። ነገር ግን ሁሉም እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። ለምሳሌ የወል እውነት አውዳዊ ፍቺ አያስፈልገውም ። የወል እውነት ቦታ ጊዜ ሁኔታ የማይቀያይሩት እውነት ነው ። ጸሀይ በምስራቅ ወጥታ በምራብ ትጠልቃለች ። ይህ የሰፈር እውነት ሳይሆን የዓለም እውነት ነው ። ውሀ ውሀ እንጅ ነዳጅ አይሆንም ። ነዳጅም እንደዚሁ ውሀ ሊሆን አይችልም ። ይህ እውነት የሆኑ ቡድኖች ያጸደቁት ሳይሆን ፣ ሁሉም ሰው አምኖ የተቀበለው እውነት ነው ። ውጤት ተኮር የሆኑ ሰዎች ግን ፣ ከቻሉ ውሀ እና ነዳጅን ቀላቅለው ፣ ነዳጅ ነው ብለው ይሸጣሉ ። ምክንያቱም ከሂደቱ በላይ የሚተማመኑት በውጤቱ ነው ። ለዚህ ደግሞ ማሳመኛ ይሆናቸው ዘንድ ፣ ውሸትን ብቻ ይዘው አይቀርቡም ። ውሸትን በእውነት ሸፍነው ያቀርባሉ ።

   ውጤት ተኮር መሆን በራሱ ስህተት አይደለም ። ስህተት የሚሆነው ለውጤቱ ሲባል የማጭበርበር ስራ ሲሰራ ነው ። ውጤቱን ጥሩ ለማድረግ ሂደቱን መጥፎ ማድረግ ትክክል አይደለም ። ከሆነ ወይም ከተቻለ ውጤቱንም ጥሩ ሂደቱንም ትክክል ማድረግ ተገቢ ነው ። ካልሆነ ግን ውጤቱ ምንም ቢሆን ፣ ሂደቱን ትክክል ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ። አንድ አንድ ሁኔታዎች ፣ የሰው ልጆች እስከሆንን ድረስ ፣ ሂደቱን በማበላሸት ውጤቱን ማሳመር እንደሚቻል ይጠቁሙናል ። ያኔ የገጠመን እውነት የወል ሳይሆን አንጻራዊ ስለሆነ ፣ ውሳኔያችንን እንደሁኔታው ማድረግ ግድ ይላል ።

    አንጻራዊ እውነት በአማራጭ የተሞላ ነው ። እንደ ሰው ፍጹም ስላልሆንን ፣በዚህ ጊዜ ውሳኔያችን ከሂደቱ በላይ በውጤቱ ላይ ቢመሰረት መልካም ነው ። ምርጫችንም የተሻለ ይሆናል ። በስህተት መንገድ ትክክል የሆነ ውጤት ማምጣት ባይቻልም ፣ በአንጻሩ ጥሩ ነገር ማድረግ ይቻላል ። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲገጥመን ፣ ውሸት ወይም እውነት ፣ ትክክል ወይም ስህተት ሚዛን አይሆኑም ። ሚዛን የሚሆኑት ማዳን ወይም መግደል ፣ ማጥፋት ወይም ማልማት ፣ ማበላሸት ወይም ማስተካከል ናቸው ። በእርግጥ የሀገሬ ሰው '' ካልደፈረሰ አይጠራም ። '' ይላል ። የደፈረሰ ሁሉ ይጠራል ማለት ግን አይደለም ። አንዳንድ ነገሮች ላይጠሩ ይደፈረሳሉ ። ላይቃኑ ይጣመማሉ ፣ ላይስተካከሉ ይበላሻሉ ፣ ላይመለሱ ይለወጣሉ ። ስለዚህ በህይወት ስንኖር ፣ ከውሳኔ በፊት ሁኔታን በጥልቀት መፈተሽ እና መመዘን ያስፈልጋል ። ምክንያቱም ማዳን የምንችለውን ልንገድል እንችላለን ። መስተካከል የሚችለው እንደተበላሸ ሊቀር ይችላል ። መቆም ያለበት ወድቆ እንክትክቱ ሊወጣ ይችላል ። ሰዎች ነን ፍጹም ልንሆን አንችልም ። ስለዚህ ሁኔታን በአንጻራዊ እውነት ከምንመዝን ፣ አንጻራዊ እውነትን በሁኔታ ( context) ብንመዝን የተሻለ ነው ።

