Monday, April 28, 2025

እይታ | Perception

                                                   ጭንቀትን መርሳት  

 

      ለሰው የጭንቀት ምክንያቱ ብዙ ነው መራብ መጠማት መክሰር ስራ ማጣት የኑሮ ውድነት ከሰው ጋር መቀያየም እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ የጭንቀትን ምክንያቶች በጠቅላላው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ብለን ልንመድባቸው እንችላለን ። ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ ሰው ራሱ ያመጣውን ጭንቀት ሲመልስም መመለስ ሲሳነውም ይስተዋላል ተፈጥሮ የሚያመጣበትን ጭንቀት ግን ቀድሞ ካልተከላከለ በስተቀር አንዴ ከሆነ አምኖ መቀበል እንጅ መልሶ መቀልበስ ፈጽሞ አይችልም ለምሳሌ የአየር ንብረትን አዛብቶ ዶፍ ዝናብ እንዳይዘንብ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ አይችልም ከሂማሊያ ተራራ በረዶ እንዳይቀልጥ መመከት አይችልም ደሃው ህዝብ በድርቅ እንዳይጎዳ መከላከል ከባድ ይሆንበታል ይህንን መቀበል እንጅ መቀልበስ አይችልም መከላከል ግን ይችላል በምን ? ከተባለ ተፈጥሮን በመንከባከብ እና በመጠበቅ አልያ ምድር በጸሃይ መጋል ብቻ ሳይሆን በካንሰር ህመምተኛ ትሞላለች ይህ በሽታ ደግሞ ፍቱን መፍትሔ ያልተገኘለት የበሽታዎች ሁሉ በኩር ነውና ለእርሱ እጅ መስጠት እንጅ መታገል እና መጋፈጥ ትርፉ ከንቱ ድካም ነው ሲቀጥል ሞትን በቀጠሮ መጠበቅ ግድ ይሆናል

ሞትን በቀጠሮ መጠበቅ ደግሞ ጭንቀትን እጅግ ከባድ ያገርገዋል ይህ በቀላሉ የሚረሳ ሳይሆን የማይረሳ ጭንቀት ነው

     ይህን መርሳት ማለት ለመማር ዝግጁ አለመሆን ነው አለመማር ደግሞ መቅለል የሚችለውን ችግር ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል በየጊዜው ለአንድ ችግር ተመሳሳይ መልስ እንድንሰጥ ያስገድደናል አንድ ሰው ለቀድሞ ችግሩ መልስ መስጠት ከከበደው ከችግሩ ተምሮ ሳይሆን በችግሩ ተማሮ ነው ያለፈው መልስ መስጠት ከቀለለው ግን ፣ በችግሩ ተማሮ ሳይሆን ከችግሩ ተምሮ ነው ያለፈው ለዚህ ነው የተማሩ ሰዎች ምን ጊዜም ችግርን አክብደው ሳይሆን አቅልለው የሚመለከቱት ዩኒቨርስቲ ገብተው የተማሩ ሳይሆን ከህይወት የተማሩ ያልተማሩ ሰዎች ደግሞ ሁል ጊዜ ችግርን አቅልለው ሳይሆን አክብደው የሚመለከቱት ፣ ዩኒቨርስቲ ገብተው መማር ስላልቻሉ ሳይሆን ፣ ከህይወት መማር ስላልቻሉ ነው ችግርን አቅልሎ ለመመልከት ከህይወት መማር ግድ ነው

          ከህይወት ለመማር ጭንቀትን ሙሉ በሙሉ መርሳት ተገቢ አይደለም ምክንያቱም ችግር ጭንቀትን ይወልዳል ጭንቀት ሀሳብን ይወልዳል ሀሳብ ፣ ጥበብ እና እውቀትን ይወልዳል ጥበብ እና እውቀት ደግሞ ችግርን ወደ መፍትሔ ፈተናን ወደ እድል ይቀይራሉ ያኔ በመጀመሪያ የከበደው ችግር ዳግም ሲከሰት ቀላል ይሆናል መቶ ኪሎ የነበረው አስር ኪሎ ይሆናል ማለት ነው  

ግን ጭንቀት ሁሉ የመፍትሔ ሀሳብ ይወልዳል ማለት አይደለም ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን እና ከመጠን በላይ ሲሆን ይለያያል

 ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን የሚያሞቅ እሳት ነው ከመጠን በላይ ሲሆን የሚያነድ እሳት ነው ስለዚህ ጭንቀት በመጠኑ ሲሆን ነው የመፍትሔ ሀሳብ የሚወልደው አልያ የመፍትሔ ሀሳብ ሳይሆን የህመም ወይም የእብደት ሀሳብ ነው የሚወልደው አሙቆ የሚያነሳሳ ሳይሆን አግሎ የሚገድል ይሆናል ።            

          ጭንቀት አማራሪም አስተማሪም ገጽ አለው ከመፍትሔ ይልቅ ችግር ላይ ካተኮርን አማራሪ ገጹ ይበዛል ከችግሩ ይልቅ መፍትሔው ላይ ካተኮርን አስተማሪ ገጹ ይሰፋል ለዚህ ደግሞ የኛ እይታ ወሳኝ ነው ደራሲው እንዳለው ‘’ አረፍተ ነገር ሲነበብ ስርዓተ ነጥብ ይታያል እንጅ አይነበብም ። በተመሳሳይ በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ እንደ ስርዓተ ነጥቡ የሚታዩ እንጅ የማይነበቡ ነገሮች አሉ አረፍተ ነገር ስናነብ ነጠላ ሰረዝ እያልን ብናነብ በጀመሪያ ስሜት አይሰጥም ፣ ሲቀጥል አረፍተ ነገሩ ትርጉም ያጣል።  እንደዚሁም በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ የማይታዩ ድርጊቶች እና ክስተቶች  የማይሰሙ ንግግሮች ቦታ ካገኙ ችግርን እድል አድርገው ሳይሆን በደል አድርገው ነው የሚያሳዩት ከዛ ህይወት ትርጉም አልባ ሆና ትሳላለች ስለዚህ በችግር ወይም በጭንቅ ጊዜ በንቀት የተሞሉ ድርጊቶች እና ክስተቶች አሉታዊ ንግግሮች ትኩረት እና ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም

ነገር ግን ተስፋ የሚሰጡ ድርጊቶች እና ትእይንቶች እምነትን የሚያጠነክሩ አዎንታዊ ንግግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል

 ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ችግርን በደል ሳይሆን እድል አድርገው ያሳዩናልና ስለዚህ እይታችንን እናስተካክል ከመጥፎው ይልቅ ጥሩውንከችግሩ ይልቅ መፍትሔውን ከፈተናው ይልቅ እድሉን በእምነት እና በተስፋ ለማየት እንጣር ያኔ የጭንቀት አማራሪ ገጹ ሳይሆን አስተማሪ ገጹ ጎልቶ ይታያል የእብደት ሀሳብ ሳይሆን የመፍትሔ ሀሳብ ይወለዳል ።  

        ጭንቀትን መርሳት ለዘላቂ ሰላም መፍትሔ አይሆንም ከችግር ወይም ከጭንቀት መማር ነው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው ጭንቀትን ለመርሳት የሚታገል ሰው ህይወቱን የሚጎዳ እርምጃ ይወስዳል ሲጨንቀው አልኮል ይታየዋል መርዝ መርዝ ይለዋል ተስፋ ቢስ ይሆናል ሞቱን ብቻ ይመኛል ለችግሩ ወይም ለጭንቀቱ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጅ ዘላቂ መፍትሔ አይታየውም  

