Tuesday, August 12, 2025

እይታ | Perception

                                                            የማያዛልቅ ነገር

    የማያዛልቅ ነገር ጊዜያዊ ነው ። መጨረሻ የሌለው ቅጽበታዊ ነገር ነው ። አለ ሲባል የሚጠፋ ፣ ጠፋ ሲባል የሚኖር አወዛጋቢ ነገር ነው ። የማያዛልቅ ነገር ስሜትን የመናጥ አቅም አለው ። ስሜትን ሰቅዞ በመያዝ ሰውን በቀላሉ ምርኮ ማድረግ ይችላል ። በቶሎ የሚለመድ ግን በቀላሉ የማይላቀቅ መንቻካ ነው ። አያዛልቅም ግን ደግሞ አይላቀቅም ። የማያዛልቅ ነገር ክብርን ፍቅርን ስሜትን ስልጣንን ጊዜያዊ ነው የሚያደርገው ። የማያዛልቅ ነገር መርህ አይመቸውም ። መርህ ደግሞ ለማያዛልቅ ነገር ቦታ የለውም ። መርህ የማይለዋወጥ ወጥ ነገር ነው ። የማያዛልቅ ነገር ግን ጋጠወጥ ነው ። በመርህ መኖር ፣ በህግና በስርዓት መኖር ነው ። ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ፣ ህገወጥ እና ስርዓት አልበኛ ያደርጋል ። 

    መርህም ሆነ ስርዓት በሂደት ነው የሚገነቡት ። በአንድ ጀምበር የማይለመዱ ፣ ውድ ነገሮች ( quality ) ናቸው ። ወድ ስለሆኑ ሰውንም ውድ ክብሩንም ዘላለማዊ ማድረግ ይችላሉ ። ቅጽበታዊ ነገር ርካሽ ነው ። ለቅጽበታዊ ነገር መገዛት ርካሽነት ነው ። ጥራት የጎደለው እቃ ርካሽ እንደሚሆነው ፣ ለማያዛልቅ ነገር የሚገዛ ሰው ርካሽ ነው የሚሆነው ። ወርቅ መሆን የሚችለው መዳብ ይሆናል ። ሸክላ መሆን የነበረበት ገል ይሆናል ። ሊቅ መሆን የነበረበት ደቂቅ ይሆናል ። ምሁር መሆን የሚችለው መሀይም ይሆናል ። ባለጸጋ መሆን የሚችለው ደሀ ይሆናል ። ክቡር መሆን የሚችለው ወራዳ ይሆናል ። ምክንያቱም መርህ አልባ ሰዎች ጎደሎ ናቸው ።

     ለማያዛልቅ ነገር መገዛት በጉድለት ውስጥ መኖር ነው ። እየጎደሉ ሙሉ መሆን አይቻልም ። እያነሱ መብዛት አይኖርም ። እየገደሉ ማዳን የማይታሰብ ነው ። በመርህ መኖር የጎደለን እየሞሉ መሄድ ነው ። በሂደት መልካም ነገርን ማሳደግ ፣ ክብርንም መጨመር ነው ። በመርህ ውስጥ የጎደለ ይሞላል ፣ ያነሰ ይበዛል ፣ የተዋረደ ከፍ ይላል ፣ የተበላሸ ሁሉ ይስተካከላል ። ለጊዜያዊ ነገር መገዛት ግን መስተካከል የሌለው መበላሸት ነው ፣ መመለስ የሌለው መውጣት ነው ፣ መዳን የሌለው መታመም ነው ፣ መነሳት የሌለው መውድቅ ነው ። በመርህ መኖር መጀመሪያ ያማል ፣ መጨረሻው ግን ያምራል ። ጊዜያዊ ነገር መጀመሪያ ያምራል ፣ መጨረሻ ለይ ግን ያማል ። ሰው ደግሞ መጀመሪያው አማረም አላመረም ችግር የለውም ። መጨረሻው ሲያምር ነው ደስ የሚለው ። ተከብሮ ከመዋረድ ፣ ተዋርዶ መከበር ይሻላል ። ይህ የሚሆነው በመርህ መኖር ሲቻል ነው ።  

