Monday, April 28, 2025

እይታ | Perception

                                                   ጭንቀትን መርሳት  

 

      ለሰው የጭንቀት ምክንያቱ ብዙ ነው ። መራብ መጠማት መክሰር ስራ ማጣት የኑሮ ውድነት ፣ ከሰው ጋር መቀያየም እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ ። የጭንቀትን ምክንያቶች በጠቅላላው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ብለን ልንመድባቸው እንችላለን ። ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ ። ሰው ራሱ ያመጣውን ጭንቀት ሲመልስም መመለስ ሲሳነውም ይስተዋላል ። ተፈጥሮ የሚያመጣበትን ጭንቀት ግን ቀድሞ ካልተከላከለ በስተቀር ፣ አንዴ ከሆነ አምኖ መቀበል እንጅ መልሶ መቀልበስ ፈጽሞ አይችልም ። ለምሳሌ የአየር ንብረትን አዛብቶ ዶፍ ዝናብ እንዳይዘንብ ፣ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ አይችልም ። ከሂማሊያ ተራራ በረዶ እንዳይቀልጥ መመከት አይችልም ። ደሃው ህዝብ በድርቅ እንዳይጎዳ መከላከል ከባድ ይሆንበታል ። ይህንን መቀበል እንጅ መቀልበስ አይችልም ። መከላከል ግን ይችላል ። በምን ? ከተባለ ተፈጥሮን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ። አልያ ምድር በጸሃይ መጋል ብቻ ሳይሆን ፣ በካንሰር ህመምተኛ ትሞላለች ። ይህ በሽታ ደግሞ ፍቱን መፍትሔ ያልተገኘለት የበሽታዎች ሁሉ በኩር ነውና ፣ ለእርሱ እጅ መስጠት እንጅ መታገል እና መጋፈጥ ትርፉ ከንቱ ድካም ነው ። ሲቀጥል ሞትን በቀጠሮ መጠበቅ ግድ ይሆናል ።

ሞትን በቀጠሮ መጠበቅ ደግሞ ጭንቀትን እጅግ ከባድ ያገርገዋል ። ይህ በቀላሉ የሚረሳ ሳይሆን የማይረሳ ጭንቀት ነው ።

     ይህን መርሳት ማለት ለመማር ዝግጁ አለመሆን ነው ። አለመማር ደግሞ መቅለል የሚችለውን ችግር ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል ። በየጊዜው ለአንድ ችግር ተመሳሳይ መልስ እንድንሰጥ ያስገድደናል ። አንድ ሰው ለቀድሞ ችግሩ መልስ መስጠት ከከበደው ፣ ከችግሩ ተምሮ ሳይሆን በችግሩ ተማሮ ነው ያለፈው ። መልስ መስጠት ከቀለለው ግን ፣ በችግሩ ተማሮ ሳይሆን ከችግሩ ተምሮ ነው ያለፈው ። ለዚህ ነው የተማሩ ሰዎች ምን ጊዜም ፣ ችግርን አክብደው ሳይሆን አቅልለው የሚመለከቱት ። ዩኒቨርስቲ ገብተው የተማሩ ሳይሆን ከህይወት የተማሩ ። ያልተማሩ ሰዎች ደግሞ ሁል ጊዜ ችግርን አቅልለው ሳይሆን አክብደው የሚመለከቱት ፣ ዩኒቨርስቲ ገብተው መማር ስላልቻሉ ሳይሆን ፣ ከህይወት መማር ስላልቻሉ ነው ። ችግርን አቅልሎ ለመመልከት ከህይወት መማር ግድ ነው ።

          ከህይወት ለመማር ጭንቀትን ሙሉ በሙሉ መርሳት ተገቢ አይደለም ። ምክንያቱም ችግር ጭንቀትን ይወልዳል ። ጭንቀት ሀሳብን ይወልዳል ። ሀሳብ ፣ ጥበብ እና እውቀትን ይወልዳል ። ጥበብ እና እውቀት ደግሞ ችግርን ወደ መፍትሔ ፣ ፈተናን ወደ እድል ይቀይራሉ ። ያኔ በመጀመሪያ የከበደው ችግር ዳግም ሲከሰት ቀላል ይሆናል ። መቶ ኪሎ የነበረው ፣ አስር ኪሎ ይሆናል ማለት ነው ።  

ግን ጭንቀት ሁሉ የመፍትሔ ሀሳብ ይወልዳል ማለት አይደለም ። ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን እና ከመጠን በላይ ሲሆን ይለያያል።

 ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን የሚያሞቅ እሳት ነው ። ከመጠን በላይ ሲሆን የሚያነድ እሳት ነው ። ስለዚህ ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን ነው የመፍትሔ ሀሳብ የሚወልደው ። አልያ የመፍትሔ ሀሳብ ሳይሆን የህመም ወይም የእብደት ሀሳብ ነው የሚወልደው ። አሙቆ የሚያነሳሳ ሳይሆን አግሎ የሚገድል ይሆናል ።            

          ጭንቀት አማራሪም አስተማሪም ገጽ አለው ። ከመፍትሔ ይልቅ ችግር ላይ ካተኮርን አማራሪ ገጹ ይበዛል ። ከችግሩ ይልቅ መፍትሔው ላይ ካተኮርን አስተማሪ ገጹ ይሰፋል ። ለዚህ ደግሞ የኛ እይታ ወሳኝ ነው ። ደራሲው እንዳለው ‘’ አረፍተ ነገር ሲነበብ ስርዓተ ነጥብ ይታያል እንጅ አይነበብም ። በተመሳሳይ በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ ፣ እንደ ስርዓተ ነጥቡ የሚታዩ እንጅ የማይነበቡ ነገሮች አሉ ። አረፍተ ነገር ስናነብ ፣ ነጠላ ሰረዝ እያልን ብናነብ ፣ በጀመሪያ ስሜት አይሰጥም ፣ ሲቀጥል አረፍተ ነገሩ ትርጉም ያጣል።  እንደዚሁም በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ ፣ የማይታዩ ድርጊቶች እና ክስተቶች  ፣ የማይሰሙ ንግግሮች ቦታ ካገኙ ፣ ችግርን እድል አድርገው ሳይሆን በደል አድርገው ነው የሚያሳዩት ። ከዛ ህይወት ትርጉም አልባ ሆና ትሳላለች ። ስለዚህ በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ ፣ በንቀት የተሞሉ ድርጊቶች እና ክስተቶች ፣ አሉታዊ ንግግሮች ትኩረት እና ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም ።

ነገር ግን ተስፋ የሚሰጡ ድርጊቶች እና ትእይንቶች ፣ እምነትን የሚያጠነክሩ አዎንታዊ ንግግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ።

 ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ፣ ችግርን በደል ሳይሆን እድል አድርገው ያሳዩናልና ። ስለዚህ እይታችንን እናስተካክል ከመጥፎው ይልቅ ጥሩውን፣ ከችግሩ ይልቅ መፍትሔውን ፣ ከፈተናው ይልቅ እድሉን በእምነት እና በተስፋ ለማየት እንጣር ። ያኔ የጭንቀት አማራሪ ገጹ ሳይሆን አስተማሪ ገጹ ጎልቶ ይታያል ። የእብደት ሀሳብ ሳይሆን የመፍትሔ ሀሳብ ይወለዳል ።  