      ከጭንቀት ለመማር የሚጥር ሰው ግን ህይወቱን የሚጠቅም እርምጃ ነው የሚወስደው ፈጣሪውን ይማጸናል መልካም ሰዎችን እርዳታ ይጠይቃል መፍትሔ ፍለጋ መጽሐፍ ያገላብጣል ለጊዜ ጊዜ ሰጥቶ ይጠብቃል ትእግስትን መርሑ ያደርጋል በጽናትም በጥናትም ችግሩን ወይም ጭንቀቱን ይሻገራል ሁሌም ተስፋ ያደርጋል በእምነት መከራን ያልፋል          

  ስለዚህ ሰው ጭንቀቱን ለመርሳት ሳይሆን መታገል ያለበት ከችግር ወይም ከጭንቀት ለመማር ነው ጥረት ማድረግ ያለበት ከጭንቀት ለመማር ስንጥር የጭንቀት ማቅለያ ስልትን እናውቃለን ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን ለህይወት ዘመን የሚያገለግል ስልት ይሆናል ጭንቀትን ለመርሳት ስንታገል ግን ራስን ማቅለያ ወይም ማጥፊያ ስልት ነው ፊታችን ላይ ድቅን የሚልብን ከጭንቀቱ የተማረ ኑሮው ይቀላል ። ጭንቀቱን ለመርሳት የታገለ ራሱ ይቀላል ። ከጭንቀት ከተማርን ጭንቀቱ ያልፋል ። ለሌላም ጊዜ ተሞኩሮ በመሆን ማለፊያ ይሆነናል ። ጭንቀትን ለመርሳት ከታገልን ግን ጭንቀቱ ሳይሆን እኛ እናልፋለን።

 

       ‘’ ጭንቀትን ከመርሳት ከጭንቀት መማር የተሻለ ነው ። ‘’   

                                 ክፍል 1

                                                                               

Sunday, April 27, 2025

እይታ | Perception

 

                       የጋራ ዓላማ

       የጋራ ዓላማ ለአብሮነት እጅግ አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን አንድ ግለሰብ ፣ የራሱ አላማ ከሌለው ፣ የጋራ አላማ ሊኖረው አይችልም ። አላማ የሌለው ሰው ፣ የአላማ ህልውና አይገባውም ። የሰው ልጅ ለአላማ እንደተፈጠረ መረዳት አይችልም ። የሰው ልጅ ለመብላት ብቻ ሳይሆን ፣ ለማብላት ጭምር እንደተፈጠረ አይታየውም ። በመልበስ ብቻ ሳይሆን ፣ በማልበስ መደሰት እንደሚችል አይሰማውም ። ያለ ዓላማ የሚኖር ሰው ፣ የማግኘት እንጅ የመገኘት ትርጉም አይገባውም ። የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን ፣ የሚለብሰውን ካገኘ በቃው ። መብላት መጠጣት መልበስ ፈልገው ፣ ለሚጣሩ ድምጾች መገኘት መቻል ለእርሱ ዋጋ ቢስ ነው ። የእርሱ መኖር ለሌሎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አያውቅም ። በሌሎች መኖር ውስጥ ፣ የእርሱ እስትንፋስ እንዳለች አይረዳም ። ህይወትን በአጋጣሚ እንጅ በእቅድ መኖር አይችልም ። በእርግጥ ሰው በእቅዱ ልክ መኖር አይችልም ። ያለእቅድ መኖር ግን ትልቅ ስንፍና ነው ። ሰው በአጋጣሚ ኖሮ ፣ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል እጅግ ያሳዝናል ። በእቅድ ኖሮ በአጋጣሚ ሞተ ቢባል ፣ የተፈጥሮ ሂደት ነው አምኖ ለመቀበል ብዙ አይከብድም ። ምክንያቱም አቅዶ የሚሞት ማንም የለም ። ምናልባት በኑሮ ጫና ወይም በተለያየ ምክንያት ፣ ሰው ራሱን ለማጥፋት ካላሰበ በቀር ። ያም ቢሆን ታስቦ ታቅዶ ሳይሆን ፣ በስሜት የሚከወን ድርጊት ነው ። ሰው አስቦ ራሱን ያድናል እንጅ ራሱን አይገድልም ። ማሰብ ማለት የሚጠቅመውን የተሻለውን መምረጥ ነው ። አለማሰብ ደግሞ የሚጎዳውን የባሰውን መወሰን ወይም መምረጥ ነው ።

        ያለ ዓላማ መኖር ያለ ማሰብ ውጤት ነው ። ሰውን ሰው የሚያደርገው ማሰብ መቻሉ ነው ። በደመ ነፍስ ከመኖር የሚታደገው ማሰቡ ነው ። የማይታየውን ማየት ፣ የማይሰማውን መስማት ፣ ከቁሱ አለም ጀርባ መንፈሳዊ አለም እንዳለ ማመን እና ማረጋገጥ የቻለው በማሰቡ ነው ። እንስሳት ለመኖር ምቹ ተፈጥሮ ይፈልጋሉ ። ምክንያቱም ተፈጥሮን ምቹ የማድረግ ብቃት የላቸውም ። እነርሱ ጫካው ምድረ በዳ ሲሆን ጥለው ይሸሻሉ ። አልያ ሁሉም አንድ በአንድ ፣ የሞት ሲሳይ ይሆናሉ ። ይህ የሚሆነው ማሰብ ስለማይችሉ ነው ። ሰው ግን እንደዛ አይደለም ፣ ማሰብ ስለሚችል ተፈጥሮ ምቹ ባትሆንም ፣ ምቹ ተፈጥሮን መፍጠር ይችላል ። ምድረበዳን ዉብ መኖርያ ማድረግ ይችላል ። ግን ይህን የማድረግ ብቃት ያለው ፣ ዓላማ ያለው ሰው ነው ። ዓላማ የሌለውማ ማሰብ ስለማይችል ፣ እንደ እንስሶቹ ምቹ ተፈጥሮን ይፈልጋል ። አልያ ሞት አፈፍ አድርጎ ይቀበለዋል ። የተሻለ ለማሰብ ዓላማ ያስፈልጋል ። ሰው ዓላማ ከሌለው ደመነፍሳዊ ይሆናል ። በደመነፍስ ያለ ሰው ፣ በስሜት እንጅ በማስተዋል መኖር አይችልም ። በስሜት ደግሞ የተሻለ ማሰብ በፍጹም አይቻልም ።

           አላማ አቅጣጫ ነው ። የህይወት መነሻም መድረሻም ነው ። አላማ የሌለው ሰው አቅጣጫ ቢስ ነው ። መነሻም መድረሻም የለውም ። እድሜው እንዲሁ ይሄዳል ፣ እርሱ ግን መሄጃ የለውም ። ቀን ይመሻል ይነጋል ፣ ለእርሱ ግን መሸም ነጋ ለውጥ የለውም ። ምክንያቱም መለወጥ አይፈልግም ። ለውጥ ጠላቱ ነው ። ከማላውቀው መልአክ ፣ የማውቀውን ሰይጣን የሙጥኝ ብል ይሻላል ብሎ የሚኖር ነው ።

