ጽኑዕ እምነት
ጽኑዕ እምነት ከጥርጣሬ የነጻ ነው ። ከጥርጣሬ በፊት ያለ ጽኑዕ እምነት ፣ የየዋህነት ውጤት ነው ። መጠራጠር ከሌለ መመራመር አይቻልም ። ማሰብ ማሰላሰል ማመዛዘን አይኖርም ። ሁሉም ነገር ማሰብ ማሰላሰል ላያስፈልገው ይችላል ። ሁሉንም ሳያሰላስሉ እንዲሁ መቀበል ደግሞ መዘዙ ከባድ ነው ። ቀላል እና ግልጽ ነገርን በየዋህነት ማመን ብዙ ጉዳት አይኖረውም ። ከባድ እና ውስብስብ ነገርን በየዋህነት መቀበል ግን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም ። የዋህነት የሚወልደው ጽኑዕ እምነት ደካማ ነው ። ልብን ለሌላ አዲስ እይታ ክፍት እንዳይሆን ቆልፎ ይይዛል ። ልብን የሚቆልፍ እይታ ደግሞ ጽንፈኛ ያደርጋል ። ልብን የሚከፍት እምነት ግን መጽናኛ ያደርጋል ። ልብ ቆላፊ እምነት ትክክለኛ እምነት ሳይሆን አጉል እምነት ነው ። አጉል እምነት ደግሞ በእውቀት ላይ ሳይሆን ፣ በልማድ ላይ ነው የሚመሰረተው ። ልማድ እውቀትን ሲቀድም በአብዛኛው ጥሩ አይሆንም ። እውቀትን ተከትሎ የሚገነባ ልማድ ግን ፣ ሁል ጊዜ ባይሆንም በብዛት ጥሩ ነው ።
የዋህነት በእውቀት ሲገዘገዝ ሳይሆን ሲታገዝ ጥሩ ነው ። የዋህነት ከተገዘገዘ ሁሉን ተጠራጣሪ ያደርጋል ። በእውቀት ከታገዘ ግን ሁሉን መርማሪ ያደርጋል ። ሰው ከጥርጥር ወደ ምርምር ከሄደ ትክክለኛ አማኝ ይሆናል ። ከጥርጥር ወደ ምርምር መሄድ ካልቻለ ግን ተንኮለኛ ከሀዲ ይሆናል ። ምንም ጭብጥ (fact) አለማግኘት ፣ የሰውን ልጅ ተጠራጣሪ ያደርጋል ። ጭብጥ (fact) ማግኘት ተመራማሪ ያደርገዋል ። ተመራማሪ ከጭብጥ (fact) ወደ ሙሉ እውነት (truth) ይሄዳል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን መሄድ አይችልም ። ጭብጥ እምነትን ይፈጥራል ። እምነት ደግሞ በእውን የማይታየውን ሙሉ እውነት ፣ ግልጽ አድርጎ በምናብ ያሳየናል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን ንባብ እንጅ ምናብ ስለሌለው ለማመን ይቸገራል ። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ፣ የቱንም የህል ብናውቅ ፣ የዋህነትን ማጣት የለብንም ። የዋህነት እና እውቀት ሲደጋገፉ ፣ ትክክለኛ እምነት እና ጥሩ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና እውቀት ሲነቃቀፉ ግን ፣ አጉል እምነት እና መጥፎ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና ክፉ እውቀት አብረው አይሄዱም ። መልካም እውቀት ከየዋህነት ጋር ግን በጣም ይዋደዳሉ ። እምነታችሁ ትክክለኛ እና ጽኑዕ እንጅ አጉል እንዳይሆን ፣ መልካሙን ሁሉ እወቁ የዋህነታችሁንም ጠብቁ ።
ሰው በየዋህነቱ ከሚከፍለው ዋጋ በላይ ፣ የዋህነቱን በማጣቱ ይከፍላል ። በየዋህነት ብዙ መከራ ሊደርስብን ይችላል ። ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ፣ የዋህነት መጨረሻው ክብር ነው ። የዋህነትን ማጣት ግን ፍጻሜው ውርደት ነው ። የባለጸጎች ትምክህት ፣ የዋህነትን ከማጣት የሚመጣ ነው ። የአዋቂዎች ተንኮል የዋህነትን የመተው ውጤት ነው ። የባለስልጣኖች ግፍ ፣ የዋህነትን ከመናቅ የመነጨ ነው ። እምነት እና ይቅር ባይነት የየዋህነት ውጤት ናቸው ። በዚህች ምድር ላይ መተማመን ከሌለ ፣ ህይወትም ስራም ከባድ ይሆናል ። በደልን መርሳት ከሌለ ፣ አብሮ መኖር ጭንቅ ይሆናል ። ማመን ፋታ ይሰጣል ። አለማመን ፋታ ይነሳል ። በደልን