        ጭንቀትን መርሳት ለዘላቂ ሰላም መፍትሔ አይሆንም ። ከችግር ወይም ከጭንቀት መማር ነው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው ። ጭንቀትን ለመርሳት የሚታገል ሰው ፣ ህይወቱን የሚጎዳ እርምጃ ይወስዳል ። ሲጨንቀው አልኮል ይታየዋል ። መርዝ መርዝ ይለዋል ። ተስፋ ቢስ ይሆናል ። ሞቱን ብቻ ይመኛል ። ለችግሩ ወይም ለጭንቀቱ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጅ ዘላቂ መፍትሔ አይታየውም ። 

      ከጭንቀት ለመማር የሚጥር ሰው ግን ፣ ህይወቱን የሚጠቅም እርምጃ ነው የሚወስደው ። ፈጣሪውን ይማጸናል ። መልካም ሰዎችን እርዳታ ይጠይቃል ። መፍትሔ ፍለጋ መጽሐፍ ያገላብጣል ። ለጊዜ ጊዜ ሰጥቶ ይጠብቃል ። ትእግስትን መርሑ ያደርጋል ። በጽናትም በጥናትም ችግሩን ወይም ጭንቀቱን ይሻገራል ። ሁሌም ተስፋ ያደርጋል ። በእምነት መከራን ያልፋል ።         

  ስለዚህ ሰው ጭንቀቱን ለመርሳት ሳይሆን መታገል ያለበት ፣ ከችግር ወይም ከጭንቀት ለመማር ነው ጥረት ማድረግ ያለበት ። ከጭንቀት ለመማር ስንጥር ፣ የጭንቀት ማቅለያ ስልትን እናውቃለን ። ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን ፣ ለህይወት ዘመን የሚያገለግል ስልት ይሆናል ። ጭንቀትን ለመርሳት ስንታገል ግን ራስን ማቅለያ ወይም ማጥፊያ ስልት ነው ፊታችን ላይ ድቅን የሚልብን ። ከጭንቀቱ የተማረ ኑሮው ይቀላል ። ጭንቀቱን ለመርሳት የታገለ ራሱ ይቀላል ። ከጭንቀት ከተማርን ጭንቀቱ ያልፋል ። ለሌላም ጊዜ ተሞኩሮ በመሆን ማለፊያ ይሆነናል ። ጭንቀትን ለመርሳት ከታገልን ግን ጭንቀቱ ሳይሆን እኛ እናልፋለን።

 

       ‘’ ጭንቀትን ከመርሳት ከጭንቀት መማር የተሻለ ነው ። ‘’   

                                 ክፍል 1

                                                                               

Sunday, April 27, 2025

እይታ | Perception

 

                       የጋራ ዓላማ

       የጋራ ዓላማ ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን አንድ ግለሰብ ፣ የራሱ አላማ ከሌለው ፣ የጋራ አላማ ሊኖረው አይችልም ። አላማ የሌለው ሰው ፣ የአላማ ህልውና አይገባውም ። የሰው ልጅ ለአላማ እንደተፈጠረ መረዳት አይችልም ። የሰው ልጅ ለመብላት ብቻ ሳይሆን ፣ ለማብላት ጭምር እንደተፈጠረ አይታየውም ። በመልበስ ብቻ ሳይሆን ፣ በማልበስ መደሰት እንደሚችል አይሰማውም ። ያለ ዓላማ የሚኖር ሰው ፣ የማግኘት እንጅ የመገኘት ትርጉም አይገባውም ። የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን ፣ የሚለብሰውን ካገኘ በቃው ። መብላት መጠጣት መልበስ ፈልገው ፣ ለሚጣሩ ድምጾች መገኘት መቻል ለእርሱ ዋጋ ቢስ ነው ። የእርሱ መኖር ለሌሎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አያውቅም ። በሌሎች መኖር ውስጥ ፣ የእርሱ እስትንፋስ እንዳለች አይረዳም ። ህይወትን በአጋጣሚ እንጅ በእቅድ መኖር አይችልም ። በእርግጥ ሰው በእቅዱ ልክ መኖር አይችልም ። ያለእቅድ መኖር ግን ትልቅ ስንፍና ነው ። ሰው በአጋጣሚ ኖሮ ፣ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል እጅግ ያሳዝናል ። በእቅድ ኖሮ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል ፣ የተፈጥሮ ሂደት ነው አምኖ ለመቀበል ብዙ አይከብድም ። ምክንያቱም አቅዶ የሚሞት ማንም የለም ። ምናልባት በኑሮ ጫና ወይም በተለያየ ምክንያት ፣ ሰው ራሱን ለማጥፋት ካላሰበ በቀር ። ያም ቢሆን ታስቦ ታቅዶ ሳይሆን ፣ በስሜት የሚከወን ድርጊት ነው ። ሰው አስቦ ራሱን ያድናል እንጅ ራሱን አይገድልም ። ማሰብ ማለት የሚጠቅመውን የተሻለውን መምረጥ ነው ። አለማሰብ ደግሞ የሚጎዳውን የባሰውን መወሰን ወይም መምረጥ ነው ።

        ያለ ዓላማ መኖር ያለ ማሰብ ውጤት ነው ። ሰውን ሰው የሚያደርገው ማሰብ መቻሉ ነው ። በደመ ነፍስ ከመኖር የሚታደገው ማሰቡ ነው ። የማይታየውን ማየት ፣ የማይሰማውን መስማት ፣ ከቁሱ አለም ጀርባ መንፈሳዊ አለም እንዳለ ማመን እና ማረጋገጥ የቻለው በማሰቡ ነው ። እንስሳት ለመኖር ምቹ ተፈጥሮ ይፈልጋሉ ። ምክንያቱም ተፈጥሮን ምቹ የማድረግ ብቃት የላቸውም ። እነርሱ ጫካው ምድረ በዳ ሲሆን ጥለው ይሸሻሉ ። አልያ ሁሉም አንድ በአንድ ፣ የሞት ሲሳይ ይሆናሉ ። ይህ የሚሆነው ማሰብ ስለማይችሉ ነው ። ሰው ግን እንደዛ አይደለም ፣ ማሰብ ስለሚችል ተፈጥሮ ምቹ ባትሆንም ፣ ምቹ ተፈጥሮን መፍጠር ይችላል ። ምድረበዳን ዉብ መኖርያ ማድረግ ይችላል ። ግን ይህን የማድረግ ብቃት ያለው ፣ ዓላማ ያለው ሰው ነው ። ዓላማ የሌለውማ ማሰብ ስለማይችል ፣ እንደ እንስሶቹ ምቹ ተፈጥሮን ይፈልጋል ። አልያ ሞት አፈፍ አድርጎ ይቀበለዋል ። የተሻለ ለማሰብ ዓላማ ያስፈልጋል ። ሰው ዓላማ ከሌለው ደመነፍሳዊ ይሆናል ። በደመነፍስ ያለ ሰው ፣ በስሜት እንጅ በማስተዋል መኖር አይችልም ። በስሜት ደግሞ የተሻለ ማሰብ በፍጹም አይቻልም ።