    ዓላማ እና የማያዛልቅ ነገር አይዋደዱም ፣ ሆድና ጀርባ ናቸው ። የማያዛልቅ ነገር ለዓላማ እንቅፋት ነው ። ዓላማ ደግሞ ለጊዜያዊ ነገር አለርጂ ነው ። በዓላማ መኖር ሩቅ አስቦ ሩቅ ለማደር መታገል ነው ። ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ቅርብ አስቦ ቅርብ ማደር ነው ። ዓላማ የማይታየውን ማሳየት ይችላል ። በዓላማ መኖር ከሚታየው በላይ ለማይታየው ነገር ዋጋ መስጠት ነው ። በማያዛልቅ ነገር መሸነፍ ለማይታየው ሳይሆን ለሚታየው ነገር ዋጋ መስጠት ነው ። ለሚታይ ነገር መገዛት እንጭጭነት ነው ። ለማይታይ ነገር መገዛት ግን ብስለት ነው ። ሰው እምነተ ጠንካራ የሚሆነው ፣ እምነቱን በሚያየው ነገር ላይ ሲመስርት ሳይሆን ፣ በማይታይ ነገር ላይ ሲመሰርት ነው ። እምነተ ደካሞች በሚታይ ነገር ያምናሉ ። እምነተ ጠንካሮች በሚታይም በማይታይም ነገር ያምናሉ ። ተጠራጣሪዎች በሚታየውም በማይታየውም ቶሎ አያምኑም ።

   በጊዜያዊ ነገር ማመን ፣ እምነተ ደካማ መሆን ነው ። የዓላማ ሰዎች ግን እምነተ ጠንካሮች ናቸው ። ለዓላማ መኖር ከቅርቡ ይልቅ የሩቁን መመልከት ነው ። ለማያዛልቅ ነገር እጅ መስጠት የሩቁን ሳይሆን የቅርቡን ማየት ነው ። የቅርቡን ማየት ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ማለት አይደለም ። የቅርብ ነገሮች ዋጋ የሚኖራቸው ፣ ለሩቁ ነገር ግብዓት ሲሆኑ ነው ። ሩቅ ላለ ነገር ግብዓት መሆን ያልቻለ ቅርብ ነገር ፣ ዋጋ ያሳጣል እንጅ ዋጋ አያሰጥም ። ዋጋው ይወርዳል እንጅ ከፍ አይልም ። ወርቅ የሚሆነው መዳብ ይሆናል ። አልማዝ የሚሆነው ተራ የመንደር ድንጋይ ይሆናል ። የሩቁን ነገር አጥርቶ መመልከት ፣ የቅርቡን ነገር በአግባቡ ለመጠቀም ይረዳል ። በአላማ ስንኖር እጃችን ላይ ያለውን ነገር ትክክለኛ ዋጋ እናውቃለን ። የማያዛልቅ ነገር ዓላማን የሚጋርድ ጥቁር መጋረጃ ነው ። 

    የማያዛልቅ ነገር ደማቅ ነው ፣ አይነ ግቡ ነው ። ከፍተኛ የስበት ሀይል ( gravitational force ) አለው ። የማያዛልቅ ነገርን መከላከል እንጅ መጋፈጥ ብዙ አያዋጣም ። '' ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ '' እንደሚባለው ፣ ለጊዜያዊ ነገር ቅድመ ጥንቃቄ ነው የሚያስፈልገው ። ለምሳሌ ጫትን ብንወስድ ለብዙ ወጣቶች ደምቆ ነው የሚታየው ፣ በጣም ያስጎመጃል ነገር ግን እድሜን ይፈጃል ። ጫት ለጊዜያዊ ደስታ እንጅ ለዘላቂ ደስታ ምንም አስተዋጸኦ የለውም ። መጀመሪያ ያደምቃል መጨረሻ ላይ ግን ያደቃል ። ጅማሬው ደስታ ነው ፣ ፍጻሜው ግን ሀዘን ነው ። ሱሰኛ ነገን ዛሬ አይኖርም ። ነገን ዛሬ ይገድላል ። በዛሬ ውስጥ የሞተ ነገ ደግሞ እድሜን በእጥፉ ነው የሚቀንሰው ። የማያዛልቅ ነገር እድሜ ማባከኛ እንጅ ፣ እድሜ ማራዘሚያ ወይም መጠቀሚያ ሊሆን አይችልም ። የማያዛልቅ ነገርን የሙጥኝ ማለት መጨረሻው ብክነት ነው ። 