   እውነት ከእውነት ይለያያል ። ሁሉም እውነት እኩል መታየት የለበትም ። የሚጠቅም እውነት ከሚጎዳ እውነት ጋር እኩል መታየት አይኖርበትም ። የሚያጣላ እውነት ከሚያፋቅር እውነት ጋር ሊስተካከል አይገባውም ። ጥቁር ታሪክ የተሸከመ እውነት ፣ የጀግንነት ታሪክ ከተሸከመ ታሪክ ጋር እኩል ትኩረት ሊሰጠው አይገባም ። ምክንያቱም ጥቁር ታሪክ ጸጸትን በቀልን ቁጭትን ነው የሚወልደው ። የጀግንነት ታሪክ ግን ሞራልን አሸናፊነትን አንድነትን ነው የሚወልደው ። ስለዚህ ለሁሉም እውነት መታመን ታማኝ አያደርግም ። ትክክለኛ ታማኝነት ፍቅርን ፍትህን አንድነትን ለሚያሰፍን እውነት መታመን ነው ። ለሁሉም እውነት መታመን ጅልነት ነው ። ለምርጥ እውነት መታመን ግን ጀግንነት ነው ። በነገራችን ላይ ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ የሚሆኑ ሰዎች አሉ ፣ እነዚህ ሰዎች ክፉዎች ናቸው ። ምክንያቱም የእነርሱ እውነት ፍቅር የለውም ። ፍቅር የሌለው እውነት ደግሞ የሞተ ነው ። ሰውን ለመጉዳት እውነተኛ ከመሆን ፣ ሰውን ለማዳን ውሸታም መሆን ይሻላል ። ነገርን ከሰው አንጻር እንጅ ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ልክ አይደለም ። የሚጎዳን እውነት ይዞ መኖር ፣ ሰውን ከነገር አንጻር መመልከት ነው ። 

   ዋናው አውዱ ( ኮንተክስቱ ) ማለት በምንም ጉዳይ ቢሆን ሰውን እናስቀድም ማለት ነው ። እውነትም አንጻራዊ እውነት ሰብአዊነትን ማስቀደም አለባቸው ። በእርግጥ የወል እውነት ፣ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰብአዊነትን ቢያስከብር እንጅ አያዋርድም ። አንጻራዊ እውነት ግን አስቸጋሪ ነው ። ፍትህን ለማዛባት ሰብአዊነትን ለመጣስ ሊውል ይችላል ። ስለዚህ አንጻራዊ እውነት ሲገጥመን መጠንቀቅ አለብን ። 

  '' ከሁኔታ የሚበልጠው እውነት የሰውን ልጅ ክብር የሚጨምር ነው ። በሁኔታ የሚገደብ እውነት ግን የሰውን ክብር ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል ። ''    

    

Tuesday, July 15, 2025

እይታ | Perception

                                                             ራስን መመርመር

  ራስን መመርመር ራስን መመልከት ነው ። አንድ የላቦራቶሪ ቴክኒሺያን በሰው ደም ውስጥ ፣ በሽታ አምጪ ህዋስ መኖሩን ለማረጋገጥ ፣ ማይክሮስኮፕን ይጠቀማል ። በተመሳሳይ የሰው ልጅ የስብእና በሽታ ሲገጥመው ፣ ራሱን ለመመርመር የስብእና ግድፈቱን የሚለይበት ማይክሮስኮፕ ያስፈልገዋል ። በሽታውን ለማወቅ ማይክሮስኮፑን በአግባቡ መጠቀም ግድ ይላል ። የሰው ልጅ የራሱን የስብእና በሽታ የሚያይበት ማይክሮስኮፕ አንዱ ጥሞና ነው ። ጥሞና የባህሪ በሽታን የመለየት ከፍተኛ አቅም አለው ። ጥሞና ሰውን ከፍተኛ መረጋጋት ውስጥ ይከታል ። ሰውን እንደ ፍሪጅ አቀዝቅዞ ፣ ባህሪን ከሚበክል ስሜት እና ሀሳብ ነጻ ያደርጋል ። ሰው በሽታውን አውቆ መድሀኒቱን እንዲፈልግ ፣ ጥሞና ብርሃን ይሆነዋል ። ጥሞና ዝምታ ነው ። ፈርቶ ዝም ማለት ሳይሆን አቅዶ ዝም ማለት ነው ።