ሰይጣን ስላወቅነው ደግ አይሆንም ። ባናውቀውም ከክፋቱ ፈቀቅ አይልም ። ክፉ ሰውም እንደዛ ነው ። ስለቀረብነው የዋህ አይሆንም ። ስለራቅነውም ተንኮሉን መስራት አያቆምም ። የለመድነው ክፉ ነገር ፣ እኛ ስለወደድነው መልካም አይሆንም ። ከጠላነው ግን ነገሩ ባይለወጥም ፣ እኛ እንለወጣለን ። ክፉን ነገር መውደዳችን የነገሩ እስረኛ ያደርገናል ። መጥላታችን ግን ነጻ ያወጣናል ። ነጻ ለመውጣት ግን ዋጋ ያስከፍላል ። ያለ ዋጋ የሚገኝ ነጻነት የለምና ። አላማ የሌለው ሰው ክፉን ወይም መጥፎን ነገር ለመተው በጣም ይከብደዋል ። በተመሳሳይ ጥሩውን ነገር ለመቀበል እጅግ ይጨንቀዋል ። የጋራ አላማ ለውጥ ይፈልጋል ። መለወጥ የማይችል ሰው ለጋራ አላማ እንቅፋት ነው ። አላማ የሌለው ሰው ፣ ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ ስላልሆነ ፣ ለጋራ አላማ መሰናክል ነው ።

      ዓላማ ያለው ሰው ግን ቢያውቅም ባያውቅም መልአክን አይጠላም ።

መልካም ነገርን አይተውም ። መልአክ መልአክ ነው ፣ እኛ ስለፈራነው መልካምነቱ አይቀየርም ብሎ ያምናል ። ከዘመድ ሰይጣን ፣ ባዳ መልአክ ይሻላል የሚል እይታ አለው ። ሁሌም አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አለው ። ለመለወጥ ዝግጁ ነው ። በጋራ መስራት በአንድነት ወደፊት መሄድ ደስታው ነው ። ነገር ግን የጋራ መልካም አላማ እንጅ ፣ ክፉ አላማ ካላቸው ጋር በፍጹም አይተባበርም ። አብረን እንስራ ከሚሉት ጋር እንጅ ፣ አብረን እናጭበርብር ከሚሉት ጋር ህብረት የለውም ። ሰርተን እንገባ እንጅ ፣ ሰርቀን እንገባ አይመቸውም ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል ሳይሆን ፣ እኔ ኖሬ ሰርዶ ላብቅል የሚል ነው ። ለዛሬ ሲል ነገን አያፈርስም ። ለነገ ዛሬ ይኖራል ።

የእርሱ ማጣት ሳይሆን ፣ የልጆቹ ማግኘት ይታየዋል ። የልጆቹ መጥገብ በምናብ ስለሚታየው ፣ የእርሱ መራብ ብዙ አይስጨንቀውም ። አላማ ያለው ሰው ፣ በዛሬ ዉስጥ ነገ ስለሚታየው ለጋራ አላማ ምቹ ፍጥረት ነው ።

     ምቾትን የሚፈልጉ ሰዎች ፣ ዓላማ ቢኖራቸውም ለጋራ ዓላማ ብዙ አይመቹም ። ትራፊ ለመስጠት ፣ ትርፍ መኪናቸውን ማጣት ይፈራሉ ። ልብሳቸውን ከመስጠት ይልቅ ፣ ቁም ሳጥናቸውን የልብስ ሙዚየም ማድረግ ይመርጣሉ ። ሀኪም ካላዘዛቸው ፣ ባዶ እግር መሄድ ይፈራሉ ። በባዶ እግር የሚሄዱትንም ይፈራሉ ። መኖር እንጅ ማኖር አይችሉም ። መስራት እንጅ ማሰራት አይሆንላቸውም ። መቀመጥ እንጅ ማስቀመጥ ህመማቸው ነው ። ሲደመጡ ደስ ይላቸዋል ። ሲያዳምጡ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል ። ሲከበሩ ጮቤ ይረግጣሉ ። ሲናቁ መብት ይረግጣሉ ። ለመከበር የተፈጠሩ እንጅ ፣ ለማክበር የተፈጠሩ አይመስላቸውም ። ለጥቅማቸው ይሽቆጠቆጣሉ ። ለክብራቸው ግን ያንቀጠቅጣሉ ። ምርጥ እና ቆንጆው የእነርሱ ፣ መጥፎ እና ቆሻሻው የሌላ ይመስላቸዋል ። አላማቸው ፍቅርን ማብዛት ሳይሆን ፣ ገንዘብን ቁስን ጌጥን ማብዛት ነው ። ራሳቸውን ጭምር ማብዛት አይፈልጉም ። ያወቁትን በማሳወቅ ፣ የቻሉትን በማሳየት ፣ እነርሱን የሚመስሉ ሌሎች እንዲፈጠሩ ምንም ጥረት አያደርጉም ። በአጭሩ ለምቾት የሚኖሩ ፣ ለጋራ አላማ አይመቹም ።

      የጋራ አላማ የተስተካከለ የግለሰብ አላማን ይፈልጋል ። በፓፒዮ መጽሐፍ ላይ ፣ እንደ ተተረከው ታሪክ አላማን ማስተካከል ያስፈልጋል ። ፓፒዮ ከእስር ቤት እንደ ወጣ ፣ ዓላማው ገንዘብ ማግኘት ነበር ።

ይህ ዓላማው ግን ህገ ወጥ እንዳደረገው ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ዉስጥ መረዳት ቻለ ። በመቀጠል አላማውን አስተካከለ ። በጀመሪያ ገነዘብ ሳይሆን ስራ ማግኘት እንዳለበት ራሱን አሳመነ ። ከስራ ገንዘብን ካስቀደምን ፣ ሥርዓት አልበኛ ወይም ህገወጥ የመሆን እድላችን ሰፊ ነው ። ከገንዘብ ስራን ካስቀደምን ግን ፣ ስርዓትም ይኖረናል ፣ ህጋዊም እንሆናለን ። ልክ ፓፒዮ እንዳደረገው ፣ ገንዘብን ከስራ ካስቀደምን ፣ ሀሳባችን መስራት ሳይሆን መስረቅ ይሆናል ። ስራን ከገንዘብ ካስቀደምን ግን ፣ ሀሳባችን መስራት እንጅ መስረቅ አይሆንም ።

               

            ‘’ የተስተካከለ አላማ ያለው የጋራ አላማን መፍጠር ይችላል ። ‘’ 

                               ክፍል 1                             

Thursday, April 24, 2025

እይታ | Perception

           ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት

  

           በብዛት ሰዎች መከራ ሲበዛባቸው ፣ ችግር ሲደራረብባቸው ፣ ለፍተው ደክመው ጠብ የሚል ነገር ሲያጡ አሁንስ ትእግስቴ አለቀ ይላሉ ። በርግጥ እውነት ነው ፣ የሰው ልጅ ትእግስቱ ውስን ነው እናም ማለቁ አይቀርም ። ያልቃል ማለት ግን አይታደስም ማለት አይደለም ፣ ህይወት አበቃላት ማለትም አይደለም ። የሰው ልጅ ትእግስቱ ቢያልቅ ይታደሳል ። ዳግም በትእግስት ሃይል ይሞላል ። ትእግስት የማያልቅበት ፈጣሪ ፣ እንደገና በአዲስ ትእግስት ይሰራዋል ።