     የማያዛልቅ ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አይደለም ። ነገር ግን ስሜት ለማያዛልቅ ነገር ቅድሚያ በመስጠት የተካነ ነው ። ሰው ደግሞ ከምንም በላይ ለስሜቱ ተገዥ ነው ። ስሜቱን መቆጣጠር የቻለ ሰው ፣ ለማያዛልቅ ነገር ፊት አይሰጥም ። ስሜታቸውን መግዛት የተሳናቸው ሰዎች ግን ፣ ፊታቸውን ብቻ አይደለም ልባቸውን ጭምር ነው ለማያዛልቅ ነገር አሳልፈው የሚሰጡት ። ሰው ልቡ ለጊዜያዊ ነገር ሲገዛ ፣ ማክበር ያለበትን ይንቃል ፣ መያዝ ያለበትን ይለቃል ። መገንባት ያለበትን ያፈርሳል ። ማንሳት ያለበትን ነገር ይጥላል ። መተው ያለበትን ነገር የሙጥኝ ይላል ። የሚጎዳውን እየተከተለ ፣ የሚጠቅመውን እየሸሸ ይኖራል ። ጥሩ ነገር የሚያመው ፣ መጥፎ ነገር የሚያስደስተው ብላሽ ይሆናል ። ለማያዛልቅ ነገር ፊት መስጠት መጨረሻው መበላሸት ነው ። 

     የማያዛልቅ ነገር ከጤና ይልቅ በሽታ ነው ። ክብር ሳይሆን ውርደት ነው ። ነጻነት ሳይሆን ባርነት ነው ። ሱስ ህመም ነው ፣ ሀሜት ውርደት ነው ፣ ሌብነት ባርነት ነው ። አለው አለው ባይነት መጨረሻው ባዶነት ነው ። ስርዓት ማጣት ፍጻሜው ሰውነትን ማጣት ነው ። መዝናናት ማብዛት መጨረሻው መጉላላት ነው ። ፊልም ሲበዛ ህይወትን ቅዠት ያደርጋል ። አሉባልታ ሲበዛ ህይወትን ጣዕም አልባ ያደርጋል ። በጠቅላላው ለማያዛልቅ ነገር መገዛት ፣ የህይወትን ጉዞ የከፍታ ሳይሆን የቁልቁለት ነው የሚያደርገው ። ለሁሉ ነገር ትክክለኛ ዋጋ እንዲኖረን የህይወት ዓላማ ይኑረን ። በመርህ እንኑር ። ያኔ መዳቡ ወርቅ ይሆናል ። ተራ ድንጋይ የመሰለን የከበረ አልማዝ ይሆናል ። 

       '' የሁሉም ነገር ዋጋ ያለው አላማ ውስጥ ነው ። አላማ ከሌለን አይደለም የሌላን ነገር ዋጋ ፣ የራሳችንን ዋጋ አናውቅም ። ''            