           አላማ አቅጣጫ ነው ። የህይወት መነሻም መድረሻም ነው ። አላማ የሌለው ሰው አቅጣጫ ቢስ ነው ። መነሻም መድረሻም የለውም ። እድሜው እንዲሁ ይሄዳል ፣ እርሱ ግን መሄጃ የለውም ። ቀን ይመሻል ይነጋል ፣ ለእርሱ ግን መሸም ነጋ ለውጥ የለውም ። ምክንያቱም መለወጥ አይፈልግም ። ለውጥ ጠላቱ ነው ። ከማላውቀው መልአክ ፣ የማውቀውን ሰይጣን የሙጥኝ ብል ይሻላል ብሎ የሚኖር ነው ።

ሰይጣን ስላወቅነው ደግ አይሆንም ። ባናውቀውም ከክፋቱ ፈቀቅ አይልም ። ክፉ ሰውም እንደዛ ነው ። ስለቀረብነው የዋህ አይሆንም ። ስለራቅነውም ተንኮሉን መስራት አያቆምም ። የለመድነው ክፉ ነገር ፣ እኛ ስለወደድነው መልካም አይሆንም ። ከጠላነው ግን ነገሩ ባይለወጥም ፣ እኛ እንለወጣለን ። ክፉን ነገር መውደዳችን የነገሩ እስረኛ ያደርገናል ። መጥላታችን ግን ነጻ ያወጣናል ። ነጻ ለመውጣት ግን ዋጋ ያስከፍላል ። ያለ ዋጋ የሚገኝ ነጻነት የለምና ። አላማ የሌለው ሰው ክፉን ወይም መጥፎን ነገር ለመተው በጣም ይከብደዋል ። በተመሳሳይ ጥሩውን ነገር ለመቀበል እጅግ ይጨንቀዋል ። የጋራ አላማ ለውጥ ይፈልጋል ። መለወጥ የማይችል ሰው ለጋራ አላማ እንቅፋት ነው ። አላማ የሌለው ሰው ፣ ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ ስላልሆነ ፣ ለጋራ አላማ መሰናክል ነው ።

      ዓላማ ያለው ሰው ግን ቢያውቅም ባያውቅም መልአክን አይጠላም ።

መልካም ነገርን አይተውም ። መልአክ መልአክ ነው ፣ እኛ ስለፈራነው መልካምነቱ አይቀየርም ብሎ ያምናል ። ከዘመድ ሰይጣን ፣ ባዳ መልአክ ይሻላል የሚል እይታ አለው ። ሁሌም አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አለው ። ለመለወጥ ዝግጁ ነው ። በጋራ መስራት በአንድነት ወደፊት መሄድ ደስታው ነው ። ነገር ግን የጋራ መልካም አላማ እንጅ ፣ ክፉ አላማ ካላቸው ጋር በፍጹም አይተባበርም ። አብረን እንስራ ከሚሉት ጋር እንጅ ፣ አብረን እናጭበርብር ከሚሉት ጋር ህብረት የለውም ። ሰርተን እንገባ እንጅ ፣ ሰርቀን እንገባ አይመቸውም ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል ሳይሆን ፣ እኔ ኖሬ ሰርዶ ላብቅል የሚል ነው ። ለዛሬ ሲል ነገን አያፈርስም ። ለነገ ዛሬ ይኖራል ።

የእርሱ ማጣት ሳይሆን ፣ የልጆቹ ማግኘት ይታየዋል ። የልጆቹ መጥገብ በምናብ ስለሚታየው ፣ የእርሱ መራብ ብዙ አይስጨንቀውም ። አላማ ያለው ሰው ፣ በዛሬ ዉስጥ ነገ ስለሚታየው ለጋራ አላማ ምቹ ፍጥረት ነው ።

     ምቾትን የሚፈልጉ ሰዎች ፣ ዓላማ ቢኖራቸውም ለጋራ ዓላማ ብዙ አይመቹም ። ትራፊ ለመስጠት ፣ ትርፍ መኪናቸውን ማጣት ይፈራሉ ። ልብሳቸውን ከመስጠት ይልቅ ፣ ቁም ሳጥናቸውን የልብስ ሙዚየም ማድረግ ይመርጣሉ ። ሀኪም ካላዘዛቸው ፣ ባዶ እግር መሄድ ይፈራሉ ። በባዶ እግር የሚሄዱትንም ይፈራሉ ። መኖር እንጅ ማኖር አይችሉም ። መስራት እንጅ ማሰራት አይሆንላቸውም ። መቀመጥ እንጅ ማስቀመጥ ህመማቸው ነው ። ሲደመጡ ደስ ይላቸዋል ። ሲያዳምጡ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል ። ሲከበሩ ጮቤ ይረግጣሉ ። ሲናቁ መብት ይረግጣሉ ። ለመከበር የተፈጠሩ እንጅ ፣ ለማክበር የተፈጠሩ አይመስላቸውም ። ለጥቅማቸው ይሽቆጠቆጣሉ ። ለክብራቸው ግን ያንቀጠቅጣሉ ። ምርጥ እና ቆንጆው የእነርሱ ፣ መጥፎ እና ቆሻሻው የሌላ ይመስላቸዋል ። አላማቸው ፍቅርን ማብዛት ሳይሆን ፣ ገንዘብን ቁስን ጌጥን ማብዛት ነው ። ራሳቸውን ጭምር ማብዛት አይፈልጉም ። ያወቁትን በማሳወቅ ፣ የቻሉትን በማሳየት ፣ እነርሱን የሚመስሉ ሌሎች እንዲፈጠሩ ምንም ጥረት አያደርጉም ። በአጭሩ ለምቾት የሚኖሩ ፣ ለጋራ አላማ አይመቹም ።

      የጋራ አላማ የተስተካከለ የግለሰብ አላማን ይፈልጋል ። በፓፒዮ መጽሐፍ ላይ ፣ እንደ ተተረከው ታሪክ አላማን ማስተካከል ያስፈልጋል ። ፓፒዮ ከእስር ቤት እንደ ወጣ ፣ ዓላማው ገንዘብ ማግኘት ነበር ።

ይህ ዓላማው ግን ህገ ወጥ እንዳደረገው ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ዉስጥ መረዳት ቻለ ። በመቀጠል አላማውን አስተካከለ ። በጀመሪያ ገነዘብ ሳይሆን ስራ ማግኘት እንዳለበት ራሱን አሳመነ ። ከስራ ገንዘብን ካስቀደምን ፣ ሥርዓት አልበኛ ወይም ህገወጥ የመሆን እድላችን ሰፊ ነው ። ከገንዘብ ስራን ካስቀደምን ግን ፣ ስርዓትም ይኖረናል ፣ ህጋዊም እንሆናለን ። ልክ ፓፒዮ እንዳደረገው ፣ ገንዘብን ከስራ ካስቀደምን ፣ ሀሳባችን መስራት ሳይሆን መስረቅ ይሆናል ። ስራን ከገንዘብ ካስቀደምን ግን ፣ ሀሳባችን መስራት እንጅ መስረቅ አይሆንም ።

               

            ‘’ የተስተካከለ አላማ ያለው የጋራ አላማን መፍጠር ይችላል ። ‘’ 

                               ክፍል 1                             

Thursday, April 24, 2025

እይታ | Perception

           ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት

  