     ዋናው ነገር የትእግስት ማለቅ ወይም አለማለቅ አይደለም ። ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ እና ያለ ጊዜው ሲያልቅ ይለያያል ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ጉዳቱ የከፋ ነው ። የሚታደስ ሳይሆን ፣ ባለበት የሚቆም ወይም ጭልጥ ብሎ የሚጠፋ ነው ። ለዚህም ነው ትእግስት የሌላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲጎዱ የሚታዩት ። ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ፣ ሰውን ትእግስተኛ ሳይሆን እልከኛ ነው የሚያደርገው ። ስለዚህ ለጥፋት እንጅ ለልማት አይሆንም ። ለውድቀት እንጅ ለስኬት አይዳርግም ። ለሃዘን እንጅ ለደስታ አይሆንም ። ወደ በቀል እንጅ ወደ ይቅርታ ልብን አይመራም ።

      ያለ ጊዜው ያለቀ ትእግስት ጥሩ ምልክት ሳይሆን የአደጋ ምልክት ነው ። አምቡላንስ ከሳይረን ድምጹ እና ከቀይ መብራቱ ጋር እንደማለት ነው ። ከጊዜው ያጠረ ትእግስት ማስጀመር እንጅ ማስጨረስ አይችልም ። ለማሳቀድ እንጅ ለማስፈጸም በቂ አቅም የለዉም ። ተስፋ ልማስቆረጥ እንጅ ሪቫን ለማስቆረጥ እድል አይሰጥም ።

            ትእግስት ያለጊዜው ሲያልቅ ነገን ብሩህ አድርጎ ሳይሆን አጨልሞ ነው የሚያሳየው ። እምነትን ገድሎ ጥርጣሬን በልባችን ላይ ይዘራል ። አስተሳሰባችንን አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ ያደርገዋል ። ይሳካል ይሆናል ከማለት ይልቅ ፣ አይሳካም አይሆንም ማለት ቃላችን እና ልማዳችን ይሆናል ። የልቦናን አይን ሞራ ገፎ ከመጣል ይልቅ ፣ የስራ ሞራልን ገፎ ይጥላል ። የሰው ልጅን በእቅድ እንዳይኖር ፣ በዘፈቀደ እንዲኖር ያስገድደዋል ። ማቀድን ሞኝነት ተስፋ ማድረግን ጅልነት አድርጎ ያሳያል ። መኖርን ከንቱ ፣ መሞትን ምርጥ መፍትሔ ያደርጋል ። ስለዚህ የትእግስት ማለቅ ሳይሆን ዋናው ቁም ነገር ፣ ያለ ጊዜው ትእግስት እንዳያልቅ መጠንቀቅ ነው የሚያስፈልገው ።

              ያለ ጊዜው የሚያልቅ ትእግስት ፣ በጊዜው ከሚያልቅ ትእግስት የሚለይባቸው ነገሮች ብዙ ናችው ። ለምሳሌ ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ ድክም ያደርጋል ።

 ያለ ጊዜው ሲያልቅ ቱግ ያደርጋል ። በጊዜው ሲሆን ይታደሳል ፣ የወደፊት ጉዞን እንድንቀጥል ያደርገናል ። ያለ ጊዜው ሲሆን በፍጹም አይታደስም ፣ የወደፊት ጉዞን እንድንቀጥል ሳይሆን እንድናቆም ያስገድደናል ። ከመሄድ መመለስ አምራጭ የሌለው ምርጫ ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ መጨረሻው አቅም ማጣት ነው ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ ግን መጨረሻው ተስፋ ማጣት ነው ። አቅም ስናጣ ፈጣሪ አቅም ይሆነናል ። ተስፋ ስናጣ ግን ፈጣሪ አቅም አይሆነንም ። ምክንያቱም ተስፋ ስናጣ ፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ነውና የምናጣው ። መንፈሰ ጠንካራ ሰዎች አቅም ሊያጡ ይችላሉ ። በፍጹም ግን በፈጣሪ ላይ ያላቸውን እምነት እና ተስፋ አያጡም ። መንፈሰ ጠንካራ ያልሆኑ ሰዎች ግን ፣ አቅም አጥተው ሳይሆን አቅም እያላቸው በፈጣሪ ተስፋ ይቆርጣሉ ፣ እምነታቸውን ያጣሉ ። አዲስ አቅም አያገኙም ፣ ባይሆን የነበራቸውን አቅም ያጣሉ ። ስለዚህ ትእግስት በጊዜው ሲያልቅ መንፈሰ ጠንካራ ያደርጋል ። ያለ ጊዜው ሲያልቅ ግን መንፈሰ ደካማ ያደርጋል ።

         ያለ ጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ውጤቱ ስሜታዊነት ነው ። ሳያስቡ ሳያሰላስሉ ሳያመዛዝኑ ፣ ዘሎ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል ይሆናል ። በጊዜው ትእግስት ሲያልቅ ግን መጨረሻው ምክንያታዊነት ነው ። ከመወሰን በፊት ማሰብን ማስቀደም መርህ ይሆናል ። ማሰብን መወሰን ሲቀድም ስሜታዊነት ነው ።

 ውሳኔን ሀሳብ ሲቀድም ምክንያታዊነት ነው ። ውሳኔ ሲፈጥንም ሲዘገይም ችግር ይፈጠራል ። ሲፈጥን የስሜት ውጤት ስለሆነ ራሳችንን ያሳጣናል ። ሲዘገይ ደግሞ ፍጹምነትን ( perfectionism ) መፈለግ ስለሆነ የምንፈልገውን ያሳጣናል ። ራሳችንንም ሆነ የምንፈልገውን እንዳናጣ ፣ ትእግስታችን ያለ ጊዜው ሳይሆን በጊዜው እንዲያልቅ ጥንቃቄ እናድርግ ። ችግር በገጠመን ቁጥር ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። ያኔ ለውሳኔ ያልፈጠነ ግን ደግሞ ያልዘገየ ምርጥ ሰው እንሆናለን ።

              ትእግስት ያለ ጊዜው ሲያልቅ መማሪያ ያደርጋል ። በጊዜው ሲያልቅ ግን አርአያ ያደርጋል ። ሰው መማሪያ ሲሆን ፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንደሌለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን ግን ፣ ሌላ ሰው ከእርሱ ምን ማድረግ እንዳለበት ይማራል ። አርአያ ሲሆን የስኬት ተምሳሌት ይሆናል ። መማሪያ ሲሆን ደግሞ የውድቀት ምሳሌ ይሆናል ። ድክም እስኪለን ከታገስን ብንወድቅም እንንሳለን ። ቱግ ካልን ግን ላንነሳ እንወድቃለን ። እስከ መጨረሻው የታገሰ ጥሩ ታሪክ ትቶ ያልፋል ። እስከ መጨረሻው ያልታገሰ ግን መጥፎ ታሪክ ጥሎ ያልፋል ። ትእግስት መጨረሻ አለው ። ለዚህም ነው ታላቁ መጽሐፍ ‘’ እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል የሚለው ’’ ።  ቱግ ማለት የትእግስት መጨረሻው ሳይሆን ያለማለቁ ምልክት ነው ። ድካም ግን የትእግስት መጨረሻ ማሳያ ነው ። ስንናደድ ልንጠፋ ነው ። ስንደክም ግን ልንድን ነው ።