  ፈርቶ ዝም ማለት ሁለት ገጽ አለው ። አንድም ለኪሳራ በሌላ በኩል ደግሞ ለትርፍ ሊዳርግ ይችላል ። የፍርሀት ዝምታ ከስሜታዊ ሰው ጥቃት ይጠብቀናል ። በስሜታዊ ሰው ፊት በፍርሀትም ይሁን በእውቀት ዝም ማለት ራስን ከአደጋ መከላከል ነው ። የፍርሀት ዝምታ ከዚህ አንጻር ሲታይ ጠቃሚ ነው ። ግን በሌላ ገጹ ሲታይ የፍርሀት ዝምታ ብዙ ነገር ያሳጣል ። ዝምታ ወርቅ ነው የሚባለውን ያህል ውድቅ የሚሆንበት ቦታም አለ ። መናገር ሲኖርብን ዝም ማለት ያሳጣል ። በእርግጥ ዝም ማለት ሲገባ መናገርም ያስቀጣል ። ሁለቱም እኩል ጉዳት አላቸው ። ከሁለቱም ጉዳት ነጻ የሚያወጣን ማስተዋል ነው ። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ጥሞና ነው ። 

 ጥሞና የነገርን ክብደት እና ቅለት ለመለየት ወሳኝ ነው ። ጥሞና የማስተዋል አቅምን ሲጨምር ፣ የፍርሀት ዝምታ ግን ማስተዋልን ይቀንሳል ። በጥሞና ውስጥ ነገርን በልኩ ማወቅ እና መረዳት ይቻላል ። ጤናማውን ከበሽተኛው ለመለየት ቀላል ይሆናል ። ይህ ደግሞ ራስን ለማስተካከል እድል ይሰጣል ። ጥሞና ራስን መመርመሪያ ምርጥ ማይክሮስኮፕ ነው ።

   ሌላኛው ራስን መመርመሪያ ማይክሮስኮፕ ተግባቦት ነው ። ከሰው ጋር መነጋገር ራስን ማያ መስተዋት ነው ። ሰው ፊቱ ላይ ያለውን ጉድፍ ለማጽዳት መስተዋት ይጠቀማል ። የባህሪ ግድፈቱን ለማጽዳት ደግሞ አጠገቡ ያለውን የቅርቤ የሚለውን ሰው ፣ እንደመስተዋት መጠቀም አለበት ። ሰው በምልአት ራሱን ማየት አይችልም ። ለእርሱ የተሰወረው አጠገቡ ላለ ሰው ግልጽ ሊሆን ይችላል ። በተለይ በሳል ሰው ካለ ፣ የማይታየውን ማየት የሚችል አቅም ስላለው ፣ ራስን ለመመርመር እና ለማስተካከል ጥሩ አቅም ይሆነናል ። ሰው ለብቻው ራሱን በመመርመር ውጤታማ አይሆንም ። የሚያግዘው እና የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል ።

   ሰው ራሱን ሲመረምር ሀቀኛ መሆን አለበት ። ስህተቱን ስህተት ፣ ልኩን ትክክል ነው ማለት አለበት ። ስህተቱን ልክ ልኩን ስህተት ካደረገ ግን ፣ ራሱን እየመረመረ ሳይሆን ራሱን እያባበለ ነው ። ራስን በማባበል ደግሞ አሉታዊ እንጅ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ። እየባሱ መሄድ እንጅ መሻሻል አይኖርም ። ሰው ወደ ላይ የሚያድገው እውነትን መቀበል ሲችል ነው ። ወደ ታች የሚወርደው እውነትን መቀበል ሲያቅተው ነው ። ለስህተት ምክንያት እየሰጡ ራስን ከእውነት ማሸሽ ፣ መጨረሻው እድገት ሳይሆን ውርደት ነው ።