           በብዛት ሰዎች መከራ ሲበዛባቸው ፣ ችግር ሲደራረብባቸው ፣ ለፍተው ደክመው ጠብ የሚል ነገር ሲያጡ አሁንስ ትእግስቴ አለቀ ይላሉ ። በርግጥ እውነት ነው ፣ የሰው ልጅ ትእግስቱ ውስን ነው እናም ማለቁ አይቀርም ። ያልቃል ማለት ግን አይታደስም ማለት አይደለም ፣ ህይወት አበቃላት ማለትም አይደለም ። የሰው ልጅ ትእግስቱ ቢያልቅ ይታደሳል ። ዳግም በትእግስት ሃይል ይሞላል ። ትእግስት የማያልቅበት ፈጣሪ ፣ እንደገና በአዲስ ትእግስት ይሰራዋል ።

     ዋናው ነገር የትእግስት ማለቅ ወይም አለማለቅ አይደለም ። ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ እና ያለ ጊዜው ሲያልቅ ይለያያል ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ጉዳቱ የከፋ ነው ። የሚታደስ ሳይሆን ፣ ባለበት የሚቆም ወይም ጭልጥ ብሎ የሚጠፋ ነው ። ለዚህም ነው ትእግስት የሌላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲጎዱ የሚታዩት ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ፣ ሰውን ትእግስተኛ ሳይሆን እልከኛ ነው የሚያደርገው ። ስለዚህ ለጥፋት እንጅ ለልማት አይሆንም ። ለውድቀት እንጅ ለስኬት አይዳርግም ። ለሃዘን እንጅ ለደስታ አይሆንም ። ወደ በቀል እንጅ ወደ ይቅርታ ልብን አይመራም ።

      ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት ጥሩ ምልክት ሳይሆን የአደጋ ምልክት ነው ። አምቡላንስ ከሳይረን ድምጹ እና ከቀይ መብራቱ ጋር እንደማለት ነው ። ከጊዜው ያጠረ ትእግስት ማስጀመር እንጅ ማስጨረስ አይችልም ። ለማሳቀድ እንጅ ለማስፈጸም በቂ አቅም የለዉም ። ተስፋ ልማስቆረጥ እንጅ ሪቫን ለማስቆረጥ እድል አይሰጥም ።

            ትእግስት ያለጊዜው ሲያልቅ ነገን ብሩህ አድርጎ ሳይሆን አጨልሞ ነው የሚያሳየው ። እምነትን ገድሎ ጥርጣሬን በልባችን ላይ ይዘራል ። አስተሳሰባችንን አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ ያደርገዋል ። ይሳካል ይሆናል ከማለት ይልቅ ፣ አይሳካም አይሆንም ማለት ቃላችን እና ልማዳችን ይሆናል ። የልቦናን አይን ሞራ ገፎ ከመጣል ይልቅ ፣ የስራ ሞራልን ገፎ ይጥላል ። የሰው ልጅን በእቅድ እንዳይኖር ፣ በዘፈቀደ እንዲኖር ያስገድደዋል ። ማቀድን ሞኝነት ተስፋ ማድረግን ጅልነት አድርጎ ያሳያል ። መኖርን ከንቱ ፣ መሞትን ምርጥ መፍትሔ ያደርጋል ። ስለዚህ የትእግስት ማለቅ ሳይሆን ዋናው ቁም ነገር ፣ ያለ ጊዜው ትእግስት እንዳያልቅ መጠንቀቅ ነው የሚያስፈልገው ።

              ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ፣ በጊዜው ከሚያልቅ ትእግስት የሚለይባቸው ነገሮች ብዙ ናችው ። ለምሳሌ ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ ድክም ያደርጋል ።

 ያለ ጊዜው ሲያልቅ ቱግ ያደርጋል ። በጊዜው ሲሆን ይታደሳል ፣ የወደፊት ጉዞን እንድንቀጥል ያደርገናል ። ያለ ጊዜው ሲሆን በፍጹም አይታደስም ፣ የወደፊት ጉዞን እንድንቀጥል ሳይሆን እንድናቆም ያስገድደናል ። ከመሄድ መመለስ አምራጭ የሌለው ምርጫ ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ መጨረሻው አቅም ማጣት ነው ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ ግን መጨረሻው ተስፋ ማጣት ነው ። አቅም ስናጣ ፈጣሪ አቅም ይሆነናል ። ተስፋ ስናጣ ግን ፈጣሪ አቅም አይሆነንም ። ምክንያቱም ተስፋ ስናጣ ፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ነውና የምናጣው ። መንፈሰ ጠንካራ ሰዎች አቅም ሊያጡ ይችላሉ ። በፍጹም ግን በፈጣሪ ላይ ያላቸውን እምነት እና ተስፋ አያጡም ። መንፈሰ ጠንካራ ያልሆኑ ሰዎች ግን ፣ አቅም አጥተው ሳይሆን አቅም እያላቸው በፈጣሪ ተስፋ ይቆርጣሉ ፣ እምነታቸውን ያጣሉ ። አዲስ አቅም አያገኙም ፣ ባይሆን የነበራቸውን አቅም ያጣሉ ። ስለዚህ ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ መንፈሰ ጠንካራ ያደርጋል ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ ግን መንፈሰ ደካማ ያደርጋል ።

         ያለ ጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ውጤቱ ስሜታዊነት ነው ። ሳያስቡ ሳያሰላስሉ ሳያመዛዝኑ ፣ ዘሎ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ግን መጨረሻው ምክንያታዊነት ነው ። ከመወሰን በፊት ማሰብን ማስቀደም መርህ ይሆናል ። ማሰብን መወሰን ሲቀድም ስሜታዊነት ነው ።

 ውሳኔን ሀሳብ ሲቀድም ምክንያታዊነት ነው ። ውሳኔ ሲፈጥንም ሲዘገይም ችግር ይፈጠራል ። ሲፈጥን የስሜት ውጤት ስለሆነ ራሳችንን ያሳጣናል ። ሲዘገይ ደግሞ ፍጹምነትን ( perfectionism ) መፈለግ ስለሆነ የምንፈልገውን ያሳጣናል ። ራሳችንንም ሆነ የምንፈልገውን እንዳናጣ ፣ ትእግስታችን ያለ ጊዜው ሳይሆን በጊዜው እንዲያልቅ ጥንቃቄ እናድርግ ። ችግር በገጠመን ቁጥር ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። ያኔ ለውሳኔ ያልፈጠነ ግን ደግሞ ያልዘገየ ምርጥ ሰው እንሆናለን ።

              ትእግስት ያለ ጊዜው ሲያልቅ መማሪያ ያደርጋል ። በጊዜው ሲያልቅ ግን አርአያ ያደርጋል ። ሰው መማሪያ ሲሆን ፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንደሌለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን ግን ፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንዳለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን የስኬት ተምሳሌት ይሆናል ። መማሪያ ሲሆን ደግሞ የውድቀት ምሳሌ ይሆናል ። ድክም እስኪለን ከታገስን ብንወድቅም እንንሳለን ። ቱግ ካልን ግን ላንነሳ እንወድቃለን ። እስከ መጨረሻው የታገሰ ጥሩ ታሪክ ትቶ ያልፋል ። እስከ መጨረሻው ያልታገሰ ግን መጥፎ ታሪክ ጥሎ ያልፋል ። ትእግስት መጨረሻ አለው ። ለዚህም ነው ታላቁ መጽሐፍ ‘’ እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል የሚለው ’’ ።  ቱግ ማለት የትእግስት መጨረሻው ሳይሆን ያለማለቁ ምልክት ነው ። ድካም ግን የትእግስት መጨረሻ ማሳያ ነው ። ስንናደድ ልንጠፋ ነው ። ስንደክም ግን ልንድን ነው ።