 መዳን ማለት መትረፍ መትረፍረፍ ፣ የጥሩ ነገር ምሳሌ ፣ የስኬት ተምሳሌት መሆን ነው ። መጥፋት ማለት ደግሞ የመጥፎ ነገር ፣ የውድቀት ምሳሌ መሆን ነው ። ስለዚህ ሀደራ ትእግስታችን ያለ ጊዜው እንዳያልቅብን ፣ቱግ አንበል ፣ ድክም እስኪለን እንታገስ ። መጨረሻችን መዳን እንጅ መጥፋት አይሆንም ።

          ‘’ ትእግስት የህይወት ቁልፍ መርህ ነው ። ’’                                                


Monday, April 21, 2025

እይታ | Perception

                                                        የትውልድ ቅብብሎሽ

               ለውጥ ስር ነቀል ሲሆን የትውልድ ቅብብሎሽ አይኖርም ። ለውጥ ስር ነቀል ነው  ብሎ ማመን ፣ ትላንት ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ፣ ጥሩ ነገር የለውም ማለት ነው ። ህይወት ጥቁር ወይም ነጭ እንጅ ግራጫ መልክ የላትም እንደ ማለት ነው ። የህይወት እውነታ ግን ይህን አያሳይም ። ትላንት ፍጹም ጥሩ ወይም ፍጹም መጥፎ ሊሆን አይችልም ። ሙሉ በሙሉ ትክክል ወይም ስህተት ሊሆን አይችልም ። የትላንት ታሪክ የሰዎች ታሪክ ነው ። የትላንት ስራ የሰዎች ስራ ነው ። ሰዎች ደግሞ ትክክልም ስህተትም ይሰራሉ ። ጥሩም መጥፎም ያደርጋሉ ። በስር ነቀል ለውጥ ማመን ፣ ይህንን መሰረታዊ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መካድ ወይም አለመቀበል ነው ። 

             የሰው ልጅ በብዛት መጥፎ ከሰራ ፣ በቀጣዩ ትውልድ በመጥፎ ታሪኩ ይወሳል ። ያ ማለት ግን ምንም ጥሩ ስራ የለውም ማለት አይደለም ። ከመጥፎ ስራው ብዛት አንጻር ፣ ጥሩ ስራው በቀላሉ የመታወስ እድል  ስለማይኖረው ነው ። በሌላ በኩል በብዛት ጥሩ ከሰራ ፣ ጥሩ ታሪኩ ለትውልዱ ይነገርለታል ። ይህ ማለት ግን መጥፎ ስራ የለውም ፣ መልአክ ነው ማለት አይደለም ። ከጥሩ ስራው አንጻር ፣ መጥፎ ታሪኩ ወደ ፊት ከመቀጠል ይልቅ በቀላሉ ስለሚቃጠል ነው ። ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ ስለሚረሳ ነው ። የስራ የመታወስ አቅሙ ብዛቱ ነው ። ብዙ ጥሩ ከሰራን ፣ በብዙ ሰዎች እና በትውልድ ልብ ውስጥ በመልካምነት እንታወሳለን ። ትንሽ ከሰራን ግን ከመታወስ ይልቅ በቀላሉ እንረሳለን ። በተመሳሳይ ብዙ መጥፎ ከሰራን ፣ በክፋት ስማችን በትውልዱ ይነሳል ። ትንሽ ከሰራን ግን ፣ አይደለም ለትውልድ ሊሻገር ፣ ከቤት የማይሻገር ታሪክ ሆኖ ይቀራል ። 

            ጥሩ ከመጥፎ ሲበዛ መልካም ያስብላል ። መጥፎ ከጥሩ ሲበዛ ክፉ ያስብላል ። ልክነት ከስህተት ሲበዛ ጎበዝ ያሰኛል ። ስህተት ከልክነት ሲበዛ ሰነፍ ያሰኛል ። መልካም ፣ ጎበዝ እና ክፉ ሰዎች ታሪክ ይኖራቸዋል ። ሰነፎች ግን ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። ሰው ጎበዝ ሆኖ ክፉ ከሆነ ፣ ትውልድ ከክፋቱ ሳይሆን ከጉብዝናው ይማራል ። ጎበዝም መልካምም ከሆነ ፣ ከጉብዝናውም ከመልካምነቱም ይማራል ። ሰነፍ ከሆነ ግን ምንም ስለሌለው ፣ ትውልድ ከእርሱ ምንም አይማርም ። ሰነፍ ሰው እና ዳተኛ ትውልድ ምንም ታሪክ አይኖራቸውም ። አይደለም የታሪክ አሻራ ፣ የጣት አሻራ ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም ። ክፉ እውቀት ከመሀይምነት ይከፋል ( Bad knowledge is more danger than ignorance ) ቢባልም ፣ ምንም አለማወቅ ክፉ ባያደርግም ፣ የክፋት ተባባሪ ያደርጋል ። ምንም አለማወቅ የዋህ ሳይሆን ጅል ነው የሚያደርገው ። የዋህነት ከክፋት ነጻ መሆን ነው ። ጅልነት ግን ከእውቀት ነጻ መሆን ነው ። ከክፉም ከመልካም እውቀት ባዶ መሆን ነው ። ከክፉ እውቀት ይልቅ ፣ ከእውቀት ነጻ መሆን ቢሻልም ግን ጥሩ አይደለም ። ጥሩውም ልኩም ፣ መልካሙን መያዝ ክፉውን መጣል ነው ። ሁሉን መያዝ ፣ ሁሉን መጣል አይቻልም ። መርጦ መያዝ ፣ መርጦ መተው ግን ይቻላል ። ስለዚህ ምርጫችንን እናስተካክል ። ምክንያቱም ምርጫችን ነው ሰውም አውሬ የሚያደርገን ። መልአክም ሰይጣንም የሚያደርገን ። ስንፍና ግን በምንም ሚዛን አያዋጣም ። 