Saturday, August 9, 2025

እይታ | Perception

                                                             አጋጣሚን መፍጠር 

    አጋጣሚ ያልታሰበ ነገር ነው ። የታሰበ ነገር ሁሉ አጋጣሚ ሊሆን አይችልም ። አጋጣሚ ድንገቴ ነው ። በድንገት ማጣት መሞት መለያየት መክሰር መጎዳት አጋጣሚዎች ናቸው ። ማጣት ብቻ አይደለም ፣ ማግኘትም ድንገተኛ ከሆነ አጋጣሚ ነው ። አጋጣሚ ሀዘንም ደስታም ነው ። ዕጣም ጣጣም ነው ። መርገምም በረከት ነው ። ስኬትም ውድቀትም ነው ። ክብርም ውርደትም ነው ። አጋጣሚ ብዙ ነገር ነው ። አጋጣሚ የምን ውጤት ነው ቢባል ፣ በቀላሉ መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ነው ። በቃ አጋጣሚ የእጣ ፈንታ ጉዳይ ነው ። በአጋጣሚ የማያምኑ ሰዎች ፣ አጋጣሚ የሚባል ነገር የለም ይላሉ ፣ ነገር ግን እነርሱ የለም ስላሉ አጋጣሚ አይኖርም ማለት አይደለም ። አጋጣሚ የፈጣሪ ድንቅ ጥበብ መገለጫ ነው ። አጋጣሚ የለም ማለት ሰው የተጻፈለት ታሪክ እንጅ ራሱ የሚጽፈው ታሪክ የለውም ማለት ነው ። የራሱ አሻራ ( legacy ) አይኖረውም ። የመምረጥ ነጻነትም ሊኖረው አይችልም ። የሰው ልጅ የነጻነቱ ማሳያ አንዱ አጋጣሚ ነው ። ፈጣሪ የሰው ልጅ የተጻፈለትን ብቻ እንዲኖር ሳይሆን ፣ አዲስ ታሪክ ጽፎ እንዲኖር ነጻ አድርጎ ነው የፈጠረው ። በዚህ የነጻነት ጉዞ ውስጥ ፣ አጋጣሚ ለሰው ልጅ ፈተና እና እድል ሆኖ ይከሰታል ። 

   አጋጣሚ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል ። ጥሩ አጋጣሚ እድል ነው ። መጥፎ አጋጣሚ ፈተና ነው ። ብልሆች መጥፎ አጋጣሚን ወይም ፈተናን ወደ እድል መቀየር ይችሉበታል ። ጥሩ አጋጣሚን ወይም እድልን በአግባቡ መጠቀምም ያውቁበታል ። ሰነፎች ግን ፈተናን ወይም መጥፎ አጋጣሚን ወደ እድል መቀየር አይችሉም ። እድልን ወይም ጥሩ አጋጣሚን መጠቀምም አይችሉም ። ሰነፎች እድልን ወደ ፈተና ፣ በረከትን ወደ መርገም ፣ መፍትሄን ወደ ችግር ፣ ዕጣን ወደ ጣጣ መለወጥ ነው የሚችሉት ። ድንገት ያገኙትን ምርጥ ወዳጅ ጠላት ያደርጉታል ። እድል ሆኖ የመጣላቸውን ገንዘብ ሱስ ይገዙበታል ። መኪና የሚገዙበትን እድል ቁማር ላፍ ያደርግባቸዋል ። የሚከበሩበትን እድል አላግባብ በመጠቀም ይዋረዱበታል ። ፍቅሩን ጥላቻ ፣ ፈውሱን በሽታ ፣ መድሀኒቱን መርዝ ያደርጋሉ ። አጋጣሚ ከምንም በላይ መማሪያ ነው ። ጥሩ አጋጣሚ ማለፊያ ነው ። መጥፎ አጋጣሚ ደግሞ መማሪያ ነው ። እንዲህ የሚሆነው ግን ለሰነፎች ሳይሆን ለብልሆች ነው ። ለሰነፎች ጥሩ አጋጣሚ መዋረጃ ፣ መጥፎ አጋጣሚ ደግሞ መማሪያ ሳይሆን መማረሪያ ነው ። 