 መዳን ማለት መትረፍ መትረፍረፍ ፣ የጥሩ ነገር ምሳሌ ፣ የስኬት ተምሳሌት መሆን ነው ። መጥፋት ማለት ደግሞ የመጥፎ ነገር ፣ የውድቀት ምሳሌ መሆን ነው ። ስለዚህ ሀደራ ትእግስታችን ያለ ጊዜው እንዳያልቅብን ፣ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። መጨረሻችን መዳን እንጅ መጥፋት አይሆንም ።

          ‘’ ትእግስት የህይወት ቁልፍ መርህ ነው ። ’’                                                


Monday, April 21, 2025

እይታ | Perception

                                                        የትውልድ ቅብብሎሽ

               ለውጥ ስር ነቀል ሲሆን የትውልድ ቅብብሎሽ አይኖርም ። ለውጥ ስር ነቀል ነው  ብሎ ማመን ፣ ትላንት ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ፣ ጥሩ ነገር የለውም ማለት ነው ። ህይወት ጥቁር ወይም ነጭ እንጅ ግራጫ መልክ የላትም እንደ ማለት ነው ። የህይወት እውነታ ግን ይህን አያሳይም ። ትላንት ፍጹም ጥሩ ወይም ፍጹም መጥፎ ሊሆን አይችልም ። ሙሉ በሙሉ ትክክል ወይም ስህተት ሊሆን አይችልም ። የትላንት ታሪክ የሰዎች ታሪክ ነው ። የትላንት ስራ የሰዎች ስራ ነው ። ሰዎች ደግሞ ትክክልም ስህተትም ይሰራሉ ። ጥሩም መጥፎም ያደርጋሉ ። በስር ነቀል ለውጥ ማመን ፣ ይህንን መሰረታዊ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መካድ ወይም አለመቀበል ነው ። 

             የሰው ልጅ በብዛት መጥፎ ከሰራ ፣ በቀጣዩ ትውልድ በመጥፎ ታሪኩ ይወሳል ። ያ ማለት ግን ምንም ጥሩ ስራ የለውም ማለት አይደለም ። ከመጥፎ ስራው ብዛት አንጻር ፣ ጥሩ ስራው በቀላሉ የመታወስ እድል  ስለማይኖረው ነው ። በሌላ በኩል በብዛት ጥሩ ከሰራ ፣ ጥሩ ታሪኩ ለትውልዱ ይነገርለታል ። ይህ ማለት ግን መጥፎ ስራ የለውም ፣ መልአክ ነው ማለት አይደለም ። ከጥሩ ስራው አንጻር ፣ መጥፎ ታሪኩ ወደ ፊት ከመቀጠል ይልቅ በቀላሉ ስለሚቃጠል ነው ። ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ ስለሚረሳ ነው ። የስራ የመታወስ አቅሙ ብዛቱ ነው ። ብዙ ጥሩ ከሰራን ፣ በብዙ ሰዎች እና በትውልድ ልብ ውስጥ በመልካምነት እንታወሳለን ። ትንሽ ከሰራን ግን ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ እንረሳለን ። በተመሳሳይ ብዙ መጥፎ ከሰራን ፣ በክፋት ስማችን በትውልዱ ይነሳል ። ትንሽ ከሰራን ግን ፣ አይደለም ለትውልድ ሊሻገር ፣ ከቤት የማይሻገር ታሪክ ሆኖ ይቀራል ። 

            ጥሩ ከመጥፎ ሲበዛ መልካም ያስብላል ። መጥፎ ከጥሩ ሲበዛ ክፉ ያስብላል ። ልክነት ከስህተት ሲበዛ ጎበዝ ያሰኛል ። ስህተት ከልክነት ሲበዛ ሰነፍ ያሰኛል ። መልካም ፣ ጎበዝ እና ክፉ ሰዎች ታሪክ ይኖራቸዋል ። ሰነፎች ግን ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። ሰው ጎበዝ ሆኖ ክፉ ከሆነ ፣ ትውልድ ከክፋቱ ሳይሆን ከጉብዝናው ይማራል ። ጎበዝም መልካምም ከሆነ ፣ ከጉብዝናውም ከመልካምነቱም ይማራል ። ሰነፍ ከሆነ ግን ምንም ስለሌለው ፣ ትውልድ ከእርሱ ምንም አይማርም ። ሰነፍ ሰው እና ዳተኛ ትውልድ ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። አይደለም የታሪክ አሻራ ፣ የጣት አሻራ ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም ። ክፉ እውቀት ከመሀይምነት ይከፋል ( Bad knowledge is more danger than ignorance ) ቢባልም ፣ ምንም አለማወቅ ክፉ ባያደርግም ፣ የክፋት ተባባሪ ያደርጋል ። ምንም አለማወቅ የዋህ ሳይሆን ጅል ነው የሚያደርገው ። የዋህነት ከክፋት ነጻ መሆን ነው ። ጅልነት ግን ከእውቀት ነጻ መሆን ነው ። ከክፉም ከመልካም እውቀት ባዶ መሆን ነው ። ከክፉ እውቀት ይልቅ ፣ ከእውቀት ነጻ መሆን ቢሻልም ግን ጥሩ አይደለም ። ጥሩውም ልኩም ፣ መልካሙን መያዝ ክፉውን መጣል ነው ። ሁሉን መያዝ ፣ ሁሉን መጣል አይቻልም ። መርጦ መያዝ ፣ መርጦ መተው ግን ይቻላል ። ስለዚህ ምርጫችንን እናስተካክል ። ምክንያቱም ምርጫችን ነው ሰውም አውሬ የሚያደርገን ። መልአክም ሰይጣንም የሚያደርገን ። ስንፍና ግን በምንም ሚዛን አያዋጣም ። 