         መልአክ እና የሰው መልአክ ይለያያሉ ። መልአክ ፍጹም ነው ። የሰው መልአክ ግን ፍጹም አይደለም ። በተመሳሳይ አውሬ እና የሰው አውሬ ይለያያሉ ። አውሬ ርህራሄ የለውም ፣ ፍጹም ጨካኝ ነው ። የሰው አውሬ ግን ፍጹም ጨካኝ አይደለም ። በትንሹም ቢሆን ልቡ መራራቱ አይቀርም ። ሰው ከሰው መልአክ ብዙ መማር አለበት ። ከሰው አውሬ ግን ትንሽ ነው መማር ያለበት ። ትንሽም ተማረ ብዙም ተማረ ፣ ዋናው ነገር መማር መቻሉ ነው ። ለውጥ ደግሞ የመማር ውጤት ነው ። ለመማር ነገርን ከስሩ መንቀል ሳይሆን የሚያዋጣው ፣ ነገርን ከስሩ መመልከት ነው የሚያስፈልገው ። ትላንትን ከስሩ መንቀል ሳይሆን ፣ ችግርን ከስሩ መንቀል ነው መፍትሔው ። '' አረምን መንቀል ስር ሳይሰድ ነው ። '' እንዲሉ አበው ፣ ለለውጥ አረምን እንጅ አለምን መንቀል አያዋጣም ። ስር ነቀል ለውጥ ግን አረምን ሳይሆን አለምን መንቀል ነው ። ስለዚህ ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂ ነው ። ስር ነቀል ለውጥ የዋህነት የጎደለው ልባምነት ፣ ይቅር ባይነት የሌለው ትጋት ነው ። ከሰው መልአክም ከሰው አውሬም መማር አለመቻል ነው ። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ሊኖር የሚችለውን የወደፊት ጉዞ ይገታል ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ትውልድ ያፈርሳል እንጅ አይገነባም ። ታሪክ ያቃጥላል እንጅ አያስቀጥልም ። ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰው ታሪክ ሀብት ነው ። ዝግጁ ላልሆነ ግን ታሪክ ሸክም ነው ። ሉሲ ፣ አክሱም ፣ ፋሲለደስ ፣ ጀጎል እና ላሊበላ ላወቀበት ሀብት ናቸው ። ላላስተዋለ ግን ዘበት ናቸው ። ትክክለኛ ለውጥ ሁሉን ጥሎ ማለፍ ሳይሆን ፣ መጥፎውን ጥሎ ጥሩውን ይዞ መሻገር ነው ። ጥሎም አንጠልጥሎም ማለፍ ነው ። ያኔ እንደ አዲስ የሚገነባ ታሪክ ሳይሆን ፣ በሂደት የሚገነባ ታሪክ ይኖረናል ። መሳሪያ የሚቀባበል ትውልድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እና ስራ የሚቀባበል ትውልድ ይታነጻል ። ሆ ብሎ የሚያቃጥል ሳይሆን ፣ ሀ ብሎ የሚያስቀጥል ትውልድ ይነሳል ። በስሜት የሚያፈርስ ሳይሆን በስሌት የሚገነባ ትውልድ ይፈጠራል ። ስር ነቀል ለውጥ ፣ ለውጥን ከመፍጠር በላይ ነውጥን የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው ። ምክንያቱም በዚህ የለውጥ ሂደት ፣ መነካት የሌለበት የህዝብ ልብ የሚነካ ነገር ሊወድም ይችላል ። መጥፋት የሌለበት ሀገራዊ  ማንነት በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል ። ሀገር ያለ ካስማ እና ያለ ምሶሶ መና ልትቀር ትችላለች ። 

         ስር ነቀል ለውጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ፣ ከልማቱ ጥፋቱ ፣ ከአዎንታዊነቱ አሉታዊነቱ ይገዝፋል ። ስለዚህ ለውጥ ጥገናዊ እንጅ ስር ነቀል መሆን የለበትም ። የተበላሸውን እያስተከከሉ ፣ የተዛነፈውን እያቃኑ ፣ የደፈረሰውን እያጠሩ ፣ በነበረው ጥሩ ነገር ላይ አዲስ ነገር እየጨመሩ መሄድ ነው ጥገናዊ ለውጥ ። የዚህ ለውጥ መርህ ፣ ታሪክ እየረሱ እና እየጣሉ መሄድ ሳይሆን ፣ ታሪክ እየጠበቁ እና እየገነቡ ወደ ፊት መሄድ ነው ። የትውልድ ቅብብሎሽ እውን የሚሆነው ፣ ለውጥ ጥገናዊ ሲሆን ነው ። 

        ጥገናዊ ለውጥ የደግነት እና የትህትና ውጤት ነው ። ለመስጠት ደግነት ያስፈልጋል ። ለመቀበል ትህትና ግድ ይላል ። የሚሰጥ ደግ ኖሮ ፣ የሚቀበል ትሁት ከሌለ ችግር ነው ። የሚቀበል ትሁት ኖሮ ፣ የሚሰጥ ደግ ከሌለ ታሪክን ለመቀበልም ለማስቀጠልም ከባድ ነው ። ስለዚህ ቀዳሚው ትውልድ ለማስተማር እና ለመስጠት ደግ መሆን አለበት ። ተከታዩ ትውልድ ደግሞ ለመማር እና  ለመቀበል ትሁት መሆን አለበት ። ያኔ የትውልድ ቅብብሎሽ እውን ይሆናል ። 

    '' ጥገናዊ ለውጥ ለትውልድ ቅብብሎሽ አስፈላጊ ነው ። ''     

Saturday, April 19, 2025

እይታ | Perception

                                                           ንቃተ ህሊና

         ንቃተ ህሊና ያለው ሰው ነገሮችን በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ይችላል ። ቀላል እና ከባድ ችግሮችን በቀላሉ መለየት ይሆንለታል ። ፍሬን ከገለባ ፣ ነገርን ከቁም ነገር ፣ ቆሻሻን ከንጹህ ፣ አጭበርባሪን ከሀቀኛ ለይቶ መመደብ መታወቂያው ነው ። ንቃተ ህሊና የእውቀት ብቻ ሳይሆን ፣ የልምድ እና ያወቁትን የመኖር ውጤት ነው ። ሰው የቱንም ያህል ቢያውቅ ፣ ሺ መጽሐፍ ቢያነብ ፣ ያወቀውን በተግባር እስካልኖረው ድረስ ፣ አወቀ እንጅ ነቃ አይባልም ። የእውቀት መኖሪያ መሆን ሳይሆን ፣ እውቀትን መኖር ነው ንቃተ ህሊናን የሚፈጥረው ። ብዙ ማወቅ ትንሽ መኖር ንቃተ ህሊናን አያጎለብትም ። ትንሽም ቢሆን ያወቁትን ያህል መኖር ነው ፣ የንቃተ ህሊና ባለቤት የሚያደርገው ። 

          ብዙ ያወቁ ግን ያልነቁ ሰዎች አሉ ። ምክንያቱ ምንም አይደለም ፣ ያወቁትን በአግባቡ መኖር አለመቻላቸው ነው ። እውቀትን የማይኖሩ ሰዎች ፣ በንቃት ከመኖር ይልቅ በንቀት ይሞላሉ ። ያወቁትን የሚኖሩ ሰዎች ግን በንቃት ያድጋሉ ። ንቃት ማበላሸት ሳይሆን ማስተካከል ነው ። ማደፍረስ ሳይሆን ማጥራት እና ማጣራት ነው ። ማጣመም ሳይሆን ማቃናት ነው ። ብዙ እናውቃለን የሚሉ ግን ያልነቁ ሰዎች ፣ ማበላሸት እንጅ ማስተካከል አይችሉም ። ለማደፍረስ እንጅ ለማጥራት ጊዜ የላቸውም ። ለማጣመም እንጅ ለማቃናት የሚሆን ህሊና የላቸውም ። ምክንያቱም ንቀት ስላለባቸው ቀና ማሰብ አይችሉም ። ተንኮለኛ እንጅ ጥበበኛ መሆን አይችሉም ። ንቃት ጥበበኛ ያደርጋል ። ንቀት ደግሞ ተንኮለኛ ያደርጋል ። 