 ስለዚህ ራስን መርምሮ ለማሻሻል ፣ እውነትን መቀበል ቁልፍ ብቻ አይደለም ፣ የቁልፎች ሁሉ ቁልፍ ( Master key ) ነው ።

   ትክክለኛ ራሱን መርማሪ ፣ ተንኮል በመስራቱ ራሱን ደግ አደረክ ብሎ አያሞግስም ። ባይሆን በመጸጸት ራሱን ለማስተካከል ይጥራል ። ባደረገው መልካም ነገር ይደሰታል ራሱንም ይሸልማል ። በሰራው ስህተት ደግሞ ራሱን ይወቅሳል ። በልኩ ያዝናል በልኩ ደግሞ ይደሰታል ። ደስታው የበለጠ ተግቶ እንዲሰራ ሀይል ይሆነዋል ። ሀዘኑ ደግሞ ስህተቱን ይቀንስለታል ። በስህተት ማዘን በመልካም ስራ መደሰት ሰውነት ነው ። በተንኮል መደሰት በመልካም ስራ መከፋት አውሬነት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ማታ ላይ ተኝተው ፣ የቀን ስራቸውን የሚያሰላስሉት ፣ በሰሩት ተንኮል ለመሳቅ እና ባደረጉት መልካም ነገር ለማዘን ነው ። ከዚያም በተጨማሪ የተሻለ ተንኮል ለማሰብ እና ለማቀድ ነው ።

     ተንኮል ለማቀድ ራሱን ከሚመረምር ሰው ፣ ራሱን የማይመረምር ብኩን ይሻላል ። ምክንያቱም ስህተትን ሆን ብሎ ሳይሆን ፣ ባለማወቅ ነው የሚሰራው ። አስቦ ራሱን መመርመር ባይችልም ፣ በሂደት በህይወት ልምድ ስህተቱን መቀነሱ አይቀርም ። ይህች ምድር ትልቅ ጥፋትን የምታስተናግደው ፣ ሳያውቁ ስህተት በሚሰሩት ሳይሆን አውቀው ሆን ብለው ስህተት በሚሰሩት ነው ። ክፉ ለማድረግ ራስን መመርመር ፣ ራስን መመርመር ሳይሆን ራስን መራር ማድረግ ነው ። ( Weak acid ) ደካማ አሲድን ጠንካራ አሲድ ( Strong acid ) ማድረግ ነው ። ይህ ደግሞ ከጎጂነት ወደ አጥፊነት መቀየር ነው ። ሰው ራሱን የሚመረምረው አጥፊ ከሆነ አልሚ ለመሆን ነው ። ተንኮለኞች ግን ራሳቸውን የሚመረምሩት የበለጠ አጥፊ ለመሆን ነው ።

   ራሳችንን መመርመር  ለክፋት ሳይሆን መልካም ለማድረግ መሆን አለበት ። ስህተትን ለመቀነስ እንጅ ስህተትን ወደ ተንኮል ለመቀየር መሆን የለበትም ። ራስን ለማረም እንጅ አረም ለማድረግ ራስን መፈተሽ አያስፈልግም ። ስራን ለማስተካከል እንጅ ለማበላሸት ራስን መመርመር አስፈላጊ አይደለም ። በዚህች ምድር ስንኖር ራስን መመርመር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን ራሳችንን መመርመር ያለብን ምድርን ለማልማት እንጅ ለማጥፋት አይሁን ።

    ‘’ ራስን ለማስተካከል ራስን መመርመር ነው ቁልፉ ። ‘’                 

Saturday, July 5, 2025

እይታ | Perception

                                                       

                       መቅናት እና ማስቀናት

      ‘’ የቀናም ያስቀናም ሁሉም ቤት ያፈርሳል ። ‘’ አለ ዘፋኙ ። ምክንያቱም መቅናትም ማስቀናትም የትዳር ማነቆዎች ናቸው ። ትዳርን የማፍረስ አቅም አላቸው ። መቅናት እኔ ብቻ ልወደድ ባይነት ስለሆነ ፣ በፍቅር ውስጥ መጋራትን እንጅ ማጋራትን አይፈቅድም ። ቅናት ከመስጠት ይልቅ መቀበል ላይ ትኩረት ያደርጋል ። ዞሮ ዞሮ ቅናት የፍቅር ተቃራኒ ነው ። ምክንያቱም ፍቅር ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ከፍ ያለ ቦታ መስጠት ነው ። መስጠት ባነሰበት ሁሉ ፍቅር ያንሳል ። በመቀበል ብቻ ደግሞ ፍቅርን ማጎልበት አይቻልም ። መስጠትም መሰጠትም ባለበት ግን ፍቅር ያድጋል ይበዛል ። ያኔ መቅናትም ማስቀናትም አቅም ያጣሉ ። ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ልብ ለቅናት ቦታ የለውም ።