   ህይወት አጋጣሚ ባይኖር የሆነ አይነት ጣዕም ይጎድላታል ። አጋጣሚ የህይወት ቅመም ማጣፈጫ ነው ። በመጥፎም ይሁን በጥሩ ፣ መጠቀም ለቻለ አጋጣሚ ቅመም ነው ። መጠቀም ላልቻለ ግን ቅመም ሳይሆን ቂም ነው የሚሆነው ። ቂም ደግሞ የህይወት ማምረሪያ ሬት ነው ። ምክንያቱም ይህ ቂም የሚሆነው በፈጣሪ ላይ ነው ። ሰው ያለምንም እድል እና ፈተና ፣ እቅዱን ማሳካት መቻሉ ደስታውን ሙሉ አያደርግለትም ። እቅድ አጋጣሚን ይወልዳል ፣ አጋጣሚ ደግሞ ደስታን ሙሉ ያደርጋል ። በአጋጣሚ ያልተፈተነ ወይም በእድል ያልታገዘ እቅድ ፣ በሰው ውስጥ አዲስ ስሜትን የመፍጠር አቅም አይኖረውም ። ስለዚህ ህይወት ወይ በድል አሊያም በእድል ነው ሙሉ የምትሆነው ። ስላቀድን ብቻ ህይወት ሙሉ አትሆንም ፣ ሙሉነትም አይሰማንም ። ለዚህም ነው '' plan for expected as well as un expected. '' የሚባለው ። ለምንጠብቀው ብቻ ሳይሆን ለማንጠብቀውም ነገር መዘጋጀት ግድ ነው ። ያኔ አጋጣሚን ለመጠቀም በቂ ስነ ልቦናዊ አቅም ይኖረናል ። አልያ በአጋጣሚ ምክንያት አቅም ሳይሆን የሚፈጠረው ፣ ቅስም ነው የሚሰበረው ።

   ሰው አስቦ አጋጣሚን መፍጠር ባይችልም ፣ አስቦ ማቀዱ ግን አጋጣሚ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል ። መልካም አጋጣሚ የማቀድ ውጤት ነው ። '' ሰው ያቅዳል ፈጣሪ ይፈጽማል ። '' አይደል የሚባለው ። አጋጣሚ ፈጣሪ የሰው ልጅ እቅዱን እንዲያሳካ የሚቸረው ድንቅ ስጦታ ነው ። አጋጣሚ ዝግጁ ለሆነ ሰው እንጅ ፣ ዝግጁ ላልሆነ አይሰጥም ። እቅድ ዝግጅት ነው ። ማቀድ የቻለ ሰው አጋጣሚን ለመቀበል ዝግጁ ነው ። ማቀድ ያልቻለ ደግሞ አጋጣሚን ለመቀበልም ለመጠቀምም አቅም አይኖረውም ። ሰው በአጋጣሚ ብቻ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ። እቅድ እና አጋጣሚ ተባብረው ነው ፣ ለውጥን ዘላቂ የሚያደርጉት ። አጋጣሚን ለመፍጠር በእቅድ መኖር አስፈላጊ ነው ። በአጋጣሚ እየኖረ የከበረ የለም ። በእቅድ እየኖረ በአጋጣሚ የከበረ ግን ብዙ ነው ። እቅድ አጋጣሚን ሲቀድም ለውጥ አዎንታዊ ይሆናል ። አጋጣሚ እቅድን ሲቀድም ግን ለውጥ አሉታዊም አዎንታዊም የመሆን እድል ይኖረዋል ። ይህ የሚወሰነው እንደየሰው አስተሳሰብ እና አቀባበል ነው ። ጎበዝ ሰዎች አጋጣሚን ይፈጥራሉ ይጠቀማሉ ። ሰነፎች ግን የተፈጠረን አጋጣሚ ያባክናሉ ። አጋጣሚ እንዳይባክን በእቅድ እና በዝግጅት እንኑር ።

  ጊዜን ማባከን አጋጣሚን ማባከን ነው ። ጊዜን በግባቡ መጠቀም አጋጣሚን መፍጠርም መጠቀምም ነው ። ጊዜም አጋጣሚም የፈጣሪ ችሮታዎች ናቸው ። በሁለቱም ላይ የሰው ልጅ ስልጣን የለውም ። ሁለቱንም መጠቀም እንጅ ማዘዝ አይችልም ። ለመጠቀም መታዘዝ ፣ ለመታዘዝ ትሁት መሆን አስፈላጊ ነው ። አጋጣሚ ለትሁታን በረከት ነው ። ለእብሪተኞች ግን መቅሰፍት ነው ። '' ለሀጥዓን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል '' እንዲባል ፣ መቅሰፍቱ ለመልካሞች  ሊተርፍ ይችላል ። አጋጣሚ መልካም እንዲሆን ፣ ጊዜን ለመልካም ነገር እናውል ። ጊዜ አጋጣሚን ይጠብቃል ፣ አጋጣሚም ጊዜን ይጠብቃል ። በጊዜው የሚከሰት አጋጣሚ ሸክም አቅላይ ነው ። ያለጊዜው የሚከሰት አጋጣሚ ግን ሸክም አቅላይ ሳይሆን ራሱ ሸክም ነው ። ሸክም አጋጣሚ ነገር የመሸከም ውጤት ነው ። ጥላቻን በቀልን ቂምን የመሸከም ማሳያ ነው ። ስለዚህ በህይወታችን መልካም ነገር እንዲገጥመን ፣ ጥላቻን ቂምን ብቀልን አንሸከም ። ፍቅርን ይቅርታን የዋህነትን እንሽከም ። ያኔ እድል በሆነው መልካም አጋጣሚ ህይወት ሰላም እና ቀላል ትሆናለች ። 

          '' ማቀድ የሰው ድርሻ ነው ። አጋጣሚ የፈጣሪ ችሮታ ነው ። ''   

                                                                

Monday, August 4, 2025

እይታ | Perception

                                                            ፍቅር እና መስፈርት

   ፍቅር መርህ እንጅ መስፈርት የለውም ። መስፈርት ለፍቅር ምንም ነው ። ለፍቅር ሰው ምንም ይሁን ምን ፣ ይኑረው አይኑረው ሰው መሆኑ ብቻ በቂ ነው ። በፍቅር ዘንድ የሰው መርዘም ወይም ማጠር ፣ ዋጋውን ከፍ ወይም ዝቅ አያደርገውም ። መቅላት ወይም መጥቆር የሚጨምረው የሚቀንሰው ነገር የለም ። ጌታም ይሁን ባርያ ከመፈቀር የሚያግደው አይኖርም ። ለመፈቀር ሰው ዶክተር እንጅነር ፕሮፌሰር ባለጸጋ ወይም አዋቂ መሆን አይጠበቅበትም ፣ መልካም ሰው መሆኑ በቂ ነው ። ለፍቅር የሰው ማእረጉ ሳይሆን መልካምነቱ ነው የሚያስፈልገው ። በትጋት ጎበዝ የሆኑ ሰዎች ፣ ለመልካምነት ግን ሰነፍ የሆኑ ሰዎች ፣ በፍቅር ዘንድ ዋጋ የላቸውም ። ትጋት ያስከብራል ግን ለስራ ባለን ፍቅር እንጅ ለሰው ባለን ፍቅር  አይደለም ። ለስራ ያለን ፍቅር ብቻ ሰው አያደርገንም ፣ ለሰው ያለን ፍቅር ነው ሰው የሚያደርገን ። ስለዚህ ስራ ስንሰራ ለሰው እንደምንሰራ እያሰብን እንስራ ። ያኔ ፍቅር ሰውን ለመጥቀም እንጅ ለመጉዳት መስራት እንደሌለብን ያሳስበናል ። ይህ የፍቅር መስፈርት ሳይሆን መርህ ነው ። 

   ሰው ገንዘብ ስላለው ሊከበር ይችላል ። ያለፍቅር ግን በገንዘቡ ብቻ ሊወደድ አይችልም ። ሰው መወደድም መከበርም የሚችለው ፣ በገንዘቡ ላይ መልካምነትን ሲጨምር ነው ። ገንዘብ ሲቀነስ ፍቅር ፣ እኩል ይሆናል ክብር ሲቀነስ መወደድ ። መወደድ የሌለው ክብር ሰውን በሰው ልብ ውስጥ አያነግስም ። ክብር ከፍቅር ጋር ነው በሰው ልብ ላይ የሚያነግሰው ። ገንዘብ ክብርም ፍቅርም መሆን ይችላል ። ሰው በገንዘቡ መልካም ስራ ከሰራበት ፣ በገንዘቡ ፍቅርንም ክብርንም ያተርፋል ። በገንዘቡ ግን ክፋት ከሰራበት ፣ ተፈርቶ  ሊከበር ይችላል ፣ ነገር ግን ተወዶ ሊከበር በፍጹም አይችልም ። ተፈርቶ ከመከበር ተወዶ መከበር የተሻለ ነው ። የክብር የመጨረሻው ከፍታ ( climax ) ፍቅር ነው ። ገንዘብን የክብር ምንጭ ማድረግ የክብርን ከፍታ ሳይሆን የሚያሳየን ፣ የሞራል አዘቅት ነው የሚሆንብን ። ገንዘብ የፍቅር መሳርያ እንጅ ፍቅር የገንዘብ መሳርያ ሊሆን አይችልም ። ገንዘብን የፍቅር መሳርያ ካደረግን ፣ በገንዘባችን መልካም ስራ በመስራት ፣ ከክብር ሁሉ የላቀውን ክብር ማግኘት እንችላለን ። ፍቅርን ግን የገንዘብ መሳርያ ካደረግን ፣ የላቀውን ክብር ሳይሆን በፈጣሪ ዘንድ የተናቀውን ክብር ነው የምናገኘው ። ይህ ክብር እውነተኛ ሳይሆን አርተፊሻል ነው ። ዘላለማዊ ሳይሆን ጊዜያዊ ነው ። ከሰው ልብ ሳይሆን ከሰው አፍ ብቻ የሚገኝ ክብር ነው ። ስለዚህ ፍቅር በገንዘብ አይሰፈርም ፣ ነገር ግን ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም ይችላል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ።     

    ፍቅርና ውበት አብረው ይሄዳሉ ። ከዉጪ ይልቅ የውስጥ ውበት ለፍቅር ቅርብ ነው ። ፍቅር የሚታይ ሳይሆን የሚኖር ነው ። ውስጣዊ ውበትም በመኖር የሚገነባ ስብእና ነው ። ስለዚህ ውስጣዊ ውበት እና ፍቅር በጣም ይጣጣማሉ ። ውጪያዊ ውበት ግን ለጊዜያዊ ስሜት ቅርብ ነው ። ምክንያቱም ውጪያዊ ውበት የሚታይ እንጅ የሚኖር አይደለም ። '' ሲያዩት ያላመረ ሲበሉት ያቅራል '' ይባላል ። ይህ ለምግብ እንጅ ለሰው ልጅ አይሰራም ። ሲያዩት ያማረ ሰው ፣ አብረው ሲኖሩ ያቅር ይሆናል ። ሲያዩት ያላማረው ግን ለፍቅር ምቹ ሊሆን ይችላል ። የአፍንጫ ጎራዳ ወይም ሰልካካ መሆን ለፍቅር ግድ አይሰጠውም ። ካማረ አይን በላይ ያማረ አመለካከት ለፍቅር አስፈላጊ ነው ። ከዉብ ከንፈር በላይ ውብ ንግግር ፍቅርን ይማርከዋል ። ከለስላሳ ጸጉር በላይ ለስላሳ ባህሪ ፍቅርን ይገዘዋል ። ትህትና ውበት ነው ። ፍቅር ካለ ትህትና አለ ። ችምችም ካለ ጥርስ በላይ ትህትና ሰውን ውብ ያደርጋል ። ትሁት ሰው ውብ ነው ፣ ውጪያዊ ሳይሆን ውበቱ ውስጣዊ ነው ። ደግነት ውበት ነው ። ደግነት የሚኖረው ፍቅር ባለበት ነው ። ከተስተካከለ ቁመና በላይ ደግነት ሰውን ውብ የማድረግ አቅም አለው ። ርህራሄም ውበት ነው ። ያለ ፍቅር ርህራሄ አይታሰብም ። ከአለንጋ ጣት በላይ ርህራሄ ለሰው ልጅ ውበቱ ነው ። የሰው እውነተኛ ውበቶች ርህራሄ ደግነት ትህትና ቅንነት እና የመሳሰሉት ናቸው ። እነዚህ ደግሞ በሌላ አነጋገር የፍቅር መገለጫዎች ናቸው ። ፍቅር ከውብ አካል በላይ ውብ ስብእና ይገዛዋል ። ይህ ሌላኛው የፍቅር መርህ ነው ። 

   ከፍቅር ሁሉ የላቀው ፍቅር ፈጣሪን መውደድ ነው ። ሲቀጥል የሰውን ልጅ መውደድ ነው ። ከእነዚህ አካላት ውጪ የሰው ልጅ አብልጦ ሊወደው የሚችለው ነገር ሊኖር አይገባም ። እነርሱን በማስቀደም ሌላን ነገር መውደድ ይችላል ። ነገር ግን ከእነርሱ አስቀድሞ የሚወደው ነገር ሊኖር አይገባም ። ከሰው አብልጦ ገንዘብን መውደድ ገብጋባነት ነው ። ገብጋባነት ደግሞ እንስሳነት ነው ። ከሰው ይልቅ እንስሳን መውደድ ልበቢስነት ነው ። ልበቢስነት እንሰሳነት ነው ። እንሰሳነትም ልበቢስነት ነው ። ከሰው ይልቅ ሱስን መውደድ ልበ ደንዳናነት ነው ። ከልጆቹ ቁማር የበለጠበት አባት ልበ ደናዳና ነው ። ከሚስቱ ይልቅ አልኮል የሚናፍቀው ባል ልበ ደንዳና ነው ። ለባል ሳይሆን ለሀሜት ቅድሚያ የምትሰጥ ሚስት ልበ ደንዳና ናት ። ከሰው በላይ እውቀትን የሚወዱ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። ከእውቀት ክብርን ለማግኘት ብለው ፍቅረኛቸውን ችላ ያሉ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው ። እውነተኛ ፍቅር ለሁሉም ውይም ከሁሉ ነገር ይልቅ ሰውን ማስቀደም ነው ። እውቀትን ገንዘብን ቁስን ሱስን አብልጦ መውደድ ሰውን ያሳጣል ። ሰውን አብልጦ መውደድ ግን እውቀትንም ገንዘብንም አያሳጣም ። ሰውን ማጣት ሁሉን ማጣት ነው ። ሰውን ማግኘት ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ማለት ሰውን እንደራስ በመውደድ ሁሉን ማግኘት ነው ። ፍቅር ካለ ሁሉም አለ ፣ ፍቅር ከሌለ ምንም የለም ። ይህ ከሁሉ የላቀው የፍቅር መርህ ነው ።  

    '' ፍቅር መነሻም መድረሻም ነው ። ምክንያቱም የመርሆች ሁሉ አለቃ ነው ። ''                 

እይታ | Perception

                                                    ስሜታዊነት እና እምነት     እምነት በስሜት አይገነባም ። እምነት ሲሞቀን የምንገነባው ፣ ሲበርደን ደግሞ የምናፈርሰው ወረት አይደለም ። ...