ስንፍና
ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉን መስራት አይችልም ። ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ብቻ ነው ። ደካማ ጎን የሌለው ፣ ጠንካራ ጎኑ ብቻ የሚነገርለት አካል ፈጣሪ ብቻ ነው ። የሰው ልጅ ግን ደካማ እና ጠንካራ ጎን አለው ። አንዱ ጠንካራ በሆነበት ሌላው ደካማ ሊሆን ይችላል ። ሌላው ጠንካራ በሆነበት አንደኛው ደግሞ ደካማ ነው ። በቃ ይህ የህይወት እውነታ ነው ። በአንድ ነገር ደካማ መሆን ግን ስንፍና አይደለም ። ስንፍና መስራት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ፣ ምንም መስራት አለመቻል ነው ። መስራት እየቻሉ መለገም ፣ ማንበብ እየቻሉ ማሳበብ ፣ መድረስ እየቻሉ መቅረት ፣ መራመድ እየቻሉ መቆም ፣ መቆም እየቻሉ መቀመጥ ፣ መቀመጥ እየቻሉ መቆመጥ ነው ስንፍና ።
ድክመት የተፈጥሮ ውጤት ነው ። ስንፍና ግን የምርጫ ውጤት ነው ። ሰው መርጦ ደካማ መሆን አይችልም ። መርጦ ግን ሰነፍ መሆን ይችላል ። ድክመትን ማሻሻል ይቻላል ፣ ማስወገድ ግን በፍጹም አይቻልም ። ስንፍናን ማስወገድ ግን ይቻላል ። ድክመትን ለማሻሻል ፈጣሪን መማጸን ግድ ነው ። ስንፍናን ለማስወገድ ግን ራስን ማሳመን በቂ ነው ። ድክመትን መቀበል እንጅ መቃወም አይቻልም ። ስንፍናን መቀበልም መቃወምም ይቻላል ። ጠንካራ ሰው ስንፍናን መቃወም የሚችል ነው ። በዚያው ልክ ድክመቱን አምኖ መቀበል የሚችል ነው ። ዳተኛ ሰው ግን ስንፍናን መቃወም አይችልም ። ድክመቱንም አምኖ መቀበል አይችልም ። ለሚያደርገው የስንፍና ድርጊት ሰበብ መፍጠር ነው የሚችለው ።
ለችግሩ መፍትሄ የማያጣ ሳይሆን ፣ ለስንፍናው ምክንያት የማያጣ ፍጥረት ነው ። ሰነፍ ማለት ደክሞ ሳይሆን አውቆ የተኛ ነው ። ’’ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም ። ‘’ ይል የለ ያገሬ ሰው ፣ ሰነፍ እንደዛ ነው ። እየቻለ የማያደርግ እያወቀ ዝም የሚል ነው ።
ንግግር አለመቻል ስንፍና አይደለም ድክመት ነው ። መናገር እየቻሉ ዝም ማለት ነው ስንፍና ። በተፈጥሮ ንግግር ላይ ደካማ የሆነ ሰው ፣ በጥረት የንግግር ችሎታውን ማሻሻል ቢችልም ፣ በፍጹም አንደበተ ርቱዕ ሊሆን አይችልም ። አንደበተ ርቱዕ ካልሆንኩ ብሎ ከሚታገል ፣ ድክመቱን አምኖ ቢቀበል ይሻለዋል ። ‘’ Change the changeable, accept the unchangeable. ‘’ እንዳለው የህይወት ክህሎት አሰልጣኙ ፣ የሚለወጠውን መለወጥ ፣ የማይለወጠውን መቀበል የተሻለ ነው ። የሚችሉት ላይ አድምቶ መስራት ፣ የማይችሉትን ለሚችሉት አሳልፎ መስጠት ብልሀት ነው ። ሁሉን ካልቻልኩ ማለት ፣ ምንም አለመቻልን ነው የሚፈጥረው ። ምንም አለመሞከር ደግሞ ስንፍናን ነው የሚፈጥረው ። መሞከር ሁሉን ወደ መቻል ሳይሆን ወደ መቻል ነው የሚወስደን ። አለመሞከር ግን ወደ ምንም አልመቻል ነው የሚወስደን ። ስንሞክር የምንችለውን እናውቃለን ፣ የማንችለውን እንለያለን ። ያኔ ድክመትን ከስንፍና እናጠራለን ።