   ቀናተኛ ሰው ለሰው ሲሰጥ ከእርሱ ላይ የተወሰደበት ይመስለዋል ። ካገኘው ይልቅ ያጣው ይታየዋል ። ከተሰጠው ይልቅ የተነፈገው ይጎላበታል ። ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ ምክንያት ይፈልጋል ። ቅናት ልብን ስለሚሰውር ፣ በቀናተኛ ሰው ዘንድ ከእርሱ ውጪ ሌላ ሰው ልክ ሆኖ አያውቅም ። ለእርሱ ልኩ ስህተት ፣ ስህተቱ ደግሞ ልክ ይሆናል ። ይህ ብቻ አይደለም ስህተትን ማጉላት ፣ ልክ የሆነውን ስራ ማኮሰስ ይችላል ። ለራስ መኖር እንጅ ለሌላው መኖር በቀናተኛ ሰው ዘንድ አይታሰብም ። ለሰዎች ሲኖር የማይደሰት ፣ ሰዎች ሲኖሩለት ብቻ የሚደሰት ራስ ወዳድ ፍጥረት ነው ። መኖር ሳይሆን ምን ጊዜም ማኖር ነው የሚፈልገው ። ከራሱ ውጪ ማየት የማይችል እውር ነው ። ቀናተኛ ሰው የራስ መንገድ እንጅ የጋራ መንገድ አይመቸውም ።

የራስ መንገድ አስፈላጊ ቢሆንም ፣ ለጋራ መንገድ ግን ክፍት መሆን አለበት ። የጋራ መንገድን ማስተናገድ የማይችል የራስ መንገድ ግትር ነው የሚያደርገው ። ይህ ደግሞ ከስምምነት ይልቅ ለግጭት ይዳርጋል ። በቀላሉ የሚፈታ ሳይሆን የማይፈታ ግጭት ነው የሚፈጥረው ።

   መቅናት መቃጠልም ማቃጠልም ነው ። መጀመሪያ በሰው ድርጊት መቃጠል ነው ። ሲቀጥል ነገር ማቀጣጠል ነው ። ሲለጥቅ በራስ ድርጊት ሌላውን ማቃጠል ነው ። በቅናት ቤቱን ያፈረሰ እንጅ የገነባ የለም ። ግንኙነቱን የተወ እንጅ በግንኙነቱ ፍሬ ያፈራ የለም ። ያፈረ እንጅ የኮራ ሊኖር አይችልም ። በጥርጣሬ እየተወጉ ሰላምን ማፍረስ እንጅ መገንባት በቅናት ፈጽሞ አይቻልም ። ‘’ ተጠራጥሮ ትዳር ኑሮ መች ያሞቃል ፣ የቀናም ያስቀናም ሁሉም ቤት ያፈርሳል ። ‘’ እንዲል ዘፋኙ ። ቅናት እና ጥርጣሬ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ። ቅናት ባለበት ጥርጣሬ ሊኖር ግድ ነው ። ጥርጣሬ ባለበት ቅናት ሊጠፋ አይችልም ። ሁለቱ ተባብረው ነው ሰውን አንድደው አመድ የሚያደርጉት ። ቅናት እና ጥርጣሬ!