         መልአክ እና የሰው መልአክ ይለያያሉ ። መልአክ ፍጹም ነው ። የሰው መልአክ ግን ፍጹም አይደለም ። በተመሳሳይ አውሬ እና የሰው አውሬ ይለያያሉ ። አውሬ ርህራሄ የለውም ፣ ፍጹም ጨካኝ ነው ። የሰው አውሬ ግን ፍጹም ጨካኝ አይደለም ። በትንሹም ቢሆን ልቡ መራራቱ አይቀርም ። ሰው ከሰው መልአክ ብዙ መማር አለበት ። ከሰው አውሬ ግን ትንሽ ነው መማር ያለበት ። ትንሽም ተማረ ብዙም ተማረ ፣ ዋናው ነገር መማር መቻሉ ነው ። ለውጥ ደግሞ የመማር ውጤት ነው ። ለመማር ነገርን ከስሩ መንቀል ሳይሆን የሚያዋጣው ፣ ነገርን ከስሩ መመልከት ነው የሚያስፈልገው ። ትላንትን ከስሩ መንቀል ሳይሆን ፣ ችግርን ከስሩ መንቀል ነው መፍትሔው ። '' አረምን መንቀል ስር ሳይሰድ ነው ። '' እንዲሉ አበው ፣ ለለውጥ አረምን እንጅ አለምን መንቀል አያዋጣም ። ስር ነቀል ለውጥ ግን አረምን ሳይሆን አለምን መንቀል ነው ። ስለዚህ ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂ ነው ። ስር ነቀል ለውጥ የዋህነት የጎደለው ልባምነት ፣ ይቅር ባይነት የሌለው ትጋት ነው ። ከሰው መልአክም ከሰው አውሬም መማር አለመቻል ነው ። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ሊኖር የሚችለውን የወደፊት ጉዞ ይገታል ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ትውልድ ያፈርሳል እንጅ አይገነባም ። ታሪክ ያቃጥላል እንጅ አያስቀጥልም ። ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰው ታሪክ ሀብት ነው ። ዝግጁ ላልሆነ ግን ታሪክ ሸክም ነው ። ሉሲ ፣ አክሱም ፣ ፋሲለደስ ፣ ጀጎል እና ላሊበላ ላወቀበት ሀብት ናቸው ። ላላስተዋለ ግን ዘበት ናቸው ። ትክክለኛ ለውጥ ሁሉን ጥሎ ማለፍ ሳይሆን ፣ መጥፎውን ጥሎ ጥሩውን ይዞ መሻገር ነው ። ጥሎም አንጠልጥሎም ማለፍ ነው ። ያኔ እንደ አዲስ የሚገነባ ታሪክ ሳይሆን ፣ በሂደት የሚገነባ ታሪክ ይኖረናል ። መሳሪያ የሚቀባበል ትውልድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እና ስራ የሚቀባበል ትውልድ ይታነጻል ። ሆ ብሎ የሚያቃጥል ሳይሆን ፣ ሀ ብሎ የሚያስቀጥል ትውልድ ይነሳል ። በስሜት የሚያፈርስ ሳይሆን በስሌት የሚገነባ ትውልድ ይፈጠራል ። ስር ነቀል ለውጥ ፣ ለውጥን ከመፍጠር በላይ ነውጥን የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው ። ምክንያቱም በዚህ የለውጥ ሂደት ፣ መነካት የሌለበት የህዝብ ልብ የሚነካ ነገር ሊወድም ይችላል ። መጥፋት የሌለበት ሀገራዊ  ማንነት በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል ። ሀገር ያለ ካስማ እና ያለ ምሶሶ መና ልትቀር ትችላለች ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ፣ ከልማቱ ጥፋቱ ፣ ከአዎንታዊነቱ አሉታዊነቱ ይገዝፋል ። ስለዚህ ለውጥ ጥገናዊ እንጅ ስር ነቀል መሆን የለበትም ። የተበላሸውን እያስተከከሉ ፣ የተዛነፈውን እያቃኑ ፣ የደፈረሰውን እያጠሩ ፣ በነበረው ጥሩ ነገር ላይ አዲስ ነገር እየጨመሩ መሄድ ነው ጥገናዊ ለውጥ ። የዚህ ለውጥ መርህ ፣ ታሪክ እየረሱ እና እየጣሉ መሄድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እየጠበቁ እና እየገነቡ ወደ ፊት መሄድ ነው ። የትውልድ ቅብብሎሽ እውን የሚሆነው ፣ ለውጥ ጥገናዊ ሲሆን ነው ። 

        ጥገናዊ ለውጥ የደግነት እና የትህትና ውጤት ነው ። ለመስጠት ደግነት ያስፈልጋል ። ለመቀበል ትህትና ግድ ይላል ። የሚሰጥ ደግ ኖሮ ፣ የሚቀበል ትሁት ከሌለ ችግር ነው ። የሚቀበል ትሁት ኖሮ ፣ የሚሰጥ ደግ ከሌለ ታሪክን ለመቀበልም ለማስቀጠልም ከባድ ነው ። ስለዚህ ቀዳሚው ትውልድ ለማስተማር እና ለመስጠት ደግ መሆን አለበት ። ተከታዩ ትውልድ ደግሞ ለመማር እና  ለመቀበል ትሁት መሆን አለበት ። ያኔ የትውልድ ቅብብሎሽ እውን ይሆናል ። 

    '' ጥገናዊ ለውጥ ለትውልድ ቅብብሎሽ አስፈላጊ ነው ። ''     

Saturday, April 19, 2025

እይታ | Perception

                                                           ንቃተ ህሊና

         ንቃተ ህሊና ያለው ሰው ነገሮችን በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ይችላል ። ቀላል እና ከባድ ችግሮችን በቀላሉ መለየት ይሆንለታል ። ፍሬን ከገለባ ፣ ነገርን ከቁም ነገር ፣ ቆሻሻን ከንጹህ ፣ አጭበርባሪን ከሀቀኛ ለይቶ መመደብ መታወቂያው ነው ። ንቃተ ህሊና የእውቀት ብቻ ሳይሆን ፣ የልምድ እና ያወቁትን የመኖር ውጤት ነው ። ሰው የቱንም ያህል ቢያውቅ ፣ ሺ መጽሐፍ ቢያነብ ፣ ያወቀውን በተግባር እስካልኖረው ድረስ ፣ አወቀ እንጅ ነቃ አይባልም ። የእውቀት መኖሪያ መሆን ሳይሆን ፣ እውቀትን መኖር ነው ንቃተ ህሊናን የሚፈጥረው ። ብዙ ማወቅ ትንሽ መኖር ንቃተ ህሊናን አያጎለብትም ። ትንሽም ቢሆን ያወቁትን ያህል መኖር ነው ፣ የንቃተ ህሊና ባለቤት የሚያደርገው ። 

          ብዙ ያወቁ ግን ያልነቁ ሰዎች አሉ ። ምክንያቱ ምንም አይደለም ፣ ያወቁትን በአግባቡ መኖር አለመቻላቸው ነው ። እውቀትን የማይኖሩ ሰዎች ፣ በንቃት ከመኖር ይልቅ በንቀት ይሞላሉ ። ያወቁትን የሚኖሩ ሰዎች ግን በንቃት ያድጋሉ ። ንቃት ማበላሸት ሳይሆን ማስተካከል ነው ። ማደፍረስ ሳይሆን ማጥራት እና ማጣራት ነው ። ማጣመም ሳይሆን ማቃናት ነው ። ብዙ እናውቃለን የሚሉ ግን ያልነቁ ሰዎች ፣ ማበላሸት እንጅ ማስተካከል አይችሉም ። ለማደፍረስ እንጅ ለማጥራት ጊዜ የላቸውም ። ለማጣመም እንጅ ለማቃናት የሚሆን ህሊና የላቸውም ። ምክንያቱም ንቀት ስላለባቸው ቀና ማሰብ አይችሉም ። ተንኮለኛ እንጅ ጥበበኛ መሆን አይችሉም ። ንቃት ጥበበኛ ያደርጋል ። ንቀት ደግሞ ተንኮለኛ ያደርጋል ። 

        እውቀት ልህቀት የሚሆነው ስንነቃ ነው ። አልያ ግን ሊቅነት ሳይሆን ልቅነት ይፈጠራል ። ሊቆች ሳይሆኑ ፣ ልቅ የሆኑ አዋቂዎች እውቀትን ማኖር እንጅ መኖር አይችሉም ። ሀቀኛ ሳይሆኑ አስመሳይ ናቸው ። የሚኖሩት ከአንጀታቸው ሳይሆን ከአንገታቸው ነው ። ወሬ እንጅ ወረት የላቸውም ። ለእነርሱ መናገር ቀላል ነው ። መኖር ግን እጅግ ከባድ ነው ። የወሬ አዋርድ ቢኖር ፣ የመጀመሪያ ተሸላሚ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው ። ወሬ እና አውሬ ውስጣቸው አለ ። እውነት እና ፍቅር ግን ውስጣቸው የለም ። እውነተኛ ሰይጣን የት ነው መገኛው ? ቢባል ፣ ምንም አያጠራጥርም አስመሳይ ሰው ውስጥ ነው ። ሰይጣን አዋቂ በሆኑ አስመሳይ ሰዎች ይቀናል ። በተንኮላቸው ሰይጣንን የሚያስቀኑ ብቸኛ ፍጥረት ፣ አስመሳይ ሰዎች ናቸው ። እነርሱ ደግሞ ንቀት እንጅ ንቃት የላቸውም ። 

       ንቃተ ህሊና ያላቸው ሰዎች ጨለማን የሚገፉ ብርሃን ናቸው ። ጨለማን የሚያስፋፉ ክፉ ሰዎች ግን ፣ ንቃተ ህሊና ሳይሆን ንቀተ ህሊና ነው ያላቸው ። ማስለቀስ እንጅ ማጽናናት አይችሉም ። እነርሱ ለምድር ደራሽ ጎርፍ ፣ ለሰዎች ደግሞ የሀዘን ጎርፍ ናቸው ። ለገንዘብ የሚሳሱትን ያህል ፣ ለሰው ነፍስ አይሳሱም ። መሰብሰብ እና ማከማቸት ይችላሉ ። መስጠት እና ማካፈል ግን በዞሩበት አይዞሩም ። እነርሱ ትርፋቸው የሌሎች ኪሳራ ነው ። ስኬታቸው የሌሎች ውድቀት ነው ። ክብራቸው የሌሎች ውርደት ነው ። ደስታቸው የሌሎች ሃዘን ነው ። 

       የነቁ ብርሀን የሆኑ ሰዎች ግን ፣ የሌላው ሀዘን ሀዘናቸው ነው ። በደስታቸው ይደሰታሉ ፣ ሲያጡ ይከፋሉ ፣ ሲራቡ ከልብ ያዝናሉ ። እነርሱ ምግብ ሲያጡ ሳይሆን ፣ ሰው ሲያጡ ነው የሚራቡት ። ውሀ ሲያጡ ሳይሆን ፍቅር ሲያጡ ነው ከልብ የሚጠሙት ። ሰው ሲቸገር ሳይሆን መከራን ሲሻገር ደስ ይላቸዋል ። ካወቁት ማካፈል ፣ ካገኙት መስጠት የህሊና እርካታ ይሰጣቸዋል ። የሚገድሉ መርዝ ሳይሆኑ ፣ የሚፈውሱ መድሀኒት ናቸው ። መድሀኒት በመስጠት ፣ እርዳታም በመስጠት ፣ ሰውን ከከፉ በሽታም ሆነ ከክፉ ነገር ያድናሉ ። እነርሱ ዉስጣቸውም ውጪያቸውም ያው አንድ ነው ። ውስጣቸው ቦሌ ፣ ውጪያቸው ጉለሌ አይደለም ። ያወሩትን ይኖራሉ ፣ የኖሩትን ያወራሉ ። ስራ መፍጠር እንጅ ወሬ መፍጠር ብዙ አይችሉበትም ። ማስመሰል ጠላታቸው ፣ እውነተኝነት ደግሞ ወዳጃቸው ነው ። አስመስለው ከሚኖሩ ፣ ከእውነት ጋር ቢቀበሩ ይመርጣሉ ። ግዴታ ከሆነ ፣ ሰውን ለማዳን ሲሉ ሊያስመስሉ ይችላሉ ። በተረፈ ሰው እንዲሞት ብለው በፍጹም አያስመስሉም ። ለፍቅር ያስመስላሉ ፣ ለጥላቻ ግን አይደለም ቦታ ፣ ትርፍ ቦታም የላቸውም ። የእነርሱ ማስመሰል ለሰዎች መርዝ ሳይሆን መድሀኒት ነው ። ሁከት ሳይሆን ሰላም ነው ። ውድቀት ሳይሆን ስኬት ነው ። 

       '' ንቃተ ህሊና ለህሊና ለአካባቢ ለሰዎች ሰላም ወሳኝ ነው ። ''     

Friday, April 18, 2025

እይታ | Perception

                                                           ጽኑዕ እምነት

       ጽኑዕ እምነት ከጥርጣሬ የነጻ ነው ። ከጥርጣሬ በፊት ያለ ጽኑዕ እምነት ፣ የየዋህነት ውጤት ነው ። መጠራጠር ከሌለ መመራመር አይቻልም ። ማሰብ ማሰላሰል ማመዛዘን አይኖርም ። ሁሉም ነገር ማሰብ ማሰላሰል ላያስፈልገው ይችላል ። ሁሉንም ሳያሰላስሉ እንዲሁ መቀበል ደግሞ መዘዙ ከባድ ነው ። ቀላል እና ግልጽ ነገርን በየዋህነት ማመን ብዙ ጉዳት አይኖረውም ። ከባድ እና ውስብስብ ነገርን በየዋህነት መቀበል ግን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም ። የዋህነት የሚወልደው ጽኑዕ እምነት ደካማ ነው ። ልብን ለሌላ አዲስ እይታ ክፍት እንዳይሆን ቆልፎ ይይዛል ። ልብን የሚቆልፍ እይታ ደግሞ ጽንፈኛ ያደርጋል ። ልብን የሚከፍት እምነት ግን መጽናኛ ያደርጋል ። ልብ ቆላፊ እምነት ትክክለኛ እምነት ሳይሆን አጉል እምነት ነው ። አጉል እምነት ደግሞ በእውቀት ላይ ሳይሆን ፣ በልማድ ላይ ነው የሚመሰረተው ። ልማድ እውቀትን ሲቀድም በአብዛኛው ጥሩ አይሆንም ። እውቀትን ተከትሎ የሚገነባ ልማድ ግን ፣ ሁል ጊዜ ባይሆንም በብዛት ጥሩ ነው ። 

           የዋህነት በእውቀት ሲገዘገዝ ሳይሆን ሲታገዝ ጥሩ ነው ። የዋህነት ከተገዘገዘ ሁሉን ተጠራጣሪ ያደርጋል ። በእውቀት ከታገዘ ግን ሁሉን መርማሪ ያደርጋል ። ሰው ከጥርጥር ወደ ምርምር ከሄደ ትክክለኛ አማኝ ይሆናል ። ከጥርጥር ወደ ምርምር መሄድ ካልቻለ ግን ተንኮለኛ ከሀዲ ይሆናል ። ምንም ጭብጥ (fact) አለማግኘት ፣ የሰውን ልጅ ተጠራጣሪ ያደርጋል ። ጭብጥ (fact) ማግኘት ተመራማሪ ያደርገዋል ። ተመራማሪ ከጭብጥ (fact) ወደ ሙሉ እውነት (truth) ይሄዳል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን መሄድ አይችልም ። ጭብጥ እምነትን ይፈጥራል ። እምነት ደግሞ በእውን የማይታየውን ሙሉ እውነት ፣ ግልጽ አድርጎ በምናብ ያሳየናል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን ንባብ እንጅ ምናብ ስለሌለው  ለማመን ይቸገራል ። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ፣ የቱንም የህል ብናውቅ ፣ የዋህነትን ማጣት የለብንም ። የዋህነት እና እውቀት ሲደጋገፉ ፣ ትክክለኛ እምነት እና ጥሩ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና እውቀት ሲነቃቀፉ ግን ፣ አጉል እምነት እና መጥፎ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና ክፉ እውቀት አብረው አይሄዱም ። መልካም እውቀት ከየዋህነት ጋር ግን በጣም ይዋደዳሉ ። እምነታችሁ ትክክለኛ እና ጽኑዕ እንጅ አጉል እንዳይሆን ፣ መልካሙን ሁሉ እወቁ የዋህነታችሁንም ጠብቁ ። 

           ሰው በየዋህነቱ ከሚከፍለው ዋጋ በላይ ፣ የዋህነቱን በማጣቱ ይከፍላል ። በየዋህነት ብዙ መከራ ሊደርስብን ይችላል ። ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ፣ የዋህነት መጨረሻው ክብር ነው ። የዋህነትን ማጣት ግን ፍጻሜው ውርደት ነው ። የባለጸጎች ትምክህት ፣ የዋህነትን ከማጣት የሚመጣ ነው ። የአዋቂዎች ተንኮል የዋህነትን የመተው ውጤት ነው ። የባለስልጣኖች ግፍ ፣ የዋህነትን ከመናቅ የመነጨ ነው ። እምነት እና ይቅር ባይነት የየዋህነት ውጤት ናቸው ። በዚህች ምድር ላይ መተማመን ከሌለ ፣ ህይወትም ስራም ከባድ ይሆናል ። በደልን መርሳት ከሌለ ፣ አብሮ መኖር ጭንቅ ይሆናል ። ማመን ፋታ ይሰጣል ። አለማመን ፋታ ይነሳል ። በደልን መርሳት ሰላም ያሰፍናል ። በደልን መያዝ ሁከት ይፈጥራል ። የሰላም ቁልፉ የዋህነት ነው ። ያለ የዋህነት ሰላምን ማሰብ በጣም ከባድ ነው ። የውጭ ሰላም የውስጥ ሰላም ነጸብራቅ ነው ። የውስጥ ሰላም ደግሞ በደልን የመርሳት ስጦታ ነው ። በደልን መርሳት የሚቻለው ፣ የዋህነትን ገንዘብ ማድረግ ሲቻል ነው ። ለሰላም የዋህነት ፣ ለጠንካራ እምነት ደግሞ ልባምነት አስፈላጊ ናቸው ። የዋህነት ብቻውን እምነትን ጠንካራ አያደርግም ። ጠንካራ እምነት የሚፈጠረው ፣ የዋህነት በልባምነት ሲደገፍ ነው ። 

            ልባምነት ጥንቃቄ ነው ። ሰውን ተማራማሪ የሚያደርገው ልባምነት ነው ። ስራ በጥንቃቄ ካልተሰራ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ። ገንዘብ በጥንቃቄ ካልተያዘ ባክኖ ይቀራል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ መድሀኒት መርዝ ይሆናል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ ትዳር ፣ ልጆችን ልጎዳና ይዳርጋል ፣ ባል እና ሚስትን ላጤ አድርጎ ያስቀራል ። ጥንቃቄ የጎደለው የስልጣን አያያዝ ወህኒ ያስወርዳል ። ለዚህ ደግሞ የምንሰራውን ማወቅ ፣ የምናውቀውን መስራት መለማመድ አለብን ። ያኔ ልባም እንሆናለን ። አልያ ልበ ቢስ እንሆናለን ። የምንሰራውን የማናውቅ ፣ የምናውቀውን ለመስራት የማንፈልግ ከንቱዎች እንሆናለን ። አንድን ነገር አውቀን ከሰራን ፣ እምነታችን የልማድ ሳይሆን የልምድ ውጤት ይሆናል ። በደመነፍስ ከሰራን ግን እምነታችን የልማድ ውጤት ይሆናል ። ልምድ ጥሩ ልማድ ነው ። መጥፎ ልማድ ግን ልምድ ሳይሆን ለምድ ነው ። የሰውን ልጅ እውነተኛ ማንነት የሚጋርድ ሽፋን ነው ። ከእውቀት የመነጨ መጥፎ ልማድ ፣ የክፋት ውጤት ነው ። ባለ መገንዘብ የተፈጠረ ልማድ ግን የየዋህነት ውጤት ነው ። ልባምነት ከሁለቱም ነጻ የሚያወጣን ሀይል ነው ። ልባምነት የዋህነትን ከአደጋ የሚጠብቅ ወታደር ነው ። ሰው በየዋህነት ብቻ ሲኖር ፣ ሁል ጊዜ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ይኖራል ። ልባም ከሆነ ግን ፣ ራሱን ከጦርነት ቀጠና ይጠብቃል ። ጽንፈኝነት ፣ ዘረኝነት ፣ አክራሪነት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ፣ የዋህነት የወለዳቸው ጽኑዕ እምነቶች ናቸው ። ልብ የሚቆልፉ እምነቶች ። ከዚህ አጉል እምነት የሚታደገን ልባምነት ነው ። ጥሩውን ከመጥፎው ፣ ትክክሉን ከስህተቱ ፣ ገለባውን ከፍሬው የሚለይልን ወንፊት ነው ልባምነት ። የዋህነት እምነትን ይፈጥራል ። ልባምነት ደግሞ እምነትን ፍጹም ያደርጋል ። የዋህነት የእምነት መስረት ነው ። ልባምነት የእምነት ጉልላት ነው ። በየዋህነት እንዲሁ እናምናለን ። በልባምነት ግን አጥርተን እናምናለን ። የጠራ እምነት ደግሞ ልብን ዝግ ሳይሆን ክፍት ያደርጋል ። 

           ክፍት ልብ ትሁት ልብ ነው ። ከዘመድም ከባዳም ፣ ከሀብታምም ከደሀ ፣ ከባለስልጣንም ከተራ ፣ ከአዋቂም ከልጅም የተሻለ ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነው ። ትሁት ልብ ሚዛናዊ ነው ። ለራሱም ለማንም አያዳላም ። ለእውነት እና ለተሻለው ሀሳብ ያዳላል ። እምነታችን ጽኑዕ ብቻ ሳይሆን ፣ ጠንካራና ትክክለኛ እንዲሆን ፣ የዋህነት ብቻውን በቂ አይደለም ፣ ልባምነት በጣም ያስፈልጋል ። 

       '' እምነትን ለመፍጠር የዋህነት ግድ ይላል ፣ እምነትን ለማጠንከር ልባምነት ያስፈልጋል ። ''       

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...