በሁሉም ነገር ላይ ጎበዝ መሆን አይቻልም ። በምንም ነገር ላይ ጎበዝ አለመሆን ግን እርሱ ስንፍና ነው ። ሰው ያለችሎታ አይፈጠርም ። ችሎታውን ማወቅ ግደታው ነው ። ምንም ችሎታ የሌለው ሰነፍ ነው ። ሁሉም ሰው የሚችለውን አለመቻልም ስንፍና ነው ።የሰው ልጅ ሁሉ መማር ማንበብ መጻፍ እንዲችል ተደርጎ ነው የተፈጠረው ። እኔ ትምህርት ንባብ ፅሁፍ አይሆነኝም ማለት ትልቅ ስንፍና ነው ። እኔ ስእል አይሆነኝም ማለት ይቻላል ። ምክንያቱም ስእል ልዩ ተሰጥኦ ይፈልጋል ። ለአንድነት የሚሰጥ ሳይሆን ለልዩነት የሚቸር ነው ። በደፈናው እኔ ትምህርት አይሆነኝም ማለት ግን ስንፍና ነው ።
ችሎታ በሁለት ይከፈላል ። ለልዩነት የሚሰጥ እና ለአንድነት የሚሰጥ ችሎታ ነው ። ሁሉም ሰው የሚችለው ነገር የአንድነት ችሎታ ነው ። የተወሰኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ግን ለልዩነት የተሰጠ ነው ። መናገር መቻል ለሁሉ የተሰጠ ነው ። አሳምሮ መናገር ግን በልዩነት የሚሰጥ ነው ። ቀላል ሂሳብን መስራት ሁሉም ሰው ይችለዋል ። ከባድ እና ውስብስብ ሂሳብን መስራት ግን ልዩ የተፈጥሮ ዝንባሌን ይጠይቃል ። መኪናን መንዳት ለሁሉም ሰው ይቻላል ። መኪናን መስራት ግን ሁሉም ሰው አይችለውም ። ስለዚህ የአንድነት ችሎታን ማጣት ስንፍና ነው ። የልዩነት ችሎታን ማጣት ግን ድክመት ነው ወይም ያለቦታ የመገኘት ውጤት ነው ።
‘’ ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል ። ‘’ ይላል ታላቁ መጽሀፍ ። ለጣረ ሁሉ ይቻለዋል ግን አላለም ። ምክንያቱም ከጥረት እምነት ይበልጣል ። ሰው ሁሉን ማድረግ ባይችልም ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችለው ፈጣሪ ፣ በእምነቱ ምንም ማድረግ ይችላል ። ይህ የሚሆነው ስለጣረ ስለለፋ ሳይሆን ስላመነ ነው ። እዚህ ጋር ከሰው ችሎታው በላይ እምነቱ በጣም ወሳኝ ነው ። ለዚህም ነው የእምነት ሰዎች ፣ የጥረት ሰዎች ብዙ የሚደክሙበትን ፣ በቀላሉ የሚያከናውኑት ።
የሰው ልጅ ደካማ ጎኑ የሚሸፈነው በእምነት ነው ። ስንፍናው ግን በምንም አይሸፈንም ። ባይሆን በቅጣት ይወራረዳል ።
አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ አለመቻል ፣ ስንፍና ስላልሆነ ብዙ መጨነቅ ተገቢ አይደለም ። ሰው መጨነቅ ያለበት ማድረግ እየቻለ ባለማድረጉ ነው ። ምንም አለመጨነቅ ልክ አይደለም ለስንፍና ይዳርጋል ። በሁሉም ነገር መጨነቅም ልክ አይደለም ፣ ለአእምሮ ህመም ይዳርጋል ። ሰው የሚችለውን ለማድረግ በመጠኑ መጨነቅ አለበት ። የማይችለውን ለማድረግ ግን ማመን እንጅ መጨነቅ የለበትም ። የሚችለውን ለመስራት በመጨነቁ ስንፍናውን ያስወግዳል ። የማይችለውን ለማድረግ ማመኑ ፣ ድክመቱን አምኖ ለመቀበል ይረዳዋል ።
‘’ ስንፍና ልዩነትን መፍጠር አለመቻል ነው ። ድክመት ልዩነትን አምኖ መቀበል ነው ። ‘’