        እውቀት ልህቀት የሚሆነው ስንነቃ ነው ። አልያ ግን ሊቅነት ሳይሆን ልቅነት ይፈጠራል ። ሊቆች ሳይሆኑ ፣ ልቅ የሆኑ አዋቂዎች እውቀትን ማኖር እንጅ መኖር አይችሉም ። ሀቀኛ ሳይሆኑ አስመሳይ ናቸው ። የሚኖሩት ከአንጀታቸው ሳይሆን ከአንገታቸው ነው ። ወሬ እንጅ ወረት የላቸውም ። ለእነርሱ መናገር ቀላል ነው ። መኖር ግን እጅግ ከባድ ነው ። የወሬ አዋርድ ቢኖር ፣ የመጀመሪያ ተሸላሚ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው ። ወሬ እና አውሬ ውስጣቸው አለ ። እውነት እና ፍቅር ግን ውስጣቸው የለም ። እውነተኛ ሰይጣን የት ነው መገኛው ? ቢባል ፣ ምንም አያጠራጥርም አስመሳይ ሰው ውስጥ ነው ። ሰይጣን አዋቂ በሆኑ አስመሳይ ሰዎች ይቀናል ። በተንኮላቸው ሰይጣንን የሚያስቀኑ ብቸኛ ፍጥረት ፣ አስመሳይ ሰዎች ናቸው ። እነርሱ ደግሞ ንቀት እንጅ ንቃት የላቸውም ። 

       ንቃተ ህሊና ያላቸው ሰዎች ጨለማን የሚገፉ ብርሃን ናቸው ። ጨለማን የሚያስፋፉ ክፉ ሰዎች ግን ፣ ንቃተ ህሊና ሳይሆን ንቀተ ህሊና ነው ያላቸው ። ማስለቀስ እንጅ ማጽናናት አይችሉም ። እነርሱ ለምድር ደራሽ ጎርፍ ፣ ለሰዎች ደግሞ የሀዘን ጎርፍ ናቸው ። ለገንዘብ የሚሳሱትን ያህል ፣ ለሰው ነፍስ አይሳሱም ። መሰብሰብ እና ማከማቸት ይችላሉ ። መስጠት እና ማካፈል ግን በዞሩበት አይዞሩም ። እነርሱ ትርፋቸው የሌሎች ኪሳራ ነው ። ስኬታቸው የሌሎች ውድቀት ነው ። ክብራቸው የሌሎች ውርደት ነው ። ደስታቸው የሌሎች ሃዘን ነው ። 

       የነቁ ብርሀን የሆኑ ሰዎች ግን ፣ የሌላው ሀዘን ሀዘናቸው ነው ። በደስታቸው ይደሰታሉ ፣ ሲያጡ ይከፋሉ ፣ ሲራቡ ከልብ ያዝናሉ ። እነርሱ ምግብ ሲያጡ ሳይሆን ፣ ሰው ሲያጡ ነው የሚራቡት ። ውሀ ሲያጡ ሳይሆን ፍቅር ሲያጡ ነው ከልብ የሚጠሙት ። ሰው ሲቸገር ሳይሆን መከራን ሲሻገር ደስ ይላቸዋል ። ካወቁት ማካፈል ፣ ካገኙት መስጠት የህሊና እርካታ ይሰጣቸዋል ። የሚገድሉ መርዝ ሳይሆኑ ፣ የሚፈውሱ መድሀኒት ናቸው ። መድሀኒት በመስጠት ፣ እርዳታም በመስጠት ፣ ሰውን ከከፉ በሽታም ሆነ ከክፉ ነገር ያድናሉ ። እነርሱ ዉስጣቸውም ውጪያቸውም ያው አንድ ነው ። ውስጣቸው ቦሌ ፣ ውጪያቸው ጉለሌ አይደለም ። ያወሩትን ይኖራሉ ፣ የኖሩትን ያወራሉ ። ስራ መፍጠር እንጅ ወሬ መፍጠር ብዙ አይችሉበትም ። ማስመሰል ጠላታቸው ፣ እውነተኝነት ደግሞ ወዳጃቸው ነው ። አስመስለው ከሚኖሩ ፣ ከእውነት ጋር ቢቀበሩ ይመርጣሉ ። ግዴታ ከሆነ ፣ ሰውን ለማዳን ሲሉ ሊያስመስሉ ይችላሉ ። በተረፈ ሰው እንዲሞት ብለው በፍጹም አያስመስሉም ። ለፍቅር ያስመስላሉ ፣ ለጥላቻ ግን አይደለም ቦታ ፣ ትርፍ ቦታም የላቸውም ። የእነርሱ ማስመሰል ለሰዎች መርዝ ሳይሆን መድሀኒት ነው ። ሁከት ሳይሆን ሰላም ነው ። ውድቀት ሳይሆን ስኬት ነው ። 

       '' ንቃተ ህሊና ለህሊና ለአካባቢ ለሰዎች ሰላም ወሳኝ ነው ። ''     

Friday, April 18, 2025

እይታ | Perception

                                                           ጽኑዕ እምነት

       ጽኑዕ እምነት ከጥርጣሬ የነጻ ነው ። ከጥርጣሬ በፊት ያለ ጽኑዕ እምነት ፣ የየዋህነት ውጤት ነው ። መጠራጠር ከሌለ መመራመር አይቻልም ። ማሰብ ማሰላሰል ማመዛዘን አይኖርም ። ሁሉም ነገር ማሰብ ማሰላሰል ላያስፈልገው ይችላል ። ሁሉንም ሳያሰላስሉ እንዲሁ መቀበል ደግሞ መዘዙ ከባድ ነው ። ቀላል እና ግልጽ ነገርን በየዋህነት ማመን ብዙ ጉዳት አይኖረውም ። ከባድ እና ውስብስብ ነገርን በየዋህነት መቀበል ግን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም ። የዋህነት የሚወልደው ጽኑዕ እምነት ደካማ ነው ። ልብን ለሌላ አዲስ እይታ ክፍት እንዳይሆን ቆልፎ ይይዛል ። ልብን የሚቆልፍ እይታ ደግሞ ጽንፈኛ ያደርጋል ። ልብን የሚከፍት እምነት ግን መጽናኛ ያደርጋል ። ልብ ቆላፊ እምነት ትክክለኛ እምነት ሳይሆን አጉል እምነት ነው ። አጉል እምነት ደግሞ በእውቀት ላይ ሳይሆን ፣ በልማድ ላይ ነው የሚመሰረተው ። ልማድ እውቀትን ሲቀድም በአብዛኛው ጥሩ አይሆንም ። እውቀትን ተከትሎ የሚገነባ ልማድ ግን ፣ ሁል ጊዜ ባይሆንም በብዛት ጥሩ ነው ። 