መርሳት ሰላም ያሰፍናል ። በደልን መያዝ ሁከት ይፈጥራል ። የሰላም ቁልፉ የዋህነት ነው ። ያለ የዋህነት ሰላምን ማሰብ በጣም ከባድ ነው ። የውጭ ሰላም የውስጥ ሰላም ነጸብራቅ ነው ። የውስጥ ሰላም ደግሞ በደልን የመርሳት ስጦታ ነው ። በደልን መርሳት የሚቻለው ፣ የዋህነትን ገንዘብ ማድረግ ሲቻል ነው ። ለሰላም የዋህነት ፣ ለጠንካራ እምነት ደግሞ ልባምነት አስፈላጊ ናቸው ። የዋህነት ብቻውን እምነትን ጠንካራ አያደርግም ። ጠንካራ እምነት የሚፈጠረው ፣ የዋህነት በልባምነት ሲደገፍ ነው ።
ልባምነት ጥንቃቄ ነው ። ሰውን ተማራማሪ የሚያደርገው ልባምነት ነው ። ስራ በጥንቃቄ ካልተሰራ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ። ገንዘብ በጥንቃቄ ካልተያዘ ባክኖ ይቀራል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ መድሀኒት መርዝ ይሆናል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ ትዳር ፣ ልጆችን ልጎዳና ይዳርጋል ፣ ባል እና ሚስትን ላጤ አድርጎ ያስቀራል ። ጥንቃቄ የጎደለው የስልጣን አያያዝ ወህኒ ያስወርዳል ። ለዚህ ደግሞ የምንሰራውን ማወቅ ፣ የምናውቀውን መስራት መለማመድ አለብን ። ያኔ ልባም እንሆናለን ። አልያ ልበ ቢስ እንሆናለን ። የምንሰራውን የማናውቅ ፣ የምናውቀውን ለመስራት የማንፈልግ ከንቱዎች እንሆናለን ። አንድን ነገር አውቀን ከሰራን ፣ እምነታችን የልማድ ሳይሆን የልምድ ውጤት ይሆናል ። በደመነፍስ ከሰራን ግን እምነታችን የልማድ ውጤት ይሆናል ። ልምድ ጥሩ ልማድ ነው ። መጥፎ ልማድ ግን ልምድ ሳይሆን ለምድ ነው ። የሰውን ልጅ እውነተኛ ማንነት የሚጋርድ ሽፋን ነው ። ከእውቀት የመነጨ መጥፎ ልማድ ፣ የክፋት ውጤት ነው ። ባለ መገንዘብ የተፈጠረ ልማድ ግን የየዋህነት ውጤት ነው ። ልባምነት ከሁለቱም ነጻ የሚያወጣን ሀይል ነው ። ልባምነት የዋህነትን ከአደጋ የሚጠብቅ ወታደር ነው ። ሰው በየዋህነት ብቻ ሲኖር ፣ ሁል ጊዜ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ይኖራል ። ልባም ከሆነ ግን ፣ ራሱን ከጦርነት ቀጠና ይጠብቃል ። ጽንፈኝነት ፣ ዘረኝነት ፣ አክራሪነት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ፣ የዋህነት የወለዳቸው ጽኑዕ እምነቶች ናቸው ። ልብ የሚቆልፉ እምነቶች ። ከዚህ አጉል እምነት የሚታደገን ልባምነት ነው ። ጥሩውን ከመጥፎው ፣ ትክክሉን ከስህተቱ ፣ ገለባውን ከፍሬው የሚለይልን ወንፊት ነው ልባምነት ። የዋህነት እምነትን ይፈጥራል ። ልባምነት ደግሞ እምነትን ፍጹም ያደርጋል ። የዋህነት የእምነት መስረት ነው ። ልባምነት የእምነት ጉልላት ነው ። በየዋህነት እንዲሁ እናምናለን ። በልባምነት ግን አጥርተን እናምናለን ። የጠራ እምነት ደግሞ ልብን ዝግ ሳይሆን ክፍት ያደርጋል ።
ክፍት ልብ ትሁት ልብ ነው ። ከዘመድም ከባዳም ፣ ከሀብታምም ከደሀ ፣ ከባለስልጣንም ከተራ ፣ ከአዋቂም ከልጅም የተሻለ ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነው ። ትሁት ልብ ሚዛናዊ ነው ። ለራሱም ለማንም አያዳላም ። ለእውነት እና ለተሻለው ሀሳብ ያዳላል ። እምነታችን ጽኑዕ ብቻ ሳይሆን ፣ ጠንካራና ትክክለኛ እንዲሆን ፣ የዋህነት ብቻውን በቂ አይደለም ፣ ልባምነት በጣም ያስፈልጋል ።
'' እምነትን ለመፍጠር የዋህነት ግድ ይላል ፣ እምነትን ለማጠንከር ልባምነት ያስፈልጋል ። ''
No comments:
Post a Comment