   መቅናት ብቻ አይደለም ማስቀናትም በሽታ ነው ። ለማቃናት ሳይሆን ለማስቀናት የሚለፉ ሰዎች አሉ ። ማስቀናት የሚወዱ ሰዎች ፣ በማስደሰት ሳይሆን በማናደድ የሚያምኑ ናቸው ። በሰው ንዴት የሚደሰቱ ሲበዛ ራስ ወዳድ ናቸው ። ዉድ መሆናቸውን ለማሳየት ፣ ርካሽ መንገድ የሚጠቀሙ ብኩኖች ናቸው ። በማስቀናት ፍቅርን ለማጎልበት የሚጥሩ ጅሎች ናቸው ። ፍቅር በቅናት ይላላል እንጅ አይጠነክርም ። ቅናት በፍቅር ውስጥ የእርጎ ዝንብ ነው ። ልብን የሚበክል ባክቴሪያ ነው ።

ቅናትን በማስቀናት ጎትቶ ማምጣት ፣ ንጹህ ልብን መበከል ነው ። የተበከለ ልብ ደግሞ ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ ምቹ ነው ። የቅናትም የማስቀናትም መጨረሻ ጥላቻ ነው ። ሁለቱም የልብ በካይ ጋስ ( Carbon di oxide ) ናቸው ። ስለዚህ ለማቃናት እንጅ ለማስቀናት አንኑር ።

   በአርአያ ( Role model ) መቅናት ክፋት የለውም ። ይህ ቅናት በጎ ነው ። በሰው ልብ ውስጥ ክፋትን ሳይሆን ፣ ለስራ መነሳሳትን ( Motivation ) ነው የሚፈጥረው ። መጥፎው ቅናት ግን ለስራ ሳይሆን ለነገር ነው ሚያነሳሳው ። እኔ እንደሱ በሆንኩ ማለት እና እኔ ተከብሬ እርሱ በተዋረደ ማለት ይለያያል ። በጎ ቅናት ራስን ለማክበር መመኘት ነው ። መጥፎ ቅናት ደግሞ ሌላውን ለማዋረድ መጣር ነው ። በጎ ቅናት ከሰው እኩል ለመሆን መጣር ነው ። መጥፎ ቅናት ግን ከሰው ሁሉ በልጦ ለመገኘት መታገል ነው ። በሰው ጉብዝና በበጎ የቀና ሰው ፣ እንደሰውየው ጎበዝ ይሆናል ። በክፋት የቀና ሰው ግን ጎበዝ ሳይሆን ግብዝ ነው የሚሆነው ። በነገራችን ላይ በቅናት የሰውን ነገር የራስ ማድረግ አይቻልም ። ነገር ግን በበጎ ቅናት ካደረብን ፣ ቅናቱ በፈጠረው መነሳሳት ፣ ትጉ በመሆን የሰውን ሳይሆን ፣ የራስን ህልም ልክ እንደሌላው እውን ማድረግ ይቻላል ። በክፋት ግን የሰውን ነገር የራስ ለማድረግ ከጣርን ያለንን እናጣለን ።

 እንደ አልበርት አንስታይን የፊዚክስ ሊቅ ብሆን ብሎ መቅናት ችግር የለውም ። እንደ አልበርት አንስታይን ለምን እኔም እኩል ችሎታ አልተሰጠኝም ብሎ መቅናት ግን ትርፉ በሽታ ነው ። ምክንያቱም ህይወት አንተ ራስህን በትጋት ስታገኝ እንጅ የምታከብርህ ፣ በቅናት ስትንጨረጨር ዞር ብላ አታይህም ።

የስኬት ምስጥሩ ሰውን ማየት ሳይሆን ፣ በሰው ውስጥ ራስን ማየት ነው ። እዚች ምድር ላይ ሰውን በማየት ብቻ የከበረ የለም ። በጎ ቅናት በሰው ውስጥ ራስን ማየት ነው ። መጥፎ ቅናት ግን ከሰው ጋር ራስን ማነጻጸር ነው ። ከሰው መማር እንጅ በሰው መማረር አያዋጣም ። መማር ወይ ከሰው እኩል አልያም ከፍ ያደርገናል ። መማረር ግን በምንም ሂሳብ ከሰው እኩል አይደርገንም ። በጎ ቅናት መማር ነው ። መጥፎ ቅናት መማረር ነው ። ስለዚህ በበጎ እንቅና ፣ በክፋት ከመቅናት ግን እንጠንቀቅ ።

   ‘’ መቅናትም ማስቀናትም በሽታ ነው ፣ በበጎ መቅናት ግን መልካም እይታ ነው ። ‘’

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...