           የዋህነት በእውቀት ሲገዘገዝ ሳይሆን ሲታገዝ ጥሩ ነው ። የዋህነት ከተገዘገዘ ሁሉን ተጠራጣሪ ያደርጋል ። በእውቀት ከታገዘ ግን ሁሉን መርማሪ ያደርጋል ። ሰው ከጥርጥር ወደ ምርምር ከሄደ ትክክለኛ አማኝ ይሆናል ። ከጥርጥር ወደ ምርምር መሄድ ካልቻለ ግን ተንኮለኛ ከሀዲ ይሆናል ። ምንም ጭብጥ (fact) አለማግኘት ፣ የሰውን ልጅ ተጠራጣሪ ያደርጋል ። ጭብጥ (fact) ማግኘት ተመራማሪ ያደርገዋል ። ተመራማሪ ከጭብጥ (fact) ወደ ሙሉ እውነት (truth) ይሄዳል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን መሄድ አይችልም ። ጭብጥ እምነትን ይፈጥራል ። እምነት ደግሞ በእውን የማይታየውን ሙሉ እውነት ፣ ግልጽ አድርጎ በምናብ ያሳየናል ። አጉል ተጠራጣሪ ግን ንባብ እንጅ ምናብ ስለሌለው  ለማመን ይቸገራል ። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ፣ የቱንም የህል ብናውቅ ፣ የዋህነትን ማጣት የለብንም ። የዋህነት እና እውቀት ሲደጋገፉ ፣ ትክክለኛ እምነት እና ጥሩ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና እውቀት ሲነቃቀፉ ግን ፣ አጉል እምነት እና መጥፎ ልማድን ይፈጥራሉ ። የዋህነት እና ክፉ እውቀት አብረው አይሄዱም ። መልካም እውቀት ከየዋህነት ጋር ግን በጣም ይዋደዳሉ ። እምነታችሁ ትክክለኛ እና ጽኑዕ እንጅ አጉል እንዳይሆን ፣ መልካሙን ሁሉ እወቁ የዋህነታችሁንም ጠብቁ ። 

           ሰው በየዋህነቱ ከሚከፍለው ዋጋ በላይ ፣ የዋህነቱን በማጣቱ ይከፍላል ። በየዋህነት ብዙ መከራ ሊደርስብን ይችላል ። ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ፣ የዋህነት መጨረሻው ክብር ነው ። የዋህነትን ማጣት ግን ፍጻሜው ውርደት ነው ። የባለጸጎች ትምክህት ፣ የዋህነትን ከማጣት የሚመጣ ነው ። የአዋቂዎች ተንኮል የዋህነትን የመተው ውጤት ነው ። የባለስልጣኖች ግፍ ፣ የዋህነትን ከመናቅ የመነጨ ነው ። እምነት እና ይቅር ባይነት የየዋህነት ውጤት ናቸው ። በዚህች ምድር ላይ መተማመን ከሌለ ፣ ህይወትም ስራም ከባድ ይሆናል ። በደልን መርሳት ከሌለ ፣ አብሮ መኖር ጭንቅ ይሆናል ። ማመን ፋታ ይሰጣል ። አለማመን ፋታ ይነሳል ። በደልን መርሳት ሰላም ያሰፍናል ። በደልን መያዝ ሁከት ይፈጥራል ። የሰላም ቁልፉ የዋህነት ነው ። ያለ የዋህነት ሰላምን ማሰብ በጣም ከባድ ነው ። የውጭ ሰላም የውስጥ ሰላም ነጸብራቅ ነው ። የውስጥ ሰላም ደግሞ በደልን የመርሳት ስጦታ ነው ። በደልን መርሳት የሚቻለው ፣ የዋህነትን ገንዘብ ማድረግ ሲቻል ነው ። ለሰላም የዋህነት ፣ ለጠንካራ እምነት ደግሞ ልባምነት አስፈላጊ ናቸው ። የዋህነት ብቻውን እምነትን ጠንካራ አያደርግም ። ጠንካራ እምነት የሚፈጠረው ፣ የዋህነት በልባምነት ሲደገፍ ነው ። 

            ልባምነት ጥንቃቄ ነው ። ሰውን ተማራማሪ የሚያደርገው ልባምነት ነው ። ስራ በጥንቃቄ ካልተሰራ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ። ገንዘብ በጥንቃቄ ካልተያዘ ባክኖ ይቀራል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ መድሀኒት መርዝ ይሆናል ። በጥንቃቄ ያልተያዘ ትዳር ፣ ልጆችን ልጎዳና ይዳርጋል ፣ ባል እና ሚስትን ላጤ አድርጎ ያስቀራል ። ጥንቃቄ የጎደለው የስልጣን አያያዝ ወህኒ ያስወርዳል ። ለዚህ ደግሞ የምንሰራውን ማወቅ ፣ የምናውቀውን መስራት መለማመድ አለብን ። ያኔ ልባም እንሆናለን ። አልያ ልበ ቢስ እንሆናለን ። የምንሰራውን የማናውቅ ፣ የምናውቀውን ለመስራት የማንፈልግ ከንቱዎች እንሆናለን ። አንድን ነገር አውቀን ከሰራን ፣ እምነታችን የልማድ ሳይሆን የልምድ ውጤት ይሆናል ። በደመነፍስ ከሰራን ግን እምነታችን የልማድ ውጤት ይሆናል ። ልምድ ጥሩ ልማድ ነው ። መጥፎ ልማድ ግን ልምድ ሳይሆን ለምድ ነው ። የሰውን ልጅ እውነተኛ ማንነት የሚጋርድ ሽፋን ነው ። ከእውቀት የመነጨ መጥፎ ልማድ ፣ የክፋት ውጤት ነው ። ባለ መገንዘብ የተፈጠረ ልማድ ግን የየዋህነት ውጤት ነው ። ልባምነት ከሁለቱም ነጻ የሚያወጣን ሀይል ነው ። ልባምነት የዋህነትን ከአደጋ የሚጠብቅ ወታደር ነው ። ሰው በየዋህነት ብቻ ሲኖር ፣ ሁል ጊዜ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ይኖራል ። ልባም ከሆነ ግን ፣ ራሱን ከጦርነት ቀጠና ይጠብቃል ። ጽንፈኝነት ፣ ዘረኝነት ፣ አክራሪነት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ፣ የዋህነት የወለዳቸው ጽኑዕ እምነቶች ናቸው ። ልብ የሚቆልፉ እምነቶች ። ከዚህ አጉል እምነት የሚታደገን ልባምነት ነው ። ጥሩውን ከመጥፎው ፣ ትክክሉን ከስህተቱ ፣ ገለባውን ከፍሬው የሚለይልን ወንፊት ነው ልባምነት ። የዋህነት እምነትን ይፈጥራል ። ልባምነት ደግሞ እምነትን ፍጹም ያደርጋል ። የዋህነት የእምነት መስረት ነው ። ልባምነት የእምነት ጉልላት ነው ። በየዋህነት እንዲሁ እናምናለን ። በልባምነት ግን አጥርተን እናምናለን ። የጠራ እምነት ደግሞ ልብን ዝግ ሳይሆን ክፍት ያደርጋል ። 

           ክፍት ልብ ትሁት ልብ ነው ። ከዘመድም ከባዳም ፣ ከሀብታምም ከደሀ ፣ ከባለስልጣንም ከተራ ፣ ከአዋቂም ከልጅም የተሻለ ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነው ። ትሁት ልብ ሚዛናዊ ነው ። ለራሱም ለማንም አያዳላም ። ለእውነት እና ለተሻለው ሀሳብ ያዳላል ። እምነታችን ጽኑዕ ብቻ ሳይሆን ፣ ጠንካራና ትክክለኛ እንዲሆን ፣ የዋህነት ብቻውን በቂ አይደለም ፣ ልባምነት በጣም ያስፈልጋል ። 

       '' እምነትን ለመፍጠር የዋህነት ግድ ይላል ፣ እምነትን ለማጠንከር ልባምነት ያስፈልጋል ። ''       

እይታ | Perception

                                                                ስንፍና   ስንፍና እየቻሉ አለመስራት ነው ። የማይችሉትን አለመስራት ግን ስንፍና አይደለም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ...